“ኮሽ ባለ ቁጥር እስር!!!!!” || ጋዜጠኛ በፈቃዱ አባይ

“ኮሽ ባለ ቁጥር እስር!!!!!” || ጋዜጠኛ በፈቃዱ አባይ

በጉማ የፊልም ሽልማት ጉዳይ በቦታው እንዳየሁት…

ትናንት ምሽት ዘጠነኛው የጉማ የፊልም ሽልማት በስካይላይት ሆቴል በደማቅ ዝግጅት ተከናውኗል። በዚህ የሽልማት ስነስርአት ላይ ከዝግጅቱ በላይ መነጋገሪያ ለመሆን የቻለው የልጅ ማኛ ፎቶ ነው። ልጅቱ በሀገሬ እየተካሄደ ያለው ጉዳይ ይመለከተኛል ብላ ተቃውሞዋን ማሰማት በፈለገችበት መንገድ እና ምርጫ መልእክቷን ከሚገባው በላይ አስተላልፋለች።

በቅድሚያ ልጅ ማኛ ፎቶዎችን ስትነሳ አጠገቧ ወይም ከቅርብ ርቀት ከነበሩት ታዳሚያን አንዱ ነበርኩ። እኔ የየልጅ ማኛ መልእክት የገባኝ ዘግይቶ ነው። ልጅ ማኛ መሆኗን አላወኩም ነበር። በ8ኛው ዙር የጉማ የፊልም ሽልማት ላይ ጾታዊ ጥቃትን አስመልክቶ መልእክት ያስተላለፈች መሰል እንስት ስለነበረች አሁንም እራሷ በመሰል መልእክት የመጣች ነበር የመሰለኝ። ብዙ ቃለ-መጠይቅ ሰርቼ እና ረዥም ሰአት ቆሜ ስለነበር ድካም የፈጠረብኝ ስሜት ስለነበር እከታተላት የነበረው ተቀምጨ ነው። እናም የልጅ ማኛ ከማንም ጋር አታወራም።ለማንም መልስ አትሰጥም። ፎቶግራፍ እና ቪዲዮ ለሚቀርጿት ብቻ ትቆምላቸዋላች። ከዚያ ያለፈ ምንም አላደረገችም። አልተናገረችም። ምላሱን ሲያወጣባት የታየው ቀይ ሳሪያን ኮት ለባሽ ታዳሚም ደጋግሞ ሊያነጋግራት ሞክሮ ምላሽ ስላሰጠችው ተናዶ ያደረገው እና ምላሱን ሲያወጣ የሆነ ምላሽ ታሳያለች ብሎ ከማሰብ ያደረገው ድርጊት እንደሆነ ታዝቤአለሁ። ወዲያ አንዱ ፌስ ቡክ ላይ “ጀግና!!” ምናምን ብሎ ጻፈለት እና እሱን የመንግስት ወገን ተቆርቋሪ አደረገው። ልጁ እንደዛ ይሁን አይሁን አላውቅም።

ልጅ ማኛ ግን ማንንም ከቁብ ሳትቆጥር በከፍተኛ የራስ መተማመን አብራት ከነበረችው ልጅ ጋር መልእክታቸውን አስተላልፈው ብዙም ሳትቆይ አዳራሹን ለቃ ወጡ። ፎቶአቸውን እንዳያችሁት ማህበራዊ ሚዲያው በፍጥነት ተቀባበለው።

ያሰበችውን/ያሰቡትን መልእክትም አስተላለፉ።
ፎቶው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ ከሆነ በኋላ እኔ በነበርኩበት የቃተኛ በር መኪና ላይ የተቀመጡ፣ሄልሜት ያጠለቁ እና መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች በሩን ይዘው ቆሙ። ዝግጅቱ እስኪጠናቀቅም እዛው ቆይተው ሄዱ። በዚያ ልክም ሲቪል የለበሱ ደህንነቶች ስካይ ላይት በር ላይ እና አዳራሽ አካባቢ በብዛት መታየት ጀመሩ። በነገራችን ላይ እነዚህን ደህንነቶች መለየት ሲበዛ ቀላል ነበር። በዝግጅቱ ላይ የታደሙ ተጠሪዎች ሁሉም ለማለት በሚቻል መልኩ ሽልማቱን የሚመጥን አለባበስ የለበሱ በመሆናቸው እና አብዛኛው ታዳሚም የሚተዋወቅ በመሆኑ ደህንነቶቹን ከአለባበሳቸው እስከ እንቅስቃሴአቸው መለየት ያን ያህል ከባድ አልነበረም። እነርሱ ሊሰልሉት የመጡበት ታዳሚ እነርሱኑ ሲጠቃቀስባቸው አመሽ። ዝግጅቱ አልቆ ስንወጣም በር ላይ በተመሳሳይ ቁጥር እና አለባበስ እንደነበሩ ታዝቤአለሁ። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን ልጅ ማኛ እና ጓደኛዋ የሉም።

እናም ከጉማ የፊልም ሽልማት መጠናቀቅ በኋላ የፊልም ዳይሬክተሩ እና የዝግጅቱ የበላይ ዮናስ ብርሀነ መዋ እንደታሰረ ሰማን። ይህንን ጽሁፍ እስክጽፍ ድረስም አልተፈታም።
በነገራችን ላይ ትናንት በብዙ አጋጣሚዎች ከዮናስ እና ባልደረቦቹ ጋር በተደጋጋሚ እየተገናኘን እንነጋገር ነበር። ምን ያህል አድካሚ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደነበሩ በሚገባ ታዝቤአለሁ።
ልጅ ማኛ ወደ አዳራሹ ስትገባ ዮናስም ባልደረቦቹም አላዩአትም። ምክንያቱም እነ ልጅ ማኛ የመጡት በጣም ዘግይተው ዝግጅቱ ከተጀመረ በኋላ ነበር።
ልጅ ማኛ ስካይ ላይት ስትደርስ ዮናስ ብርሀነ መዋ አዳራሹ ውስጥ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር እያደረገ ነበር። በእርግጠኝነት የልጅ ማኛን
መምጣትንም መሄድን ዮናስ አልተመለከተም።
ፎቶውን እንደማንኛውም ሰው በሶሻል ሚዲያ ላይ ሊያየው እንደሚችል አውቃለሁ። ግን መታሰር አልቀረለትም።
በግል እምነቴም ሆነ በቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ እንደሰማሁትና እንደተስማማሁበት “ኮሽ ባለ ቁጥር ምላሽ መስጠት ተገቢ አይደለም።”በሚለው ሀሳባቸው እስማማለሁ።
ሰዎች የሚቃወሙበትን እድል መንፈግም አግባብ አይሆንም። ድፍረትና ዕድል አጥቶ እንጂ ሀገር በሙሉ ተቃዋሚ በሆነበት በዚህ ጊዜ ስንቱን አስሮ መጨረስስ ይችላል??? ብልጽግና እንደ መንግሥት ከህወሓት መንግሥትስ በምን ይለያል???

የመንግስት ለውጥ አንደኛው መለኪያ መሆን የሚኖርበት የሚቃወሙትንም ማድመጥ እና ዕድል መስጠት መሆን ይኖርበታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርጫ አሸንፈው ስልጣን ሲይዙ ከተናገሩት መሐከልም “የመረጠንን ብቻም ሳይሆን ያልመረጡንም ህዝብ ለማገልገል ዝግጁ ነን።” ማለታቸውን ሳስታውስ “የሚደግፉንን ብቻም ሳይሆን የሚቃወሙንንም እንሰማለን።” ማለታቸው ይመስለኛል። መንግሥትን መደገፍ ከተቻለ መንግሥትን መቃወምስ ስለምን ይከለከላል?????

እናም ዮናስ ብርሀነ መዋም የታሰረው ምንም በማያውቀውና ባልዋለበት በመሆኑ ልትለቁት ህግ ግድ ይላል።

LEAVE A REPLY