የበኩር ልጃቸው ሰለሞን ጃገማ ኬሎ ማረፍ አባቱ አልሰሙም
/Ethiopia Nege News/፦ ጥር 20 ቀን 1913 ዓ.ም የተወለዱትና በኢትዮጵያ የአርበኞች ታሪክ ውስጥ ከፍተኛውን ስልጣን ይዘው ረዥም እድሜ በህይወት የቆዩት ታላቁ የጦር አርበኛ ሌ/ጄኔራል ጃገማ ኬሎ የመጀመሪያ ልጃቸው ሰለሞን ጃገማ በ67 አመቱ ባረፈ በ10ኛ ቀኑ የልጃቸውን ሞት ሳይሰሙ በ96 አመታቸው አረፉ። አስከሬናቸው በጦር ሃይሎች ሆስፒታል የክብር ሽኝት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
ጣሊያን አደዋ ላይ ድል ከተደረገ በኋላ 40 ዓመት ቆይቶ በድጋሚ በ1929 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለመውረር ጦሩን በከፍተኛ ሁኔታ አጠናክሮ ሲመጣ በ15 አመት ጨቅላ እድሜያቸው ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ ወደ 5ሺህ የሚጠጋ ጦር አደራጅተው በመምራት ጣሊያንን በማርበድበዳቸውም በላይ በ20 አመታቸው ከቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ጋር በመገናኘት ከፍተኛ ማእረግ ተቀዳጅተው ነበር።
በጣሊያን ወረራ ወቅት በፈጸሙት ጀብዱ የአውሮፓ ጋዜጦች ላይ በመውጣት ታሪክ የሰሩት አኩሪ የኢትዮጵያ ልጅ ጃገማ ኬሎ ከእድሜ ጋር በተያያዘ ህመም ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ ህይወታቸው ማለፉ ይፋ ሆኗል።
በሶማሊያ ጦርነት ወቅትም የሃገራቸውን ዳር ድንበር በማሰከበር ከፍተኛ ድል በማስመዝገብ የሚታወሱት ሌ/ጄኔራል ጃገማ ኬሎ በቀዳማዊ ወያኔ ጦርነት ወቅት በእንግሊዝ ታግዘው የራስ ጉግሳን ልጅ ለማንገስ በትግራይ በተደረገው ጦርነት ድል በማድረጋቸው ዝናቸው መናኘቱ ይታወቃል።
‘ጃገማ’ የአባታቸው የፈረስ ስም ሲሆን ይህ አባታቸው የሚወዱት ስም በኦሮምኛ ቃንቋ ሲተረጎም ‘ኃይለኛ’ ማለት ሲሆን አባታቸው የሚመርጡት ልጅ እስኪያገኙ ድረስ ይዘውት እንደቆዩ ታሪካቸው ይገልጻል። ሌ/ጄኔራል ጃገማ ኬሎ የአንድ ወንድ ልጅና የአምስት ሴት ልጆች አባት የነበሩ ሲሆን አምስት የልጅ ልጆችና አራት የልጅ ልጅ ልጆችን አፍርተዋል።
ለታላቁ ሃገር ባለውለታ ሌ/ጄኔራል ጃገማ ኬሎን ነፍስ አምላክ በቀኙ ያድርግ፤ ለመላ ቤተሰባቸው፣ ዳር ድንበሩን ለማስከበር ጀብዱ ለፈጸሙለት ህዝብና ዘመድ ወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።
የኢትዮጵያ ነገ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍል /ኢነዝግ/