ሀዋሳ የአዲስ ዓመት ፌስቲቫል እያስተናገደች ነው

ሀዋሳ የአዲስ ዓመት ፌስቲቫል እያስተናገደች ነው

/Ethiopia Nege News/:- የሲዳማ ዞን የደቡብ ክልል ርዕሰ መዲና በሆነችው ሀዋሳ ከተማ ዙሪያ የሚገኝ ሲሆን ዞኑ 3.8 ሚሊዮን ህዝብ የያዘ ነው።

የሲዳማ ህዝብ የራሱ ባህላዊ የሆነ የዘመን መለወጫ ”ፊቼ ጨምበላላ” የተሰኘ በዓል በየዓመቱ ተሰባስቦ በጋራ ያከብራል።
የሲዳማ ህዝብ ባህላዊ ዘመን መለወጫ ”ፊቼ ጨምባላላ” በዓል በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ ትምህርትና ባህል ማእከል (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው በ2008 ዓ.ም ሲሆን ዘንድሮም ለሁለት ቀናት በሃዋሳ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።

download (4)

ከጎሳው አባላት ጠይቀን እንደተረዳነው የ “ፊቼ ጨምበላላ” በዓል ታሪካዊ አጀማመር የሚከተለውን ይመስላል:-
አንዲት የሲዳማ “ሴት” ቤተሰቦቿ ከሚገኑበት ራቅ ያለ ቦታ ባል ታገባለች፤ ከቦታው ርቀት የተነሳ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ቤተሰቦቿን ትጠይቃለች። ለመጠየቅ ስትመጣም ከቆጮ፣ ወተትና ቅቤ የተሰራ “ብሪሳሜ” የተባለ ምግብ ይዛ ትመጣለች ።ይህንን ለቤተሰብ የመጣ ምግብ ለጎረቤትም ታጋራለች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፊቼ ለዚዳማ ህዝብ የመሰባሰቢያና የአንድነት ምልክት ተደርጎ በየአመቱ መከበር ጀመረ።
በበዓሉ ላይ በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ የጎሳው አባላት የሚሳተፉበት ሲሆን የተለያዩ ዘፈኖችና ባህላዊ ውዝዋዜዎች አንዲሁም የፈረስ ጉግስ ያካተተ ነው።

በዓሉ የሚከበርበት ቀን በጎሳ መሪዎች የሚወሰን ሲሆን የመጀመሪያው ቀን ህፃናትና ወጣቶች ጎረቤቶቻቸውን እየዞሩ እንኳን አደረሳችሁ በማለት ይጀምራሉ።

በበዓሉ ዕለትም የጎሳ መሪዎች የሲዳማ ህዝብ ጠንካራ ሰራተኛ እንዲሆን፤ ሽማግሌዎችን እንዲያከብርና እንዲከባከብ፤ ዛፎች ያለ አግባብ እንዳይቆረጡና ስርቆት አፀያፊ ተግባር እንደሆነ ይመክራሉ። በሲዳማ ህዝብ እንዲሁም በሌላው መካከል እኩልነት፣ መልካም አስተዳድር፣ የባህል መከባበርና ተከባብሮ በጋራ መኖርን መሪዎቹ አጥብቀው የሚሰብኩት መሆኑን ተመልክቷል።
ለበዓሉ ታዳሚዎች እንኳን አደረሳችሁ ብለናል /ኢ.ነ.ድ.ገ.ዝ.ክ/

LEAVE A REPLY