ሆነና ነገሩ የተገላቢጦሽ ፣ አህያ ወደ ቤት ውሻ ወደ ግጦሽ /ይገረም አለሙ/

ሆነና ነገሩ የተገላቢጦሽ ፣ አህያ ወደ ቤት ውሻ ወደ ግጦሽ /ይገረም አለሙ/

አበው መሆን ያለበት ቀርቶ የማይሆነው ሲሆን ፣ ያለ አባቱ ያለወግ ሥርዓቱ የሆነ ነገር ሲያጋጥማቸው የሚገልጹበት ይህ አባባል ተቀዋሚ ተብሎ ለተሰለፈው ግን ምን ለምን እንዴት? አንደሚወም ለማያውቀው ቢያወቅም በወሬ እንጂ በተግባ  ለማይገኘው ወገን ድርጊት በጣሙን ገላጭ ይመስለኛል፡፡ ድርጊት እየጠቀሱና ማስረጃ እያጣቀሱ በዚህ አባባል የሚገለጹ በርካት ጉዳዮችን ማንሳት የሚቻል ቢሆንም ለዛሬ ግን አንዱን ብቻ በእጅጉ የተጠናወተንን የመርሳት በሽታ/ችግር ብቻ ላንሳ፡፡ ግን ከዛ በፊት ርእስ ያደረኩትን አባባል ባስታወሰኩ ቁጥር ፈጥኖ በአእምሮየ የሚመጣ አንድ ነገር አለ፣፡ ፕሮፌሰሩ ከአሜሪካ ወደ ትግል ሜዳ ኮረኔሉ ከትግል ሜዳ ወደ አውሮፓ ከአባባሉ ጋር የተዛመደ አይደለም ትላላችሁ፡፡ ኮረኔሉ ግዴለም መሄዱን ይሂድ እዛ ሆኖ ታጋይ ነኝ ማለቱ እንዲህም ብሎ አጃቢና ተከታይ ማግኘቱ ግን አዬ! እኛ ያሰኛል፡፡

የወጋ ቢረሳ የተዋጋ አይረሳ፣

አባባሉ የሚገልጸው በተግባርም የሚሆነውና መሆን ያለበት በዳይ ይረሳል ተበዳይ ግን ሁሌም ያስታውሳል ነው፡፡ እኛ ግን ሥልጣኔ ገብቶን ይሁን ይኼ የመንደር/የጎሳ ፖለቲካ አፍዝዞ አደንዝዞን፣  በደሉ ሳይሰማን ቀርቶ ይሁን  የዲያስፖራ ኑሮ አቅል ነስቶን ባይታወቅም የትናንቱን በደል እየረሳን ለዛሬው እንጮኻለን፣ የዛሬውን ደግሞ ነገ እንረሳውና ሌላ አዲስ ሲገጥመን ኡ.ኡ እንላለን፡፡ ለዚህ ዝርዝር ማቅረብ ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ ደግሞስ ሰንቱን አቀርቤ እችለዋለሁ፡፡ሌላው ቀርቶ ዛሬ በፕ/ር ዓሥራት ወልደየስ ስም ለመነገድ የሚጣጣሩት ወገኖች እንዴትና በምን ሁኔታ እንደሞቱ አያስታውሱም ማስታወስም አይፈልጉም፡፡ በአስክሬናቸው የሽኝት ፕሮግራም ላይ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን ያቀረቡትን ግጥም ማግኘት ባልችልም አሰራት…በሽታህ እንኳን ሳይታወቅ ያሉትን እነዚህ ወገኖች ስለማወቃቸው እጠራጠራሉ፡፡ ለሞት ያበቃቸው በሽታ ምንነት መታወቅ ትልቅ ፋይዳ ያለው ቢሆንም ይህን ያሰበበት ቀርቶ የሚያስታውሰው የለም፡፡  ይህም በመሆኑ ከዛ ወዲህ በተለያየ ግዜ ታስረው የተፈቱ ፖለቲከኞች እነርሱ እንኳን በማያውቁት ሁኔታ በእስር ቤት የተለያየ ነገር ተሰጥቶአቸው  ጤናቸው ታውኮ እንኳን ለእስር የበቁበትን ፖለቲካ ሊቀጥሉ  ኑሮአቸው ደራሲው  አቤ ጉበኛ  “ባልሞትም ሞቻለሁ” አይነት ኑሮ የሚገፉ ቢኖሩም እኛ ግን አናውቃቸውም፡፡ እኛ ጉደኞቹ የገደለንንም የሞተልንንም እኮ ነው የምንረሳው፡፡

በተደጋጋሚ አስረውት እምቢ ሲላቸው አፍነው ወስደው የት እንዳደረሱት፣ ምን እንዳደረጉት የማይታወቀውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪና የመአህድ አባል የነበረውን ወጣት  ስንት ሰው ያስታውሰዋል፡፡ የሚገርመው ፓርቲዎችም የተገደሉ የተሰወሩ በወህኒ ያሉ አባሎቻቸውን ማስታወስ አይደለም አይውቋቸውም፡፡እንዲህ እንዲህ እየተባለ ሰንቱ ተነስቶ ይዘለቃል፡፡ የወያኔ የግፍ ተግባር ብዛቱ ይሆን እንድንረሳ የሚያደርገን? አይመስለኝም፡፡ እንደውም የሀገሬ አርሶ አደር “ሰው ግደሉ ሰው መግደል ይበጃል እንዲህ እንዲሁ ሲል ጠላት ይደረጃል” ነበር የሚለው፡፡ እኛ ግን በወያኔ የሚፈጸመው ማናቸውም ነገር ሊያደረጀንና ሊያደራጀን ቀርቶ በደሉ ግፉ ራሱ አይታወሰንም፡፡ ይህም ለወያኔ በእጅጉ ጠቅሞታል በሥልጣን የመቆያው ዋናው መፍትሄም ሆኖታል፡፡

የትናትን ግድያ አፈናና እስር የሚያስታወስ ፈጻሚው በቦታው እስካለ ድረስ ዛሬም መደገሙ ነገም መቀጠሉ አይቀሬ መሆኑን ስለሚረዳ መላ ይመታል ዘዴ ይዘይዳል፡፡ የመላውም የዘዴውም ማጠንጠኛው ደግሞ አንድ ነው፡፡ አጥፊ እስካለ ጥፋት ገዳይ እስካለ አለአግባብ መገደል ወዘተ አይቀርምና አጥፊውን ማስወገድ ገዳዩን አስቀድሞ መግደል ፡፡ የሸረሪቷን ድር በየቀኑ በማጽዳት ከመቸገር እሷን አስወግዶ መገላገል የሚባለው ለዚህ አይነቱ ነገር ይመስለኛል፡፡

እኛ ግን የትናቱ ለዛሬ የሚረሳን በመሆኑ ሲፈጸም ማላዘን እንጂ  አጥፈውን አስወግደን እፎይ ለማለት ቀርቶ  እንዳይደገም ለመከላከልም ለመጠንቀቅም የምንችል አልሆንምና በአንድ አስተሳሰብ እየተመራን በአንድ መንገድ እየተጓዝን ወያኔ እየረገጠን እኛ ደግሞ ርስ በርስ በምንችለው በአለ አቅማችን እየተረጋገጥን እንዳለነው አለን፡፡ ይቀጥላልም፡፡

ወያኔ ግን የተሰራበትን አይደለም የሰራውንም አይረሳም፣ አያችሁ! እዚህም ጋር የተገላቢጦሽ ነው ነገሩ፡፡ የሚባለው መሆንም ያለበት “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ” ነበር፣ ግና የተገላቢጦሽ ሆነና ነገሩ እኛ ተወግተን ስንረሳ ወያኔ ግን የወጋውንም የተወጋውንም  አይረሳ፡፡ ለዚህም ነው አንድም ነገር በቸልታ የማያልፈው፣ ንቆ የማይተወው፡፡እንደውም በገዛ ጥላው ሳይቀር እየደነበረ ኮሽ ባለ ቁጥር የሚተኩሰውና ንጹሀንን የሚገለው፣የሀሰት ክስ እየፈበረከ የሚያስረው፡፡አሰቡ ብሎ የሚወነጅለው፡፡

ከደደቢት አንስቶ በተናጠል በዜጎች ላይ በጅምላ በሀገርና በሕዝብ ላይ የፈጸመውን የማይረሳው  ግዝፈቱን ኢህጋዊና ኢሰብአዊነቱን ስለሚያውቀው ከሥልጣን ቢወርድ ስለሚጠብቀው የህግ ተጠያቂነት በማሰብ ነው፡፡ ለወያኔ ይህን መርሳት ማለት የሥልጣን ማጥበቂያ ሰንሰለቱን፣ ማስጠበቂያ ጡንቻውን አላላ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም  አያደርገውም፣ ሁሌ ያስታውሰዋል፣እናም ትንሽ ኮሽ ሲል ጠመንጃውን ወልውሎ ምላሱን ስሎ ይሰለፋል፡፡ ራሱን ይሰድባል ባለሥልጣናቱን ይወነጅላል ( ነገር ግን አይጠየቁም) ይህን እደርጋለሁ በዚህም በኩል እዘምታለሁ በማለት ይቀላምዳል፡፡ ውሸትህ ሰለቸን ፣ የበሰበሰ ይጣላል እንጂ አያገለግልም፣ ስሩ የደረቀ ዛፍ ተነቅሎ ይወገዳል እንጂ ውኃ አያጠጡትም አይኮተኩቱትም ሲባል የተካነበትን ጠመንጃውን ያሰቀድማል፡፡

የተደረገበትን የሚያስታውሰው ደግሞ እንዳይደገምበት ነው፡፡ በገፍ ያሰራቸውን ዜጎች “አይደገምም” የሚል ጽሁፍ ያለበት ካናቴራ አልብሶ መልቀቁን ረሳነው ይሆን! ፡፡ ሥልጣን ለወያኔ የቤተ መንግሥት ዙፋን ብቻ አለመሆኑ ብዙ የተባለበትም የተባለለትም ነው፡ደግሞ ለማለት ማን ብሎን ማንስ አህሎን፡ የምንለውን የመሆን ጥያቄ እይምጣ እንጂ፡፡ ታዲያ ወያኔ ይሄን ሁሉ ነገሩ የሆነውን ሥልጣን የሚነቀንቅበት ነገር ሲያጋጥመው ፈጥኖ ገዳይ በማሰማራት ጸጥ ያደርጋል፡፡ እኛም ለቀናት ወይ ለአንድ ሁለት ሳምንታት አናላዝንና እንረሰዋለን፡፡ የምንረሳው ደግሞ የተደረገብንን ብቻ አይደለም ያደረግነውንም የሞከርነውንም እንጂ፡፡ ያ ባይሆን ትናንት ሞክረን የከሸፈብንን ዛሬ በዛው ስልትና መንገድ አንደግመውም ነበር፡፡ ወያኔ ግን አይደለም መርሳት ለአፍታም መዘንጋት ብሎ ነገር አያውቅምና እኛ ወያኔ እንዲህ አደረገ ብለን ስንጮህ ስንጯጯህ እሱ ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት፣ ለምን፣ በምን፣ ምክንያትና በእነማን ወዘተ ነው? ብሎ ምርመራ ይቀመጣል፣ከዛም እንዳይደገም ማድረግ ያሰችለኛል ያለውን ርምጃ ሁሉ ይወስዳል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከምርጫ 97 በኋላ የወጡ አዋጆችን የተወሰዱ ርምጃዎችን ማስታወሱ በቂ ነው፡ ይህንንም ካልረሳነው፡፡ ቅንጅቶች የታሰሩት ብቻቸውን ሳይሆን ለሥልጣን ሊያበቃቸው ከነበረው “እንከን የለሽ ምርጫ” ጋር እንደነበረ ምን ያህሎቻችን እናስታውስ ይሆን? እነርሱ በይቅርታ ተፈቱ ምርጫ ግን የሚያስፈታው ወይ ሽማግሌ፣ ወይ ፖለቲከኛ፣ ወይንም አርበኛ ጠፍቶ ዛሬም ቃሊቲ ነው የሚገኘው፡፡ ይሄን ማስታወስ ተስኖን ምርጫ እያልን በ2002 እና በ2007 የወያኔ አድማቂ ከመሆን ያለፈ ያልፈየድነው ለዚህ ነው፡፡

ወያኔ ማረሳሳቱን እኛ መርሳቱን ተክነንበታል፣ ወያኔ ከደደቢት እስከምንይልክ ቤተ መንግሥት የሥልጣን ጎዙውን ለማደናቀፍ ከዛም ወዲህ ወንበሩን ለመነቅነቅ የተደረጉ የተሞከሩበትን አይደለም የታሰቡ ያላቸውን ሁሉ ፈጽሞ አይዘነጋም፣ በተመሳሳይም እርሱም የፈጸማቸውን  አይረሳም፡፡ እኛ ተቀዋሚ የምንባለው አይነተ ብዙዎቹም ተሞክሮ ከከሸፈው፣ ታስቦ ካልተፈጸመው ተምረን በሚያደርስብን በደል ከመማረር ወደ ማምረር ተሸጋግረን ለወንበሩ ስጋት የሚሆን ኃይል እንዳንፈጠር  አዳዲስ ነገር እየሰጠ ያለፈውን ያስረሳናል ያረሳሳናል፡፡ ተሀድሶ፣ ግምገማ፣ህዛባዊ ውይይት፣ከምሁራን ጋር ውይይት፣ የድርድር ጥሪ፣የተወሰኑ ትናንሽ ባለሥልጣናትን ማባረር፣ ራስን ተጠያቂ አድርጎ ማውራት ወዘተ ከማረሳሻ ዘዴዎቹ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡የሚገርመው የእኛ ለዚህ ምቹ መሆን ነው፡፡ አምና ካቻምና  ተሀድሶ ብሎ  ምንም ለውጥ እንዳላሳየ እያየን ዘንድሮም ታድሼ እመጣለሁ እኔው እሻላችኋለሁ ሲል ይለወጣል ብሎ ተስፋ ማድረግ ትናንትን መርሳት ብቻ ሳይሆን ይቅርታ ይደረግልኝና መጃጃል ነው፡፡ይህም በመሆኑ ነው ወያኔ በአንድ መንገድ እየተጓዘ በአንድ አስተሳሰብ እየተመራ ሀያ አምስት አመት ለመግዛት የበቃው፡፡ተበዳዩ ለመጃጃል ራሱን ካዘጋጀ በዳዩ እያጃጃለ ለመግዛት ምን ይገደዋል፡

የወያኔ ባለሥልጣናት በጨነቃቸው ቁጥር ለማስተንፈሻ፣ ቁጣ ባየለባቸው ግዜ ለማረሳሻ የተናገሩዋቸው ነገሮችን ብቻ ማስታወስ ብንችል በሥልጣን መቀጠል እንደሌለባቸው የራሳቸው ምስክርነት ብቻ በቂ ነው፡፡በኦሮምያ የህዝቡ አመጽ ሊገቱት ቀርቶ ሊገድቡት የማይችሉት ሲሆንባቸው የተወሰኑት የህዝቡ ጥያቄ ትክክልና ዴሞክራሲያዊ ነው አሉ፣ሌሎቹን አዘዙና ደግሞ የጸጥታ ኃይሉ የወሰደው ርምጃ ተገቢ ነው ለዚህ ተግባሩም ምስጋና ይገባዋል አስባሉ፡፡ይህ ራሳቸው በራሳቸው ላይ የመሰከሩበት በሥልጣን ላይ አንድም ቀን እንዲያድሩ የማያበቃቸው ትልቅ ወንጀል ቢሆንም እኛ  በእለት በእለቱ የሚሰጠንን  እየያዘን መጮህ እንጂ ትናንትን ማስታወስ ስለ ነገም አርቆ ማሰብ የተነፈግነው አይነተ ብዙዎቹ እኛ ግን ይህን አይደለም በገፍና በግፍ የተገደሉትንም የታሰሩትንም እረስተን ለዛሬ በዛሬ ጉዳይ እንጮሀለን፡፡

ዳኞች በስልክ ትዕዛዝ ውሳኔ እንደሚሰጡ፤ አቃቤ ህግ የሀሰት ምስክር አሰልጥኖ እንደሚያስመሰክር፣አስፈጻሚው አካል በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ ጣልቃ እንደሚገባ ወዘተ በጥናት ደረስንበት ብለው ከነገሩን አመት ያለፈው መሰለኝ፣ያው መርሳት አይደል ችግራችን፡፡ ይህ ውይ! እነዚህ ሰዎች ችግራቸው ገብቷቸዋል ሊለወጡ ነው መሻሻያ ሊያደርጉ ነው ብለን ሁሉን እንድንረሳ የቀረበ ማረሳሻ እንጂ ሌላ ባለመሆኑ ከነገሩን አንዱንም አልሰሩትም፡፡ ሰሞኑንም ሌላ በጥናት ደረስንበት ያሉትን እየሰማን ነው፡፡ እነርሱ በሥልጣን ያቆየን አንዱ ብልሀት ይሄ ነው ብለው አምነው የሚፈጽሙት ነውና ትክክል ናቸው፡፡ በየግዜው በሚሰጠን ማዘናጊያ የምንዘናጋ በማረሳሻው የምንረሳ  ለመታለል/ለመጃጃል የተዘጋጀነውስ.. ልብ ይስጠን፡፡

LEAVE A REPLY