ኢትዮጵያ ነገ ዜና || መንግሥት የአገር ሰላም፣ የሕዝብ ደኅንነት ማስጠበቅ እና የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት እንዳለበት ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የሕዝብ ውይይት መድረክ ላይ የተለያዩ የሕዝብ ተወካዮች በከተማዋ የሚስተዋሉና መንግሥት በአፋጣኝ ሊመልሳቸው ይገባል ያሏቸውን ጥያቄዎች እያቀረቡ ይገኛሉ።
መንግሥት በተለይም በአገሪቱ የሚስተዋለውን የሰላም እጦት ችግር መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ እንዲሁም፤ ከዕለት ወደ ዕለት እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ማረጋጋትና ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወስድ አንስተዋል፡፡
የህግ መላላትና ፍርድ ቤቶች ላይ የሚስተዋል የሙስና ችግር እንዲሁም ብልሹ አሰራርን ማስወገድ ያስፈልጋልም ተብሏል።
በከተማዋ የሥራ አጥነት ችግር፣ የቤት ኪራይ መናር፣ የመንግሥት ሰራተኞች ደሞዝና ወጪ አለመመጣጠንም ከሕዝብ ተወካዮች የተነሱ ጥያቄዎች ናቸው።
በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሕዝብን የሚያማርሩና ብልሹ አሰራር ውስጥ የሚገኙ አመራሮችን መንግሥት ታች ድረስ ወርዶ እንዲፈትሽም ተጠይቋል። ከመንግሥት ተቋማት ጀምሮ ታች ድረስ በከተማዋ እየተንሰራራ የመጣውን ሌብነትና የተደራጀ ሥርቆት ላይ መፍትሄ እንዲሰጥም ጥያቄ ተነስቷል፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ የኮንዶሚኒየምና የቤት ጥያቄም ምላሽ እንዲያገኝም በመድረኩ ጥያቄ ቀርቧል፡፡