የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ከስልጣናቸው ሊነሱ ነው ተባለ

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ከስልጣናቸው ሊነሱ ነው ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ በቀጣዮቹ 2 ወራት ውስጥ ከስልጣናቸው እንደሚነሱ ሮይተርስ ዘግቧል።

ሮይተርስ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ሰምቻለሁ እንዳለው የዴቪድ ሳተርፊልድ ምክትል ፔይቶን ኖፍ ስልጣናቸውን ሊረከቡ ይችላሉ ብለዋል።

ከጥር ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በቀጠናው የአሜሪካ ልዩ መልዕከተኛ ሆነው የተሾሙት ሳተርፊልድ እና ምክትላቸው ፔይቶን ኖፍ ከመንግስት አካላት፣ ከሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች እና የዲፕሎማት ማህበረሰቦች ጋር ለመነጋገር ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ እንዳስታወቀው የጉብኝታቸው ዓላማ ጦርነቱን ተከትሎ የተከሰቱ ጥፋቶች እንዲቆሙና ድርድር እንዲደረግ፣ ያልተገደበ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀርብ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ግልፅ በሆነ መንገድ እንዲመረመር በሚያስችሉ ሁኔታዎች መነጋገር ነው።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በተለይም ኢትዮጵያ እና ሱዳን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሚገኙበት በዚህ ወቅት የኃላፊዎቹ መቀያየር ክፍተት ሊፈጥር ይችላል ሲል የሮይተርስ ዘገባ አመልካቷል።
ዴቪድ ሳተርፊልድ ከሶስት ወራት በፊት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በመሆን ለዘጠኝ ወራት ያገለገሉትን ጄፍሪ ፌልትማንን በመተካት መሾማቸው የሚታወስ ነው።

LEAVE A REPLY