አየር ላይ || በእውቀቱ ስዩም

አየር ላይ || በእውቀቱ ስዩም

በቀደም ለት፥ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ባውሮፐላን መጣሁ ፤ እና በሎንቺና ልትመጣ ኑሯል? አለኝ አንዱ አሁን በውስጥ መስመር፥ እስቲ ትረካውን እስክጨርስ እንኳ ታገሱኝ!

ወደ አይሮፕላኑ ገብቼ ሻንጣ ለመስቀል ሳንጋጥጥ እግረመንገዴን ፈጣሪየን አመሰገንሁ:: “ ጌታየ ሆይ! ከሙስና ባስ የሰወርከኝ፥ ባውሮፕላን ያሳፈርከኝ እኔ ማነኝ? በግሬ ንቅቃት መሀል አንድ ቁና ቀይ አቧራ ተሸክሜ ከማንኩሳ የወጣሁ ልጅህ በደመና ላይ እንድረማመድ ስለፈቀድክልኝ አመሰግናለሁ “ አልሁና ጅንን ብየ ወንበሬ አመራሁ፤ አውሮፐላኑ ሲነሳ እንደ ጀማሪ ሹፌር እጄን ካውሮፐላኑ መስኮት አውጥቶ ማናፈስ አማረኝ::

ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ሽንት ቤት ጎራ ለማለት ስሞክር በስህተት የ” የቢዝነስ ክላስ” መንገደኞች ክፍል ውስጥ ራሴን አገኘሁት፤ እዚያ በተመለከትኩት ነገር እጀግ ከመደንገጤ የተነሳ ቆቡ ላይ ደርሶ የነበረው ሽንቴ ወደ ፊኛየ ተመለሰ! እንደኛው፥ የቢዝነስ ክላስ መንገደኛ አባቴ ድሮ እሚተኛበትን ሞዝቦልድ አልጋ በሚያክል ሶፋ ላይ ፈልሰስ ብሏል:: ከፊትለፊቱ ባለው ጠረጴዛ ላይ Diamond label ውስኪና ጣፋጭ የአማልክት ምግቦች ተደርድረውለታል፤ በቃ ምን ልበላችሁ ዙርያውን ፍሬሽ ኮርነርን አስመስለውለታል! የተቀመጠበት ሶፋ መደገፍያ ጀርባውን ማሳጅ ሲያደርገው የሚያወጣው ድምጽ እኔ ከሚስቴ ጋራ ግብረ- ፍስክ ስፈጽም ከማወጣው አንጸባራቂ ድምጽ ጋራ ይቀራረባል፤ ከፊትለፊቱ ያለው ቲቪ መለስተኛ ሲኒማ ያክላል፤ ጫማውን ሲያወልቅ የበረራ አስተናጋጇ ፈጠን ብላ መጥታ የእግር ውሀ እና ነጠላ ጫማ አቀረበችለት፤ ነጠላ ጫማው ሲራመድበት ፥ነጠላ ዜማ እንዳይለቅ ፥ ሳይለንሰር (ማፈኛ) ተገጥሞለታል፤

እኔም ይህን አይቼ፥ እንደ ድንክ ከዘራ አቀርቅሬ ወደ ወንበሬ መመለስ ጀመርኩ፤ ሰፊው ህዝብ ተገጥግጦ የተቀመጠበትን ኢኮኖሚ ክላስ አለፍሁ፤ ያውሮፐላኑ ጅራት ማብቂያ ላይ Under-developed economy class እሚባል አለ፤ እዚያ ውስጥ የኤሌክትሪክ መግደያ በሚመስል ወንበር ላይ ተጎልቼ እንደሚከተለው ማማረር ጀመርሁ” ጌታሆይ ! ከሰው የተለየ ምን በድየ ነው ክንፍ ያለው ሀይገር ባስ ውስጥ ያሳፈርከኝ? በውኑ በዚህ አለም ስኖር፥ “ለቢዝነስ ክላስ” እሚያበቃ ትሩፋት አልሰራሁምን? በውኑ ጌቶች በምባልበት እድሜየ “ ጌቶ” ውሰጥ ስማስን መገኘት ነበረብኝ ? እኔ ጀርባየን ማሳጅ የሚያደረግ ወንበር አልጠየቅሁህም! ግን ቢያንስ ጀርባ የሚያክ ወንበር አያምረኝም? ወይ ወረድ ወይ እኔ ልውጣና እንዋቀስ! “

የኢራንን ሰማይ ስናቋርጥ፥ በቀኝ በኩል ከጎኔ የተቀመጠው ህንዳዊ መንገደኛ እንደ ፍቅረኛ ትከሻየ ላይ ተኛ፤የሰውየው ራስ፥ ራስ ሆቴልን ያክላል፤ ይባስ ብሎ ግብዳ ጥምጥም ጨምሮበታል፤ ትከሻየን ሸክሽኮ ሆዴ ውስጥ ከመክተቱ በፊት ገፈተርኩት::

የበረራ አስተናጋጅዋ ስለ በረራ ድህንነት ገለጻ ስታደርግልን፥
“ አውሮፐላኑ ባህር ላይ ለማረፍ ቢገደድ ለቢዝነስ ክላስ መንገደኞች መንሳፈፍያ ከረጢት እና ሞተር ጅልባዎች አዝጋጅተናል፤ ለኢኮኖሚ ክላስ መንገደኞች ደግሞ “ ውሀ ዋና ያለ አስተማሪ “ የሚል መጽሀፍ እናድላለን ስትል ፤ በተራየ የህንዱ ትከሻ ላይ ዘንበል ብየ አለቀስኩ::

በግራየ በኩል ለተቀመጠው አበሻ ተሳፋሪ፥ ስለ ቢዝነስ ክላሱ ምቾት ነገርኩት::

“ ትርፍ ቦታ ካላቸው ይሰጡሀል፤ ሰለብሪቲ መሆንህን ብቻ መንገር ነው እሚጠበቅብህ “ አለኝ::
“ ሰመጥር መሆኔን እነሱ የት ያውቁልኛል ?”

“ አታስብ ! ከተጠየቅህ እኔ እመሰክርልሀለሁ”

ተነሳሁና ወደ ቢዝነስ ክላሱ ሄድኩ፤ እንደመታደል ሆኖ አንድ ስራ የፈታ ወንበር አየሁ::
ሳላቅማማ ተንሰራፋሁበት::

ካንድ ደቂቃ በላይ አላጣጣምኩትም::

“ የሰው ወንበር ለመንጠቅ እንዲህ ያለ ድፍረት ካለህ ለምን ኩዴታ አትሞክርም?” የሚል ድምጽ ሰማሁ::

ሰውየው ሸንቶ መመለሱ ነው፤ ራሴን ለማስተዋወቅ እንኳ ጊዜ አልሰጡኝም፤ የአውሮፕላኑ ደህንነት አስጠባቂ ተጠርቶ መጣ! ያድዋ ዋዜማ ስለነበር ትንሽ ልታገለው ሞከርኩ፤ እንደ ሰርቶ ማሳያ ካሮት አንጠልጥሎ ወስዶ ወንበሬ ላይ ጣለኝ፤ በመጨረሻ አጋዥ ፍለጋ ወደ አበሻው ተሳፋሪ ዞርሁ ::

አጅሬ በተቀመጠበት ወደ ደንብ አስከባሪው ቀና ብሎ እያየ እንዲህ አለው፥

“Thank you for your service “

LEAVE A REPLY