ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጸጥታ ችግር ለመፍጠር የሞከሩ ተማሪዎች እና በግቢው ግጭት ለመፍጠር የሞከሩ አካላት ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በቅንጅት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና የጸጥታ ሁኔታውን ለማረጋገጥ ከከተማው የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተቀሰቀሰው ግጭት ቁጥራቸው በወል ያልታወቁ ተማሪዎች እንደተጎዱ የተነገረ ሲሆን ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ምሽት ውስጥ ከነበሩ ተማሪዎች ጋር የተዘጋው ቤተ መፀህፍትም ሲነጋ ለመከፈት እንደተገደደ ማወቅ ተችሏል።
በዩኒቨርሲቲው የፀጥታ ችግር ለመፍጠር የሞከሩ ተማሪዎች እና በግቢው ግጭት ለመፍጠር የሞከሩ አካላት ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በቅንጅት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ከአድዋ ድል በዓል በኋላ በግቢው ውስጥ በአማራ እና ኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች መሀል በተደጋጋሚ አለመግባባት ሲከሰት እያስተዋልን ነው። የኦሮሞ ተወላጆችም ባለፈው ሳምንት በግቢው ውስጥ ሁለት ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው ነበር።
አሁን ላይም ዩኒቨርሲቲው መደበኛ የመማር ማስተማር ተግባሩ እንደቀጠለ መግለጻቸውን ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።