የኢህአዴግ የኢኮኖሚ አብዮት ሲዳሰስ በተስፋየ ከበደ ኢህአዴግ ጥልቅ ተሀድሶ አድርጊያለሁ ካለ በኋላ በተቃዋሚ ብሄርተኞች ጭምር የተደገፈ የኢኮኖሚ አብዮት ይዞ ብቅ ብሏል። ያው እንደተለመደው ኢህአዴግ ለችግሮች ሁሉ አብዮታዊ መፍትሄ ነው ይዞ የሚቀርበው። አብዮታዊ ዴሞክራሲም ምን ዓይነት ዴሞክራስ እዳስገኘልን እያየነው ነው።
አዲሱ የኢኮኖሚ አብዮት እንዲሁ በግርድፉ ሲታይ ህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በቀናነት ታስቦበትና ጥናት ተደርጎበት የተዘጋጅ ፕሮግራም ቢመስልም አላማው፣ዘለቄታዊነቱና ተፈጻሚነቱ የሚያጠያይቅ፣ የብሄርተኞች የፓለቲካ ማስፈጸሚያና የሃገርን ህልውና የሚፈታተኑ ነገሮችን ያዘለ ነው። እነዚህንም ነገሮች ከዚህ በታች ለማየት እንሞክራለን። 1. የኢኮኖሚ አብዮት አሁን ለምን አስፈለገ? ኢህአዴግ ከአስር ዓመት በላይ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግብያለሁ እያለ ሲያደርቀን ከርሟል።
ይህ እድገትም ማንን እንደጠቀመና አብዛኛው ህዝብ ከእጅ ወደአፍ የሆነውን ኑሮ እንኳን መምራት እንዳቃተው ግን የታወቀ ነው። ይህን ባለበት አፉ ደግሞ የኢኮኖሚ አብዮት ካልተካሄደ በተለይ የወጣቱን ህይወት መለወጥ አይቻልም ይላል። የኢኮኖሚ አብዮቱ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ግን በህዝቡ ዘንድ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የቆየና በቅርቡ ተቀስቅሶ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ጎልቶ የወጣውን ፍትሃዊ ያልሆነ የአንድን ብሄር የኢኮኖሚ የበላይነት ጉዳይ ለማስተንፈስ ነው። እንደሚታወቀው የአገሪቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ አውታሮች በኢፈርት፣ በህወሃት ጀነራሎች በሚመራው ሜቴክ እና ከህወሃት ጋር በተወዳጁ ነጋዴዎች ስር ወድቀዋል።
ኢህአዴግ ታግየለታለሁ የሚለው የብሄረሰቦች እኩልነትም እንዳየነው ከሆነ የአንድን ብሄር ፍጹም የኢኮኖሚና የፓለቲካ የበላይነት ከማስጠበቅ ውጭ ጠብ ያለ ነገር የለም። የብሄሮች እኩልነት እስከመዝፈን ብቻ ነው እንዴ ከተባለ ቆይቷል። ያለፉት መንግስታት የተወሰነውን አከባቢ ወይም ህዝብ በተለየ ተጠቃሚ አድርገዋል የሚል አከራካሪ ሙግት ቢቀርብም በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ኢህአዴግ ስርዓት ግን ስልታዊ በሆነ መልኩ ብሄርን መሰረት አድርጎ አንድን ብሄር ብቻ ፍፁም ተጠቃሚ ያደረገ ስርዓት ግን የለም ማለት ይቻላል። በአብዮቱ ስም አሁን የተፈለገው ይህን ዓይን ያወጣ ዘረፋ ከህዝቡ እይታ ዘወር ለማድረግ በየአከባቢው የመሰረት ድንጋይ በመጣል ፋብሪካ ልንተክል ነው እያሉ ማስጮህ ነው።
ይሄ አካሄድ ሁለት ችግሮች አሉት። አንደኛ ለ 26 ዓመታት ከህዝብ ተዘርፎ በህውሃት ስር ስለወደቀው የአገሪቱ ሃብት መፍትሄ አይደለም። መፍትሄው ኢፈርትን አፍርሶ ወደ ህዝብ ንብረትነት መመለስ እንጅ ሌላ ኢፈርትን የመሰሉ ነገር ግን እንደ ኢፈርት ሊሆኑ የማይችሉ ድርጅቶችን በየብሄሩ ስም ማቋቋም አይደለም። ሁለተኛ አብዮቱ ሊካሄድ የታሰበው በአብዛኛው ከህዝብ በሚሰበሰብ ገንዝብና የክልል መንግስታት በሚያደርጉት መዋጮ ነው። ህውሃት ግን ኢፈርትን ያቋቋመው ከህዝብ አሰባስቦ ወይንም ከትግራይ ክልል በጀት ቆርሶ ሳይሆን የሀገርን ሃብት በተለያየ መልኩ ዘርፎ ነው። የክልል መንግስታት መዋጮም ቢሆን የሚመጣው ለሌላ ልማት ሊውል የሚችል የነበረ ገንዘብ እንጅ ትርፍ ሀብት ስላላቸው አይደለም። ትምህርት ቤትና ሆስፒታል ከምትሰራ የህዝቡን ዓይን ከኢፈርት ላይ ዘወር ለማድረግ አዋጭነቱ እንኳን የማይታውቅ ፋብሪካ ትተክላለህ።
ከዚህ በተጨማሪ የኢኮኖሚ አብዮቱ ያተኮረባቸውን ዘርፎች ስንመለከት በግሉ ዝርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች እየሰሩ ያሉባቸውና ወደፊትም ከመንግስት በተሻለ ሊሰሩባቸው የሚችሏቸው ናቸው። በፊት የመንግስት የነበሩ ድርጅቶች ተሸጠው ወድ ግል እንዲዘዋወሩ የተደረገበትም ዋና ምክንያት ይሄ ነበር።
መንግስት በኢኮኖሚው ላይ መሳተፍ እንኳን ካለበት መወሰን ያለበት የግሉ አቅም በሌለበት ወይንም መሳተፍ በማይፈልግበት ሁኔታ ብቻ ነው። የመንግስት ዋናው ስራ መሰረታዊ የልማት ዓውታሮችን መገንባት እንጅ የነጋዴን ስራ እየቀማ ልማት አምጥቸልሃለሁ ማለት አይደለም። 2. ከብሄር ፓለቲካ ወደ ብሄርተኛ ኢኮኖሚ ከላይ እንደተመለከትነው የኢኮኖሚ አብዮቱ የአጭር ጊዜ ዓላማ የህዝቡን ተቃውትሞ ማስተንፈስ ቢሆን የረጅም ጊዜ ግቡ ግን ብሄርተኝነት ከፓለቲካው ባለፈ ኢኮኖሚያዊ መሰርት ማስያዝ ነው።
የኢህአዴግ ፓለቲካ መነሻውም መድረሻውም ብሄር ነው። አሁን ደግሞ አንድ ደረጃ ከፍ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ብሄርተኝነት ለመፍጠር ተግቶ እየሰራ ነው። ከዚያ ሰው ብቻ ሳይሆን ንብረትም በብሄር ይታወቃል። ለዚህም ነው ተቃዋሚ አክራሪ በሄርተኞች ጭምር እየደገፉት ያሉት። ይህም እየተደረገ ያለው የአንድ ብሄር ተወላጆች ከክልላቸው መንግስት ጋር በመሆን የተለያዩ ድርጅቶችን በማቋቋም ነው። ይሄ የተጀመረው በህወሃት ኢፈርት ቢሆንም አሁን በሌሎች ክልሎች በሰፊው ሊሰራበት ታስቧል። ኢፈርትን በምሳሌነት በመጥቅስም ጠቀሜታ እንዳለው ለማሳየት እየተሞከራ ነው። ነገር ግን ኢፈርት ሃብት ከማካበት አንጻርቅ ቢሳካለትም ያለመንግስት ለዩ ድጋፍ በነጻነት በመላ አገሪቱ መንቀሳቀስ ይችል ነበር ወይ? የመሰቦ ስሚንቶ ከመቀሌ ጋምቤላ ድረስ የሚሄደው ከሙገር ስሚንቶ የተሻለ ዋጋ ወይንም ጥራት ስላለው እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቃለን።
በየክልሉ ከኢፈርትጋ ርወይንምእርስበእርሳቸውየሚወዳደሩብሄርተኮርድርጅቶችሲቋቋሙ ከክልላቸው ውጭ በነጻነት መንቀሳቀስ ይችላሉ ወይ የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው። ስርዓቱ በሰራ አደገኛ የመከፋፈል ስራ ግለሰቦች ከክልላቸው ውጭ በነጻነት ተንቀሳቅሶ ስራ መስራትና ንብረት ማፍራት ይቅርና ያላቸውን ስይቀር እየተቀሙ እንዲባረሩ ተደርጓል። አሁን ደግሞ ብሄርተኛ ኢኮኖሚ በተጠናከረ ቁጥር ድርጅቶች ምርቶቻቸውን በነጻነት ወደ ተለያዩ ክልሎች የማከፋፈል አቅማቸው ይታቀባል።
ለጊዜው ህወሃት መሳሪያ በእጁ ስላለ ምርቱን ከክልሉ ውጭ ሊያቀርብ ይችል ይሆናል ወደፊት ግን ክልሎች የብሄራቸው ያልሆኑ ምርቶችን አናስገባም ላለማለታቸው ምንም ዋስትና የለም። በተግርም ከአሁኑ በአንዳንድ ቦታዎች እየታየ ነው ። የህዝብ ተቃውሞ ሲነሳ የመጀመሪያ ኢላማ የነበረው ሰላም ባስ እንደነበረ ማስታወስ ያስፈልጋል። ተቃውሞ በተነሳ ቁጥር ዳሽን ቢራን ያለመጠጣት ዘመቻ የተለመደ ሆኗል። ሰሞኑን እንኳን ባህርዳር ላይ የህዝቡን ልብ ለማሽነፍ ዳሽን ቢራ ያዘጋጀው የሙዚቅ ድግስ በቦንብ ፍንዳታ ምክንያት ተበጥብጦ ተበትኗል። ይህ ፓሊሲ በ አክራሪ ብሄርተኞች በተለይ በእነ ጃዋር ቡድን ዘንድ ለምን ድጋፍ አገኘ? ህወሃት በሌሎች ክልሎች ኢፈርትን የሚወዳደሩ ጠንካራ ድርጅቶች እንዲፈጠሩ ይፈቅዳል ብለው ባያምኑም መቋቋማቸው ግን በራሱ ጥቅሞች አሉት ይላሉ።
አንደኛ ባለፈው ዓመት ሲያስተባብሩት የነበረው ህዝባዊ ዓመፅ እንዳስገኘው ውጤት (ሰሞኑን በአዲስ አበባ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ልዩ ተጠቃሚ የሚያደርገው ረቂቅ ህግ ከመቅረቡ በፊት) እንዲቆጠርላቸው ይፈልጋሉ። ይህም ያን ሁሉ ህዝብ አስጨርሳችሁ ምን ለውጥ መጣ ለሚለው ክስ እንደመልስ ይጠቀሙበታል። ሁለተኛው ከብሄር ተኮር ፓለቲካው በተጨማሪ ኢኮኖሚው የብሄር ገፅታ እየያዘ በመጣ ቁጥር በክልሎች መካከል ያለው ልዩነት እየጎላ ይመጣል። አገራዊ አንድነት እንዲላላ ያደርጋል። ብሄርተኛ ማንነትን በማጉላት ክልሉን ራሱን ወደ ቻለ አገርነት የመቀየር ህልማቸውን ለማሳካት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። 3. የኢኮኖሚ አብዮቱ ይሳካስ ይሆን? ብሄርን ያማከለው ፓለቲካችን የት እንዳደረሰን እያየን ኢኮኖሚውንም በብሄር ካላዋቀርን ማለት መሰረታው የኢኮኖሚ መርሆችን አለመረዳት ነው። ይህ ሁሉ ደግሞ የሚሆነው በምስራቅ አፍሪካ ነጻ የኢኮኖሚ ገበያ እፈጥራለሁ በሚልና የወደፊት ራዕዩም በሃገር ውስጥ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር በሆነ መንግስት ነው። ነጻ የሰውና የንብረት እንቅስቃሴ በሌለበት ሁኔታ ጠንካራ ኢኮኖሚ እገነባለሁ ማለት የማይታሰብ ጉዳይ ነው።
በዚህ አብዮት ይፈጠራሉ ተብለው የታሰቡ ድርጅቶች በቀጥታ የኢፈርት ተወዳዳሪ መሆናቸው በራሱ አብዮቱ በህውሃት ኢትዮጵያ ውስጥ ይሳካል ብሎ ማሰብ ከንቱ ነው። ኢህአዴግ ከሙስና የተረፈውን ሃብት ልማት ላይ የማዋል ፍላጎት እንኳን ቢኖረው ደግመን ደጋግመን እንዳየነው የማስፈጸም ብቃት የለውም። ለምሳሌ የስኳር ፋብሪካ እገነባለሁ ብሎ በቢሊዮን የሚቆጠር የሃገር ሃብት እንዲሁ ባክኖ ሲቀር ታይቷል። በየብሄሩ ስም ኢህአዴግ ከህዝብ ገንዝብ ሰብስቦ ያቋቋማቸው የልማት ማህበሮች የት እንደደረሱም መዘንጋት የለበትም። ስለዚህ የኢኮኖሚ አብዮት ጨዋታው ልክ እንደ ከአሁን በፊቱ የአንድ ሰሞን ህዝብን የተስፋ ዳቦ የመመገብ ስራ ሆኖ መቅረቱ አይቀርም። ባይሳክም ይህ አብዮት በብሄር የተጀመረውን ሃገር የመከፋፈል ስራ ኢኮኖሚያዊ መሰረት እንዲይዝ የማድረግ ዓቅሙ ግን በቀላሉ መታየት የለበትም።