አቶ ሀብታሙ አያሌው እሱም ብዙ እያለ ስለ አርሱም እየተባለ ነው፡፡ ፖለቲካችንም ማህበራዊ ኑሮአችንም የተቃኘው በእውነት ላይ ሳይሆን በስሜት ላይ ሆነና አፍቅረን ሰንደግፍ ሆነ ጠልተን ስንነቅፍ ምክንያት ብቻ አይደለም ለከትም የለንም፡፡ሜዳው ላይ ልጆች በዙና፣ጨዋነት እየኮሰመነ ዋልጌነት እየገነነ መጣና ትላልቆቹ እድሜ ጠገቦቹ ተግባራቸው ሀገር ሊያድን፣ ረጋ ሰከን ብሎ ነገሮችን ግራ ቀኝ አይቶና መዝኖ የመደገፍም የመንቀፍም ባህል የሌለን መሆናችን ሰሞኑን በአቶ ሀብታሙ አያሌው ዙሪያም እየታየ ነው፡፡ ሜዳው ላይ ልጆች በዝተው ጨዋነት እየኮሰመነ ዋልጌነት በመግነኑ ትላልቆቹ ስራቸው ሀገር ሊያድን ምክራቸው ትውልድ ሊቀርጽ የሚችሉቱ አፋቸው ከመናገር እጃው ብእር ከማንሳት በመቆጠቡ ነገራችንን በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ እንዲሉ አድርጎታል፡፡
በአንድ በኩል ሀብታሙ በጠና ታሟል ተብሎ በኦክስጂን እንደሚኖር የሚያሳይ ፎቶ በፌስ ቡክ እያሰራጨ እንዴት ለማስረገዝ በቃ እስከ ማለት ከደረሰው ሰዋዊ መንፈስ ከሚጎድለው ተቃውሞ፣በሌላ በኩል ብቸኛ የለውጥ አርበኛ አድርጎ እስከ መሳል የደረሰ ድጋፍ እየን እየሰማን እያነበብን ነው፡፡ ይሄ ለአድራጊዎቹም ለሚደረግለት/ ለሚደረግበት ሀብታሙም አይጠቅምም፡፡
ማን ስለሆነ፣ ምን ስለሆነ፣ ምን ስላደረገ ምን እንዲያደርግ ስለምንፈልግ እንደምናደንቅ እንደምናሞግሰው የእንደምናወግዝ እንደምናንቋሽሸው በማስረጃ ማሳየቱ በምክንያት መግለጹ ነበር የሚበጀው፡፡ግን አልሆነም ሊሆን የሚችልም አይመስልም፡፡ አጀንዳ ቀርጸን ለጋራ ጉዳያችን ለነገ ግባችን የሚበጅ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር አቅሙም እውቀቱም ፍላጎትም የለሌለን ሰዎች ግለሰቦችን ማእከል እናደርግና ደጋፊና ነቃፊ ሆነን እንሰለፍና ከሙግት ክርክር የዘለለ የቃላት ጦርነት እንከፍታለን፡፡የፖለቲካ ንግድ የፕሮፓጋንዳ ጨዋት እንጀምራለን፡፡ በዚህ መመንገድ ስንቶች አለፉ፣ስንቶችን ዳግም ወደ መድረኩ እንዳይመለሱ አድርገን ሸኘን፤ ስንቶች ህይወታቸውንአጡ ስንቶች ከበሩ፣ስንቶች ተገለባበጡ ስንቶች በማተቤ ልዳኝ (የአቶ አሰፋ ጫቦ ቃል ነች ነብስ ይማር) እንዳሉ አሉ/ይህችን አለም ተሰናበቱ፣ ወዘተ መልስ አልባው ጥያቄ ብዙ ነው፡፡
ስለ ሀብታሙ መነጋገሩ ካለፈው ለመማር ለመጪው ለትግሉ የሚሆን ነገር ለማትረፍ ከሆነ ዛሬም አንደትናንቱ ምንም አንዳላስገኘው በሆያ ሆዬ መሆን የለበትም፡፡ የሚሻለው ሀብታሙ የተጓዘባቸውንና የደረሰበትን አራት የፖለቲካ ምዕራፍ በጥሞና በመፈተሸ መነጋገሩ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ላይ መረጃና ማስረጃ በስፋት ኖሮኝ ዘለግ ብዬ ብሄድበት በወደድኩ ነበር፡፡ግና የለኝምና ይህ በሌለበት መጻፍ ደግሞ ከመነሻው የተቃወምኩት ከእውነት የተፋታ አጉል ደፋርነት ወይንም አጉላ ዘለልነት ስለሚሆን አልሞክረውም፡፡ የዝምታ ድባቤን ጥሼ ግዝት መሀላየን አፍርሼ ይችን ጽሁፍ የመጻፌ ዓላማም ሆነ ፍላጎት የሚያውቁ እንዲነግሩን ለመጠየቅ ብዙ እያወቁ ዝምታ የመረጡትን እሽኮለሌው አስጠልቷቸው ነገሩ የልጅ ጨዋታ ሆኖባቸው የዳር ተመልካች መሆንን የመረጡ ወገኖችን እባካችሁ ዝምታ አጥፊን ያበረታታል አሉባልታን ያሰፋል ሀሰትን በእውነት ላይ ያነግሳልና በቅ በሉ የምታውቁትን ጻፉ ተንፍሱ ንገሩን አስተምሩን ለማለት ነው፡፡ ለመነሻም ለመኮርኮሪያም ይሆን ዘንድ ሲባል ከባጀው ትንሽ ልነካካ፡፡
ምዕራፍ አንድ፣ የሀብታሙ ፖለቲካ፣እሱም እንደሚነገርን እኛም እንደምናውቀው የወያኔ የወጣት ማህበር ሊቀመንበር ሆኖ ነው የሚጀምረው ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አቶ ጌታቸው ረዳ አንድ ሰሞን የግንኙነት መስሪያ ቤቱ ምኒስትር የነበረውና አሁን የትና እንዴት እንዳለ የማይታወቀው በአንድ የቴሌቭዝን ክርክር ወቅት ከሀብታሙ ጋር መንግሥትንና ተቀዋሚን ወክለው ግራና ቀኝ ተቀምጠው አንተ እኮ በዚህ ጉዳይ ከእኛ በላይ ስትከራከር ነበር ብሎ የመሰከረለት እንበለው የመሰከረበት ደንበኛ ካድሬ ነበር፡፡ ካድሬም ሆነ የወጣት ሊቀመንር የነበረ መሆኑ በተለይ ንስሀ ከመግባቱ ጋር ተያይዞ ሊያስውቅሰውም ሊያስነቅፈውም አይገባም ባይ ነኝ፡፡ የመደራጀት መብት ይከበር ስንል ወያኔ መሆንንም ጭምር መሆን አለበት፡፡ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ስንል የሚጥመንንም የሚጎመዝዘንም ሀሳብ የሚያራምዱትን መሆን አለበት፡፡ ነገርን ከስሩ ውሀን ከጥሩ ነው ከተባለ ጥያቄ ሊሆን የሚችል የሚመስለኝ አገባቡ እንዴት ነበር? በቆይታው ምን ሰራ? ከጳጳሱ ቄሱ ለመሆን ይዳዳው ነበር ወይ? ወዘተ የሚለው ነው፡ ይህ መታወቁ በቀጣዮቹ ምዕራፎች ለሆኑት ጉዳዮች እንዴትነትና ምንነት መሰረት ይሆናሉ፡፡
ምዕራፍ ሁለት፣ የሀብታሙ ምዕራፍ ሁለት የአጭር ግዜ ጎዞ ፖለቲካውን ከኢኮኖሚው ያዛመደ ወይንም በፖለቲካው መሰላል ወደ ኢኮኖሚው ለመንጠላጠል የሞከረበት ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር፡፡ ደቡብ አፍሪካ ተገኝታችሁ ጨዋታውን መከታተል ትችሉ ዘንድ አመቻችተንላችኋል ብሎ ከአያሌ ኢትዮጵያውያን ከዘረፈው አጭበርባሪ ሰው ጋር ተባባሪ ሆኖ መስራቱ በሰፊው ሲወራ ነበርና ይህን ማወቁም መጨረሻ ላይ ሊነሳ ለሚችለው ጥያቄ መደላድል ይፈጥራል፡፡በተለይም ከዚህ በኋላ ነውና ወደ አንድነት የገባው፡፡
ምዕራፍ ሶስት፣የሀብታሙ ምዕራፍ ሶስት የፖለቲካ ጉዞ አንድነት የገባበት ነው፡፡እዚህ ምዕራፍ ላይ ትንሽ ቆይትም ዘለቅም እንበል፡፡በምዕራፍ አንድና ሁለት ማንነቱን ያየነው ሀብታሙ አንድነት ፓርቲ መግባቱ በወያኔ ስለተገፋ፣ ወይንስ እዛ ያለው የነበረው ሁኔታ እንደሚፈልገው ስላልሆነለት ስላልተመቸው፣ ወይንስ የወያኔዎቹ ነገረ ስራቸውን ተጸይፎ በእምነት በአመለካከት ተለይቶ፣ ወይንስ…. ብዙ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ሌላው ከመምጣቱ ለሹመት መብቃቱ የእሱ ብቃት ወይንስ አንድነት የሰው ድርቅ የመታው ስለነበረ ወይንስ ሌላ ምክንያት ነበረው? ሹመት ያዳብር ተብሎ ሳይጠግብ በውስጡ ያለው እምነት ቀርቶ በሸሚዝና በጃኬቱ ላይ የነበረው የወያኔ ጠረን በቅጡ ሳይለቅ በአደባባይ ወያኔን አውጋዥ ለመሆን መብቃቱስ፣ ተቀዋሚነት ወይንስ ቂም የመወጣት ስሜት? የትግል ቁርጠኝነት ወይንስ እዛ ያጣሁትን እዚህ አገኘሁት እዩኝ ማለት? ወይንስ አንደ ስየ አብርሀ አንድነትን በቁልቁለት መንገድ የማስሮጥ ስልት፣ ሌላም ሌላም ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ ግን ሂሳብ ለማወራረድ ሳይሆን ከትናንት ለመማር፤ ለዛሬ መራመጃ ለነገ መዳረሻ የሚሆን ነገር ለማትረፍ፡፡
በረራው ከተገቢው ፍጥነት በላይ ሲሆን መጠርጠር የደህንነት ሰራተኞች ብቻ ሳይሆን የፖለቲከኞችም ተግባር መሆን አለበት፡፡ይህ ግን የለም አብሮ መብረር ወይንም ዳር ቆሞ ውግዘት ነው፡ ትናንትም ዛሬም ያለው፡፡ አንድነተን ለሞት ያበቃውም ሌሎቹንም በዳዴ የሚያስኬደውም ይሄው ነው፡፡ ከወያኔነት ወደ ተቀዋሚነት ያውም በአባልነት ሳይሆን በሹመት ከዛ በቅጽበት ወደ ፉከራ መሸጋገር ፉከራው ተሰምቶ ሳያልቅ ወደ እሰር ቤት፣እስር ቤት ከእርሱ ቀድመው ከታሰሩም አብረውት ከገቡትም በላይ ስሙ መግነን፤ ከዛ በነጻ መሰናበት፣ከዛ ወደ ምዕራፍ አራት ሽግግር፡፡ ይህ እንዴት ሆነ ብሎ ያልመረመረና በስሜት ሳይሆን በእውነት፣በአጉል ጥላቻ ወይንም ፍቅር ሳይሆን በመረጃና ማስረጃ ጭብጡን ያልጨበጠ ተቃውሞም ሆነ ድጋፍ ከንቱ ነው፡፡ምን አልባት አንዱ ወገን እርሱን ከፊት አስቀድሞ ገንዘብ የመቃረም፣ ሌላው በእርሱ ላይ የጥላቻ ናዳ በማውረድ እንዲሁ ፈረንካ የማግኘት እቅድ ካልተያዘ በስተቀር፡፡
ምዕራፍ አራት ሀብታሙ በአሜሪካ፡፡ ዲያስፖራውና የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንድ ራሱን የቻለ መጽሀፍ ሊያጽፍ የሚችል ነው፡፡ሙያውና ፍላጎቱ ብሎም ለነገሩ ቅርበቱ ላለው፡፡እነርሱ ሀብታሙን ይቃኙት ወይንም እርሱ እነርሱን መንገድ ያሲዛቸው በርቀት የለኝ ምልከታ ይህን ለመረዳት የማያስችለኝ ቢሆንም ለግዜው ሰምና ወርቅ ሆነው ዓላማና ግቡ ባይታወቅም ከከተማ ከተማ እያዞሩ እያናገሩት ነው፡፡ዓላማና ግቡ ባይታወቅም ስል ምክንያት አልባ አይደለም፡፡ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው፤ስለ ወያኔ ማንነትና ምንነት እንዲያስረዳ ነው፣ ወያኔ ስለሚፈጽመው ግፍ የአይን ምስክር እንዲሆን ነው ወዘተ የሚባል ከሆነ ሀያ ስድስት አመት ያልደረሰብን ያላየነውና ያልሰማነው ምን አዲስ ነገር በሀብታሙ አንደበት ተነገረ የሚል ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡
የወያኔ ድርጊት መች ነጋሪ መች አስረጅ ይሻና፡፡ በይፋ በአደባባይ የሚፈጸም አይደለም እንዴ፡፡ እየነገሩን አይደለም እንዴ ሁሉን የሚያደርጉን፡፡ ሰምቶ የሚቆጨው፣ አይቶ የሚመረው፣ ቁጭት የሚያንገበግበው ቁጥሩ ሚዛን አልደፋ ማለቱ እንጂ ክፋቱ፡ ከንፈር እየመጠጠ የሚያልፈው፣ ሞኝ የሰማ እለት እንዲሉ ትናንት የሰማውን/አይደለም የተፈጸመበትን ዛሬ አንደ አዲስ ደግመው ሲነግሩት እየየ! ያዙኝ ልቀቁኝ ብሎ ነገ መልሶ የሚረሳው፣ የወያኔን ባላሥልጣኖች በተናጠልም ሆነ ድርጅቱን በጅምላ በማህበራዊ ድረ- ገጽ ተሳድቦ በዚሁ ረክቶ ለሽ ብሎ የሚተኛው መብዛቱ እንጂ ችግሩ፤ አየር ላይ በቃላት የሚዋጋው(ይህም እርስ በአርስ ነው) ተግባሩ ላይ መሳሳቱ እንጂ ጉዳቱ መች የወያኔን ማንነት አለማወቅ መች ነጋሪ አስረጅ ማጣት ሆነና፡፡
እናም አበው ነገርን ከስሩ ውሀን ከጥሩ እንደሚሉት ሀብታሙን ለመደገፈፍም ሆነ ለመቃወም እነዚህን አራት ምዕራፎች ሌላ የሚታወቅም ካለ ተጨምሮ በቅጡ ተመርምሮ የተጓዘው እየተገለባበጠ ወይንስ እምነት አመለካከቱን እየለወጠ፣ ለትግሉ ራሱን እየሰጠ ወይንስ ለጥቅም ጌታ እያማረጠ፣ እንዲሁም በእያንዳንዱ ምዕራፍ ከእርሱ እውቅና ውጪም ይሁን በእርሱ ይሁንታ በሶስተኛ ወገን የተሰራ ካለ ይህን በቅንነት ለመነታረኪያ በሚሆን ሳይሆን ለመማሪያ በሚበጅ መልኩ መቃኘቱ ለነገረ ጭብጡ መሰረት ሊሆን የሚችል የሚገባም ይመስለኛል፡፤እናም የምታውቁ አንድ በሉ፡፡
ይህችን አስተያየት ለመጻፍ ሳስብ አንዳንድ አንድነት ቤት የነበሩ ሰዎችን ለማግኘት ሞክሬ ነበር፣ ከአንድነት መፍረስ በላይ የሚያሳዝኑም የሚያሳፍሩም የሚያበሳጩም ነገሮች ነው የሰማሁት፡፡ ለሁሉም ግዜ አለውና አንድ ቀን ይወጣ ይሆናል፡፡ነገረ ስራው ሁሉ የወረት ፣የአንድ ሰሞን ሁካታና ጫጫታ የሆነው አብዛኛው ዲያስፖራ ሌላው ቀርቶ ዛሬ ከእስር ቤት ተፈቶ ከወያኔ መንጋጋም ተላቆ በነጻነት ሀገር በነጻነት ከሚኖረው ጋራ እየሆነ ያለውን ሲሆን ፣ከሀብታሙ ቀድመው የአንድነት አባል የነበሩ (እንደውም መስራቾች) በወያኔ እስር ቤት በስቃይ ላይ እያሉ ከእነ ስማቸውም መርሳቱ ሁሉ ነገራችን የተመሰረተው በእውነት ላይ ሳይሆን በስሜት፣በምክንያት ሳይሆን በቡድንተነኝነት፣ብሎም በጥቅም ትስስር ላይ ስለመሆኑ አጋላጭም አረጋጋጭም ነው፡፡እንዴት ናትናኤል ይረሳል፣አንዱአለም እንኳን አልፎ አልፎም ቢሆን ስሙ ይነሳል፡፡( ለአብነት ሁለቱን አነሳሁ እንጂ ከሰዎቹ የሰማሁት ብዙ ) ለነገሩ ለታሰሩ አባሎቻቸው እንኳን ሲሉ ነገሮችን በውይይት ማስተናገድና ወንዙን መሻገር ተስኖአቸው ፓርቲን ለመፍረስ የዳረጉ ሰዎች፣እነዚህንም አይዟችሁ እያሉ እስከ ቀብር የሸኙ ሰዎች እንደምን እስር ቤት ያሉ አባሎቻቸውን እንዲያስታውሱ ይጠበቃል፡፡
እነዚህ ከነመኖራቸው የተረሱ ወገኖች የታሰሩበት ፓርቲ አመረራር አባላት የነበሩ ሰዎች ከፓርቲው በዘረፉት ንብረት ሀብት አካብተው ቢጠሩዋቸው የማይሰሙ ሆነዋል ተብሎ በማስረጃ ቢነገርዎት ምን ይሰማዎታል፡፡ እኔ ዓሳ ጎርጓሪ ዘነዶ ያወጣል ሆኖብን ይሄ ነው ያጋጠመኝ፡፡ ለእውነት ስለ እውነት የቆምን ቢሆን ሙስናና ዘረፋን ክህደትና በስልጣን መባለግን አንባገነንነትንና ህገ ወጥነትን ወዘተ የፈጻሚውም ሆነ የተፈጸመበት ማንነትና ምንነት ሳያግደን እኩል መቃወም መቻል ነበረብን፡፡ ግን ጉዳዩ ከዚህ በተቃራኒ ሆነና በፓርቲ ንብረት የከበሩ፣ በእስር ቤት በሚሰቃዩ ዜጎች መስዋዕትነት የሚነግዱ ወዘተ ወገኖችን አይተን እንዳላየን እናልፋለን ወይንም የጥቅም ተጋሪ ሆነን አፋችንን እንለጉማለን፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋል ሆኖብኝ ከርእሰ ጉዳዬ ወጣሁ፡ልመለስ፡፡ድጋፋችንም ሆነ ተቃውሞአችን አንድ ሰሞን የሞቅታ የሚሆነው የቆምንለት ዓላማና አሸጋግረን የምናየው የጠራ ግብ የሌለን ወይንም ግዜያዊ የሆኑት አለማዊ ጉዳዮች ይህን እየጋረዱብን በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ባይሆን ኖሮ ለእያንዳንዱ ንግግራችንንም ሆነ አድራጎታችን መነሻ የምናደርገው ዓላማና ግባችንን፡ ድርጊቶቻችንን የምንመዝነውም ለዓላማችን ስኬት ወደ ግባችን ለመዳረሻ ጎዞአችን ፍጥነት ምን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ በሚል ይሆን ነበር፡፡ የሀብታሙ አያሌው በየመድረኩ እየተገኘ ወያኔ ገዳይ ነው፣ ገራፊ ነው ማለቱ ታማኝ በየነ እንደሚለው የእኛ ብሶት ማውራት ለቅሶና ኡኡታ ማሰማት እነርሱን ያስደስት ሌላ ማሰቃያ ሌላ ማስለቀሻ ማስጮሂያ ስልት እንዲያስቡ ያደርግ ካልሆነ በስተቀር ሀያ ስድስት አመት የተባለ እንደመሆኑ አዲስ ይዞት የመጣ ፋይዳ አይታየኝም፡፡ የሰው ልጅ ከደረሰበት በደል በላይ ስለ በደሉ ሲነግሩት ያለቅሳል እንዲሉ ማስለቀስ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ይህንም ለምደን ተለማምደነዋል፣አዳራሹ ውስጥ አልቅሰን አጨብጭበን ገና ከበሩ ሳንወጣ ምን እንደተባለ እንኳን እንረሳዋለንና ሌላ ሌላ ጥቅም ካለው እኔ አላውቅም እንጂ ዛሬም ብሶት ማውራት ዛሬም ወያኔን ማውገዛ ማጥላላት መዝለፍ መፎከር የትም አያደርስም፡፡ በዚህ በዚህ ቢሆን ወያኔ ሀያ ስድስት አመት አይደለም አስር አመት አይቆይም ነበር፡፡በዚህ በዚህ ቢሆን እነ አንቶነኔ ዛሬ የምናያቸው ምንይልክ ቤተ መንግሥት ነበር፡፡ አቦ ሰከን እንበል! አንገት የተሰራው አዙሮ ለማየት ነው የሚባለው ለምን ይሆን!