የአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ያለ ማስረጃ ክፍያ ተፈጽሟል...

የአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ያለ ማስረጃ ክፍያ ተፈጽሟል አለ

/ውድነህ ዘነበ/
• የኦዲት ግኝት የቀረበባቸው ተቋማት በአንድ ወር ውስጥ ምላሽ እንዲሰጡ ታዘዙ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር ባቀረበው የስድስት ወራት ሪፖርት ለማን እንደሚከፈል ማስረጃ ያልቀረበለት 1.099 ቢሊዮን ብር ክፍያ እንደተፈጸመ ይፋ አደረገ፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የአንበሳውን ድርሻ ይዟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ 89.9 ሚሊዮን ብር በጉድለት መገኘቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ በዚህ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን 71.5 ሚሊዮን ብር፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት 18.5 ሚሊዮን ብር፣ በድምሩ 89.9 ሚሊዮን ብር ጉድለት ተመዝግቦባቸዋል፡፡

አዲስ ዙ ፓርክ፣ ራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት 11 እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤቶች ግንባታ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ደግሞ 767.6 ሚሊዮን ብር በወቅቱ ፈሰስ አላደረጉም ይላል የኦዲት ግኝት ሪፖርቱ፡፡

የዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል ደግሞ 2.7 ሚሊዮን ብር በማነስ የተመዘገበ ሒሳብ እንዳለው ታውቋል፡፡ የኦዲት ሪፖርቱ እንደሚለው ለማነስ ምክንያት በሥራ ተቋራጮች ቅድመ ክፍያ 2.7 ሚሊዮን ብር በእያንዳንዱ የክፍያ ሰርተፍኬት ተቀንሶ ሳይሰበሰብ መገኘቱ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ቤቶች ግንባታ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትና ዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል በድምሩ 168.09 ሚሊዮን ብር ማስረጃ ያልቀረበበትና ለማን እንደሚከፈል የማይታወቅ ክፍያ ፈጽመዋል ሲል ሪፖርቱ ገልጿል፡፡

በተጨማሪ ከግዢ ደንብና መመርያዎች ውጪ በጨረታ አሸናፊ ካልሆነ ድርጅት ግዢ መፈጸም፣ ውል ሳይገባ ግዥ መፈጸም፣ ያለ ጨረታ ግዥ መፈጸም፣ በቴክኒክ ኮሚቴ አስተያየት ሳይሰጥበት ግዥ መፈጸም በሪፖርቱ ቀርበዋል፡፡ በዚህ መሠረት 12.5 ሚሊዮን ብር ግዥ የፈጸሙ ተቋማት ተብለው በኦዲት ሪፖርቱ የተጠቀሱት የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ አዲስ ዙ ፓርክ፣ የአዲስ አበባ የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ቢሮ ናቸው፡፡
ተከታታይ ቁጥር በሌለውና ሕጋዊ ባልሆነ ደረሰኝ 87.2 ሚሊዮን ብር ክፍያ የፈጸሙት ደግሞ የካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ፣ ዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል፣ ራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታልና ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት 11 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ናቸው ተብሏል፡፡

የመንግሥት የግዢ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 3/2002 ክፍያ መፈጸም ያለበት ሕጋዊ በሆነ የገቢ ክፍያ መለያ ቁጥር ባለው ደረሰኝ መሆን እንዳለበት ቢገልጽም፣ ተቋማቱ ይኼንን መመርያ መተላለፋቸውን የአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር ሪፖርት ይገልጻል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ 107.6 ሚሊዮን ብር ንብረት ክፍል ገቢ ስለመደረጋቸው ማስረጃ ሳይያያዝ ክፍያ መፈጸሙን ሪፖርቱ ገልጿል፡፡

አስገራሚ ሆኖ የተገለጸው ክስተት ደግሞ፣ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በኮንትራክተሮች ስም የተሽከርካሪ ግዥ 34.5 ሚሊዮን ብር የፈጸመ መሆኑ በኦዲት ምርመራ ወቅት ተሽከርካሪዎቹ ወደ ባለሥልጣኑ ሳይዛወሩ መገኘታቸው ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር ወ/ሮ ጽጌ ወይን ካሳ ዓርብ የካቲት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባቀረቡት በዚህ የኦዲት ሪፖርት፣ የኦዲት ግኝት በተገኘባቸው ተቋማት ላይ የተጠያቂነት ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

ይኼ ሪፖርት በቀረበበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡

ከንቲባ ድሪባ ኩማና ምክትል ከንቲባ አባተ ስጦታው ይኼ ጉዳይ በአስቸኳይ ተጣርቶ ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡ የኦዲት ግኝት ያለባቸው መሥሪያ ቤቶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲሰጡ ከንቲባው ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

LEAVE A REPLY