ከመማረር ማምረር (ይገረም አለሙ)

ከመማረር ማምረር (ይገረም አለሙ)

ሰሞኑን የአቶ ኃብታሙ አያሌውን ቃለ ምልልስ በአሜሪካ ድምጽ ራዲ የአማርኛው ክፍል አዳምጠን ብዙዎች አዝነናል፣ አልቅሰናል፣ ተናደናል፣ ወያኔን ተሳድበናል አውግዘናል ወዘተ፡፡በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው ቦታ በደረሰው አልቂትም እንዲሁ፡፡ ይህ ሁሉ ግን በሰማን ቁጥር አዲስ ለሚሆንብን ለእኛ አንጂ አዲስ አይደለም፡፡ አቶ ኃብታሙ በህይወት ተርፎ በነጻናት መናገር የሚቻልበት ሀገር ተሻግሮ ሊነግረን በመቻሉ እንጂ ከዚህ የባሱ ብዙ አጅግ ብዙ ኢ-ሰብአዊ የሆኑ ዘግናኝ ድርጊቶች በኢትጵያውያን ላይ ተፈጽመዋል፡፡ የቆሼውም እልቂት መሀል ከተማ በመሆኑና የመገናኛ ብዙኃን ፈጥነው ስላስተጋቡት ታየ ተሰማ እንጂ ከከተማ በራቁ፣ ከመገናኛ ቴክኖሎጂ እይታ በተደበቁ ቦታዎች ብዙ ድርጊቶች ተፈጽመዋል እየተፈጸሙ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሀገር የመውጣት እድሉን ያገኙ ሰዎች ያጋለጡትን በሶማሌ ክልል የተፈጸሙ ኢሰብአዊ ድርጊቶችን በዋቢነት መጥቀስ እችላለሁ፡፡Ato Habtamu Ayalew (UDJ)

እንኳ የተደበቁትን ያየን የሰማናቸውን በሳምንት የምንረሳ፣ዋይታችን የአንድ ሰሞን፣ ለቅሶአችን እስከሰልስት፣ ፉከራ ድንፋታችን በመገናኛ ብዙኃን ሆነና ድርጊቱ ቀጥሏል፡፡ሙቀታችን እንደ ብረት ምጣድ፣ ወኔአችን የአንደበት ነውና አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው እንዲሉ ወያኔ አይቶ ገምቶ ምንም አያመጡም ብሎ ንቆ “ግመሉም ይሄዳል ውሾቹም ይጮሀሉን” እየተረተብን ግዞቱን ቀጥሏል፣ ይቀጥላል፡፡

አቤት! የአንድ ሰሞኑን ዋይታ ሰንችልበት፣ደግሞ ለማልቀስ ብቻ አይደለም ለማላቀስም የተካንን ነን፣ ቁስል እየነካካን፣ብሶት እየቀሰቀስን በበደል ላይ በደል መጨመሩን ሀዘን ማክበዱን እናውቅበታለን፡፡ወያኔን ማማረሩን ማውገዝ መኮነኑን አንችልበታለን፤ ይህ ሁሉ ግን የችግሩ ምክንያት የሆነውን ወያኔን ማስወገድ ቀርቶ ችግሩን መቅረፍ እንኳን አላስቻለም፣ አያስችልምም፡፡

ቢሆንማ ኖሮ የሩቁን ትተን ከእሬቻ እልቂት በኋላ፣ ከቂልንጦ እስር ቤት ቃጠሎ በኋላ በችሎት ከሰማናቸው በየእስር ቤቱ ከተፈጸሙ አረመኔያዊ ደርጊቶች በኋላ ወያኔ በጥፋቱ በአረመኔያዊ ተግባሩ ባልቀጠለ ነበር፡፡ ታዲያ ዋይታ፣ለቅሶ፣ጩኸት ውግዘትና ፉከራ ወዘተ ፋይዳ ካላመጣ መልሶ ቀልሶ ያንኑ ብቻ መፈጸም ምን ይሉታል፡፡ የሞኝ ለቅሶ መልሶ ቀልሶ ካልሆነ በስተቀር፡ ታማኝ በየነ ተጠያቂ ሆኖ በቀረበበት የቴሌቪዥን ፕግራሙ በወያኔ ስለደረሰብህ ነገር ተብሎ ሲጠየቅ፣“በፍጹም አልናገርም ..ለሰከንድም ቢሆን ደስ እንዲላቸው አልፈልግም..ደግሞስ ካደረጉት ሌላ ከእነርሱ ምን እጠብቃለሁ፣ ”ወዘተ (ቃል በቃል አልጠቅሼ ይሆናል) በማለት የተናገረው ለሚረዳው ትልቅ መልእክት ያለው ነው፡፡

ከመማረር ማምረር-

አቶ ሌንጮ ለታ በትብብሩ በተዘጋጀ አንድ መድረክ ላይ ሀያ አምስት አመት በየኤምባሲው እየሄድኩ ወያኔን አምቻለሁ ያመጣው ለውጥ ግን የለም ሲሉ የመጣንበትን መንገድ እንለውጥና ከሀሜት ወደ ድርጊት እንሸጋገር ማለታቸው አንደሆነ አድርጌ ነው የተረዳሁት፡፡ ከብዙ ጩኸት ጠብታ ድርጊት ይበልጣል፡፡

በተለያየ መንገድ በወያኔ ውስጥና ዙሪያ ተሰልፈው ተጠቃሚ ከሆኑት ጥቂት ሰዎች በስተቀር ሀያ አምስት አመታት ሙሉ ወያኔን ያላማረረ የለም፡፡በጣም የባሰበት በየቀኑ፣ እንዲያ ያለው በየሳምንቱ ፣ሻል ያለው በወሩ ዲያስፖራው ደግሞ ምክንያት በተገኘ ቁጥር በተለያየ መልክና መንገድ ያማርራል፣ግን በወያኔ ላይ የፈጠረው አንዳችም ነገር የለም፣በርግጥ ከዚህ ተጠቃሚ የሚሆኑ ይህንኑም ስራም የትግል ዘይቤም ብለው የያዙ መኖራቸው አጠራጣሪ ነው፡፡ እንደውም ተዋቂ ሰው እንዲታሰር የሚጸልዩ ሲፈታ የሚከፋቸው አሉ የሚል ነገር ከወደ ባህር ማዶ ነፋስ አመጣሽ ወሬ እንሰማለን፡፡

መማረር ብቻውን ውጤት እንዳላመጣ ሀያ አምስት አመት በተግባር ያየን ሰዎች ወደ ማምረር አለመሸጋገራችን በወያኔ የሚፈጸመው ሁሉ ወደዛ ደረጃ የማያደርሰን ሆኖ ነው? ለዚህ የአዎንታ መልስ የሚሰጥ ወያኔ ያልሆነ ወይንም ያልተከተበ ሰው ይኖራል ብዬ ማሰብ ይቸግረኛል፡፡ ታዲያ ወያኔ በየግዜው የሚፈጽማቸው ኢ.-ሰብአዊ፤ኢ-ህጋዊ የሆኑ አረመኔያዊ ተግባራት እያስቆጡን እያስጮኹን፣ እያስለቀሱን ሰልፍ እያስወጡን ወዘተ ከመማረር አልፈን ለማምረር ደረጃ መድረስ ያልቻልነው ለምንድን ነው? ይህ ጥያቄ አምርረው በርሀ የወረዱትን “ትእግስት ፍርሀት ሆኖ መናቅ ካስከተለ እኛም ቤት ጠብ-መንጃ እኛም ዘንድ ወኔ አለ” ብለው ቃታ መሳብ የጀመሩትን አይመለከትም፡፡

ለዚህ የሚቀርቡ ምላሾች ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ምክንያቶቹ እንደ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ሰብስቦች የሚለያይ በመሆኑ፡፡በዋነናት ሊጠቀሱ ከሚችሉት አንዱ ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም አዳፍኔ በተሰኘው መጽኃፋቸው “የመክሸፍ ምንጭ ትናንትና እና ነገን አለማሰብ ነው፤የወጣነውን ዳገትና የወረድንበትን ቁልቁለት ለይተን አለመረዳት፣ዳገቱን እንዴት እንደወጣንና ቁልቁለቱን እንዴት እንደወረድን በትክክልና በእውነት አለመገንዘብ ናቸው፤” ያሉት ይመስለኛል፡፡ ትናንትን የማያስታውስ ስለነገ የማያስብ ለእርሱ ህይወት ዛሬና የዛሬው ብቻ የሆነለት ወይንም የሆነበት እንደምን ከመማረር አልፎ ያመራል፡፡

ሌላኛው ምክንያት መማረር ማውራት ከፍ ካልም ሰልፍ መውጣት ሲሆን ማምረር ግን ድርጊት የሚጠይቅ መሆኑ ነው፡፡በፌስ ቡክ ወያኔንና ባለሥልጣናቱን ማወገዝ መስደብ ማብጠልጠል ለደቂቃዎች መተየቢያው ማሽን ፊት ከመቀመጥ ውጪ የሚያስከፍለው ነገር የለም፣ በራዲዮ ወይንም በቴሌቭን ወጥቶ መደስኮሩም እንዲሁ፣ አይደል የሚያስር የሚገላምጥ ፖሊስ በሌለበት ሀገር ሰልፍ መውጣትም ምን አልባት በእለቱ ይገኝ የነበረን ገቢ ያስቀር እንደሁ እንጂ ሌላ ጉዳት አየስከትልም፡፡ ሌላም ሌላም፡፡ እነዚህ የመማረር ውጤቶች ወይንም መማረር ያሚያመጣቸው ነገሮች ናቸው፡መደረጋቸውም አስፈላጊ ነው፡

ነገር ግን በመማረር ብቻ ያደረግናቸው ነገሮች ሀያ አምስት አመታት የሥርዓት ለውት ሊያስገኙልን ቀርቶ ወይኔን ከአረመኔያዊ ተግባሩ ሊመልሱት አልቻሉም፣ውጤት የሚገኘው በማምረር መሆኑ ባይጠፋንም ጎንደሮች አምርረው ሞክሩን ብትተኩሱ አንተኩሳለን ካሉበት ድርጊትም ማስታወስ ብንችል ማምረር ተግባር ይጠይቃል ለውጥም ያስገኛል፡፡ ነገር ግን የእኛ ተቃውሞ በማማረር ብቻ በመገደቡ ወያኔን ለማስወገድ መታገሉ ቀርቶ በአንጻሩ ሲንገዳገድ የምንደገፈው ምርኩዝ ሆነነው ይኼው እያላዘንን እያለቀስንና እያላቀስን አለን መኖር ከተባለ፡፡

ከዚህ ሁሉ የሚከፋው ግን የህዝቡን ምሬት ያስመራሪውን ኢሰብአዊ ድርጊት መጠቀሚያ የሚያደርጉት ናቸው፣ ለዚህ ደግሞ ማስረጃ ፍለጋ ብዙ ሳንማስን በኦሮምያና በአማራ ከመማረር ወደ ማምረር ተሸጋግሮ በነበረው የህዝብ እንቅስቃሴ ተጠቃሚ ለመሆን አልመው ሲሯሯጡ የነበሩ ሰዎችን አንዘነጋቸውምና በማስረጃነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ ታሪክ ላይ ድሪቶ እየሰፉ የወያኔን ድርጊት ትተን ከመቶ አመት በፊት የነበሩ ነገስታት ፈጸሙት በሚሉት የፈጠራ ታሪክ ላይ እንድናተኩር ሌት ተቀን የሚማስኑትም በዚሁ ጎራ ቢመደቡ ቦታቸው ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ሁሉም ወያኔ እንዲወርድ የማይፈልጉ ብቻ ሳይሆን በሥልጣን ላይ ሆኖም ህዘብን የማማረር ተግባሩን እንዲቀንስ እንኳን የማይሹ ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ሰው ካልታሰረ ወይ ካልተገደለ ንግዳቸው አያተርፍምና ልብ ብላችሁ አስተውላችሁ ከሆነ ወያኔ “በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እንዲሉ ሆኖ በሰላም ሀገር እየባነነና እየበረገገ በዜጎች ላይ በደል እንዲፈጽም በተለያየ መንገድ ያስደነብሩታል፡፡

ምን ይበጃል፤

መልሱ በቃል ደረጃ ቀላል በተግባር ግን ከባድ ነው፣ከመማረር ወደ ማምረር መሸጋገር፡፡ ከባዱ ነገር ለለውጥ አስፈላጊያችን ከአምባገነን አገዛዝ ለመላቀቅ አማራጭ የለሻችን መሆኑን ካመንን ሀምሳ ሎሚ ለሀምሳ ሰው ጌጡ አንደሚባለው በትንሽ በትንሽ እንደየአቅማችን ብንሸከም ከባዱን ቀላል እንዳርገዋለን፡፡ ማምረር ሲባል ሁሉም በአንድ ግዜ ሆ ብሎ መነሳት አይደለም፣ቢባልም መሆን አይችልም፡፡መሆን ያለበት የመማረር ውጤት በሆኑት በመድረክ ዲስኩር፣በፌስ ቡክ ቀረርቶ፣በሰላማዊ ሰልፍ ውግዘት፣በመገናኛ ብዙኃን ፉከራና ቀረር ብቻ (ብቻ የሚለውን ያጤኗል) ወያኔን የሚያህል አምባገነን ማስወገድ እንዳልተቻለ እንደማይቻልም ማመንና ከመማረር ወደ ማምረር መሸጋገር ከዛ ማምረሩ የሚጠይቀውን ነገር አቅም፣ ግዜ፣ ሁኔታና ያሉበት ቦታ በሚፈቅደው መጠን በመፈጸም ከውግዘት ወደ ድርጊት መሸጋገር፡፡ “ጋን በጠጠር ይደገፋል” የሚለውን ብሂል ማስታወስ ሳይጠቅም አይቀርም፡፡

ማምረሩ የሚጠይቀውን ለማድረግ ጠጠር እንኳን ማስቀመጥ ካልቻሉ ደግሞ በየመንገዱ ቆሻሻ እየጣሉ ያመረሩ ሰዎችን ጉዞ ላለማስተጓጎል መጠንቀቅ፡፡በህዝብ ምሬትና በወያኔ አስመራሪነት እየነገዱ ትርፉ የጣማቸው ሰዎችንም ከገበያው ማስወጣት ባይቻልም አውቆ በጥቅም ተጋሪነት ሳያውቁ በስህተት አናጋጅ ከመሆን መውጣት ፡፡

ቪነስ ሎምባርድ የተባለ ሰው የተናገረው ተብሎ እንደተጻፈው “ድል ማድረግ (ማሸነፍ) ምንግዜም ለጠንካሮች ወይንም ለፈጣኖች ብቻ አይደለም፣ ቢዘገይም ቢፈጥንም ድል እንደሚያደርግ ለሚያስብም ሰው ይሆናል” እና ይዘገይ እንደሁ እንጂ ለማይቀረው ድል በተልከስካሽነት በመቆም ለዛሬ ትዝብት አናትርፍ፣ ለነገ ለልጆቻችንም መጥፎ ታሪክ አናውርስ፣ የእገሌ ልጅ መባል ቀላል ነገር አይደለምና!

LEAVE A REPLY