የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ይባላሉ። ከመንጋው የኢህአዴግ ሠራዊት ጋር በግላቸው ተወዳድረው በማሸነፍ ኮሚኩን የኢትዮጵያ ፓርላማ በመቀላቀል፤ እንደ አንድ ዜጋና እንደ አንድ የህዝብ እንደራሴ ፤ ከመንጋ ሙሉ የኢህአዴግ የፓርላማ ተመራጮች ጋር አምስት ዓመት ሙሉ ሲተጋተጉ የከረሙ ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ ናቸው።
አቶ ግርማ ሰይፉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታይ ሲሆኑ ፤ በየዓመቱ መስከረም 21 ቀን የጌታችን እና የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል ባረፈበት በግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን በመገኘት ነገረ መስቀሉን በማሰብ ሃይማኖታዊ ሥርዓትም እየፈጸሙ የሚመለሱ መሆናቸውንም በቅርበት አውቃለሁ።
እኔ እመራ የነበረው “አንጋፋው የኢያቄም ወሐና መንፈሳዊ የጉዙ ማኅበር” ከሚገኝበት አዳራሽ አጠገብ ወደ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው ” የማኅበረ ጽዮን የተክለሃይማኖት የጉዞ ማኅበርተኞች ” አባል ሲሆኑ፤ ከማኅበሩ ጋር በየዓመቱ ወደ ግሸን የሚጓዙና ፤ በማኅበሩ ተጉዘውና ግሸን ደርሰው መመለስ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን እንደ ፓርላማ አባል ሳይቆጥሩና ሳይኮፈሱ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ጋወን በመልበስም ፤ የኔቢጤዎችን በማስተናገድና የበረከት ሥራም ሲሠሩ የሚታዩ ኢትዮጵያዊም ጭምር ናቸው።
ታዲያ እኚህ የህዝብ እንደራሴ በአንድወቅት በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ በተሰጠቻቸው” የመብረቅ ብልጭታ” በምትመስል ሰዓታቸው ውስጥ የንግግራቸውን መዝጊያ እንዲህ በማለት ነበር የተጠቀሙት፤
” … በመጨረሻም ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም መልካም የሥራና በኢትዮጵያም ታሪክ ውስጥ አሻራቸውን የሚያኖሩበት የሚችሉበት ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ ። አመሰግናለሁ። ኢትዮጵያ ሀገራችንን እና ሕዝቧን እግዚአብሔር በበረከት ይጎብኛት” ብለው ንግግራቸውን ቋጩ.!። ከፓርላማው የሚጠበቀው አሜን ወይም ዝም ማለት የነበረ ቢሆንም ፤ ፕሮቴስታንቶቹ የፓርላማ አባላት አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳና ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ መላው የኢህአዴግ አባላት ምን እንዳሳቃቸው ሳይታወቅ ፍርፍር ብለው ሳቁ። አስካኩም። አስካኩም አይገልጠውም አላገጡ። የምን በቡራኬ ነው?፣ የምንስ ረድኤት ነው? የሚሉም ይመስሉ ነበር።
በሌላ ቀን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ቢንጃሚን ኔትንያሁ በዚያው በኢትዮጵያ ፓርላማ ተጋብዘው ንግግር አደረጉ። እናም በዚያው ቤት ፣ በዚያው አዳራሽ አይሁዳዊው ጠቅላይ ሚንስትር በንግግራቸው ፍጻሜ ላይ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፣ እግዚአብሔር እስራኤልን ይባርክ ፣ ብለው ንግግራቸውን ቋጩ ። ፈፀሙም ። ከዚያ የተፈጠረውን ሁኔታ ሁላችሁ ቪድዮውን ተመልከቱ።
አቶ ግርማ በአማርኛ የመረቁት ምርቃት መሳቂያ መሳለቂያ ሲያደርጋቸው ፤ እስራኤላዊው በኢንግሊዝኛ የመረቁት ምርቃት ግን መንጋውን በሙሉ አሜን አስብሎ ቆሞ አስጨበጨበ። አባዱላም ፣ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም ፣ ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖምን ጨምሮ ሙሉው የፓርላማ አባል ቆሞ አሽቃበጠ። ማየት ከተሳነቸው ከአቶ አስመላሽ በቀር ያላጨበጨበ አንድም ሰው አልነበረም ። ፓርላማው የፕሮቴስታንት ቸርች መሰለ ። ★ሙስሊሙ አቶ ደመቀ መኮንን እንኳ ሳይቀሩ አሜን ብለው አጨበጨቡ። ኔትኒያሁ የተናገሩት ቃል ግን በነጭ አፍ ከመነገሩ በቀር ያው ኢትዮጵያዊው አቶ ግርማ ሰይፉ በአማርኛ የመረቁት ምርቃት ነበር።
እናም ይሄን አሰብኩ የበቀደሙን የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በእስራኤል ጉብኝታቸው በእስራኤል ሀገር በኢየሩሳሌም ከተማ የሚገኘውን ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዴርሱልጣን ገዳምን ሲጎበኙ ለቤተክርስቲያኒቱ ያሳዩትን ንቀት እንመለከታለን። እናያለንም። ጠቅላይ ምኒስትሩ ፍጹም ንቀት በተመላበት ሁኔታ እሳቸውን ጨምሮ ፕሮቴስታንቷ ባልተቤታቸው ወ/ሮ ሮማን እና ጠቅላይ ሚንስትሩን በመከተል በስፍራው የተገኙት ባለስልጣናት በሙሉ የተከበረውን መቅደሳችንን በጫማ ሲጠቀጥቁት እናያለን። እናታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ ኃይለማርያም በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጫማ እንደሚወለቅ ሳይገባቸውና ሳያውቁትም ቀርተው አይደለም ። የሚገርመው ግን በዚያ መቅደስ ውስጥ በድፍረት ከነጫማው የቆመ እስላም ባለስልጣን መኖሩ ጭምር ነው።
ይህን ታላቅ ድፍረት በራሳቸው በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ የፈጸሙት ጠቅላይ ሚንስትር በዚያው ዕለት የአይሁድን “ኪፓ” አጥልቀው የመጠባበቂያውን ግንብ ተደግፈው በአይሁድ ሕግ መሠረት ጸሎት ሲያደርሱ ታዩ ። እናም ይሄን ይሄን ስናይ ከማዘን በቀር ምን እንላለን ። ምንም ። ምንም ማድረግ አንችልም።
እነሱስ ምን ያድርጉ አሰጠቂዎቹ እኮ የራሳችሁ ሰዎች ነን ብለው የእኛን ቀሚስና ቆብ አጥልቀው መስቀልም በእጃቸው ጨብጠው በስፍራው የተገኙት መነኮሳት ተብዬዎቹ ናቸው።
ታዲያ ይኽ ሁሉ ነገር በዚያች ምድር ሲፈፀም እያየን እስከ ጊዜው ድረስ “የጌታ ፈቃድ” ይሁን ብለን ዝም አልን።