ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ባለፈው ሳምንት ምግብና ነዳጅ
ጭነው ወደ ትግራይ ተንቀሳቅሰው የነበሩ ከ20 በላይ ተሽከርካሪዎች በገጠማቸው ችግር ምክንያት መመለሳቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ዶ/ር ለገሠ ቱሉ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የትግራይ ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው የአፋር ወረዳዎች በኩል የእርዳታ አቅርቦት ይዘው ወደ ትግራይ እንቅስቃሴ ጀምረው የነበረ ቢሆንም በህወሓት ኃይሎች ጉዟቸው መደናቀፉን ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባሳለፈው ሳምንት ማብቂያ የእርዳታ ምግብ እና ነዳጅ የጫኑ ተሸከርካሪዎች ከሰመራ ወደ ትግራይ ክልል መዲና መቀሌ እየተጓዙ መሆናቸውን መግለፁ ይታወሳል።
በዚህም ወደ ትግራይ የተንቀሳቀሱት 20 የእርዳታ ምግብ እንዲሁም ሦስት ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውንና፣ በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ለማሟላትም በየቀኑ 40 መኪኖች የሰብዓዊ አቅርቦቶችን እንዲያጓጉዙ እንደሚደረግም ጨምሮ ገልጾ ነበር።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከረዥም ጊዜ በኋላ ባለፈው ሣምንት 23ቱ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲጓዙ የተደረገው፤ የህወሓት አማፂያን በአገር መከላከያ ሠራዊትና በአፋር ክልል ኃይሎች ስለተዳከሙ “መንገዱን ሊከፍቱ ይችላሉ የሚል ተስፋ ስለነበረ” ነው ብለዋል።
ምግብና ነዳጅ የጫኑት ተሽከርካሪዎች ሐሙስ ዕለት ወደ መቀለ ጉዞ ጀምረው እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ለገሠ፣ አብአላ መቀለ ኮሪደር በሚባለው መስመር ላይ የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ከሄዱ በኋላ ተኩስ ስለተከፈተባቸው ለመመለስ መገደዳቸውን ገልፀዋል።
ኃላፈው አክለውም ለትግራይ ክልል ሕዝብ እርዳታ ለማቅረብ የህወሓት ኃይሎች መንገድ እንቅፋት መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨባጭ የእርዳታ መኪኖች ወደ ክልሉ እንዲገቡ መንገዱን ክፈቱ ሲባል አይከፍቱም” በማለት ለእርዳታ አቅርቦቱ መሠረታዊ ችግር የመንገድ መዘጋት መሆኑን አስረድተዋል።
ዶክተር ለገሠ ቱሉ ወደ መቀለ እንዲሄዱ ጉዞ ጀምረው የነበሩት የእርዳታ አቅርቦት የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመነጋገር በዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች አማካኝነት የቀረቡ መሆናቸውን አመልክተዋል።
መንግሥት ለእርዳታ አቅርቦቱ መስተጓጎል ምክንያት ነው ካለው ህወሓት በኩል ቢቢሲ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ማድረጉን ገልፆ፤ ጥረቱ እንዳልተሳካለትም በዘገባው አመላክቷል።