ጋሼ አሰፋ ጫቦ የኢትዮጵያን ፍቅር እንደማተብ በአንገቱ አስሮ፤እንደ እንደ መልካም ሽቶ ለሌሎችም ሲረጨው የኖረ ሰው ነው፡፡ ሃገሩን የሚወድበት ውድ የልክፍት አይነት ብርቱ ነበር፡፡ በሰው ሃገር ተኝቶ በኢትዮጵያ ሰማይ ምድር፣ በሃገሩ ወንዛ ወንዝ፣በጋሞ ጭጋጋማ ተራሮች ግርጌ፣ በሰላሌ ሜዳ፣ በጣና ገዳማት፣ በሊማሊሞ አቀበት የሚያዞር ህልም የሚያሳልም የሃገሩ ፅኑ ፍቅር የወደቀበት ሰው ነበር፡፡
ከህልሙ ነቅቶ ብዕር ሲያነሳ ያለ ሃገሩ እትብት የመጓተት ፖለቲካ ደዌ፣ገዳዳ የፍትህ ስርዓት፣የልመና አቁማዳ የሚያስነግት አዋራጅ ጠኔ፣ወልጋዳ ፕሮፖጋንዳ፤ ሌላ አይታየውምና እሱኑ ያነሳል ይጥላል፤ለሚሰማው የሚሻል የመሰለውን መንገድ ያሳያል፡፡ የጋሼ አሴን የሃገር ፍቅር ተራራ አይጋርደውም! ለዚህ ነው ምቹው የስደት ሃገር ያልተስማማው፤ስንቱ በእግር በፈረስ የሚሞክረው ስደት ለእሱ እንደ ምርግ ከብዶት ከሃገር ከአፈሩ፤ ከወፍ ከዛፉ ያላስማማው፤ባይተዋር ያደረገው፤ሞቱን ሳይቀር በድብቅ ለማድረግ ያስጨከነው! የሃገር ፍቅር ረሃብ በሰው ሃገር መልካም ምግብ አይጠረቃም፡፡ በቅንጡ ሆስፒታልም አይታከምም!
የጋሼ አሰፋ ነፍስ ለስጋዋ በተመቻት ቦታ ትረጋጋ ዘንድ እምቢ ብላ ‘ሃገሬን’ እያለች ስታስጨንቀው የኖረች ይመስለኛል፡፡መላ ስትዘይድም ያልተመቼውን ስጋዋን ገድላ ከሙት በቀር ህያው የማይወዱትን ነገስታት ጠመንጃ በሞት ተከልላ ሃገሯ ለመግባት መርጣ ይመስላል ጋሼ አሰፋን የተነጠቅነው፡፡እሱን የመሰለ ብዕረ-መልካም ሰው መነጠቅ በቀላሉ የሚተኩት ኪሳራ አይደለም፡፡ በወር አንድ ጊዜ እንኳን አንድ ገፅ የብዕሩን ቱፍታ ቢያጋራን ብዙ እናተርፍ ነበር፡፡ በልጅነት በጉልምስና የማያጠፋ የለምና ጥፋት ቢኖረው እንኳን ከጥፋቱ ሳይቀር የሚያስተምርበት ብዕሩን እንድንጠቀም በሚያደርግ መልኩ ሁሉን ማድረግ ይቻል ነበር-የቂም በቀል ክስ ፈብርኮ የማምሻ እድሜውን የሚያስፈጅ የቅጣት ድግስ ከመደገስ፡፡
እንደ መዥገር እላያችን ላይ የተጣበቁት ነገስታት ግን ለመንግስትነት የሚበቃ ምህረትም ሆነ አርቆ አስተዋይነት የላቸውምና እነሱ እጁን ይዘው የማይመሩት ሰው በሃገር አይኖርም፡፡ ይሄው እኩይነታቸው ወርቁን ሰው ጋሼ አሰፋን ከሚወዳት ሃገሩ ብን ብሎ በሰው ሃገር መዳብ ሆኖ ጎኑን ሳይመቸው እንዲኖር አደረገው፡፡ሃገራቸውን ‘ቅኝ ገዥ’ ብለው አነውረው ‘ለሰው ሃገር’ እንሙት የሚሉ፤ ርጋፊ የሃገር ፍቅር ያፈጠረባቸው የባንዳ ልጆች የማይወዷት ሃገር ባለቤት ሆነው ሃገሩን የሚወድ ሰው በስደት ምድር ነፍሱ እንድትራቆት ማድረጋቸው መራር ነው፡፡ ከሰው እንዳልተፈጠረ፣ወገን እንደሌለው፣ ቢያንስ በብዕሩ ለሃገር እንዳልጠቀመ በመጨረሻው ሰዓት ከሞት ጋር ሲተናነቅ እንኳን የኔ የሚለው ሰው በሌለበት እንዲሆን ከማድረግ ሌላ ምን የበቀል ጥግ ሊገኝ? የዚህ ቁጭትስ እንዴት ሆኖ ከወገን ሆድ ይወጣል?!ይህን ሁሉ ክፋት በክንዳቸው ብርታት ያደረጉ ለሚመስላቸው በቀለኛ ነገስታት የኛ በሃዘን ማረር የሃሴት ጊዜያቸው ነው፤አንድ ባለጋራ ወድቆላቸዋልና “ጎፈሬ” ያበጥሩ፤እኛ ብዙ የጎደለብን ደግሞ ብዙ እናልቅስ! ፈልገናቸው “የልባችን ናችሁ” ብለን አልሾምናቸወምና ሃዘናቸው እና ሃዘናችን ገጥሞ አያውቅም፡፡ዘር ቆርጥመው የሚበሉ ናቸውና ዘር እንዳይተርፍልን በክፋታቸው የዋኖቻችንን እድሜ አሳጥረው በታላላቆች መክሊት ሳንጠቀም እንዲሁ ቀረን!
ጋሼ አሰፋ በግል ህይወቱ ባህሪው ምን አይነት እንደሆነ አላውቅም፡፡ሰው ነውና እንከንም አይጠፋበትም፡፡በግል ባህሪው ወደድነው ጠላነው ባለ ወርቅ ብዕር እንደሆነ ግን ማንም አይክደውም፡፡ የብዕሩ ቱፍታ ለዛ የማይጠገብ፤የወርቅ ብዕሩ ክታብ የተጓዘበት ፍኖት ቢሄዱበት የማይሰለች፤ ቢያፈጡበት የማይደክም እንደሆነ በወዳጁም በጠላቱም ፊት የተሰወረ አይደለም፡፡በደልን የሚተው የይቅርታ ሰውነቱም የሚካድ አይደለም፡፡ አስራ አንድ አመት መታሰሩን አሁንም አሁንም እያነሳ የሞኝ ለቅሶ ሲያለቅስ አላየንም፡፡ ይልቅ “ያለፈው አለፈ አሁን የጋራቤታችንን እንዴት ገንብተን በምን እናሙቅ” በማለቱ ላይ ይበረታል:: ስለዚህ ነገሩ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ተገርሞ ‘አንተ ግን እንዴት ነው የአስር አመት እስርህን በመፅሃፍህ ላይ በለሆሳስ ያለፍከው’ ብሎ ጠይቆት ነበር፡፡ ‘አስሬ ባወራው ምን ይጠቅማል፤ደጋግሞ ማውራቱ የሆነን ነገር ከመሆን አይቀንስ አይጨምር ምን ዋጋ አለው፤ ይልቅ ትርፍ ስላለው የወደፊት ነገር ማውራቱ ይበጅ ይመስለኛል’ ሲል ነበር የመለሰው::
ጋሼ አሰፋ የኢትዮጵያ ፍቅር ያመጣበትን ለኢትዮጵያዊነት የመቆም ሙግት ሲያስረዳ ስሜትን ሳይሆን ምክንያትን ተላብሶ እንደሆነም አይካድም፡፡ በዚሁ የሚተቹት “ኢትዮጵያን ካላፈረስን” ባዮች በፊቱ ቆመው ከመሞገት ይልቅ ማዶ ሆነው ሽምግልናውን በማይመጥን ሁኔታ ስድብ የተሞላ አፋቸውን የሚከፍቱበት ምክንያት ስሜታዊነታቸው የምክንያታዊነቱን ጉልበት፤የግንዛቤውን ጥልቀት፤ የንባቡን ስፋት ይቋቋመው ዘንድ ስለማይችል ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ጋሼ አሰፋ የብሄር ፖለቲካን የሙጥኝ ቢል ኖሮ ይህን ሁሉ የስደት ስንክሳር ባላየ ነበር፡፡ እንደማንኛውም የጎሳ ፖለቲከኛ ያኔ አስራ አንድ አመት ሲታሰር የጋሞን ህዝብ ሁሉ ይዞ እስርቤት የገባ አስመስሎ፤ራሱን ህዝብ አሳክሎ ቢያላዝን ተከታይ እንዳይጠፋ ነው?! በጎሳ ፖለቲካ ተፀንሶ ተወልዶ ለዚህ የበቃው ህወሃትም ይህን አይጠላም ነበር፡፡ “በነጋ በጠባ የምበጥስ የምቀጥለው ማተብ የለኝም” የሚለው ጋሼ አሰፋ ግን አለማቀፍ ወዛደራዊነትን በዘመረበት አፉ በጋሞ ሸለቆዎች ብቻ በሚሽሎከሎክ ጥበት ኢትዮጵያዊነቱን ቸል ይል ዘንድ የግንዛቤው ስፋት በጄ አላላውም፡፡ ይልቅስ ጋሞነቱ ከኢትዮጵያዊነቱ ተጣልተውበት ሊያስታርቅ ቁጭ ብሎ እንደማያውቅ በብሩክ ብዕሩ አስነብቦናል፡፡ ነፍሰ-ስጋውን አልተመቼውም እንጅ ያልተበጠሰ ማተቡን በአንገቱ እንዳሰረ ማንቀላፋቱ ተገለባባጭ በበዛበት ምድር አርአያነት ነው፡፡ እኛ ብዕሩን የለመድን ግን ክፉ ጉዳት ተጎዳን!
ስለ ጋሼ አሰፋ የሰማሁት የተስፋየ ገብረአብን ተግተልታይ ማስታወሻዎች በማነብ ሰሞን ነበር፡፡ ሁለተኛውን ማስታወሻውን ካነበብኩ በኋላ ከጓደኞቼ ጋር ሰብሰብ ብለን ስላነበብናቸው መፃህፍት በምናነሳሳበት የማኪያቶ ሰርክል ከተስፋየ ማስታዎሻዎች ውስጥ የሳበኝ ነገር ቢኖር የአማርኛው ውበት እንደሆነ ገለፅኩ፤ ብዙዎች ተስማሙ፡፡ ከመሃላችን አንዱ “በቃ ተስፋየን ተንኮሏን ብቻ አሳቅፋችኋት ቀራችሁ ማለት ነው” ሲል “እንዴት?” አልኩኝ፡፡ “ተስፋየ የአማርኛ ውበቱን የቀዳው አንድ አሰፋ ጫቦ ከሚባል የአርባምንጭ አካባቢ ሰው ብዕር እንደሆነ ራሱ ተስፋየ እንደተናገረ የሆነ ቦታ አንብቤያለሁ” ብሎ ጀምሮ ስለ ጋሼ አሰፋ ብዙ አጫወተን፡፡ “እኛ እንዴት አናውቀውም ታዲያ?” ጥያቄያችን ነበር፡፡ “ተፈጥሮ ምቀኛ ሆነችባችኋ! ወያኔ ሲገባ እያንዳንድሽ ትምህርትቤት ከገባሽ አነሰሽና ነው ጋዜጣ አንባቢ የሆንሽው?” ብሎ ቀልዶ ጋሼ አሴን ያላወቅንበትን ሚስጥር አስረዳን፡፡ “እስኪ የፃፈው ነገር ካለ አውሰኝ” ብየ ለመንኩ፤ አባቱ የከዘኑትን የጋሼ አሰፋ በጋዜጣ መፅሄት የተዘራ ምርት፣ የሰጣቸውን አንድ ሁለት ቃለ ምልልሶች አምጥቶ ዘረገፈልኝ፡፡
የጋሼ አሰፋ ብዕር ከሰማሁት በላይ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ብዕሩን ወደድኩት፤ርቱዕ አንደበቱን አደነቅኩ፤ቅልል ጥፍጥ ያለ ቋንቋው በመንፈስ የቅርቤ ሰው አደረገው!!!!! “አሁን ከወዴት አለ?” ብየ ጠየቅኩ ባስቀር የምወደውን የተዋስኩትን ጋዜጣ መፅሄት ስመልስ፡፡ “አሁን ያው ወያኔ የሽብርተኛ ህጉን ሳታወጣ የደበራትን በምትከስበት የሆነ አንቀፅ ተከሶ ድንገት እንደወጣ ቀረ፤ከዛም የገባበት እንደጠፋ አባቴ ነግሮኛል” ሲል አጫወተኝ፡፡ ‘የገባበት ጠፋ’ ውስጥ ሞትም እንዳለ ጠረጠርኩ፤በአሉ ግርማ ትዝ አለኝ፤አለመታደል ተሰማኝ! የዋና እና የመደዴ፤የምርት እና የግርድ ቦታ ያቀያየረችው ሃገሬ መጨረሻ አሳዘነኝ፡፡ “ሞትም ይኖራል በለኛ” አልኩ ቅዝዝ ብየ፡፡ “ከሞተ እንኳን ይሰማ ነበር፤ ካለም የበላው ጅብ አንድ ቀን ይጮሃል” ብሎኝ ተለያየን፡፡
የሞቱን ስጋት ሽውታ ችላ ብየ የበላው ጅብ በቶሎ እንዲጮህ ተመኘሁ፡፡
እግዜር ይስጠው ቶሎ ጮኽ! ጭራሽ “የትዝታ ፈለግ”ን እነሆ አለን፤ትልቅ ሆኖ ሳለ ከእኛ ጋር ወርዶ በፌስቡክ ሜዳ ላይ አብሮን ሰነበተ፤የቅርባችን ሆነ፤የሃገሩን ጠረን ሃገርቤት ባለን ወገኖቹ በኩል ማሽተት ጀመረ፤ሃገሩ የገባ ሳይመስለውም አልቀረም፡፡ በዚህ ነፍሱ ደስ እንዳላት በፌስ ቡክ መስኮት አጫውቶኛል፤በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ!ጋሼ አሰፋ ራሱ እንዳጫወተኝ ሃገሩን አደራ የሚላቸው ወጣቶችን በመብራት ይፈልጋል፡፡ብዙ ባዝኖ ሲያገኝ ትቂቷን ጅማሬያቸውን አግዝፎ አይዟችሁ ይላል፡፡ ሞቱን ትከሻው ነግሮታል መሰል የተተኪ አሳቢ አሰላሳይ ነገር እጅግ ያሳስበው እንደነበረ፤አሁን ፌስቡክን ተቀላቅሎ ሲያይ ካሰበው በላይ ሃገሩ ደጀን እንዳላት በመረዳቱ በጣም እንደረካ ያጫውተኝ ነበር፡፡ እኔ ቀደም ብየ ልወቀው እንጅ እሱ ያወቀኝ ከአውስትራሊያው SBS ሬዲዮ ጋር የነበረኝን ቆይታ አዳምጦ “በርቺ በልልኝ” ሲል ለጋዜጠኛ ካሳሁን ኢሜል አድርጎ ካሳሁን ካደረሰኝ በኋላ ነው፡፡
ጋሼ አሴ እንደ አብዛኞቹ የዘመን አጋሮቹ ያሁኑን ትውልድ በመናቅ በመርገም አይነሳም፡፡ይልቅስ ልጆች ናቸው ብሎ ሳይንቅ ለመራመድ መውተርተራችንን እንደ ትልቅ ቆጥሮ በርቱ ይላል፡፡የራሴን ባወራ ትንሽ ቀላጤ ስፅፍ ከእውቀቱ በላይ የማውቅ ይመስል የሚያበረቱ ቃላት ከሽኖ ይልክልኛል፤ “ፅሁፍሽን ለማውቃቸውም ለማላውቃቸውም ሳጋራ፣እንዲያነቡ ስጋብዝ ሰነበትኩ፤እናንተን በማየቴ ሃገሬ አውላላ ሜዳላይ እንዳልቀረች አስባለሁና ነገ አያስፈራኝም” ይላል የሚወዳትን ሃገሩን በሁነኛ አደራ ተቀባይ መዳፍ ላይ ለማኖር ሲቃትት!
ምን ያደርጋል እንደተመኘው ሃገሩ ሻል ሳይላት እንደታመመች ቁርጧን ሳያይ፤ሰሚ ባልሆነ የፈርኦን ጆሮ ላይ “ኢትዮጵያን ማሯት” ሲል እንደለፈፈ፤ለእናት ምድሩ እንደማለደ፤ሰምቶ የሚመልስ ሳያገኝ ወደ ማይመለስበት ሄደ፡፡ ርቱዕ አንደበቱ ተዘጋ፡፡አይጠገብ ብዕሩ ድንገት ነጠፈ፡፡አቻቻይ ማንነቱ ተነነ፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚያዜምበት በገናው ወደቀ፡፡ “የጋራቤታችንን” ማገር የሚያጠብቅበት የመልካም ሽማግሌ ድንቅ ምክሩ ሲያምረን ቀረ! ከእውቀቱ ጥልቅ የምንቀዳው ውሃ፤የምንቋጥረው ስንቅ ጎደለ፡፡የምንሰባሰብበት የኢትዮጵያዊነት አንድ ባንዲራ ወደቀ፡፡ ከእድሜው ድርና ማግ የምንሸምነው የእውቀት ቡልኮ አጠረ፡፡
ከመውደቅ መነሳቱ፤ከ‘ትዝታ ፈለጉ’ የምንቀስመው የልምድ ሰፈፍ ተቆረጠ፡፡የሆነው ሆኖ በድኑ የናፈቃት ሃገሩ መጥቶ እንዲያርፍ እየተሞከረ ያለው ነገር ከተሳካ ጥሩ መፅናኛ ነው፡፡ አምላክ የትልቁን ሰው ውብ ነፍስ በአፀደ ገነት እንዲያኖርልን፤ለእኛም መፅናናቱን እንዲሰጠን እየተመኘሁ ገጣሚ ዮሐንስ ሞላ የጋሼ አሴን ሞት አስመልክቶ የገጠማትን ከእንባ ጋር የምታታግል ግጥም አስከትየ ላብቃ!
ናፍቆታል ሃገሩ፣ጥያሜው ጠረኑ
በስጋው ተሳዶ፣ይያት በአስከሬኑ፤
“አሻም!” በሉት ውጡ፣ አበባ ጎንጉኑ
ገላው ላይ በትኑ፣አፈሩን ዝገኑ….
የዕድሜ እንቆቅልሹ፣ የዘመን ትብትቡ
የትዝታው ፈለግ፣ፍቅር የሃገር-ሰቡ
ያንድነት ሃሳቡ፤ያብሮነት ረሃቡ…..
ይፈታለት ህልሙ፤
ይውጣለት ህመሙ
ናፍቆት ሰቀቀኑ
ይሁንለት መጥኑ፤
ሃገሩ መድረሱን፣በሰው መከበቡን
ቡና መወቀጡን፣ወጡ መወጥወጡን
ክረምትና በጋ
ቆላ ወይና ደጋ
በሃሴት መውቀጡን ሌሊቱ እስኪነጋ
ሰስቶ መታየት፣ማውጋት ከእንግዳ ጋ፤
ያውቀዋል አየሩን
ይረዳዋል ነፍሱ
ባያይ እንኳን ዐይኑ
ያውቃል ደመነፍሱ
ለመላ ነው ሞቱ
ለመግባት ከቤቱ፤
“አሻም!” በሉት ውጡ፣አበባ ጎንጉኑ
ገላው ላይ አብኑ፣አፈሩን ዝገኑ
ይብረድለት ሱሱ
ቃናዋ ነው ምሱ
ይቁረጥለት ጥሙ
አፈሯን ይቅመሰው
መለስ ይበል ቅስሙ
ቸሰስ ይበል ጅስሙ…
ሃሳቡን ትውረሰው፣
ገላውን ትጉረሰው
አገር ያጊጥበ፣ተጓትቶ ይልበሰው
ከበቀለበት ሰው፣ተሻምቶ ይቅመሰው፡፡
/ግጥም በዮሐንስ ሞላ/