እንዴት! ያውም አድዋን!? (በድሉ ዋቅጅራ፤ የወይራ ስር ጸሎት)

እንዴት! ያውም አድዋን!? (በድሉ ዋቅጅራ፤ የወይራ ስር ጸሎት)

ምነው!?
አድዋን ያህል ታቦት!
ነጻነትን ያህል ጽዋ!
ምነው አጣ፣ አንጋሽ – ደጋሽ፣
የጀግና አባቱን፣ ድል ወራሽ?
ምነው?
ምነው?
ምነው! ጭር አለ ቀዬው፣ ዳዋ ዋጠው ደብሩ፤
ፎካሪ ናፈቀ ፈፋው፣ ሸላይ ጠፋ ባገሩ፡፡
ምነው?
ምነው?
በደም፣ በነፍስ የተጻፈ ገድል፤
የጥቁር ህዝቦች፣ የነጻነት ውል፤
አድዋን ያህል ድል?
ምነው!?
የአፍሪካ ወንድሞቻችንማ! ያታደሉ – የታገሉ፤
‹‹ኢትዮጵያን!›› ብለው እየማሉ፤
ነጻነታችንን እየዘመሩ፣ በድላችን እየሸለሉ፤
የአባቶቻቸውን ትግል ወርሰው፣
. . . . . . ነጻነትን አፈሩ፤
እስከ የልጅ ልጅ – ታግለው፤
ባንዲራቸውን ሰቀሉ፡፡
ምነው!?
ምነው እኛ፤
ጭነቱ እንዳልተራገፈለት፣ ገባጣው እንደሚያኝከው ጌኛ፤
አድዋ ጌጡ ቀልሎ፣ ሸክሙ ከበደን፣
እረፍት ነስቶ አኘከን!
እንደመጥበትን ልቦና፣ እንናገርበትን ልሳን፣
አንከበርበትን ግርማ፣ እንከብድበት ሚዛን፣
ምነው! . . . . ያውም አድዋን!?
ምነው!?
በጎሰኝነት ችካል፣ በየጎጡ ጋጥ ታስረን፤
‹‹አድዋ!›› ማለት ከበደን፤
‹‹ኢትዮጵያ!›› ማለት ሸከከን፡፡
ባንባረክ ልንባርከው፣ ቅርጫ ʽናረገው አማረን፡፡
የአባቶቻችን ድል አሳከከን፤
ለትርክት አንደበት አጠረን!
ጀግንነትን አንውረስ – እንፍራ፣ እዳ አለው፣ ያስከፍላል፤
ቆንጣጭ – ገላማጭ በመጣ፣
. . .. . . . .‹‹ዘራፍ›› ብሎ ያገረሻል፤
ጀግንነት ጣር አለው ይቅር፣
. . . . . እንዴት ድል መውረስ ያቅታል!?
ምንስ ድንቁርና ቢጎራበተን፤
ጎሰኝነት ቢያባትተን፤
እንዴት ድል መውረስ ያቅተን!
ያውም አድዋን! ከሀገር፣ ከሰንደቅ፣ ከነጻነትም በላይ፤
የሰው መሆንን ማተብ፣ . . . .
የ‹‹ሳቬጅ›› ተረት ተርትን ስራይ፤
የአፍሪካን የነጻነት አዋይ፤
እንዴት!
ኧረ ወገኔ ውሉን ስቷል፤
አድዋ ተራራ መስሎታል!
ሸንሽኖ ሊከፋፈለው፣ ኮረብታ ሊያደርገው አምሮታል፡፡
አድዋ የአንድ ቀን ውሎ፣ . . .
አድዋ ተራራ መስሎታል፡፡
መንፈስ እኮ ነው አድዋ፣ . . . .
ፈለግ – ለመንገዳችን፣ ለታሪካችን – ልሳን፤
ዙፋን – የነጻነታችን፣ የአብሮነታችን ቁርባን፤
የመረዳዳት ፍሬ – የኢትዮጵያዊነት መልህቅ፤
የደገፈን – እንዳንወድቅ፤
ያጸናን – እንዳንዋዥቅ፡፡
እንዳንፈርስ ያጠነከረን፣ . . .
እንዳነጎድል – ቀድሞ የሰፈረን፡፡
. . . . . ምነው ዘመን አወረን!?
አድዋ እንደሁ መንፈስ ነው!
እንኳን ጎጥ – ሀገር ያልቻለው፤
ጽናት – አህጉር የጠበበው፤
አይገድቡት – ይፈሳል፤
አያቅቡት – ይዳረሳል፡፡
ታዲያ ምነው!?
ምንስ ድንቁርና ቢጎራበተን፤
ጎሰኝነት ቢያባትተን፤
እንዴት ድል መውረስ ያቅተን!
ያውም አድዋን!
ምነው!?
አድዋን ያህል ታቦት!
ነጻነትን ያህል ጽዋ!
ምነው አጣ፣ አንጋሽ – ደጋሽ፣
የጀግና አባቱን፣ ድል ወራሽ?
ምነው?
————-
የካቲት 23፣ 2009፤ አዲስ አበባ

LEAVE A REPLY