ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኘው መኖርያ ቤታቸው እንደወጡ አለመመለሳቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ መነን ኃይሌ ለቢቢሲ አሳወቁ።
ብርጋዴር ጄነራሉ ትናንት ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2014 ከቤታቸው 5 ሰዓት አካባቢ የወጡት ከጓደኛቸው ጋር ቀጠሮ እንደነበራቸው ገልፀው መሆኑን የሚያስረዱት ወ/ሮ መነን ከዚያ በኋላ ግን ወደ ቤታቸው ባለመመለሳቸው ደጋግመው ወደ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ቢደውሉም ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልፀዋል።
አያይዘውም ጄኔራል ተፈራ ያገኟቸው ሰዎች በዕለቱ እስከ 10 ሰዓት ድረስ አብረው መቆየታቸውን እና ከዚያ በኋላ እንደተለያዩ እንደነገሯቸው በመጥቀስ ከዚያ በኋላ ግን የደረሱበትን ለማወቅ እንዳልቻሉ ተግረዋል።
ወ/ሮ መነን የባለቤታቸውን መጥፋት አስመልክቶ ወደ ፌደራል ወንጀል ምርመራ እንዲሁም አዲስ አበባ ፖሊስ በመሄድ ቢጠይቁም ግለሰቡ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንደማይገኙ እንደተገለፀላቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ለዓመታት በከፍተኛ መኮንንነት ያገለገሉት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ከአስር ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ አሲረዋል በሚል ከሌሎች ጋር ተከሰው ለዓመታት በእስር ቆይተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎም ከእስር ተለቀው በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲያገለግሉ የቆዩት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በቅርቡ ደግሞ የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ ሆነው መስራታቸው ይታወሳል። ከአዛዥነት ከተነሱ በኋላም በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ በመቅረብ አስተያየታቸውን ይሰጡ እንደነበር ይታወቃል።
በቅርቡም የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመግባት ጥቃት በሰነዘሩበት ጊዜ የክልሉን ልዩ ኃይል በበላይነት ሲመሩ የነበሩ ሲሆን ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ ከዚሁ ኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጋቸው ይታወሳል