እኔን እንደለቀቃችሁ ጓደኞቼንም ልቀቁልኝ ስል እጮሃለሁ /ኢዩኤል ፍስሃ-አዲስ አበባ/

እኔን እንደለቀቃችሁ ጓደኞቼንም ልቀቁልኝ ስል እጮሃለሁ /ኢዩኤል ፍስሃ-አዲስ አበባ/

ትላንት ኤልያስ ገብሩ እና ዳንኤል ሺበሺን ለመጠየቅ 24 አካባቢ ወደሚገኘው የቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ “ጊዜያዊ” ማቆያ ወደ ሆነው ጣቢያ ጎራ ብዬ ነበር።

ጣቢያው እንደደረስኩ የሁለቱንም ስም አስጠርቼ በጉጉት እነሱን መጠባበቅ ያዝኩ። አፍታም ሳይቆዩ ሁለቱም ተከሰቱ። ፊቴን ሲያዩ የሁለቱም ፊት በፈገግታ አበራ። እኔም ኤሊ፣ ዳኒ ስል ተጣራሁ። ተጠያቂን ከጠያቂ የሚለየውን ፍርግርግ ብረት የሆነውን በማለፍ፣ ምግብ የሚፈትሸው ፖሊስ ወደሚቆምበት ቦታ ትሁቱ እና ሩህሩህ ወዳጄ ዳንኤል ሺበሺ ተከሰተ። እጁን ሰዶልኝ “እዩ እንኳን ለቤትህ አበቃህ!” አለኝ። እጄን በመስደድ አፀፋውን መለስኩ። ዳንኤል ፊት ላይ ደስታ ይነበባል። ስለጤናዬ ሁኔታ እና ከእስር ስለተለቀኩበት መንገድ አወራን።

እነሱ ላይ ፖሊስ አለኝ ስለሚለው የሰነድ “ማስረጃም” አወጋን። የሰነድ የሚባሉት “ማስረጃዎች” ከስልኮቻቸውና ከፌስቡኮቻቸው የተገኙ ናቸው።

ከዳኒም ሆነ ኤሊ መዝገብ ላይ ፖሊስ የሰነድ ማስረጃ ናቸው ሲል ያያዛቸው ኮተቶቹ ለክስ የማያበቁ ናቸው ባይ ነኝ። እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረስኩት በግምት አይደለም! ፖሊስ አለኝ የሚላቸው የሰነድ ማስረጃዎቹ ለክስ የሚያበቁ ቢሆን ዳንኤልም ሆነ ኤልያስ ይህን ያህል ጊዜ ሳይከሰሱ ባልተቀመጡ ነበር። እነሱ በሚገኙበት ክ/ከተማ የተከሰሱና ፍርድ ያገኙ ግለሰቦች እንዳሉ ይታወቃልና።

ይህን ስል ግን ጓደኞቼ በጭራሽ ሊከሰሱ አይችሉም እያልኩ እንዳልሆነ ይሰመርበት። በእኔ እምነት ፖሊስ እነሱን የመክሰስ ከፍተኛ ፍላጎት አለው። ነገር ግን አለኝ የሚላቸው የሰነድ ማስረጃዎች በዓቃቤ ሕግ እምነት ለክስ የማያበቁ ከሆነ መደበኛ ክስ በእነሱ ላይ ለመመስረት ከቶም አይቻልም! ፖሊስ በበኩሉ እንቶፈንቶና ፍሬከርስኪ ነገሮችን ይዞ በመምጣት ክስ መስርቱ በማለት ዓቃቤ ሕግ ላይ ጫና ያሳርፋል። በእስር ላይ በቆየሁባቸው ወራት ይህንን በሚገባ ታዝቤያለሁ። ከፖሊስም ሆነ ከዓቃቤ ሕግ ጋር በተደጋጋሚ እየተገናኘሁ የተለያዩ ጥያቄዎች ለሁለቱም አካላት አነሳላቸው ነበር። አንዱ አንዱን አያምንም። ሁለቱም ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት ተልካሻ ምክንያቶችን ይዘረዝራሉ። አንድ ዓቃቤ ሕግ ያለኝን እዚህ ጋር ሳላነሳው ማለፍ የለብኝም።

“ይኸውልህ ኢዮኤል በእናንተ ላይ ውሳኔ ለማስተላለፍ ተቸግረናል። እዚህ በቆየኽባቸው ወራት በደረቅ ወንጀል ተጠርጥረው የሚገቡ እስረኞች በአፋጣኝ ውሳኔ ሲያገኙ የታዘብክ ይመስለኛል። የእናንተ ጉዳይ ግን የሀገር ጉዳይ ነው። በሌላ ነገር ገብታችሁ ቢሆን ኖሮ እኔ በስራዬ ላይ ጣልቃ እንዲገባ በጭራሽ አልፈቅድም! ይሄ ግን……”

ይህኛው ዓቃቤ ሕግ ሌሎቹ ደፍረው ሊናገሩ ያልቻሉትን ተናግሯል። እጁ የማይታይ አካል በስራቸው ጣልቃ እየገባ እንዳለና በ’ወቅታዊ’ ጉዳይ ላይ ለመወሰን የሙያ ነፃነታቸውን መነጠቃቸውን ከዓቃቤ ሕጉ ንግግር ለመረዳት ይቻላል። በዚህ የተነሳ እኔም ሆንኩ እስር-ገጠም ጓደኞቼ ከ5-6 ወራት ያለውሳኔ በእስር ለመማቀቅ ተገደን ነበር።

የጓደኞቼ ኤልያስም ሆነ ዳንኤል ያለውሳኔ 5 ወራት በእስር መቆየትም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፣ ባይ ነኝ። ኤልያስም ሆነ ዳንኤል ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መልስ ለማግኘት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጋር ሰው ልከው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ ገልፀውልኛል።

ኤልያስ እንደገለፀልኝ አሁንም ድረስ ኮማንድ ፖስቱ የያዛቸው ግለሰቦች እየተለቀቁ ይገኛሉ። እነሱ ታስረው በሚገኙበት ቦታ በኮማንድ ፖስቱ ብቻ ከ170 በላይ እስረኞች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ኤልያስ አስረድቷል። እየተለቀቁ ያሉት ሰዎች በምን መንገድ እየተለቀቁ እንዳሉ ላነሳሁለት ጥያቄ ኤልያስ፣ “በመታወቂያ ዋስ ነው እየተለቀቁ ያሉት።”ሲል ምላሹን ሰጥቶኛል።

ዓቃቤ ሕግ እነሱን ለመክሰስ ከተቸገረ የእነሱም ዕጣፈንታ ተመሳሳይ ነው የሚሆነው። ኤልያስንም ሆነ ዳንኤልን ስሰናበት በርቱ የሚባሉ ግለሰቦች ስላልሆኑ በርቱ እንደማልላቸውና በሌላ ቀን እንደምመጣ ነግሬያቸው ተሰናበትኳቸው። ሰሚ ባይኖርም እኔን እንደለቀቃችሁ ጓደኞቼንም ልቀቁልኝ ስል እጮሃለሁ።

LEAVE A REPLY