የኢትዮጵያና የሱዳን ወታደሮች በድንበር አካባቢ በተጠንቀቅ ላይ ናቸው ተባለ

የኢትዮጵያና የሱዳን ወታደሮች በድንበር አካባቢ በተጠንቀቅ ላይ ናቸው ተባለ

/Ethiopia Nege News/:- በሱዳን ካርቱም የደህንነትና የስለላ ምንጮች ለሚድል ኢስት ሞኒተር (MEMO) ሚዲያ ተቋም በሰጡት መረጃ መሰረት ግብፅ በህዳሴው ግድብ ላይ ጥቃት ለማድረስ መዘጋጀቷንና ኢትዮጵያም ከሱዳን ጋር በመተባበር በሁለቱ ድንበር አካባቢ ላይ ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት በሚል በጋራ በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን መረጃው አመልክቷል።

የግብፅ አየር ሀይል እስከ 1500ኪ.ሜ ርቀት ጥቃት ማድረስ የሚያስችል 24 Rafale የተባለ የጦር አውሮፕላን ከፈረንሳ ግዥ መፈፀሟን ተከትሎ፤ኢትዮጵያም በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚሳይል መቃወሚያ አስፍራ ወታደሮቿም በተጠንቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከስድስት አመት በፊት የሀገሪቱን የሀይል ፍላጎት ለማሟላት በሚል በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሀይል ማመንጫ ግንባታ መጀመሩን ተከትሎ በተለይ ከግብፅ ጋር የከረረ ውዝግብ ውስጥ እንደከተተው የሚታወቅ ሲሆን ግብፅ በበኩሏ ለዘመናት ስጠቀምበት የኖርኩት የአባይ ወንዝ ግድቡን ተከትሎ የውሃ እጥረት ይገጥመኛል በማለት ስትቃወም ቆይታለች። በኢትዮጵያ መንግስት መረጃ መሰረትም ሀገራት ለግድቡ የገንዘብ ድጋፍ እንዳያደርጉ አሻጥር ሰርታብኛለች በማለት ግብፅን ሲከስ ቆይቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአልሲሲ መንግስት በጅቡቲ፣ደብቡ ሱዳንና ኤርትራ የጦር ሰፈር ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱንና በኤርትራ ቀይ ባህር አካባቢ ኖራ በምትባል ደሴት ላይ የባህር ሀይል መሰረት ለመክፈት ሚስጥራዊ ስምምነት ማድረጓን የተለያዩ ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን ባለፈው ሳምንት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ግብፅ በኤርትራ 30000 ወታደር በኤርትራ ልታሰፍር መሆኗን ምንጮቸ ነገሩኝ በማለት ለህትመት አብቅቷል።

ይሁንና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ወር በጋዜጠኞች “የአረብ ሀገራት በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ስለሚያደርጉት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን አያሰጋም ወይ” ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ

” ይህን የሚሉ ሰዎች ጂኦ ፖለቲካውን በደንብ ያላጤኑ ናቸው፤

ምንም አይነት ስጋት ሊፈጥር አይችልም።” በማለት መልሰዋል።

ባለፈው ሚያዝያ ወር የኢትዮጵያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ወርቅነህ ገበየሁ በግብፅ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት “ኢትዮጵያና ግብፅ በብዙ ጉዳዮች ላይ አብረን ለመስራት ተስማምተናል” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን ስምምነታቸው ግን ወራትን ሳይሻገር እንከን የገጠመው ይመስላል።

/ethiopia Nege May 6,2017/

LEAVE A REPLY