/EthiopiaNege News/፦ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተከሰተው ህዝባዊ ተቃውሞ የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) እና የአውሮፖ ህብረት በነፃና ገለልተኛ ተቋም እንዲጣራ ጥያቄ መቅረቡ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው እለት ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጥያቄው በመንግስታቸው በኩል ውድቅ መደረጉን ለቢቢሲ(BBC) የዜና አውታር ተናግረዋል።
እንደ ጠሚንስትሩ ገለፃ “ኢትዮጵያ ተአማኒነት ያለው ምርመራ ማድረግ የሚያስችላት አቅም እንዳላት ተናግረው፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በማጣራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።በዚህ ጉዳይ ምርመራ ለማድረግ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተሻለ በመሆኑ ለሌላ አካል ሊሰጥ እንደማይችል የመንግስታቸውን አቋም ለዜና ተቋሙ አስረግጠው ተናግረዋል።
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑም ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባቀረበው ሪፖርት “በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው ሁከት 462 ሰላማዊ ሰዎችንና 33 የፀጥታ ኃይሎችን በአጠቃላይ 495 ሰዎች ህይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት ሲሆን፤ በአማራ ክልል ለተከሰተው አመፅ ምክንያት የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አልተመለሰም፤ የትግራይ የበላይነት አለ፤ የዳሽን ተራራ በመማሪያ መፅሐፍ ውስጥ በትግራይ ክልል ስር እንዲካተት መደረጉ፤ የጠገዴ ወሰን ድንበር ምላሽ ሳያገኝ መቅረቱ እና የአማራ መሬት ለሱዳን ተሰጥቷል የሚሉት ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን” ጠቅሷል።
በመጨረሻም አቶ ሀይለማሪያም አክለው እንዳሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሀገሪቱን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ መመለሱንና በዓመፁ ተሳትፈው በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ዜጎች ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ብለዋል።
በአስኳይ ጊዜ አዋጁም ሆነ በህዝባዊው ተቃውሞው ወቅት የት እንደደረሱ የማይታወቁ በርካታ ዜጎች መኖራቸውንና ባልታወቁ እስር ቤቶች የሚገኙ ታሳሪዎችን ያካተተ ምርመራ ሊደረግ እንደሚገባ የሚገልጹ ተንታኞች የኃይለማሪያም መንግስት ሁኔታውን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማረጋጋት ችያለሁ ማለቱ በሀገሪቱ ለወደፊት ሊፈነዱ የሚችሉ የህዝብ እምቅ ተቃውሞ እያየለ መምጣቱን ካለማስተዋል የመነጨ ‘የመሳሪያ አስተሳሰብ’ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ካወጣው የሟቾችና የጉዳተኞች ቁጥር ጋር እውነታው እጅግ የተራራቀ ነው የሚሉት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ የምርመራውን ውጤት ጥያቄ ውስጥ ማስገባታቸው ይታውቃል።