ወያኔ የመጨረሻውን እርሾ እየጋገረ ነው፡ ምዕራፍ ፫ /መስቀሉ አየለ/

ወያኔ የመጨረሻውን እርሾ እየጋገረ ነው፡ ምዕራፍ ፫ /መስቀሉ አየለ/

ባለፈው የክፍል ሁለት ትንታኔ ለማሳየት እንደሞከርኩትሁለቱም አንጃዎች የሃይል ቀጠናቸውን በማስፋት ክልሎችን በየስራቸው ለማሰለፍ በሩጫ ውስጥ መሰነበታቸውን፤ የሳሞራ የኑስ በኮማንድ ፖስቱ ሽፋን የኦሮሚያን፣ የሱማሌ ክልልና የትግራዩን ዋርሎርድ አባይ ወልዱ ከጎኑ ሲያሰልፍ ጌታቸው አሰፋ ደግሞ የአማራን ክልል ሙሉ ለሙሉ እና በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ሚዲያውን ጨምሮ ቁልፍ የሆኑ የማእከላዊውን መንግስት ተቁዋማት መቆጣጠራቸውን የዚህ የነፍሽን አድን እሩጫ አዲስ አበባና ማእከላዊዉን መንግስት ሙሉ ለሙሉ ቀድሞ በመቆጣጠር ላይ ይወሰናል የሚል ነበር።

ይኽ ውስጥ ውስጡን የሚንተከተክ የእሳት እረመጥ ዛሬም አልቆመም። ይልቁንም ከቀን ወደ ቀን በመጠን እየሰፋና እየገዘፈ የሚሄድ ማእበል ወደ መሆን ደረጃ በመቃረቡ በማንኛውም ሰአት ምንም ነገር ሊፈጠር እንደ ሚችል ማንም እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚችል የወያኔ ቁንጮ የለም።ያም ሆኖ መንግስት ነኝ ብሎ ከላይ የተቀመጠው አካል ምንም ማድረግ አልቻለም ብቻ ሳይሆን አይኑ እያየ ገደል ከመግባት ውጭ ምንም ማድረግ አይችልም። ባጭሩ ምርጫ የለውም።

አሁን ሁለቱም ሃይል አይኑን ያፈጠጠው ክፍቱን በተቀመጠው የሃይለማሪያም ደሳለኝ ወንበር ላይ እና በጥርስ አልባው ክቢኔት ላይ ነው። አባይ ጸሃየ በእልህና በድንፋታ ዕምንም ማድረግ የማይችልዕ እያለ በዚህ ካቢኔትና ሃይለማርያም ላይ መዛቱ ሌላ አንድምታ የለውም።እስቲ በጋሸ አሰፋ ጫቦ አባባል ነገሩን ትንሽ ከፈት አድርገን እንየው።

የአገሪቱን ስልጣን የያዘው የፖለቲካ ድረጅት ላለፉት ሁለት አስርተ አመታት ከላይ የሚንስትሮች ምክር ቤት ጀምሮ እስከ ታችኛው የቀበሌ መዋቅር ምንም አይነት መፈናፈኛ በሌለው መልኩ ስልጣኑን ጨብጦ ኖሯል። ይኽ ማለት በህግ አስፈጻሚው በህግ ተርጉዋሚው እና በህግ አውጭው መካከል ቀዳዳ ቀርቶ ለተለዬ አመለካከት እድል የሚሰጥ አስራር አልነበረም ማለት ነው። ባጭሩ ዕዓብሶሉተዕ የሆነ ስልጣን የመፍጠር ቅዠታቸው ጣራ ነክቶ የፓርላማውን ወንበር በመቶ ፐርሰንት የያዙበት ስግብግብነት ከዚሁ ቅዠት የመነጨ ነበር።

ዛሬ ግን በአንጻሩ የተፈጠረው የውስጥ ቅራኔ ጣራ ነክቶ የሳሞራና የጌታቸው አሰፋ ጎራ በየፊናቸው ክልሎችን ለመቆጣጠር በሚያደረጉት እርብርብ መካከለኛውንና ታችኛውን የፖለቲካ ሃያል (ካድሬዎች) በየግላቸው ለማስገባት በመቻላቸው ከላይ የተቀመጡት ሚንስትሮች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የስልጣን መሰረታቸውን አጥተው ከላይ የተንሳፈፉበት ዋነኛው ምክንያት በብሄረሰብ ተዋጽኦ ወደ ካቢኔቱ የተሳቡት ሚንስትሮች ክልሎቻቸው በዚህ በሁለቱ አንጃ ስር በመውደቃቸው የተነሳ ከስልጣን መሰረታቸው በመተነጠላቸው ሲሆን ይኽን ካቢኔት እንደ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጥርስ አልባ ያደረገው ሌላው ተጨማሪ ምክን ያት ደግሞ ከሁለቱም ተጻራሪ ሃይላት የሚደርስበትን ገመድ ጉተታ ለመቋቋም ባለመቻሉም ጭምር ነው።

በመሆኑም በሳሞራ የሚመራው የወታደሩ ክንፍም ይሁን በጌታቸው የሚመራው የደህንነቱ ክንፍ ሁሉም በየፊናቸው የመንግስትን ስልጣን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ግብግብ ይኽን ከሚስትሮቹ ጀርባ ያለውን ተጻራሪ ሃይል በራሳቸው መንገድ መምታቱን የግድ ብሏቸዋል።እንግዲህ ከሁለቱ ተጻራሪ ሃይላት መካከል ሳያመነታና ሳይዘናጋ ቀድሞ እርምጃ መውስድ የሚችለው አካል ካቢኔቱን በመጨፍለቅ ብሎም በራሱ ታማኝ ሰዎች በመተካትና በማስከተልም ከጀርባ ያለውን ዋነኛ የፖለቲካውን ሃይል እስከ መጨረሻው እርከን ድረስ በመጥረግ እንደገና ስልጣኑን ዕለማጠናከርዕ ተስፋ ያደረጋል ማለት ነው።እዚህ ላይ መንግስቱ ሃይለማርያም ምሳ ሊያደርጉን ያሰቡንን ቁርስ አደረግናቸው ያለበትን የሂሳብ ቀመር ልብ ይሏል።

አባይ ጸሃዬ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ምን ያህል ያስኬዳል የሚለውን ስናዬው ግን መልሱ አጭር ነው፤ ምንም ነው። አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ህወሃት ከገባበት ቅርቃር መውጫ የማርያም መንገድ ማጣቱ ብቻ ሳይሆን የዚህ ፍጥጫ ፍጻሜ በደም የሚቋጭ መሆኑ ፍንትው ብሎ የወጣ ሃቅ የመሆኑ ነገር እረፍት የነሳው አባይ ጸሃየ ዕየሚነገረውን አልሰማ ካለ በአደባባይ አውጀን እናወርደዋለንዕ እያለ ሃይለማርያምና ካቢኔቱ ላይ ባዶ ዛቻ ሲዝት የሰማነንበት ምክንያቱም ይኽ ካቢኔት እርምጃ መውሰድ ያልቻለው ማንን ፈርቶ እንደ ሆነ እየታወቀ፣ ማን ከማን ጀርባ እንዳለ የታወቀ አባይ ጸሃየ ግን ገና ለገና የሚዲያ አክሰስ ስላገኘ ብቻ እንዲህ ያለ ዛቻ ለማስተላለፍ መሞከሩ በእርግጥ እርሱ እንደሚለው ማድረግ የሚችል ሆኖ ሳይሆን በውስጥ የተፈጠረው ስር የሰደደ ስጋት ነጸብራቅ መሆኑን ከላይ ያሳየሁት የወቅቱ የሃይል አሰላለፍ እና ቅራኔው የደረሰበት የእድገት ደረጃግንዛቤ ይሰጣል የሚል እምነት አለኝ።

ተጨማሪ

አባይ ጸሃዬ የሚታወቀው የሃይል ክፍፍል በሚፈጠር ግዜ ወላዋይ በመሆን በአንድ ግዜ ሁለት ዛፍ ላይ መሰቀል የሚወድና የማይታመን፤ ካሁን በፊትም ህወሃት ሲከፈል ለነ ተወልደ ወልደማሪያም ካደረ ቦሃላ በይቅርታ የተመለሰ ህሊና ቢስ ሰው መሆኑን ሳንረሳ ነገ የሚሆነው ባይታወቅም ቢያንስ አሁን ባለው አሰላለፍ ግን በተወሰን ደረጃ ወደ ወታደራዊው ክንፍ ያዘነበለ ይመስላል። …ይቀጥላል!

LEAVE A REPLY