Ethiopia Nege News:- የቀድሞዉ የሠማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዮናታን ተስፋዬ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ በጻፈው ምክንንያት ለአንድ አመት ከስድስት ወር በተለያዩ እስር ቤቶች ሲንገላታ ከቆዩ ብኋላ ዛሬ በፍርደ ገምድልነቱ የሚታወቀው ኢትዮጵያ ፍርድ ቤት የ 6 ዓመት ከስድስት ወር የእስር ቅጣት ወስኖበታል፡፡
የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን ሽፋን በማድረግ አመጽ አነሳስቷል በሚል ክስ የተመሰረተበት ዮናታን በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ያወጣቸውን መለክቶች ተቆራርጠው ፍርድ ቤ ከመቅረባቸውም በተጨማሪ ከኦነግ ጋር ተባብረሃል ተብሏል፡፡
የዮናታን ተስፋየን የ 1ዓመት ከ 5 ወር የእስርና የፍርድ ሂደት የተክታተለው የኢዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት /ኢሰመፕ/ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡
የፓለቲካ መብቶች አራማጁና የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ወጣት ዮናታን ተስፋዬ አንድ ከአመት ከ5 ወር ያስቆጠረው የፍርድ ቤት ሂደት
የጊዜ ቀጠሮ — ከታህሳስ 18/2008 እስከ ሚያዚያ 26/2008 ዓ.ም
ታህሳስ 18/2008 ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 26/2008 ድረስ በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማእከላዊ) ቆይቷል። በፀረ ሽብር ህጉ ለምርመራ በጊዜያዊ ቀጠሮ ለመቆየት ከሚፈቀደው በላይ (ከአራት ወር በላይ) ክስ ሳይመሰረትበት ቆይቷል።
የቀረበበት ክስ
አራት ወር ከአንድ ሳምንት በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማእከላዊ) ከቆየ በኋላ ሚያዚያ 26/2008 ክስ ተመስርቶበታል። የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ዓም የወጣውን አንቀፅ 4 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ የቀረበ ክስ ነው። የቀረበበት አንድ ክስ ሲሆን በመዝገቡም ብቸኛ ተከሳሽ ነው።
“ተከሳሽ የፖለቲካ አይዲዮሎጂ ዓላማን ለማራመድ በመንግስት ላይ ተጽእኖ ለማሳደር፣ ህብረተሰቡን ወይም የህብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራራት እና የሀገሪቱን መሰረታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሕገ መንግስታዊ. ኢኮኖሚያዊ ወይም ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋትና ለማፈራረስ አስቦ እራሱን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ብሎ በሚጠራው አሸባሪ ቡድን በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ህብረተሰቡን የአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞኖች የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሽፋን በማድረግ ከህዳር 24 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በሚጠቀምበት ድህረ-ገፅ በተለይም በፌስ ቡክ ተጠቅሞ በሽብር ቡድኑ [ኦነግ] የተጀመረውን አመጽና ብጥብጥ ለማስቀጠል” በማቀድ፣ በማዘጋጀት፣ በማሴር እና በማነሳሳት ወንጀል መከሰሱን በክሱ ተገልፇል።
የማስረጃ ዝርዝር
★የሰው ማስረጃ (በፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 መሰረት እና በምስክሮች ጥበቃ አዋጅ መሰረት ስማቸው አልተጠቀሰም)
★የሰነድ ማስረጃ (11 ገፅ ከዮናታን ፌስቡክ ፔጅ የተገኙ ፅሁፎች እንዲሁም 20 ገፅ በማእከላዊ እያለ የሰጠው ቃል)
★ኤግዚቢት (አንድ ኖክያ ሞባይል፣ ሁለት ሲም ካርድ እና አንድ 64GB ሜሞሪ)
የክስ መቃወሚያ
ቀጣይ ቀጠሮ የተያዘው የክስ መቃወሚያ ለመስማት ነበር። በሚያዝያ 15/ 2008 ዮናታን ላቀረበው የክስ መቃወሚያ፤ በሚያዝያ 25/2008 አቃቤህግ ምላሽ ሰጥቶ ነበር። በዮናታን በኩል የቀረበው መቃወሚያ “በመቃወሚያው ላይ የተነሱት ሃሳቦች በማስረጃ የመስማት ሂደት ወቅት የሚታይ ይሆናል” ተብሎ በሰኔ 14/2008 ቀን ውድቅ ተደርጎ በተመሳሳይ እለት የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ ተደርጓል። “ክሱ በቀረበበት መንገድ የተገለጸውን የሽብር ተግባር አልፈጸምኩም፡፡ ሀሳቤን በነጻነት የመግለጽ መብቴን ተጠቅሜ ግን ጽፌያለሁ፡፡ በመሆኑም የሽብር ተግባር አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛ አይደለሁም” ብሏል።
የአቃቤ ህግ ምስክር —ሃምሌ 22/2008
አቃቤ ህግ አቶ አብርሃም ወልዴ እና አቶ መኮንን በላይ የተባሉ ሁለት ምስክሮችን አቅርቦ “ጥር 24/2008 ዓ.ም ተከሳሹ በፌስቡክ ገጹ ላይ የፃፋቸው ጽፅሁፎች በፈቃዱ ታትመው (ፕሪንት ተደርገው) ተከሳሹ የእሱ ስለመሆናቸው አምኖ መፈረሙን የስረዱልኛል” በማለት ጭብጡን አስይዞ ነበር። ሆኖም ዮናታን ምስክሮቹ የደረጃ ምስክሮች ናቸው፤ እነሱ የሚመሰክሩትን ነገር የምክደው ነገር አይደለም፣ ከፌስቡክ ገፄ የተገኙ ናቸው፤ ስለሆነም ጊዜ ከመውሰድ ውጪ መመስከራቸው ጥቅም የለውም ሲል ያቀረበውን ሃሳብ ዳኞች ተቀብለውት፤ የፍርድ ቤቱን ጊዜ እንደሚሻማ ገልፀዋል። አቃቤ ህግ ዮናታን ያነሳውን መቃወሚያ የህግ አግባብ ያለው መከራከሪያ አይደለም በሚል ቢከራከርም፣ ዮናታን በችሎትም ጽሁፎቹ የእሱ መሆናቸውን ስላረጋገጠ ፍርድ ቤቱ የምስክሮቹ መደመጥ አግባብነት የሌለውና የችሎቱንም ጊዜ ማባከን መሆኑን ገልጾ ምስክሮቹ ሳይደመጡ ውድቅ መሆናቸውን ወስኗል፡፡
ብይን — ሐምሌ 28/2008
አቃቤ ህግ ያያዛቸው የሰነድ ማስረጃዎች ተመርምረው፤ በፀረ ሽብር ህጉ አንቀፅ 4ት ስር የተከሰሰው ተቀይሮ የፀረ ሽብር ህጉን አንቀፅ 6ትን እንዱከላከል ብይን ተሰጥቷል።
በቀን ህዳር 24/2008 ዓ.ም ‹‹ህግ የመጨቆኛ መሳሪያ ሲሆን፣ አመጽ የህሊና ህግ ይሆናል››፣
በቀን ታህሳስ04/2008 ዓ.ም በጻፈው ‹‹መሸወድ የለም››፣
በቀን ህዳር 28/2008 ዓ.ም በጻፈው ‹‹እነሆ ሰባት መልዕክቶች››፣
በቀን ታህሳስ 06/2008 ዓ.ም በጻፈው ‹‹የኦሮሞ የተቃውሞ ሰልፎች››፣
በቀን ታህሳስ 08/2008 ዓ.ም በጻፈው ‹‹መንገድ መዝጋት፣ ስራ ማስተጓጎል…›› እና ንብረት ማውደምን በተመለከተ የፃፋቸው ፅሁፎችን መከላከል እንደሚያስፈልገው ተገልፇ ጥቅምት 14/2009 መከላከያ ምስክሮቹን እንዲያሰማ ተቀጠረ።
መከላከያ ምስክር የማሰማት ሂደት (ከጥቅምት 14/2009 እስከ መጋቢት 7/2009 – አምስት ወራት)
የመከላከያ ምስክሮቹን እንዲያቀርብ በተቀጠረበት የመጀመሪያው ቀጠሮ (ጥቅምት 14/2009)፤ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጉዳይ አስፈፃሚዎች ቀርበው ነሃሴ 28/2008 በማረሚያ ቤቱ በደረሰው አደጋ ታራሚዎቹን ወደ ተለያየ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች በመወሰዳቸው ዮናታን ያለበትን ማረሚያ ቤት እንደማያቁ ተናግረው ሌላ ቀጠሮ ተሰጥቷል። [በወቅቱ ዮናታን ቂሊንጦ እንደነበረ እና ወደ የትኛውም ማረሚያ ቤት አለመዛወሩን ከቤተሰቦቹ ማረጋገጥ ተችሏል። በቀጣይ ቀጠሮ (ህዳር 19/2009) ዮናታን የቀረበበትን ክስ ያስረዱልኛል ያላቸውን ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ግለሰቦች በመከላከያ ምስክርነት አስመዝግቧል።
1 ዶ/ር መረራ ጉዲና (የኦፌኮ ሊቀመንበር)
2 ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ
3 አቶ በቀለ ገርባ (የኦፌኮ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር)
4 አቶ ሙላቱ ገመቹ (የኦፌኮ አመራር)
5 ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም (የህግ ምሁር)
6 ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ (የፍልስፍና እና ህግ መምህር)
7 ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ
8 ቀሲስ ተስፋዬ ረጋሳ (አባት)
9 ወ/ት ገዳምነሽ ተስፋዬ (እህት)
10 አቶ ኤፍሬም ታያቸው (ጓደኛ)
የመከላከያ ምስክሮቹ ከመደመጣቸው በፊት ዮናታን የምስክርነት ቃሉን በችሎት አሰምቷል። “…….“ህግ መጨቆኛ መሳሪያ ሲሆን፡ አመፅ የህሊና ህግ ይሆናል፡፡” የሚለው ሃሳብ የተፈጥሮ እና አለምአቀፋዊ ህግ ነው፡፡ ማንም ሊቀይረው አይችልም፡፡ የፍልስፍና መርህም ነው፡፡ ምናልባትም ያን የተናገርኩ ጊዜ የሚሰማ አካል ቢኖር ኖሮ ይሄ ሁላ ችግር ባልደረሰም ነበር፡፡………. በአደባባይ ሰዎች ሲሞቱና ሲገደሉ እነርሱን ዲፌንድ ማድረግ ነበረብኝ፡፡ ይህንንም ሃሳቤን የመግለፅ መብቴን ተጠቅሜ የተለያየ ሃሳብ አቅርቤአለሁ፡፡ ይሄ ጥፋት የሚባል ከሆነ እቀበለዋለሁ፤ ለኔ ክብሬ ነው፡፡ ፍርዱን ከታሪክ እና ከእግዚአብሄር አገኘዋለሁ፡፡” በማለት የተከሰሰባቸውን የፌስቡክ ፅሁፎች ከሽብርተኝነት ጋር እንደማይገናኝ አስረድቷል። [ታህሳስ 27/2009]
· የኦፌኮ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ በ2008 ህዳር ወር በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አካባቢዎች የጀመረበትን ምክንያት እና የነበረውን ሁኔታ እንደሚያስረዱ ጠበቃ ሽብሩ ሲገልፁ አቃቤህግ መመስከር የለባቸውም ሲል ያቀረበው ተቃውሞ በድጋሚ ጠበቃ አቶ ሽብሩ በለጠ ባነሱት መከራከሪያ ሃሳብ ተረትቶ ውድቅ ሆኖ ምስክሮቹ እንዲሰሙ ታዞ ተሰምተዋል። [ታህሳስ 27/2009]
ምስክሮች የመሰከሩባቸው ጭብጦች
· የህግ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ያእቆብ ኃይለማርያም ፣ የፍልስፍና መምህሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እና ጦማሪ በፍቃዱ የሙያ ምስክርነት እንደሚሰጡ፤ ዶ/ር ያእቆብ እና ዶ/ር ዳኛቸው ዮናታን የፃፈው ፅሁፍ ሃሳብን ከመግለፅ ነፃነት አንፃር እና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ህጎች አንፃር ገደቡን ያለፈ አለመሆኑን እንደሚያስረዱ፤ ጦማሪ እና አክቲቪስት በፍቃዱ ሃይሉ ደግሞ በፌስቡክ በግለሰብ አካውንት የሚለጠፉ ፖስቶች ከመደበኛ ሚዲያ እና ከዜና ድህረገፆች የሚለይበትን እንደሚያስረዳ ጠበቃው አቶ ሽብሩ በጭብጥነት አስመዝግበዋል፡፡ አቃቤ ህግ ምስክሮቹ እንዳይሰሙ ሲል ያቀረበው መቃወሚያ የዮናታን ጠበቃ አቶ ሽብሩ በለጠ ባነሱት መከራከሪያ ሃሳብ ተረትቶ ውድቅ ሆኖ ምስክሮቹ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል። [ታህሳስ 27/2009]
· “ዮናታንን ሲያቁት በባህሪው የሽብር የአመጽ ተግባርን እንደሚቃወም እንዲሁም በአስተዳደግም ሆነ በማህበራዊ አኗኗሩ እና አመጣጡ ከተከሰሰበት ወንጀል ጋር ግንኙነት እንደሌለው” የሚል ጭብጥ እንደሚከላከሉለት የተመዘገቡት እህቱ፣ አባቱ እና ጓደኛው ሲሆኑ፤ የእህቱ እና የአባቱ ምስክርነት ተሰምቶ የጓደኛው ተመሳሳይ ጭብጥ በመሆኑ ሳይመሰክር ቀርቷል። በቤተሰባዊ ባህሪውም ከጸብ እና ከግጭት የራቀ መሆኑን እንዲሁም በአስተዳግም ሆነ በማህራዊ ባህሪው ከሽብር ሃሳብ የራቀ መሆኑን አባቱ ቀሲስ ተስፋዬ እና እሁቱ ገዳምነሽ ምስክር ሰጥተዋል። [ጥር 19/2009]
· ዶ/ር መረራ ጉዲና የመከላከያ ምስክሮች ለመስማት ከተቀጠረበት ጊዜ አንስስቶ ፓሊስ ሊያቀርባቸው ባለመቻሉ በርካታ ተለዋጭ ቀጠሮዎች ተሰጥተዋል። ለምስክርነት እየተባለ ቀጠሮ በተያዘበት ፓሊስ እንዲያመጣቸው ተብሎ በታዘዘባቸው 8ት ቀጠሮዎች ሳይቀርቡ ቀርተዋል። ዶ/ር መረራ በሚመሰክሩበት ጭብጥ ላይ የሚመሰክረው ጋዜጠኛ እስክንድር፤ ዶ/ር መረራ ባልቀረቡበት ቀጠሮዎች ሁሉ ተመላልሶ ቀርቧል። በስተመጨረሻም መጋቢት 6/2009 ዶ/ር መረራ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ቀርበው ነበር። ሆኖም ከጋዜጠኛ እስክንድር ጋር በአንድ ጭብጥ ላይ ስለሚመሰክሩ እና እሱ ደግሞ በእለቱ ስላልቀረበ ሌላ ቀጠሮ ተሰጥቷል። መጋቢት 7 ቀን 2009 በነበረው፤ ዶ/ር መረራ እና ጋዜጠኛ እስክንድር በችሎት ቀርበዋል። የሚመሰክሩበት ጭብጥ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ከሽብርተኝነት ጋር እንደማይያዝ ለመመስከር መሆኑን ጠበቃ ሽብሩ ሲናገሩ፤ አቃቤህግ መመስከር የለባቸውም ሲል ያቀረበው ተቃውሞ በድጋሚ ጠበቃ አቶ ሽብሩ በለጠ ባነሱት መከራከሪያ ሃሳብ ተረትቶ ውድቅ ሆኖ ምስክሮቹ እንዲሰሙ ታዞ ተሰምተዋል።
የማረሚያ ቤት አያያዝ
· ዮናታን ሃምሌ 20/2008 በነበረው ቀጠሮ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ቀርቷል። በእለቱ የነበሩት የማረሚያ ቤቱ ጉዳይ አስፈፃሚ በህመም ምክንያት አለመቅረቡን ለፍ/ቤት በችሎት ተናግሯል። በቀጣዩ ቀጠሮ (ሃምሌ 22/2008) ዮናታን ሲቀርብ በማረሚያ ቤት ያለምንም ምክንያት ከሌሎች እስረኞች ተገልሎ በጨለማ ቤት እንዲኖር መደረጉን፣ በቤተሰብ የመጎብኘት መብቱን እና ሌሎች ሰብአዊ መብቶቹ እንደተጣሱ ለፍርድ ቤት አስረድቷል። ሃምሌ 20 በነበረው ቀጠሮ ያልቀረበው የሚደርስበትን የመብት ጥሰት ተቃውሞ ከሳምንት በላይ የረሃብ አድማ ላይ ስለነበረ ሰውነቱ በመዳከሙ መሆኑን ገልፇል። ‹‹ለ9 ቀናት ምግብ ሳልቀምስ ሰውነቴ ተዳክሞ በቆየሁባቸው ቀናት አንድም የፍትህ አካል አልጠየቀኝም›› በማለት ቅሬታውን ያቀረበው ዮናታን ‹‹ቤተሰቦቼን ካድሬና ደህንነት እያዋከባቸው ነው መጥተው የሚጠይቁኝ፡፡ እነዲህም ሆኖ አትገቡም ተብለው ሲመለሱ አዝናለሁ›› ሲል በችሎት ተናግሯል።
· ዮናታን ከህዳር 2/2009 ጀምሮ ቀንና ሌሊት በሰንሰለት ታስሮ ነበር። ዮናታን ተስፋዬ ለዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የዳረገው ህዳር 2/2009 ዓ.ም የፍርድ ቤት ቀጠሮ የነበራቸው እነ አቶ በቀለ ገርባ ወደ ፍርድ ቤት አንሄድም በሚል ከቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር ጋር አለመግባባት ተፈጠሮ ድብደባ ሲደርስባቸው አቶ ዮናታን ‹‹ለምን ትደበድቧቸዋላችሁ፤ በመግባባት ቢሆን አይሻልም ወይ›› በማለት ለመገላገል በመሞከሩ ነው። አቶ ዮናታን ተስፋዬ በተለይ አብሮት የታሰረው አቶ አዲሱ ቡላላ ላይ ድብደባ ሲደርስበት ‹‹ተው አትደባደቡ›› በማለቱ ‹‹ምን አገባህ›› ተብሎ በራሱም ላይ ከፍተኛ ድብደባ ከተፈፀመበት በኋላ ነው በሰንሰለት የታሰረው። ዮናታን ሰንሰለቱ የሚፈታለት ቤተሰቦቹ ሊጎበኙት ሲጠራ ብቻ ነበር።
· ከግንቦት 27/2008 ጀምሮ ከሌሎች እስረኞች ተገልሎ [ከሌሎች እንደሱ የተገለሉ 9 የፓለቲካ እስረኞች ጋር የተገለሉ ብቻ] ጨለማ ክፍል ከሁለት ወር በላይ ቆይቷል፤ ከቤተሰብ ጋርም የሚገናኝ የነበረው በቢሮ በኩል ስንቅ ለመቀበል ብቻ ነበር። የሚደርስበትን መገለል እና የሰብአዊ መብት ጥሰት በመቃወም ለ9ቀን የረሃብ አድማ አድርጎአል።
· ነሃሴ 28/2008 ቀን ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በደረሰው ቃጠሎ ተያይዞ በርከታ ሰብአዊ መብቶቹን ተነፍጓል። ማረሚያ ቤቱ ሳንሱር አድርጎ አስገብቶለት የነበሩ መፅሃፍቶች ተወስደውበታል። አዲስ መፅሃፍም አይገባለትም። ወረቀት እና እስክብሪቶም አይገባም። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከቤተሰብ ጋር እንዲገናኝ የሚፈቀድለት ለጥቂት ደቂቃ ያክል ብቻ የነበረ ሲሆን ከቅርብ ቤተሰብ እና ጓደኛ ውጪ እንዲጠይቀው አይፈቅድለትም ነበር። አሁን ላይ በቀን ከ30 ደቂቃ እስከ 40 ደቂቃ ለሚያክል ጊዜ ብቻ ነው ከቤተሰብ ጋር የሚገናኘው። የቃጠሎው አደጋ ከደረሰ ጊዜ ጀመሮ እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ ምንም አይነት ብር አይገባለትም ነበር።
በመከላከያ ማስረጃነት የቀረቡ ሰነዶች
ዮናታን በመከላከያ ማስረጃነት ያስመዘገበው ጠ/ሚ ሃይለማሪያም ደሳለኝ መጋቢት 1/2008 ቀን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በኦሮሚያ ክልል በተነሳው ተቃውሞ ጋር ተያይዞ ይቅርታ የጠየቁበትን ቪድዮ ማስረጃ ከተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ በታዘዘው መሰረት መጋቢት 27 ቀን 2009 በነበረው ቀጠሮ ከመዝገብ ጋር ተያይዟል። በተጨማሪም ጠ/ሩ ያደረጉትን ንግግር ያለበት መጋቢት 2/2008 ቀን የታተመዘገባ/ዜና የተሰራበት አዲስ ዘመን ጋዜጣም ከመዝገቡ ጋር ተያይዟል። ዮናታን መከላከያነት ያቀረባቸው እና ባስቀረባቸው ማስረጃዎች ላይ ያላቸውን አስተያየት ማቅረብ እንደሚችሉ ለዮናታንም ለአቃቤ ህግም ገልፀዋል።በዮናታን በኩል የሚቀርበውን የክርክር ማቆሚያም ከሚቀጥለው ቀጠሮ በፊት በፅ/ቤት ማስገባት እንደሚቻል ተገልፇል።