ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በትግራይ ክልል የባንክ አገልግሎት በመቋረጡ የተፈጠረውን የጥሬ ብር ዕጥረት ተከትሎ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች አላማጣ ድረስ ጥሬ ብር ለመላክ የተደራጁ ግለሰቦች ከላኪዎች ወይም ከተቀባዮች ከፍተኛ ገንዘብ እያስከፈሉ ነው።
በክልሉ የተከሠተውን የጥሬ ብር ዕጥረት ተከትሎ፣ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ የተደራጁ ግለሰቦች ገንዘቡን ከላኪው ወደ ተቀባዩ ለማድረስ ወይም ከትግራይ ክልል ውጭ የሚኖሩ ሠዎች ትግራይ ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው የሚልኩትን ገንዘብ ለማድረስ መቀመጫቸውን አላማጣ አድርገው ከፍተኛ ገንዘብ እያስከፈሉ መሆኑን ተገልጿል።
የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የባንክ አገልግሎት በመቋረጡ የተነሳ ጥሬ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ውድ ንብረቶቻቸውን እየሸጡ እንደሆነ ዶቸቨለ ዘግቧል።
ወደ ትግራይ ለግለሰቦች ከሚላክ 100 ብር ውስጥ ገንዘብ አስተላላፊዎች 35 ብር እንደሚቆርጡ ዘገባው ጠቁሟል። በመቀሌ አንድ የአሜሪካ ዶላር በጥቁር ገበያ ከብሄራዊ ባንክ መደበኛ የምንዛሪ ተመን ባነሰ መጠን ከ35 እስከ 40 ብር ድረስ ይመነዘራል መባሉንም ሰምተናል።