ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ገፊ-ምክንያቴ በጉለሌ የእጽዋት ማዕከል ውስጥ የፊልም ሥራ ላይ እያለ የደረሰበት ባልታወቀ ሁኔታ የጠፋው (“የታገተው” ለማለት ስለቸገረኝ ነው) ኤፍሬም አበበ አሳዛኝ ገጠመኝ ነው፡፡ ጉዳዩ ስር-እየሰደደ በመሆኑም በጊዜ መፍትሔ ካልተበጀለት አገራችንንና ሕዝባችንን ወደማንወጣው አዘቀት የመግፋቱን አይቀሬነት ለመናገር ነብይነትን አይጠይቅም፡፡
በዚህ ዐውድ ይህን መሰሉን ወንጀል በወፍ-በረር እንቃኘዋለን፡፡
እንደ መንደርደሪያ
በዓለማችን በየጊዜው በታወቀም ሆነ ባልታወቀ ምክንያት የሚጠፉ ሰዎች በርካታ ስለመሆናቸው በክስተቱ ዙሪያ የሚወጡ ዘገባዎች ያስረግጣሉ፡፡ ይሁንና፣ በሠለጠኑት አገራት አንድ ሰው የመሰወሩ መርዶ በተሰማ ቅጽበት መንግሥትም ሆነ ዜጎቹ ከፍተኛ ትኩረት ስለሚሰጡት በአጭር ጊዜ እልባት ሲያገኝ ይስተውላል፡፡ በተለይ፣ በዘመናት መሃል የተገነባውና እጅግ በሰለጠኑ ባለሙያዎች የሚመራው የፖሊስ ተቋም ዋንኛውን ኃላፊነት ወስዶ ለፍለጋ ይሰማራል፡፡ የአገሪቱ ሚዲያዎችም ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ያግዙታል፡፡
የጠፋው ሰው እስኪገኝ (መጨረሻው እስኪታወቅ) የመንግሥት ባለሥልጣናት (የከተማው ከንቲባ) መግለጫ ይሰጣሉ፤ ፖሊስ ቶሎ ቶሎ የደረሰበትን ይገልጻል፤ ሚዲያዎቹም እየተከታተሉ ይዘግባሉ፡፡ ፖሊስ በተነባቢ ጋዜጦችና መጽሔቶች በራሱ ወጪ ማስታወቂያ ደጋግሞ በማስተላለፍ ሕዝብ በጥቆማ እንዲተባበር ያደርጋል፡፡
በዚህም ችግሩን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደተቻለ በተለያዩ ጥናቶች ተረጋግጧል፡፡
በአጭሩ፣ በእነሱ ዘንድ ከፖሊሰዊ ግዳጆች ዋንኛው ይህንን መሰል ወንጀል በቶሎ መቆጣጠር ነው፡፡
ወደ ኢትዮጵያችን እንመለስ…
በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ማኀበራዊ ቀውስ እየበዛ በሄደ ቁጥር እገታን ጨምሮ፣ የሀብታ መራራቅ፣ የተቋማት ነፃነት ማጣት፣ የፍትሕ መዛባት፣ አድሎአዊ አስተዳደር፣ የአደባባይ ውንብድና እና የመሳሰሉት ወንጀሎች የአዘቦት ክስተት መሆናቸው አይቀርም፡፡ በእኛይቷም ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነቱ እንግዳ ነገር እየተለመደ ለመምጣቱ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡
በዋኛነት በአዲስ አበባ ከ2000 ዓ.ም ወዲህ በኤሌትሪክ ማስተላለፊያ ምሶሶዎች እና ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢ የጠፉ ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት የሚለጠፉ “የአፋልጉኝ” ማስታወቂያዎችን ማየት አዲስ ነገር እንዳልሆነ ነዋሪዎቹ እናስታውሳለን፡፡ በተለይ ከ2002 እስከ 2004 ዓ.ም ከቤት ወጥተው ያልተመለሱ መሆናቸውን የሚገልጹ ያፋልጉኝ ማስታወቂያዎች እጅግ የበረከቱበት ጊዜ ነበር፡፡
ይህም ሆኖ፣ ፖሊስ ስለ ጠፋ ሰው ሲያመለክቱ በእለት ሁኔታ መዝገብ ላይ መዝግቦ በየጣቢያው እንዲፈልጉና ፍንጭ ካገኙ በስልክ ወይም በግንባር እንዲያስታውቁት መክሮ ከማሰናበት ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም፡፡ ለዚህ ደግሞ የራሴን ገጠመኝ ማጋራት እችላለሁ፡፡ በ2003 ዓ.ም ግንቦት ወር እና በ2004 ዓ.ም ጥቅምት በሁለት የማውቃቸው ሰዎች የቤተሰብ አባላት ላይ ችግሩ ደርሶ ሰብሰብ ብለን ፖሊስ ጣቢያ ሄደን ስናመለክት የተሰጠን መልስ ከላይ የገለጽኩት ነው፡፡
በዚህ ላይ በቅርብ ከምናውቃቸው ሰዎች ወጪ፣ ስለመጥፋታቸው ከተለጠፉት ፎቶዎች መሃል ምን ያህሉ እንደተገኙ፣ ምን ያህሉ ደብዛቸው ጠፍቶ እንደቀረ የሚታወቅበት ሁኔታ የለም፡፡ ስለጉዳዩ የተጣራ መረጃ ማግኘትን እንደ ኒዩክለር ሳይንስ ያጠጠረውም ይህ ነው፡፡ በዩንቨርስቲ ተማሪዎች ወይም በሌላ የሚመለከተው ተቋም በእንዲህ ዓይነት ክስተቶች ዙሪያ የተዘጋጀ ጥናት ስለመኖሩ አልሰማሁም፡፡
ሁኔታው ውስብስብ እንደሆነ የተረዳሁት ግን፣ በ2010 ዓ.ም የመጣውን ለወጥ ተከትሎ በሚዲያ ከተነገሩ ወንጀሎች መሃል በዚህ አገር ከኦርጋን ትራፊክ (Organ Trafficking) ጋር የተገናኘ ድርጊት ይፈጸም እንደነበረ መጠቀሱ ነው፡፡ በወቅቱ ወደኋላ ተመልሼ ሰዎች በብዛት ይጠፉ ከነበረበት ከስተት ጋር ግንኙነት ይኖረው ይሆን እንዴ? የሚል ጥያቄ አጭሮብኝ ነበር፡፡
መቼም፣ እንደ ሕዝብ ለራሳችን የምንሰጠው የሞራል እና የሥነ-ምግባር ደረጃ በእጅጉ ከፍ ከማለቱ አኳያ፣ እንዲሁም ወደ 99% የሚጠጋው ሕዝባችን በፈጣሪ አማኝ በመሆኑ፣ ‹እንዲህ ዓይነት ሰቅጣጭ ወንጀል የሚፈጽም ሰው ይኖራል› ብሎ ማሰቡ ሊከብድ ይችላል፡፡ ግና፣ ከዚያን በኋላ በመጡት አምስት ተከታታይ ዓመታት ሃይማኖትም ሆነ ህሊና (ወይም ‹ተገራንበት› የምንለው መልካም ሥነ-ምግባር) የወል ጭካኔያችንን ለማለዘብ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ከገዛ ሃፍረቶቻችን በበቂ አይተናል፡፡
ከደንቢዶሎ ዩንቨርስቲ ሴት ተማሪዎች መሰወር ጀምሮ በርካታ መሰል ክስተቶች በስፋት ተፈጽመዋል፡፡ በአንድ ወቅት የጠቅላይ ሚንስትሩ የፕሬስ ኃላፊ ንጉሡ ጥላሁን የታገቱት ተማሪዎች ያሉበትን መንግሥት እየደረሰበት እንደሆነ ጠቁመው ነበር፡፡ ነገሩ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ እንጂ፡፡
አሁንም የተማሪዎቹ እገታ በቸልታ መታለፍ የለበትም፡፡ ውሸት ከሆነም ለጉዳዩ መነሾ የነበሩት ቤተሰቦቻቸውን እና እጃቸውን የነከሩ ሰዎች ቢያንስ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ መደረግ አለበት፡፡
ይህ እስካልሆነ ድረስ ‘እህቶቻችንን መልሱልን?’ የሚለው ጥያቄ ብልጭ-ድርግም እያለም ቢሆን መነሳቱ አይገታም፡፡
(ሰሞነኛው የአዋሳው ጠለፋም ‘በብዙ ጥረት እየቀነሰ ለነበረው ጎጂ ባህል ዳግማ ተንሳኤ እየመጣለት ይሆን’ የሚል ከባድ ስጋት ያጭራል፡፡ በመጨረሻ የእህታችን መገኘት ቢያረጋጋንም ቅሉ፤ ደስታችን ምልኡ የሚሆነው ወንጀለኛው ለፍርድ ሲቀርብ ነው፡፡)
ኤፍሬም አበበ
መሳለሚያ ተወልዶ ያደገ ወጣት ነው፡፡ ለዐቅመ-ሥራ ከደረሰ በኋላ በፊልሞች፣ በቴሌቪዥን ድራማዎች፣ በሙዚቃ ቪዲዮዎች እና ተያያዥነት ባላቸው የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ላይ የፕሮዳክሽን መናጀርነቱን በብቃት የሚወጣ ባለሙያ መሆንም ችሏል፡፡ በሥራው ቀልድ የማያውቅ ምስጉን እንደነበረም ይታወቃል፡፡ ባህሪው ዐመለ-ሸጋ፣ ተግባቢና ጨዋታ አዋቂ በመሆኑም የሁሉም ወዳጅ ነው፡፡ “መታዘዝ ከመስዋትነት ይበልጣል” እንዲል ቃሉ፤ ለሁሉ የሚታዘዝ የትህትና ባለቤት ስለመሆኑም በተለይ የቅርቦቹ በደንብ ያውቃሉ፡፡
ግና፣ ይህ ባለሙያ በድንገት ከጠፋ ዛሬ 51ኛ ቀኑን ቢደፍንም፤ እምጥ ይግባ ስምጥ ፈጽሞ ሊታወቅ አልቻለም፡፡
በወቅቱ መጥፋቱን በተመለከተ በማኀበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው ዜና እንዲህ የሚል ነበር፡-
“ሚያዚያ 3/2015 ጉለሌ እፅዋት ማዕከል ለቀረጻ ሥራ ከእሱ የሚጠበቅበትን አመቻችቶ ‘ሥሩ እኔ እዚህ አረፍ ልበል’ ካለበት ቦታ ከሁለት ሰዓት በኋላ የፕሮዳክሽኑ አባላት ኤፍሬምን በቦታው ላይ አጡት፡፡ ስልኩም ዝግ ሆነ፡፡”
ጌታዬ ጉለሌ፣ ባሌ ወይም መቀሌ እንዳይመስልህ፡፡ እዚሁ አፍንጫህ ስር የአዲስ አበባ ጫፍ ነው፡፡
እናሳ፣ የከተማዋ ፖሊስ ወንድማችንን ለማፈላለግ ያደረገው ጥረት አለ ወይ? መስተዳድሩስ ስለችግሩ ምን አለ? ይህንን የመሰለ አስደንጋጭ ክስተትስ የአንድ ሰሞን የማኀበራዊ ሚዲያ ወሬ ብቻ ሆኖ መቀጨት ነበረበት?
ኧረ ጎበዝ እየተለማመድን ያለነው ምንድን ነው?
ምስኪኑ ኤፍሬም አበበ የት ይሆን ያለከው?
መቼም ይህንን ያህል ጊዜ የት እንደደረሰ ባይታወቅም ተስፋ አለመቁረጡ ይበጀናልና፤ ከደበበ ሰይፉ “ጉልበቴ በርታ፣ በርታ” ግጥም ጥቂት ስንኞችን መዝዘን እናዝግም፡-
“እስቲ በሉ፣
ጉልበቴ በርታ፣ በርታ በሉ፣
በዛሬ ፆማችን ይታየን ስዕሉ፣
የነጋችን ድሉ፡፡
…ቢያንዘፈዝፈንም ክብደቱ የመስቀሉ
ቢጠይምብንም ዛሬያችን ፀዳሉ
ቢያንገዳግደንም የህላዌ ትግሉ፣
ለእምነታችን እምነት፣ ለተስፋችን ተስፋ
ከኛ ዘንድ አይመንን፣ ከኛ ዘንድ አይጥፋ፡፡”
…የሙያ ባልደረባዬ ሆይ፡- የኢትዮጵያ አምላክ፣ የምታምነው አምላክ፣ የአባትና እናትህ አምላክ፣ የደጋጎች ጸሎት ክፉን አርቆልህ በሰላም ለቤትህ ያብቃህ፡፡
አሜን!!!
ታሪኩ ደሳለኝ (ሚኪ)
ግንባት 24/2015