ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ ፕላስቲክ እና ጎማ አምራቾች ማህበር ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከ4500 በላይ ፋብሪካዎች ውስጥ 450 የሚሆኑት አባላት በማድረግ ይንቀሳቀሳል።
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፋብሪካዎቹ እያጋጠማቸው ባለው የውጭ ምንዛሬ ማጣት የተነሳ የጥሬ እቃ እጥረት ስላጋጠማቸው እየተዘጉ ነው ሲሉ የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ምንተስኖት ለማ ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት ከ20 በላይ የፕላስቲክ ፋብሪካዎች መዘጋታቸውን ሲያነሱ ይህ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ይሄዳል የሚል ስጋት ላይ መሆናቸውን ለብስራት ሬዲዮ ገልፀዋል።
በውጭ ምንዛሬ አደላደልና እጥረት ሰበብ ስራ እየተሰራ አይደለም ያሉ ሲሆን ከፍተኛ የጥሬ እቃ ግብአት እጥረት ያለ በመሆኑ የሀገር ውስጥ አምራች ኩባንያዎች ከኢኮኖሚ ውስጥ እየወጡ ነው ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ውዲህ በታሸጉ ውሃ ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ የፕላስቲክ አማራቾች ባጋጠማቸው ችግር መሆኑም ፕሬዝዳንቱ አስታውሰዋል።እንዲሁም ከውጭ ምንዛሬ አፈቃቀድና ከብድር ጋር በተገናኘ እየተፈጠረ ስላለው ችግር ማህበሩ ለብሄራዊ ባንክ ማስታወቁን በማንሳት ማሻሻያ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም የንግድ መርከብ መንቀሳቀስ አለመቻላቸው ፣ የዩክሬን እና ራሺያ ጦርነት እና የተለያዩ ምክንያቶች ኩብንያዎች በሙሉ አቅማቸው ማምረት አልቻሉም ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።