ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ፍ/ቤት ታስሬ እንድቀርብ ማዘዙ አግባብ አደለም ሲሉ አቤቱታቸውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በጽሁፍ አቀረቡ።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ከዚህ በፊት እንዲቀርቡ መታዘዙ እንደማያውቁና መጥሪያ እንዳልደረሳቸው ገልጸው፤ መጥርያ ተረክቤ እንቢ ባላለኩበት ሁኔታ ታስሬ እንድቀርብ በፍ/ቤት መታዘዙን አግባብ አደለም ሲሉም አቤቱታቸውን አቅርበዋል።
በጥር 30 ቀን 2014 ታስሬ እንድቀርብ መታዘዙን ማህበራዊ ሚዲያ ነው የሰማሁት ሲሉ በጽሁፍ ለፍርድ ቤቱ በላኩት አቤቱታ አብራርተዋል።በደረሳቸው አገራዊ ጥሪ መሰረት ለአገር እና ለህዝብ ጥቅም እየሰሩ መሆናቸውን ተከትሎ ለሥራ በውጭ አገር እንደሚገኙ ጠቅሰው በማንኛውም ሰዓት ለመቅረብ ታዛዥ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሆኖም ካላቸው የሥራ ሁኔታ አንጻር በአካል ለመገኘት እንደሚቸገሩ ገልጸው፤ ነገር ግን ምስክርነቱን ባሉበት ቦታ ሆነው በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ ጥያቄውኝ ማስተናገድ እንደሚችሉ ፍርድ ቤቱ በላኩት ምላሽ አብራርተዋል።
የእነ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ጠበቃ ሀፍቶም ከሰተ በበኩላቸው፤ ሀይለማርያም ደሳለኝ መጥሪያ መላኩን አላውቅም ፈርሜ አልተቀበልኩም ማለታቸው እንደማይቀበለው ገልጿል።በተደጋጋሚ መጥሪያ እንዲደርሳቸው መታዘዙን ተከትሎ ለሮማንና ሀይለማርያም ፋውንዴሽን ድርጅት ጸሀፊ መሰጠቱንና ጸሀፊዋ በኢሜል ለሀይለማርያም እንደላከላቸው መግለጿንም ጠበቃ ሀፍቶም አብራርቷል።አገር ውስጥ መሆናቸውን በሚዲያ ከመመልከት ውጪ የሚኖሩበት አድራሻን እንደማያውቁና በቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት በኩል ምላሽ ተሰቶ እንደነበር አስታዋሷል።
ሀይለ ማርያም እንደሚፈለጉ አውቀዋል ይህ በሆነበት ሁኔታ ትዛዙን አያውቁም ለማለት አይቻልም ሲል ምላሽ የሰጠው ጠበቃው፤ ነገር ግን በችሎት ለመቅረብ የሚቸገሩ ከሆነ በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ ባሉበት ሆነው ምስክርነታቸው ቢሰማ አንቃወምም ብሏል።
ከሳሽ ዓቃቢህግ ሀይለማርያምም ሆኑ የቀድሞ የጀርመን አንባሳደር ፍስሀ አስገዶም ካውንስለር ካሳን ጨምሮ ሌሎችም ካላቸው ሥራ ጫና አኳያ ባሉበት ሆነው ምስክርነታቸው ቢሰማ እንደማይቃወም አስተያየት መስጠቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።