በጅጅጋ ከተማ ዙሪያ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

በጅጅጋ ከተማ ዙሪያ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢፌፖሚ)፡- በሱማሌ ክልል በጅጅጋ ከተማ ዙሪያና በሲቲ ዞን ወጪና ገቢ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ።

ብሄራዊ የኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ግብረ-ኃይል በምስራቁ ሀገራችን ያለው ከፍተኛ የኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ዝውውርን ለመቆጣጠር የሚያስችል ውይይት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድ ዑመር በተገኙበት በጅግጅጋ ከተማ ባካሄደው ምክክር በአካባቢው ያለው ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱም በላይ በፀጥታም ላይ ብሄራዊ ስጋት እየደቀነ መምጣቱን በመግባባት ላይ በመድረስ ወደ ኦፕሬሽን በመግባቱ ከፍተኛ የኮንትሮባንድ እቃዎች እየተያዙ እንዳሉ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ግብረ-ኃይሉ በአካባቢ ያለውን የገቢ ወጪ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ከገመገመ በኋላ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከሶማሌ ክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በከፍተኛ ደረጃ ከሀገራችን ወደ ውጭ የሚወጣውን ጫትና የቀንድ ከብት እንዲሁም ሌሎች የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ መቻሉን በመግለጫው አመላክቷል፡፡

ግብረ-ኃይሉ ባካሄደው ኦፕሬሽን በሱማሌ ክልል ሲቲ ዞን በኩል ወደ መሀል ሀገር በመግባት ላይ ያሉ በሶስት ትራከተር ላይ የተጫኑ የኮንትሮባንድ እቃዎችን ለመያዝ የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 3:00 ጀምረው ከኮንትሮባንዲስቶቹ ጋር በተደረገ ከፍተኛ ትንቅንቅ አንድ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባል በጥይት የተመታ ሲሆን አንድ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አመራር ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 11: 00 ሰዓት ላይ የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን በመያዝ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ማስገባት የቻለ መሆኑን በመግለጫው ገልጿል።

ከዚህም ባሻገር ግምቱ 4 ሚሊየን 5መቶ ሺህ ብር በላይ የሆነ ጫት በሁለት ተሽከርካሪ ተጭኖ በድሬዳዋ በኩል በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር ሊወጣ ሲል ደንገጎ ላይ መያዙን በመግለጫው የጠቀሰው ግብረ-ኃይሉ በተጨማሪ የተለያዩ የአርማታ ብረት ፌሮ መያዙን አስታውቋል፡፡

በቀጣይም የጀመረው የፀረ-ኮንትሮባንድ ኦፕሬሽን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቀው ግብረ-ኃይሉ ህብረተሰቡ የሀገር ሀብትና ኢኮኖሚ የሚጎዳውን ኮንትሮባንድ አምርሮ መታገል እንዳለበት በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።

LEAVE A REPLY