የትግል አደራ አይታጠፍም፤ ዳግም በጅምላ አንገደልም!
ጠፍጣፋ ድንጋይ መሮ አይበሳውም
የአባቱን ታሪክ ልጁ አይረሳውም
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የማንነት እና ወሰን ጥያቄ ቀን ጠብቀን፤ ሒሳብ ሰርተን ብቅ ያደረግነው የዘር ካርድ ሳይሆን በመራር የፈተና እና የመከራ ወቅት ሳይቀር እስከ ኢያሪኮ ጎልቶ የተሰማ እውነተኛ የሕዝብ ድምጽ ነው፡፡ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ግፈኞች ቀን ሰጣቸው ብሎ ሳይፈራ፤ በጀምላ ተገደልኩ ብሎ ለነፍሱ እና ለቤተሰቡ ሳይራራ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በጽናት እና በብርታት ፊት ለፊት እንደተጋፈጣቸው ታሪክ ህያው ምስክር ነው፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጀግንነት እና ጽናት ራሳቸውን ግፈኞቹን መልሶ እስኪገርማቸው ድረስ ታንኩንም ባንኩንም ጠቅልለው በያዙበት ፈርጣማ ዘመናቸው ሳይቀር በእውነት እና በእውቀት፤ በመርህ እና በእልህ ታግሏቸዋል፡፡ “ማን ከገፋኝ ወደኩ” እንዲሉ ኢትዮጵያዊያን በብሂላቸው የትህነግ አፋኝ አገዛዝ እና ቆሞ ቀር ፖለቲካ ከመሀል ሀገር ተገፍቶ በአንድ ቦታ ብቻ እንዲወሸቅ ያደረገውም እውነተኛ የሕዝብ ትግል ውጤት ነበር፡፡
የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሕግ እና ሥርዓትን መርዂ አድርጎ በሰላማዊ የትግል መንገድ የወከለውን ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ለማስመለስ ከፍተኛ ትግል ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ኮሚቴው ሕግ እና ሥርዓትን በተከተለበት በሰላማዊ ትግሉ ሂደት የተሰጠው ምላሽ ግድያ እና አፈና ሆኖ በርካታ አይተኬ አባሎቹንና ወገኖቹን ሕይወት ገብሯል፡፡ እውነትና መርኽ በእጁ የሌለው አፋኙ እና ግፈኛው የትሕነግ አገዛዝ በሰላም የቀረበለትን ጥያቄ በጉልበት ለመቀልበስ ቃታ ስቦብናል፤ ከጅምላ ፍጅት እስከ ጅምላ እስር ድረስ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ተመጋጋቢ ወንጀሎችን ያለአንዳች ምህረት ፈጽሞብናል፡፡ ይሁን እንጂ ትግላችን እውነተኛ እና ፍትሐዊ በመሆኑ በርካታ ፈተናዎችን በጽናት ያለፈው የወልቃይት-ጠገዴ የአማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ፣ የአማራ ማንነት ትግላችን አጋር የሆኑ ፍትሕ ወዳድ ኢትዮጵያዊያንን በመያዝ መከራውን በብርታት፤ ችግሩን በጽናት፤ ሴራውን በትግል አሸንፈን አሁን ላለንበት ወሳኝ እና ታሪካዊ ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡
ከዚህ እስክንደርስ የተከፈለው መስዋዕትነት ግን እንኳን በወልቃይት ጠገዴ የአማራ ሕዝብ ቀርቶ በጎረቤቶቻችን የትግራይ ሕዝቦች ላይ እንኳ እንዲፈጸም አንፈልግም፡፡ ዛሬ እውነተኛ ማንነታችን፣ ሰላማችን አና መብቶቻችን ተከብረው እንደ ሰው መኖር ከጀመርን ሦስት ዓመታት ቢቆጠሩም ትናንት የሆነብንን እና የተፈጸመብንን ግፍ እና መከራ ግን ፈጽሞ ለአፍታ አንዘነጋም፡፡ እንዘንጋ ብንልስ ግህንብ፣ ማይካድራ፣ ጭና፣ተከዜና ሌሎች ሕያው ምስክሮች እያሉ እንዴት መዘንጋት ይቻለናል፡፡
ኮሚቴው፣ ባሳለፋቸው የሰላማዊ ትግል ጊዜያትም ሆነ ከነጻነት በኋላ ባሉ ወሳኝ የትግል ምዕራፎች ውስጥ የአማራ ሕዝብ ለዘመናት ዋጋ የከፈለበት የማንነት እና የወሰን ጥያቄው በዘላቂነት በሕግ ለማጽናት የመንግስትን አቅጣጫና የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት እየተከታተለና እየተጠባበቀ ባለበት በዚህ ወቅት ወያኔ-ህወሕት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ እና ከስምምነቱ በማፈንገጥ ዛሬም እንደ ትናንቱ ከስህተቱ የማይማር የደም ነጋዴ መሆኑን በግላጭ ለዓለም ሕዝብ አሳይቷል፡፡
እንደ ወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ፣ ትሕነግ ለአራተኛ ዙር በከፈተው የጦር ወረራ የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረም እና ዛታ አካባቢዎችን በኃይል መውረሩን፣ በዚህም የደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አጠቃላይ ሁኔታውን በአንክሮ እየተከታተልን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይህ ሕገ-ወጥ የጦር ወረራ በትሕነግ መከፈቱን ተከትሎ በራያ እና አካባቢው አመራሮችና የጸጥታ መዋቅሩ አባላት ላይ በደረሰው ህልፈተ ሕይወት ኮሚቴው ሐዘኑን ይገልጻል፡፡
ትህነግ አሁን የጀመረውን አደገኛ ጠብ-አጫሪነት አደብ ማስያዝ ካልተቻለ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ዳግም ላለመወረር አስፈላጊውን የትግል አማራጮችን በመጠቀም ያገኘውን ነፃነት በዘላቂነት ለማጽናት ሞት አይቀርም፤ሥም አይቀበርም!! ብሎ ለእውነት፣ ለነጻነት እና ለማንነት እስከ ወዲያኛው ለማለፍ ዝግጁ መሆኑን ኮሚቴው ያሳስባል፡፡
ትሕነግ ራሱ በለኮሰው እሳት ተለብልቦ የፕሪቶሪያውን የሠላም ስምምነት ሳይወድ በግድ የተቀበለ ቢሆንም፣ በስምምነቱ መሠረት የተቀመጡትን ከእሱ የሚጠበቁ ኃላፊቶችና ግዴታዎች ተግባራዊ እንዳላደረገ የሚታወቅ ነው፡፡ ድርጅቱ ሁልጊዜም በቅጥፈትና በማታለል ዓላማዬን አሳካለሁ ብሎ የሚያምን፣ ለራሱ የተጋነነ ግምት የሚሰጥ፤ በየትኛውም የሕግ፣ የሞራልና የፖለቲካ መርሆ የማይታጠር በየትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው ፈሊጥ የሚጓዝ ኃይል ነውና እርሱ ያላከበረውን ስምምነት እንዲከበርለት ሲወተውት ቆይቶ፣ ሲገዘግዘው የቆየውን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ዛሬ በግላጭ ራሱ ጥሶታል፡፡
የትሕነግ የዘመናት ባሕርይ ‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል› በሚለው የአበው ብሂል የሚገለጽ ነው፡፡ ሁልጊዜም ጩኸት በመቀማት የታወቀ ቡድን በመሆኑ የሰላም ስምምነቱን ከምር ተቀብሎ የታጠቀውን መሣሪያ ማስረከብ፣ ያደራጀውን ሠራዊት መሸኘት እና ቀጠናው ወደተሟላ ሰላም እንዲመለስ የሚጠበቅበትን መፈፀም ሲገባው እንደለመደበት ማጭበርበር ሲብስ ደግሞ ኃይል በመጠቀም ዳግም ወረራ በመፈጸም ፍላጎቱን በጉልበት ሊያሳካ በመሞከር ላይ ነው፡፡ ትሕነግ ዛሬም እንደትናንቱ ከስሌት ይልቅ በስሜትና በማን-አህሎኝነት አስተሳሰብ የሚመራ በመሆኑ ወልቃይት ጠገዴ በእኔ ሥር ይሁን፣ ካልሆነ በኃይል ለመውረር ተከዜን እንደሚሻገር በወንድም የራያ አማራ ሕዝብ ላይ የጦር ወረራ በመፈጸም ቀጣይ አቅጣጫውን ከወዲሁ እያሳየን ነው፤ በርግጥ በዚህ ድርጊቱ ፀረ-ሰላምነቱን ለመላ ኢትዮጵያዊያንና ለዓለማቀፉ ማኀበረሰብ ለአራተኛ ጊዜ አረጋግጧል፡፡
ዓለም በአደባባይ እንደሚመለከተው እኛ ጥያቄያችን ተፈጥሯዊ የሆነ የእውነት እና የፍትሕ ጥያቄ ነውና የዘመናት ጥያቄያችን ሕጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እየሠራን እንገኛለን፡፡ በሌላ በኩል እብሪት ከሚነዳው ወራሪ ቡድን ራሳችን ለመከላከል ሁልጊዜም ሁላችንም ዝግጁዎች ሆነን መገኘት እንዳለብን ኮሚቴው በአጽንዖት ያሳስባል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት ትግል የሁሉም፣የሁልጊዜምና በሁሉም ቦታ ሁሌም ዝግጁ ሆኖ መገኘት ነው ብሎ ኮሚቴው ያምናል፡፡
እንደሚታወቀው የወልቃይት-ጠገዴ የማንነት እና የወሰን ጥያቄ ታሪክን፣ ፖለቲካን እና ነባራዊውን ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሕግ አግባብ ለባለቤቶቹ እንዲጸና አለመደረጉ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ሊኖር የሚገባውን መተማመን ሸርሽሯል፡፡ ጤናማ ግንኙነት እንዳይኖር ይልቁንም የሀገረ-መንግሥቱ ጠላቶች በሚፈልጉት መንገድ ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶች የደስታ ምንጭ፤ ለገዛ ሕዝቧና ለወዳጆቿ ደግሞ አሳዛኝ፣ የታሪክ ጠባሳ የሚያሳርፍ ታሪካዊ ስህተት በመሆኑ በፍጥነት ሊታረም ይገባል፡፡
አሁንም ቢሆን ወንድም በወንድሙ፤ ወገን በወገኑ ላይ በመተኮስ የሚወሳሰብ እንጂ የሚፈታ ችግር የለም፡፡ በመንግሥት በተለይም በፌዴራል መንግሥት በኩል መሠረታዊዎቹን የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ ከመመለስ ውጭ የኃይል አማራጭ መከተል አደጋው የከፋ ነው፡፡ ከግጭት አዙሪት መውጣት የሚቻለው መሠረታዊውን የሕዝብ ጥያቄ በሰከነ መንገድ፣ ከልብ በመመለስ ብቻና ብቻ ነው፡፡
ስለሆነም፡-
የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ ፍትሐዊ እና ሕጋዊ ብቻ ሳይሆን፤ የትግሉ አስኳልና የ2010ሩ የፖለቲካ ለውጥ መነሻ በመሆኑ፤ ገዥው ብልጽግና ፓርቲና የሚመራው የኢፌዴሪ መንግሥት ጉዳዩን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያየው በድጋሚ እናሳስባለን!
ምንጊዜም ቢሆን ትግላችን ሕዝባዊ መሰረት ያለው እንጅ በመዋቅር ላይ የሚንጠለጠል አይደለም፡፡ መዋቅር የሚያስፈልገው የሕዝብን የትግል ዓላማ በተሰናሰለ መልኩ ለማስፈጸም ነው፡፡ አሁንም ቢሆን መዋቅር በማፈረስ የሚጣል የማንነት ትግል አጀንዳ የለንም፡፡ ለአማራዊ ማንነታችን በዘላቂነት መከበር እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ ሕዝባችን ኃይላችን፤ ጉልበታችን ሕዝባዊነታችን ሆኖ ይቀጥላል፡፡በመሆኑም ትግላችን ሕዝባዊ ሆኖ እንደሚዘልቅ እናረጋግጣለን!!
የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ ፍትሐዊ እና ሕጋዊ መሆኑን በመጣንባቸው የትግል ምዕራፎች አስመስክረናል፡፡ ለዚህ እልፎችን በሰማዕትነት ለገበርንበት፣ የአማራ ሕዝብ የትግል አስኳል ሆኖ ለቀጠለው የወሰንና ማንነት ጥያቄያችን በዘላቂነት መመለስ እስከመጨረሻው ፀንተን እንቆማለን!! ‹ወልቃይት ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ› በሚል በመላ አማራ ዋጋ የከፈሉ ወገኖቻችን ሁሉ ሰማዕትነታቸውን እንዘክራለን፤ ቃላቸውን እንፈጽማለን፤ መቼውንም ቢሆን የትግል አደራ አይታጠፍም; ዳግም በጅምላ አንገደልም!!
የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ትላንት፣ ዛሬም ሆነ ነገ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊነት ክብር ዘብ ቆሞ የኖረና የሚኖር ሀገር ወዳድ ፍቃደኛ ጠረፍ ጠባቂ ሕዝብ ነው፡፡ ሠላምን ለሚመርጡ ሁሉ ለአብሮነት ልቡ ክፍት ነው፡፡ በዚህ የሕዝባችን እሴት መሰረት የአማራ እና የትግራይ ሕዝብ ግንኙነት እንዲሻሻል እንጅ ወደለየለት ደምአፋሳሽ ግጭት እንዲሄድ አንፈልግም፡፡ ይሁን እንጂ የሁለቱን ሕዝቦች ለሺህ ዓመታት የዘለቀ አብሮነት አደጋ ላይ የጣለው ደደቢት በረሃ ላይ የተጸነው ጸረ-አማራ የጥላቻ ትርክትና ድኀረ-1983 ጀምሮ በመዋቅር ገቢር የተደረገው የጥላቻ ፖለቲካና የግዛት ተስፋፊነት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ህወሓት በትርክትና በተግባር ለሦስት አስርት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ያደረሰው የወል ሰቆቃ፣ የዘር ፍጅትና የታሪክ ቁስል በትልቁ ሰንጠረዥ መገኛው ወልቃይት ጠገዴ ላይ ነው፡፡ይህ ምድር በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ‹አሀዱ› ተብሎ የተጀመረበት የግፉዓን ምድር ስለመሆኑ ከፍትሕና ነጻነት ወዳድ ትግራዋያን የተሰወረ አይደለም፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ የጅምላ እስራት፣ ከርስትና ቀየ በግፍ መፈናቀል፣ ያለፉት ሰላሳ ዓመታት የሕዝባችን የወል ሰቆቃዎች መሆናቸውን የትግራይ ሕዝብ ያውቀዋል፡፡ ይህም ሆኖ የወልቃይት-ጠገዴ ሕዝብ ዋነኛ ቅራኔው በሕግ፣ በሞራልና በፖለቲካ መርሆ ከማይመራው፣ በየትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው ፈሊጥ ከሚጓዘው ትሕነግ ጋር እንጅ ተፈጥሯዊ ድንበራችን የሆነውን ተከዜ ወንዝን በጋራ ከምንጋራው የትግራይ ወንድም ሕዝብ ጋር አይደለም፡፡ ከተከበረው የትግራይ ሕዝብ ጋር በሰላማዊ ጉርብትና ተከባብሮ መኖር ጽኑ ፍላጎታችን ነው፡፡ ዛሬም ‹ሥርዓት ይመጣል፣ ይሄዳል፤ የህዝብ ግንኙነት ግን ቋሚና ዘላቂ ነው› ብለው ያመኑ የኩናማ፣ የኢሮብ፣የትግራይ… ተወላጆች በዞናችን ውስጥ ደህንነታቸው ተጠብቆ በሰላም እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ በትሕነግ የአገዛዝ ዘመን የወንጀል ተሳትፎ የሌላቸው፣ ሕግና ሥርዓትን አክብሮ የሚንቀሳቀስ ትግራዋይ በወልቃይት ጠገዴ ምድር በሠላምና በነጻነት መኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን እኛ የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች፣ ማንነታችን አማራ በመሆኑ አስተዳደራዊ ክልላችን የማንነታችን አካል ከሆነው የአማራ ክልል ጋር ሆኖ በሕግ እንዲጸናልን ዛሬም ሆነ ነገ በጽናት የምንታገልለት ሕዝባዊ ዓላማችን በመሆኑ የተከበረው የትግራይ ሕዝብ የትግላችን አጋር እንዲሆን ጥሪ እናቀርባለን፡፡
የወልቃይት-ጠገዴ የአማራ ማንነት ትግላችን ፍትሐዊ እና ሕጋዊ በመሆኑ፤ ሌሎች ፍትሕ ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የጥያቄያችን ተጋሪ ሆነው ከጎናችን የቆሙትን እያመሰገን የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ የአማራን የህልውና ጥያቄ የመመለስ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዘረፈ ብዙ የኢትዮጵያ ደህንነት ጉዳይ በመሆኑ መላ ኢትዮጵያዊያን ለጋራ ህልውናችን እስከመጨረሻው ከጎናችን እንዲቆሙ ጥሪያችንን በድጋሚ እናቀርባለን!
ዓለማቀፉ ማኀበረሰብ ሊያውቀው የሚገባ እውነት፡- በወልቃይት-ጠገዴ የዘመናት የአማራ ማንነት ጥያቄ ላይ የሚሰራ ስህተት ከኢትዮጵያም አልፎ የመጭውን አርባና ሃምሳ ዓመት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን ሊያወሳስብ የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ይህ ቀጠና ተጨማሪ ጦርነት የማስተናገድ አቅም የለውምና የፕሪቶሪያውን የሠላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ የጣሰው የትሕነግ ኃይል አሁንም ለቀጠናው አለመረጋጋት ቁልፍ ስጋት መሆኑ ታውቆ ከዚህ አጥፍቶ ጠፊነት ተግባሩ እንዲታረም፣ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄም ከታሪክ፣ ከሕግ፣ ከሞራል፣ ከፖለቲካና ነባራዊ ሁኔታዎች አኳያ ምላሽ እንዲሰጠው በጎ ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን!!
በመጨረሻም
ኮሚቴው፣ዛሬም ትግል ላይ ነው፡፡ ትግሉ ደግሞ ራስን የመሆን ክቡር ትግል ነው፡- የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ትግል፡፡ ወልቃይት ጠገዴ ጎንደር በጌምድር አማራ ነው! የትግሉ ዓላማ ግን ከዚህም የተሻገረና ከፍ ያለ ነው፡፡ ትግሉ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራን ኮሪደር አስከብሮ የኢትዮጵያን ህልውና የመጠበቅ ሀገራዊ ትግልም ነው፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ትሕነግ እያለን ያለው ወደ ወልቃይት ጠገዴ አስገቡኝና ዛሬም እንደ ትናንቱ ከሰው በታች ላድርጋችሁ፣ ዛሬም እንደትናንቱ ላዋርዳችሁ፣ እንደተለመደው ማንነታችሁን ላጥፋ፣ ልጨፍጭፋችሁ ነው፡፡ ይህን መፍቀድ ራስን በራስ እንደማጥፋት ይቆጠራል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ይህ የሚሆነው በመቃብራችን ላይ ነው ብሎ ከወከለው ሕዝብ ጋር የትግል ቃል ኪዳኑን አድሶ ተነስቷል፡፡
ስለሆነም ትናንት የወልቃይት ጠገዴ አማራ ህዝብ ሲጨፈጭፍህ፣ሲያሳድድህ፣ሲገድሉህ የነበረው ትህነግ/ወያኔ/ ታግለህ ማንነትህንና ነፃነትህን ተጎናጽፋሃል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም እንደ እባብ አፈር ልሶ ማንነትህንና ነፃነትህን ለመቀማት፣ህልውናህን ለማጥፋት ሙሉውን የትግራይ ህዝብ አሰልፎ ታጥቆ እየመጣብህ ነውና ማንነትህንና ነፃነትህን ለማስጠበቅ፣ህልውናህን ለማረጋገጥ መላው የወልቃይት ጠገዴ ህዝብና መላ የአማራ ህዝብ ዛሬም እንደ ትናንቱ ጨርቄን ማቄን ሳትልና የውስጥህ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለደመኛውና ለጥንተ-ጠላትህ ወያኔ ለማጥፋትና ለመደምሰስ በጋራ እንቁም ይላል ኮሚቴው፡፡
ምንግዜም ለአማራዊ ማንነታችን ትርጉም ያለው መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን!
አንድ ሞት እንጂ ሁለት ሞት የለም!!
ከወልቃይት-ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
ሁመራ-አማራ-ኢትዮጵያ
ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም