መታወቂያ መስጠት ማቆሙን የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ

መታወቂያ መስጠት ማቆሙን የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ላልተወሰነ ጊዜ አዲስ መታወቂያ የመስጠት አገልግሎት ማቆሙን የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ የመታወቂያ፣ የልደት፣ የጋብቻ እና የሞት ማስረጃዎችን ይመዘግባል፤ ዜጎች በሚፈልጉበት ወቅትም አገልግሎቱን ይሰጣል፡፡

በአገልግሎት አሰጣቱ ውስጥ በተለይም የመታወቂያ አገልግሎቱ ላይ በተቋሙ ውስጥ እና ከተቋሙ ውጭ ባሉ ሃሰተኛ ማስረጃን በሚያድሉ ግለሰቦች የተነሳ ለማይገባቸው ሰዎች መታወቂያ አላግግባብ እየተሰጠ መሆኑን የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክትር ዶክተር ታከለ ነጫ ገልጸዋል፡፡

ህገ ወጥ ድርጊቱን ሲፈጽሙ የተያዙ ግለሰቦች ላይም እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡ የነዋሪነት መታወቂያ ለማግኘት ሲባል ህገወጥነት እየተባባሰ በመምጣቱ ችግሩን በሚገባ ለማጥራት እንዲቻል በከተማ አስተዳደሩ ደረጃ በተላለፈ ውሳኔ መሰረት አዲስ መታወቂያ እንዳይሰጥ ላልተወሰነ ጊዜ መታገዱን ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ታከለ ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱ ላልተወሰነ ጊዜ ታግዶ የሚቆይ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሪክተሩ፤ በህወጥ ድርጊቱ ውስጥ የተሳተፉ አካላትን ወደ ህግ የማቅረብ እና ተቋሙ ውስጥ ያሉ ህገ-ወጥነቶችን የማጥራት ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡የመታወቂያ እድሳትም ሆነ ሌሎች የወሳኝ ኩነት አገልግሎቶች ባሉበት ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡

LEAVE A REPLY