ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ውስጥ እጅግ ደማቅ ሆነው ለምን ይጠራሉ?
/ግንቦት30 ቀን 2009 ዓ.ም በሰንደቅ ጋዜጣ የታተመ/
ይህን ከስር ያለውን ፅሁፍ ግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም የፃፍኩት ነው። የዚያን ጊዜ የንጉሳችን ሽሩባ /ቁንዳላ/ ገና ከእንግሊዝ ሐገር አልመጣም ነበር። ቴዲ አፍሮም በዘፈነው ዘፈን ኢትዮጵያ ከዳር እስከ ዳር እያነቃቃት ነበር። የለውጥ ጉዞው የፍጥነት ማርሹን ቀይሮ እየሮጠ ነበር። ብቻ እስኪ አንብቡት።
/ግንቦት30 ቀን 2009 ዓ.ም በሰንደቅ ጋዜጣ የታተመ/
በጥበቡ በለጠ
ባለፈው ጊዜ “ቴዲ አፍሮ እና የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር” በሚል ርዕስ አንድ ፅሁፍ አቅርቤ ነበር። ፅሁፉ የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር ከነ ፀጉር ቆዳቸው ጋር ተገሽልጦ ተወስዶ ዛሬም ድረስ ለንደን ከተማ ውስጥ እንደሚገኝ እና ከአፄ ቴዎድሮስ ሞት በኋላ እንግሊዞች ኢትዮጵያን እንዴት አድርገው ዘርፈው እንደሔዱ የሚያሣይ ጽሁፍ ነበር። ይህን ፅሁፍ ያነበቡ በርካታ ሠዎች አስተያየት ሰጥተውኛል፣ በእንግሊዞች ድርጊት በጣሙን አዝነዋል። ስለ አፄ ቴዎድሮስ ለየት ያሉ ታሪኮች የጠየቁኝ በርካታ ወጣቶች አሉ። ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ውስጥ በጣም ደማቅ ሆነው ለምን ይጠራሉ? ቴዎድሮስ የደራሲያንን፣ የኪነ-ጥበብ ስዎችን ቀልብ ለምን በቀላሉ ገዙት? የሚሉ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ቀርበውልኛል። ሁሉንም መመለስ አልችልም። ነገር ግን ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ አለም ውስጥ የጀግንነት እና የትራጄዲ ጥበባት ማሣያ ሆነው ብቅ ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ከዚህ በፊት በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች የፃፍኩትና በመድረከም ጭምር እንደ ጥናትና ምርምር አድርጌ ካቀረብኳቸው ፅሁፎች ውስጥ ጨምቄ ላወጋችሁ ወደድኩ።
ወደ ዋናው ነጥቤ ከመግባቴ በፊት አንድ ወጣት በስልክ ደውሎ ያለኝን ልንገራችሁ። እንዲህ አለኝ “እንግሊዞች የቴዎድሮስን ፀጉር፣ አስር ታቦታትን፣ የብራና መፃህፍቱን፣ ብርቅ እና ውድ የኢትዮጵያ ቅርሶችን የማንነት መገለጫዎቻችንን በሙሉ ዘርፈውን መሔዳቸውን ከፅሁፍህ ተረዳው። ግን በጣም አዘንኩ፣ አለቀስኩ። ያዘንኩትና ያለቀስኩት በራሴ ነው። እኔ ዛሬ ለእንግሊዙ የእግር ኳስ ቡድን ለማንችስተር የማልሆነው የለም። የእኔ እኩያ ወጣቶችም የእንግሊዝ የእግር ኳስ ክለቦች ደጋፊዎች ናቸው። ግን እነዚህ እንግሊዞች የማንነቴ መገለጫ የሆኑ የቅርስ አንጡራ ሀብቶቼን ዘርፈው የሔዱ ናቸው። ቅርሴን መጠየቅ ማስመለስ የማልችለው እኔ ደካማው፣ ባለማወቅ የእንግሊዞች እግር ኳስ ደጋፊ ሆኜ ስንት አመት ሆነኝ መሠለህ። ካዛሬ ጀምሮ የእንግሊዝ እግር ኳስ ደጋፊ ሆኜ እንደማልጮህ፣ እንደማላባርቅ ልነግርህ ፈልጌ ነው። አለማወቄን ሣውቅ አሣፈረኝ። የዘራፊዎቼ ክለብ ደጋፊ ሆኜ ራሴን ሳገኘው ምሸሸግበት አጣሁ። አለኝ ስሙን የማልጠቅሠው ወጣት። ጉዳዩ ስለገረመኝ ነው ያወጋኋችሁ። አሁን ወደ ዋናው ርዕሠ ጉዳዬ ላምራ፡-
አፄ ቴዎድሮስ በየዘመኑ ብቅ እያሉ የሚያወያዩ ንጉስ ናቸው። ስለ እኚሁ ሠው በርካታ ደራሲያን ብዕራቸውን አንስተዋል። ታሪካቸው በአሉታም በአወንታም ተፅፏል። ግን ግዙፉን ቦታ የያዘው ጀግንነታቸው ከዘመናቸው ቀድመው የተወለዱ መሆናቸው፣ ሃሣብና አመለካከታቸው ለተፈጠሩበት ዘመን ቀድሞ የሔደ እንደሆነ ይነገርላቸዋል።
ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን ስልጣኔ፣ እድገት፣ አንድነት ከመፈለጋቸው ብዛት ስሜተ ስሱ (Sensetive) የሆኑ ሠው ናቸው። ስልጣኔን አፈቀሩ። ከዚያም ለስልጣኔም ስሱ ሀይለኛ ሆኑ። በስልጣኔና በኢትዮጵያ ፍቅር ያበዱ ናቸው የሚሏቸውም አሉ።
አፄ ቴዎድሮስ፣ ፀጋዬ ገ/መድህንን የሚያክል ግዙፍ የጥበባት ዋርካን ማርከው በቁጥጥራቸው ስር ያዋሉ፣ ብርሃኑ ዘሪሁንን የሚያክል የሥነ-ጽሁፍ ዋልታና ማገርን ማርከው አንድ ግዜ የቴዎድሮስ ዕንባ፣ ሌላ ጊዜ የታንጉት ምስጢር እያለ አስደማሚ ጥበባትን አበርክቷል።
አፄ ቴዎድሮስ አቤ ጉበኛን የሚያክል የድርሰት መስዋዕትን ማርከው አንድ ለእናቱ አስኝተውታል። አፄ ቴዎድሮስ፣ ከጃዝማች ግርማቸው ተ/ሐዋርያትን የሚያክል አበው የሥነ-ፅሁፍ ስብዕናን ማርከው ቴዎድሮስ ታሪካዊ ድራማን አፅፈዋል። እኚህ ንጉስ እንዲህ አይነት የጥበብ ልሒቃንን የሚማርኩበት ምክንያት ምንድን ነው?
ከኢትዮጵያ ነገስታት ሁሉ የደራሲያንን ቀልብ በመግዛት እና ብዕራቸውንም በተደጋጋሚ እንዲፅፉበት ያደረጉ አፄ ቴዎድሮስ ብቻ እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ። የአፄ ቴዎድሮስ ሕይወት በራሱ ድርሰት ነው። መራር ድርሰት። ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ደረጃ የደረሰ። በሕይወት ጉዟቸው ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ ጉዞዎችን በድል እየተወጡ የምድራዊው አለም የነገስታት ንጉስ የሆኑ ባለታሪክ ናቸው። ከተራ ሽፍትነት እስከ አገር አመራርነት። የተበጣጠቀችን ሀገር መልሶ “የጠቀመ” አንድ ያደረገ። ህልማቸው፣ ርዕያቸው፣ ፍላጐታቸው… ሰፊ የነበረ። የውስጥና የውጪ ተፅዕኖዎችን የተቋቋሙ የኖሩ። ግን ደግሞ በዘመኑ የዓለም ሀያል የነበረችው እንግሊዝ ብዙ ሺ ጦር አሰልፋ የመጣችባቸው። ህልማቸውና እውነታው መጨረሻ ላይ የሚጋጩባቸው፣ ሩቅ አሳቢው ቅርብ አዳሪው የሆኑት ቴዎድሮስ፣ ከሰሩት ይልቅ ያልሰሩት የሚቆጫቸው ቴዎድሮስ፣ ሽንፈትን በዓይናቸው ማየት የማይፈልጉት ቴዎድሮስ፣ ህይወታቸው የትራጄዲ መድረክ ናት። ህይወታቸው በራሷ ድርሰት ናት። ለዚህ ነው ቴዎድሮስ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ብዕር በቀላሉ የሚስቡት።
ቴዎድሮስ ብሔራዊ ጀግና (National Hero) ናቸው። ምክንያቱም ሕይወታቸው ትውልድን ማስተማሪያ ነው። ሀገርን መውደድ ስልጣኔን መሻት ሩቅ ማለም፣ ለሀገር ክብር ራስን መሰዋት የሚያስተምር ስብዕና የተላበሰ ተፈጥሮ የነበራቸው ንጉስ። ስለዚህ በየትኛውም ዘመን የታሪክን ኬላ የጣሰ ከሕዝብ ህሊና ውስጥ በቅርበት የሚኖር ስብዕና ያላቸው መሪ ናቸው። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ደራሲያን ህዝባቸውን ሊያስተመሩ ሲሹ ወይም አእምሯቸውን በጀግኖች ታሪክ ማጠብና መሙላት ሲፈልጉ አፄ ቴዎድሮስን የሚያነሳሱት።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ በደራሲያን አማካይነት የተፈጠረ ነው ይላሉ። ቴዎድሮስ ጨካኝ መሪ ናቸው። ትዕግስት የምትባል ነገር ውስጣቸው የለችም። በዚህም ምክንያት ብዙ ሕዝብ ጨርሰዋል። ከርሳቸው በተፃራሪ የቆሙትን ሀይላት ከመግደል ውጪ ሌላ ዘዴ የላቸውም። አሁን ስለሳቸው የሚፃፉት ታሪኮች እውነተኛውን ቴዎድሮስ አይወክሉም። አሁን ያሉት ቴዎድሮስ የነ ፀጋዬ ገ/መድህን ፈጠራ ነው። እነሱ የፈጠሩት ጫና ነው ይላሉ። ይህን አባባል የሚያሰሙት ሰዎች አደባባይ ላይ ይዘው የሚወጡት ማስረጃ ባይኖራቸውም በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ሲናገሩ ይደመጣል። ግን ይህ አባባል ከየት መጣ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። በተወሰነ መልኩም ቢሆን መልስ ማግኘት ስለሚገባው አንዳንድ ሃሳቦችን ልሰንዝር።
አፄ ቴዎድሮስ ሶስት አይነት ታሪክ አላቸው። አንደኛው በስልጣን ዘመናቸው አብሮት ቤተ-መንግስት ውስጥ የኖረው ደብተራ ዘነብ የፃፉላቸው ታሪካቸው ነው። ዘነብ በየቀኑ የቴዎድሮስን ታሪክ የሚመዘግብ የዜና መዋዕል ፀሐፊ (Chronicler) ነበር። ስለዚህ ዘነብ ስለ ቴዎድሮስ የፃፈው ታሪክ የመጀመሪያው ተጠቃሽ ነው። ሁለተኛው የቴዎድሮስ ታሪክ ደግሞ ልዩ ልዩ ታሪክ ፀሐፊዎች ያሳተሟቸው መፅሐፍት ናቸው። እነዚህ መፅሐፍት በአብዛኛው በውጭ ደራሲያን የተዘጋጁ ናቸው። በተለይ እንግሊዞች በተለያየ መልኩ የቴዎድሮስን ስብዕናዎች ገልፀዋል። የኛም ሀገር ፀሐፊዎች እነዚህን ደራሲዎች ዋቢ አድርገው የቴዎድሮስ ታሪክ ሲፅፉ ቆይተዋል። በዚሁ በሁለተኛው ክፍል ውስጥ የመደብኳቸው ፀሐፊዎች ከ1950 ዓ.ም ብቻ ድረስ ያለውን ዘመን የሚወክሉ ናቸው። ከ1950 ዓ.ም በኋላ የመጡት ፀሐፊዎች ደግሞ ቴዎድሮስ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለየት ባለ መልኩ በመገንዘባቸው በሶስተኛው የታሪክ መደብ ውስጥ ይካተታሉ። ስለዚህ ቴዎድሮስ ሶስት ዓይነት ፀሐፊዎች አሉዋቸው ማለት ነው። ግን የነዚህ የሶስቱ ፀሐፊዎች ልዩነት ምንድን ነው?
ዘነብ የፃፈው የቴዎድሮስ ታሪክ ከሌሎቹ የሚለይበት የራሱ የሆነ ተፈጥሯዊ እውነታዎች አሉ። ዘነብ ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር የነበረ ፀሐፊ ነው። የቤተ-መንግስት ሰው ነበር። ከዚህ አልፎ ተርፎ የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ የቤት ውስጥ አስጠኚ ነበር። በቴዎድሮስ ውስጥ ያለው ህልም ዘነበ ውስጥ አለ የሚሉ ሰዎች አሉ። ስለዚህ እነዚህ እውነታዎች ካሉ ዘነበ የአፄ ቴዎድሮስ ደካማ ጐኖች አይታዩትም፣ በመሆኑም ታላቁን ሀገርና ሕዝበ ወዳዱን ቴዎድሮስን ነው የፃፈው ይላሉ። /ቴዎድሮስን ታሪክ እንደሰው ደካማ ጐኑን አልፃፈም ተብሎም አስተያየት ይሰጥበታል። ወይም በሙሉ ልብ በነፃነት የቴዎድሮስን ታራክ ጽፎ አላሳየንም ይላሉ። ዜና መዋዕል ፀሐፊዎች ክፉ ነገር አይፅፉም በማለትም ያክላሉ። በነገራችን ላይ አለቃ ዘነብ ታላቅ ፈላስፋና አዋቂ የነበረ ሰው ነው። “መፃሐፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሳዊ” የተሰኘች በእምነት ላይ ተመስርታ ትልልቅ ሃሳቦችን አንስታ የምትጠይቅ መፅሐፍ አለችው። በሀገራችን ውስጥ ከዘርአያቆብ ባለተናነሰ ፍልስፍናን በማንሳት እና በመጠየቅ ወደር ያልተገኘለት ሰው ነው። የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ የቤት ውስጥ አስጠኚ የነበረ፣ የቴዎድሮስ ፈላስፋ!
የቴዎድሮስን ታሪክ በመፃፍ በሁለተኛው ምድብ ውስጥ የተካተቱት አስከ 1950 ዓ.ም የነበሩት ፀሐፊያን ናቸው። እነዚህ ፀሐፍት በአብዛኛው የውጭ ሀገር ስዎች ናቸው። በተለይ ደግሞ እንግሊዛውያን ናቸው። ስለ ቴዎድሮስ በብዛት ያሰፈሩት ነገር ቢኖር ጨካኝ መሆኑን ነው። ለምሳሌ ሔነሪ ብላንክ A Narrative of Captivity in Abyssinia በሚል ርእስ ፅፎት ዳኘው ወ/ስላሴ የተረጐሙት “የእስራት ዘመን በአበሻ አገር” የተሰኘው መፅሐፍ የቴዎድሮስን ጭካኔ ያሳያል። በርግጥ ደራሲው የመቅደላ አምባ እስረኛ የነበረ ነው። ከሞት ፍርድ አምልጦ የደረሰው መጽሐፉ ነው። ስለዚህ የቴዎድሮስን አሉታዊ ገጽታዎች ለመግለጽ ቅርብ ነው። ቂም አለበት። ሁሉም ግን የማይክዱት የቴዎድሮስ ነገር እጅግ ደፋር እና ጀግና መሆነቸውን ነው። በዚህ ምድብ ውስጥ የሚካተቱት ፀሐፊዎች የቴዎድሮስን አርቆ አሳቢነትና ህልም ያሳዩ ወይም ማየት ያልፈለጉ ናቸው እየተባሉም ይወቀሳሉ። ስለዚህ እነሱም ትክክለኛው ቴዎድሮስ አልሰጡንም እየተባሉ ይተቻሉ።
አፄ ቴዎድሮስ እጅግ ግዙፍ ስብዕና ተላብሶ የመጣው በሶስተኛው ምድብ ውስጥ ባሉት ፀሐፊያን ነው። እነዚህ ፀሐፍት “የፀጋዬ ገ/መድህን ትውልዶች” በመባል ይታወቃሉ። በአንዳንዶች አጠራር ደግሞ “ነበልባለ ትውልድ” ይባላሉ። ምክንያቱም የኢትዮጵያን ታሪከ፣ ሥን ፅሁፍ፣ ስነ ጥበብን እና ሙዚቃን በማይታመን ለውጥ ውስጥ ያካተቱ በኪነ ጥበቡ ዓለም ውስጥ አሻራቸውን ግዙፍ ሆኖ በመገኘቱ ነው። እነዚህ ትውልዶች ወደ ኋላ ሄው ታሪክን ካነበቡ በኋላ አሁን የምናውቀውን አፄ ቴዎድሮስን ፈጠሩ የሚሉ አሉ።
ፀጋዬ ገ/መድህን “ቴዎድሮስ” የሚል ታላቅ ቴአትር ፃፈ። በዚህ ቴአትር ውስጥ ጨካኙ ቴዎድሮስ የለም። ከ1950 ዓ.ም በሰው ገዳይነቱ፣ በቅፅባዊ እርምጃው ብዙ የተሳሳቱ ውሳኔዎችን የወሰነ በጅምላ የሚገድለው ቴዎድሮስ በፀጋዬ ገ/መድህን ቴአትር ውስጥ የለም። ይልቅስ ለአንዲት ኢትዮጵያ ነፃነት የሚታገለው ቴዎድሮስ፣ከሰራው ይልቅ ያልሰራው ነገር የሚቆጨው ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ የዓለም ሁሉ እያል ለማድረግ ህልም የነበረው ቴዎድሮስ፣ ከራሱ ክብር ይልቅ ለኢትዮጵያ ክብር ሲል ሽጉጡን ጠጥቶ የሚሰዋው ቴዎድሮስ፣ በፀጋየ ቴአትር ውስጥ መጣ። ብሄራዊ ጀግና ተፈጠረ።
አንዳንድ የፖለቲካ ታሪክ የሚተነትኑ ፀሐፍት ሲገልፁ፣ የኢትዮጵያ የአብዮት መቀጣጠል ከመጀመሩ በፊት የለውጥ ጥንስሱ እዚህ ላይ ነው የተጀመረው ይላሉ። ለምሳሌ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የአፄ ቴዎድሮስ ታላቅነትና ጀግንነት እንዲነሳ የማይፈልጉ መሪ ነበሩ ይሏቸዋል። ማስረጃም ሲጠየቁ የሚመልሱት ነገር አለ፣ እነዚህ ተንታኞች። ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የቴዎድሮስን ታሪክ የማይወዱት ቴዎድሮስ “ከሞዓ አንበሳ ዘምነ ነገደ ይሁዳ” የሚመዘው ዘር የለውም። የሰለሞናዊ ዘር አይደለም። ከተራ ሽፍትነት ተነስቶ ነገስታትን የጣለ “ንጉሰ ነገስታት” የሆነ ሽፍታ ነው። የሰለሞንያዊያንን ስርዓት የናደ ሽፍታ ነው ብለው የሚያስቡ ናቸው ብለው ጃንሆይን ይወቅሷቸዋል። በሌላ አነጋገር አንድ ሰው እንደ ቴዎድሮስ ጠመንጃ ይዞ ጫካ ከገባ የንጉስ አስተዳደርን ጥሎ መንግስት መሆን ይችላል የሚል አንደምታ ያለው ቴአትር ነው ተብሎ በቤተ-መንግስት አካባቢ ይታማ እንደነበር ይወሳል።
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “ቴዎድሮስ” የሚለውን ቴአትር የፃፈው ብሔራዊ ጀግና ለመፍጠር ነው ይሉታል። ካረጀውና በለውጥ በማያምነው በአፄው ስርዓት ላይ የቴዎድሮስን ስብዕና ጫነበት። በቴዎድሮሰ ውስጥ ገብቶ ለውጥን አስተማረበት እያለ ክፍሉ ታደሰ ፅፈዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የፀጋዬ ገ/መድህን ትውልዶች ቴዎድሮስን የተቀባበሉት ብሄራዊ ጀግንነቱን የበለጠ አጉልተው አወጡት። ለምሳሌ ብርሃኑ ዘሪሁን በዚሁ በ1950ዎቹ ውስጥ “ቴዎድሮስ ዕንባ” የተሰኘ ቴአትር ፃፈ። አሳየ። የቴዎድሮስ ማንነት በትውልድ ውስጥ መስረፅ ጀመረ። ቀጥሎም በዚያው ዘመን አቤ ጉበኛ “አንድ ለናቱ” የተሰኘ ግዙፍ መፅሐፍ አሳተመ። በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ቴዎድሮስ እጅግ አሳዛኝ ስብዕና ያለው ታሪኩ ሲነበብ የሚያሰለቅስ፣ ኢትዮጵያ እና ሕዝቦ በቴዎድሮስ ውስጥ የሚታዩ ሆነው ተሳሉ። የነዚህን ደራሲያን አካሄድ በሚገባ የተገነዘበው በአሉ ግርማ ደግሞ ሰፊ ፅሁፍ አወጣ።
የበዓሉ ግርማ መጣጥፍ እነዚህን የታሪክ አካሄዶች በአንክሮ ተገንዝቦ የፃፈው ነው። ርዕሱ “አፄ ቴዎድሮስ ከሞቶ ዓመት በኋላ ተወለዱ” ይላል። ፅሁፉ የትኩረት አቅጣጫውን ያደረገው በፀጋዬ ገ/መድህን፣ በብርሃኑ ዘሪሁን እና በአቤ ጉበኛ ላይ ነው። በዘመኑ ወጣት የነበሩት እነዚህ ታላላቅ ደራሲያን አፄ ቴዎድሮስን የብሔራዊ ጀግና ቁንጮ አደረጉት። ቴዎድሮስ ጭቆናን ታግሎ የሚጥል፣ ያረጀ ያፈጀን ሥርዓት የሚገረስሰ፣ በዘርና በቀለም፣ በትውልድ ሐረግ የሚተላለፍን ሹመትና ሥልጣን የማይቀበል፣ ከተራ ጫካ እስከ ቤተመንግስት የሚደርስ፣ እንዲሁም ለሀገሩና ለሕዝቡ ክብር የሚሰዋ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ መድረከ ላይ ናኘ። ደራሲውና በዘመኑ የጋዜጣና የመፅሔት ዋና አዘጋጅ የነበረው በዓሉ ግርማ እውተኛው ቴዎድሮስ የነ ፀጋዬ ገ/መድህን ነው አለ። ቴዎድሮስ የተወለደው አሁን ነው። አስከ ዛሬ ድረስ የተፃፈለት ቴዎድሮስን ስህተት ነበረው እያለ በዓሉ ግርማ በወርቃማ ብዕሩ ፃፈ።
አንዳንድ አጥኚዎች እንደሚገልፁት አንድን ሕዝብ ስለ ለውጥ ለማስተማር አርአያ የሚሆን ጀግና መኖር አለበት። ስለዚህ እነዚያ ነበልባል የሚባሉት የድርሰት ትውልዶች ቴዎድሮስ ውስጥ የነበረውን መስዋዕትነት ወስደው ብሔራዊ ጀግና ማለት እንዲህ ነው እያሉ ሕዝባቸውን ለለውጥ አነሳስተውታል ይላሉ። በነገራችን ላይ የደጃዝማች ግርማቸው ተ/ሐዋርያት “ቴዎድሮስ ታሪካዊ ድራማ” የተሰኘውን ቴአትርም መዘንጋት የለብንም። ይህ የደጃዝማች ግርማቸው ቴአትር ከነ ፀጋዬም ቀድሞ የተፃፈ ነው። እርግጥ ነው ቴአትሩ ለቴዎድሮስ ቀና አመለካከት ያለው ሆኖ አገኝቸዋለሁ። ምንም እንኳ ደራሲው ግርማቸው ተ/ሐዋርያት በወቅቱ ከነበረው ገዥ መደብ ውስጥ በሚኒስትር ደረጃ ያሉ ቢሆንም ቴዎድሮስን በነ ፀጋዬ ዓይነት አተያይ ባይገልፁትም ብሔራዊ ጀግናነታቸውን በመጠቆም ግን ቀዳማዊ ደራሲ ናቸው። ለነ ፀጋዬ ገ/መድህን ቴዎድሮስም የመነሻና የማነቃቂያ ሃሳብ የሰጡ ደራሲ ናቸው ማለት ይቻላል። ግርማቸው ተ/ሐዋርያት “አርአያ” በተሰኘው ልቦለድ መፅሐፋቸው ይታወቃሉ። አባታቸው ተ/ሐዋርያት ተክለማርያም ደግሞ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር የሚባለውን “ፋቡላ የአውሬዎች ኮሜዲያ” የተሰኘውን የፃፉ ናቸው።
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ብሔራዊ ጀግናን በመጠቀም የሀገርን ክብርና ሞሰ አገልቶ የማሳየት አቅም ያለው ልዩ ፀሐፊ ነው። የቴዎድሮስን እና የሰማዕቱን የአቡነ ጴጥሮስን ታሪክ በመውሰድ ታሪካዊ ቅኔዎቹን እና የመድረክ ስራዎቹንም በማቅረብ ትውልድን አስተምሯል።
የፀጋዬ ገ/መድህን ችሎታ ገዝፎ የሚወጣው ገፀ-ባህሪው ሊሞት ትንሽ ደቂቃዎች ሲቀሩት በሚያዘንባቸው ቃሎች ነው። ለምሳሌ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ሊያጠፉ በሚዘጋጁበት ወቅት ስለ ሐገር፣ ስለ ትግል፣ ስለ ህልም፣ ስለ ትዝብት.. የሚናገሯቸው ውብ ቃላት በትውልድ ሕሊና ውስጥ ቴዎድሮስን ከማገዘፉም በላይ የኢትዮጵያን ማንነት ያስረዳል። ምን ያህል አገር እንደሆነች ማለት ነው። “ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” በሚለውም ቴአትሩ አቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው በኋላ ሞታቸውን ከፊታቸው አስቀምጠው ስለ ራሳቸው፣ ስለሀገራቸው፣ ስለ መስዋዕትነት የሚናገሩበት ትዕይንት እጅግ ግዙፍ ነው። ስለዚህ ፀጋዬ ገ/መድህን በሞት ጫፍ ላይ የቆመ ስብዕና በመጠቀም ብሔራዊ ጀግንነትን ያስተምርበታል። ፀጋዬ ገ/መድህን ካሉት በርካታ ችሎታዎች ውስጥ አንዱ ይህን በሞት የመጨረሻዋ ሰዓት ላይ ያለን ገፀ-ባህሪ በመውሰድ በርሱ ውስጥ ሆኖ የሚገልፀው ሀሳብ ነው።
ልክ እንደ ፀጋዬ ሁሉ ብርሃኑ ዘሪሁንም “የቴዎድሮስ ዕንባ” እና “ባልቻ አባነፍሶ” በተባሉት ቴአትሮቹ አሳይቷል። ብርሃኑ “የታንጉት ምስጢር” የተሰኘ ታሪካዊ ልቦለድም በመፃፍ ታሪክን በመጠቀም የድርሰት ስራዎቹን ለከፍተኛ ስኬት ያበቃ ነው።
የጌትነት እንየው ታሪካዊ ቴአትር ቅርፅ “ሙዚቃዊ ቴአትር” ጽፎ በመድረክ አቅርቧል። ይህን የቴዎድሮስን ታሪክ እውን ለማድረግ ጌትነት በቴክኒክ የተዋጣለት ቴአትር እንደፃፈ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥበባት ዲን የሆነው የነብዩ ባዬ ጥናት ይገልፃል። በሙዚቃዊ ቴአትር ስልት በርካታ የተሳኩለት ነገሮች መኖራቸውን ነብዩ በጥናቱ ያብራራል አብራርቷል።
ነብዩ ባዬ ሲናገር የቴዎድሮስ ስብዕና ደራሲያንን በቀላሉ ይማርካል። የቴዎድሮስ አነሳሱ፣ አስተዳደጉ፣ ሕልሙ፣ ስኬቱ፣ “ውድቀቱ” ራሱ የተፃፈ ድርሰት ይመስላል። በዚህም የደራሲያንን ቀልብ በመውሰድ ተወዳዳሪ የሌለበት ንጉስ እንደነበር ነብዩ ጠቁሟል። በዚህም የተነሳ ጌትነት እንየው በዚህ በኛ ዘመን ውስጥ ካሉት ደራሲያን በቴዎድሮስ ስብዕና የተመሰጠውና ቴአትሩ የፃፈው።
ደራሲዎቻችን ወደ ኋላ እየሄዱ በታሪክ ውስጥ ትልልቅ ስብዕና ያላቸውን ሰዎች መጠቀም እያቆሙ መጥተዋል። ኢትዮጵያ በታሪክ የዳበረች ሐገር ስለሆነች ብዙ ለድርሰት ታሪክ የመነሻ ምንጭ የሚሆኑ ሃሳቦች ስላሉ እሱን መመርመር እንደሚገባቸው ይመከራል።
እርግጥ ነው አለቃ ዘነብ፣ እስከ 1950 ድረስ ያሉት ደራሲያን፣ ከ1950 በኋላ የመጣው የእነ ፀጋዬ ገ/መድህን ትውልድ በሶስት ደረጃ ተከፍለው ቴዎድሮስን ገልፀዋቸዋል። በዚህ ዘመን ካሉት ፀሐፍት ደግሞ ጌትነት እንየው በቴዎድሮስ ስብዕና ላይ ፃፈ። ቴዲ አፍሮ ዘፈነ። ስለዚህ ቴዎድሮስ ወደ አራተኛው ትውልድ የተሸጋገረ ነው። ግን መጠየቅ የሚገባው ትልቅ ርዕስ ጉዳይ የጌትነት ቴዎድሮስ ከነ ፀጋዬ ቴዎድሮስ ይለያል ወይ? የሚለው ነው። እርግጥ ነው ቴአትሩ በአቀራረቡ ሙዚቃዊ በመሆኑ በፊት ከነበሩት ሁሉ ቅርፁ ይለያል። ሃሳቡ ገን በ1950ዎቹ የመጣሙ ትውልድ የተረጐመው ወይም ያየው ቴዎድሮስ እንደሆነ መናገር ይቻላል።
በአጠቃላይ ግን ለብዙ ደራሲዎች ስለ ቴዎድሮስ ብዙ የመነሻ ሃሳብ የሰጡት ከደብተራ ዘነብ በኋላ ሞንዶ ቪዳዬ ያሳተሙት እና አለቃ ወልደማርያም የፃፉት የቴዎድሮስ ታሪክ፣ በሄነሪ በላንክ በ1868 የተፃፈው A Narrative of captivity in Abyssinia የተሰኘው መፅሐፍ፣የኘሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት “The Emperor Theodore and the Question of Foreign artisans in Ethiopia” እንዲሁም የታሪክ ፀሐፊዎች የሆኑት እንደ ገሪማ ታፈረ ያሉት ደግሞ “አባ ታጠቅ ካሳ የቋራው አንበሳ” የተሰኘ መፅሐፍ ካሳተሙ ቆይተዋል። ተክለፃዲቅ መኩሪ የእና ጰውሎስ ኞኞም በቴዎድሮስ ታሪክ የተለከፉ ፀሐፊያን ናቸው።
በአጠቃላይ አፄ ቴዎድሮስ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ቀልብ የሚገዙት ታሪካቸው በራሱ ተፅፎ ያለቀ የትራጄዲ ጽሁፍ ስለሆነ ነው። ከአነሳስ እስከ ንግስና ከዚያም አሳዛኙ የሕይወት ፍፃሜ ውስጥ የታዩት የትራጄዲ ጉዞዎች ተፅፈው ያለቁ ድርሰቶች ናቸው።