ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ያለው የሽንኩርት ምርት አቅርቦት ማነስ ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት እንዳስቻላቸው የኬኒያ ሽንኩርት አምራቾች እየተናገሩ ነው።
የሽንኩርት ገበያው በድንገት የናረው ታንዛኒያ ውስጥ የጣለው ዝናብ በሽንኩርት እርሻ ላይ ባስከተለው ውድመት ምክንያት መሆኑ ተዘግቧል።
ወደ ጅቡቲና ሶማሌላንድ የሽንኩርት ምርትን በገፍ በማቅረብ የምትታወቀው ኢትዬጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሽንኩርትን ከጎረቤት ሱዳን እያስገባች ሲሆን የኬኒያ ሽንኩርት አምራች ነጋዴዎችም የኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ምርታቸውን ለማቅረብ እየሠሩ መሆኑ ታውቋል።
በምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ያለው የሽንኩርት ገበያን ለመቆጣጠር ያለሙ የኬንያ ሽንኩርት ነጋዴዎች ደቡብ ሱዳን ኡጋንዳን ታንዛንያን እና የኢትዮጵያ ገበያ ለመቆጣጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ እና የምርት እጥረትን ሊያስከትል ይችላል ተብሎ መሰጋቱንም የሚናገሩ የኬንያ የግብይት ባለሙያዎች ይህንን ምቹ የገበያ እድል የኬንያ ሽንኩርት እምራች ገበሬዎች እንዲጠቀሙ መሰራት አለበት ሲሉ ያበረታታሉ።
ከባለፈው ስድስት ወራት ኬንያ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከሽንኩርት ገበያ የዋጋ መውጣት እና መውረድ ጋር ስትታገል ኖራለች።
ዴይሊ ኔሽን ያነጋገራቸው የኬንያ ሽኩርት ነጋዴዎችም ከሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ገዢዎች ከፍተኛ ፉክክር እንደሚገጥማቸው አምነዋል።
“ሽንኩርታችንን ከታንዛኒያ ከማንጎላ እና ከሲንጊዳ እናስመጣ ነበር። ነገር ግን እየጣለ ባለው ዝናብ ሰብሉ ወድሟል፤ በታንዛኒያ የዝናብ መጠኑ ከቀጠለ በሚቀጥሉት ወራት እጥረቱ እና የዋጋ ንረቱ ሊባባስ ይችላል። የኬንያ የሽንኩርት ምርት የምስራቅ አፍሪካን ፍላጎት ማርካት ባይችልም ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳ ሁሉም ከኬንያ በመጡ የሽንኩርት አቅርቦቶች ላይ የተመሰረቱ ናቸው” ሲል በናይሮቢ ማሪኪቲ ገበያ ላኪ የሆኑት ሚስተር ቻርለስ ዋምቡጉ አብራርተዋል።
የኬንያ ሽልንግ ከታንዛኒያ ምንዛሪ አንፃር አለመረጋጋት ታይቷል፣ ይህም ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱንና ለኬንያ ነጋዴዎች ተጨማሪ ወጪ እንዳስከተለ ዴይሊ ኔሽን ዘግቦል።