ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ቢሮ 22 ሠራተኞች የስር ፍርድ ቤት የፈቀደውን የዋስትና መብታቸው በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 1ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተሻረ።
የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንንነት ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ያሬድ ዘሪሁን እና የተቋሙ የፀረ ሽብር ጉዳዮች መምሪያ ሀላፊ ተስፋዬ ኡርጌን ጨምሮ 22 ተከሳሾች የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ፍርድ ቤቱን ጠይቀው የነበረ ሲሆን፤ ከሳሽ ዓቃቢህግም ዋስትናው ሊፈቀድ እንደማይገባ እና ተደራራቢ ክስ እንዳለባቸው በማመላከት ተከሳሾቹ ቢወጡ ላይመለሱ እንደሚችሉ እና ከህወሃት ቡድን ጋር ሊቀላቀሉ ይችላሉ ሲል በመቃወም ዘጠኝ ነጥቦችን ጠቅሶ መቃወሚያ አስገብቶ ነበር።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት መርምሮ በጥር 19 ቀን በዋለው ችሎት ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ በተባሉበት አንቀጽ 423 እና በአንቀጽ 556 መሰረት 30 ሺህ ብር ዋስ አስይዘው ጉዳያቸውን በውጪ ሆነው እንዳከታተሉ ዋስትና በመፍቀድ ከአገር እንዳይወጡ እግድ እንዲጣል ማዘዙ ይታወሳል።
ዓቃቢህግ ዋስትናውን በመቃወም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 1ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዋስትና መፈቀዱ አግባብ አደለም በማለት ይግባኝ ጠይቋል።
መልስ ሰጪ የተከሳሽ ጠበቃ በበኩሉ ዋስትና መፈቀዱ አግባብ እና ህገመንግስታዊ መብታቸው መሆኑን በማብራራት ወተው ላይመለሱ ይችላሉ የሚለውን እና ቢወጡ ከህወሃት ጋር ሊቀላቀሉ ይችላሉ የሚለው ምክንያት በማስረጃ የተደገፈ አለመሆኑን ጠቅሰው ነበር።
ተከሳሾቹ ይከላከሉ የተባሉበት አንቀጽ ዋስትና የማያስከለክል በመሆኑ የስር ፍርድ ቤቱ ዋስትና መፈቀዱ የህግ አግባብ ያለው በመሆኑ የተፈቀደው የዋስትና መብት ይጽናልን ሲሉ በመከራከሪያ ነጥባቸው ጠቅሰው መልስ ሰጥተዋል።
መዝገቡን የመረመረው ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ በዛሬው ቀጠሮ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን በመሻር በሁለት አብላጫ ድምጽ በአንድ ዳኛ ልዪነት ተከሳሾቹ ከነበራቸው ስልጣን አንጻር በወንጀለኛ መቅጪያ ሥነ ሥርዓት ህግ አንቀጽ 67/ሀ መሰረት የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታን በዋስ ቢወጡ ግዴታቸውን አክብረው ላይቀርቡ ይችላሉ የሚለውን ግምት በመያዝ እና ተደራራቢ ክስ የቀረበባቸው እና ቅጣቱን በመስጋት ቢወጡ ተመልሰው ላይመጡ ይችላሉ የሚል ግምት በመያዝ ጭምር ዋስትናውን መሻሩን ችሎቱ በጽ/ቤት ማብራራቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ዘግባለች።
ተከሳሾቹ ባሉበት ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉም ውሳኔ ተሰቷል።