/Ethiopia Nege News/፦ ለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መኖሪያውን በአሜሪካን ሃገር በስደት ስላደረገው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ዛሬ ሀይል የተቀላቀለበት ምላሽ ሰጥቷል።
እንደ ኤምባሲው ገለፃ ከሆነ አትሌቱ እሁድ ዕለት በሚደረገው የለንደን ማራቶን ላይ ‘በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተቃውሞ ለማሰማት በዝግጅት ላይ ነው።’ ብሏል። በ2016 ‘አዲስ አለም’ በሚል መሪ ቃል ሪዮ ላይ በተካሔደው የኦሎምፒክ ውድድር የብር ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነው ፈይሳ የውድድሩ ማጠናቀቂያ ላይ 3 ቢሊዮን ህዝብ በላይ በቀጥታ በሚከታተለው የቴሌቪዥንስርጭት ላይ ሁለት እጆቹን ከፍ አድርጎ በማጣመር ካሳየ በኋላ በኢትዮጵያ በመካሔድ ላይ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ይበልጥ ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገው መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
የ27 ዓመቱ ፈይሳ ሌሊሳ ትናንት ከቢቢሲ (BBC) ጋር ባደረገው ቆይታ ‘ኢትዮጵያ ውስጥ ደም እየፈሰሰ ነው።’ ብሏል።የኤምባሲው ቃል አቃባይ ለኒውስ ዊክ (Newsweek) ዛሬ እንደተናገሩት ደግሞ ‘ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈስ ደም የለም፤ ይሔ የተለመደና ፍሬ የሌለው ክስ ነው። የተፈጠረውን ለማጋነን የተጠቀመበት መንገድ ነው።’ ሲሉ በስሜት በመናገር ለማጣጣል ሞክረዋል። ቃል አቀባዩ አክለው እንዳሉትም፦
”ሀሳቡን በፈለገው መንገድ መግለፅ ይችላል። መብቱ ነው። ወደ ሀገሩ ቢመለስም የሚነካው የለም። ነገር ግን አክራሪ ዲያስፖራዎች ከጀርባው ሆነው የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ በእርሱ ላይ እያራመዱ ነው።” በማለት ከሰዋል።
የለንደኑ ኤምባሲ ይህን ይበሉ እንጅ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው ህዝባዊ እንቅስቃሴ በየቀኑ አድማሱን በማስፋት ላይ ይገኛል። በሺህ የሚቆጠሩ ንፁሀን ዜጎች ህይዎታቸውን አጥተዋል። አስር ሺህዎች ደግሞ በየ እስር ቤቱ ያለምንም ጥፋት እየማቀቁ ሲሆን ቀላል የማይባሉትም ለስደት ተዳርገዋል።
በእሁዱ የለንደን ማራቶን ላይ ኢትዮጵያዊያንና ኬንያዊያን ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ፤ በተለይ ለኢትዮጵያዊያን ደግሞ ”የሰብአዊ መብት”ተሟጋቹ ፈይሳ ሌሊሳ እና ለህዝብ ሞትና ስቃይ ግድ አይሰጠውም ተብሎ የሚታማው የሦስትጊዜ የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ አንድ ላይ የሚሳተፉበት መሆኑ ቀልብ ስቧል።