“ደም መፋሰሱ የእርስ በርስ ግጭቶችን በአስቸኳይ ይቁም!!” 

“ደም መፋሰሱ የእርስ በርስ ግጭቶችን በአስቸኳይ ይቁም!!” 

የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ

በሀገራችን ያሉ የእርስ በርስ ግጭቶችን ለማስቆም “ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ” በሚል በነፃነትና እኩልነት ፓርቲ  የተዘጋጀውን የእርቅ እና የሰላም ሀሳብ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ  ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል።

በሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ የእርስ በርስ ጦርነቶች መካሄደቸው የሚታወስ ሲሆን በተለይም ባለፉት ጥቂት አመታት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ግጭቶች መበራከታቸው ከህዝባችን የተሰወረ አይደለም። የእርስ በርስ ጦርነት ላፍታም ተለይቷት የማታውቀው ሀገራችን ባለፉት ጥቂት አመታትም የጦርነት አረር እየለበለባት ትገኛለች። በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ሀገራችን ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ዋጋ ከፍላለች።   

ለሁለት አመታት በትግራይ፣ በአማራ እና አፋር ክልሎች የተካሄደው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ህይወት ቀጥፏል። በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ዛሬም ድረስ የቀጠለው የወንድማማቾች ጦርነት የወገኖቻችንን ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል። በየአካባቢው በተለኮሱ ጦርነቶች ሳቢያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ውድ ህይወታቸውን አጥተዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ እድሜ ልካቸውን ያፈሩት ንብረት እና የሀገራችን ኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት ወድሟል፣ እየወደመም ይገኛል። በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ያለ አሳዳጊ፣ አረጋውያን ያለ ጧሪ ቀርተዋል። 

በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት አያሌ ኢትዮጵያውያን ለርሀብ፣ ለእንግልት፣ ለስደት እና ለሞት ተዳርገዋል። ወጣቶች በአፍላ እድሜአቸው በጦርነት እየተማገዱ ይገኛሉ። የሌሎች መጠጊያ የነበረች ሀገራችን፣ ዜጎቿ ጥለዋት እግራቸው ወደ መራቸው እንዲሰደዱ ተገደዋል።በጦርነት ምክንያት የእናቶች እንባ እንደ ጅረት እየፈሰሰ ነው። ሀገራችን ውስጥ ባሉ የእርስ በርስ ጦርነቶች ሟችም ገዳይም ኢትዮጵያውያን መሆናችን ጉዳቱን እጅግ አሳዛኝ ያደርገዋል።

በየአካባቢው የተከሰቱ ግጭቶች ማህበራዊ ግንኙነታችን እንዲበጣጠስ፣ በዜጎች መካከል ጥርጣሬ እንዲነግስ፣ ማህበራዊ ትስስራችን እንዲላላ፣ ጥላቻ፣ እልህ፣ በቀል እንዲስፋፋ፣ ስጋት እና ጭንቀት በዜጎች ልቦና እንዲሰፍን አድርገዋል። በጦርነት ምክንያት ሀገራችን የድህነት እና የርሀብ ተምሳሌት ሆናለች። ጦርነት ወደ ድህነት፣ ድህነት መልሶ ለጦርነት እየዳረገን በግጭት፣ በድህነት፣ በኋላ ቀርነት ቀለበት ውስጥ እየተሽከረከርን ዛሬ ላይ ደርሰናል። ዜጎች ሰላም ክፉኛ ናፍቋቸዋል። በሀገራችን እርቅ እና ሰላም ይወርድ ዘንድ ይጸልያሉ። ማን ያስታርቀን ብለው በተስፋ እና በጉጉት ይጠብቃሉ። 

#ነጻነትና_እኩልነት_ፓርቲ በሀገራችን ሁለንተናዊ ሰላም እንዲሰፍን፣ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲቆም፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነት፣ ከመከፋፋል ይልቅ መሰብሰብ፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፣ ከግጭት ይልቅ ሰላም፣ ከጥርጣሬ ይልቅ መተማመን እንዲሰፍን በመላው የሀገራችን ክፍል አስተማማኝ ሰላም እና መረጋጋት እንዲነግስ ባለፉት አምስት አመታት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። 

#ነጻነትና_እኩልነት_ፓርቲ ጦርነት መቼም ቢሆን የፖለቲካ ልዩነቶችን ለመፍታት የተሻለ አማራጭ እንዳልሆነ ያምናል። #ነእፓ የእርስ በርስ ጦርነት አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ የሌለው የመጨረሻ ውጤቱ የዜጎች ሞት፣ ስደት፣ ስቃይ፣ ሀዘን እና የሀገር ድቀት እና መፍረስ ነው ብሎ ያምናል። ጦርነት የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን ይበልጥ የሚያሰፋ እና የሚያባብስ፣ የሀገርን ምሰሶ የሚያፈርስ፣ ጥሪትን የሚበላ፣ ወረት የሚያሳጣ እኩይ ተግባር ነው ብሎ ያምናል። ጦርነት የዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍ፣ የሀገራችን አንጡራ ሀብት እንዲወድም፣ ልማታችን እንዲጨናገፍ ከማድረግ ያለፍ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል በቅጡ ይገነዘባል። 

#ነጻነትና_እኩልነት_ፓርቲ  ባለፉት አምስት አመታት በሰላም ዙሪያ በርካታ የውይይት መድረኮችን አዘጋጅቷል። በሰላም እና በአብሮነት ዙሪያ አባላቱን፣ ደጋፊዎቹን እና ዜጎችን ለማስተማር ልዩ ልዩ ሁነቶችን አሰናድቷል። በሰላም እና እርቅ ዙሪያ እጅግ በርካታ የአቋም መግለጫዎችን አውጥቷል። ለሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ምክረ ሀሳቦችን  ለግሷል። ጦርነትን በመቃወም፣ ግጭቶችን በማውገዝ፣ ሰላምን በመስበክ ላለፉት አምስት አመታት በተለያዩ መድረኮች በርካታ መልእክቶችን አስተላልፏል። “የጦርነት ጥሩ የሰላም መጥፎ የለውም” ብሎ የሚያምነው #ነእፓ፣ ጦርነት ከኢትዮጵያ ምድር እንዲጠፋ የበኩሉን አስተዋጾ ለማበርከት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል። ሀገራችንን ለክፉ ችግር፣ ህዝባችንን ማባሪያ ለሌለው ሰቆቃ የዳረጉ ጦርነቶች እንዲቆሙ #ነጻነትና_እኩልነት_ፓርቲ ዛሬም ጥረቱን የቀጠለ ሲሆን “#ኢትዮጵያ_በልጆቿ_ትታረቅ” በሚል ስያሜ አዲስ የእርቅ እና የሰላም ሀሳብ ነድፏል። ። 

“#ኢትዮጵያ_በልጆቿ_ትታረቅ” በሚል መጠሪያ የተዘጋጀው ይህ የእርቅ እና ሰላም ሀሳብ ፓርቲው በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን ሲያደርገው የቆየው ዘርፈ ብዙ የሰላም ጥረት አንድ አካል ነው። #ነጻነትና_እኩልነት_ፓርቲ የተጣላን የሚያስታርቁ የእምነት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ያሏት ሀገር በእነዚህ አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ያሉ ጦርነቶች በእርቅ ሊቆሙ ይገባል ብሎ ያምናል። #ነእፓ የሰላም አባቶች እና እናቶች፣ መክረው፣ ገስጸው፣ ገዝተው የሚያስታርቁ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ኡጋዞች፣ ሱልጣኖች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ስንቄዎች፣ የቤተክርስቲያን አባቶች፣ ቃዲዎች፣ ኢማሞች ያሏት ሀገር በእነዚህ የሰላም አባቶች እና እናቶች አማካኝነት የልጆቿን መገዳደል ልታስቆም ይገባል ብሎ ያምናል።   

የተጣሉ፣ ደም የተቃቡ ወገኖችን ማስታረቅ በሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ዘንድ የተለመደ አኩሪ ባህላችን እንደሆነ በጽኑ የሚያምነው #ነእፓ፣ ይህን ባህላችንን ተጠቅመን በጦርነት ምክንያት የሚጠፋው ህይወት፣ የሚፈሰው ደም፣ አላባራ ያለው የዜጎች ስደት፣ ዋይታ እና ለቅሶ በእርቅ ሊቆም ይገባል ብሎ ያምናል። #ነእፓ በጦርነት ምክንያት ልጆቻቸውን ያጡ እናቶች እምባ፣ የአባቶች ሀዘን እና ትካዜ፣ ጦርነትን ለመሸሽ ሀገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ ወጣቶች ስቃይ እና መከራ ማሳረጊያ ሊበጅለት ጊዜው አሁን ነው ብሎ ያምናል።  

#ነእፓ በሀገራችን ዘላቂ እና ሁለተናዊ ሰላም ለማስፈን የሚያደረገውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል “#ኢትዮጵያ_በልጆቿ_ትታረቅ” የሚል የእርቅ እና የሰላም ሀሳብ አዘጋጅቷል። #ነእፓ “#ኢትዮጵያ_በልጆቿ_ትታረቅ” ብሎ የሰየመው ይህ የእርቅ እና ሰላም ሀሳብ ዋና ዓላማ በመንግስት እና ከመንግስት ጋር ነፍጥ አንግበው በሚፋለሙ ማናቸውም ኃይሎች መካከል በሀገር ሽማግሌዎች፣ በኃይማኖት አባቶች እና በሌሎች ታዋቂ ስብእናዎች አማካኝነት እርቅ ማውረድ ነው። 

ይህ የእርቅ እና የሰላም ሀሳብ ይሳካ ዘንድ ተፋላሚ ወገኖች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም መላ የሀገራችን ህዝቦች የበኩላቸውን እንዲያደርጉ #ነእፓ ጥሪ እያቀረበ “ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ” መርሀ ግብር ተጨማሪ መረጃ እና ሂደት አስመልክቶ በቀጣይ ዝርዝር መረጃ የሚሰጥ መሆኑን እንገልጻለን። ሲልነጻነትና እኩልነት ፓርቲ   

መጋቢት 9 2016 ባወጣው መግለጫ ጥሪ አድርጎል።(en ኢትዮጵያነገ)

LEAVE A REPLY