አቶ መርሻ በቅርቡ ለጥቁር ሕዝብ፣ ለአፍሪካውያን፣ ለራሳችን (ለኢትዮጵያውያን) መጭ፡ትውልድ፣ በማሰብ ኢትዮጵያን ጠብቀን እናቆይላቸው በሚል ርዕስ ምክር አዘል ጽሑፍ በሰባት ሽህ ቃላት ታጅበው የሃያ አንደኛው ክፋለ ዘመን ኢትዮጵያዊ ወጣት ትውልድ ለሀገራዊ አንድነቱና ነፃነቱ ቀናዔ የሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም ያገናዘበ ሀገራዊ ዓላማ አንግቦ፣ በሙሉ ልቡ ለኢትዮጵያ ትንሳዓኤ እና ነፃነት ቆርጦ እንዲነሳ እና እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል ። እርሳቸው እና መሰሎቻቸውም ከወጣቱ ጎን ቆመው ሃሳብ እና ምክር እንደሚለግሱ በአጽንዖት ቃል ገብተዋል። ከጽሁፋቸው መገመት እና መረዳት እንደሚቻለው ከፖለቲካው መድረክ እራሳቸውን በጥሮታ መልክ ያገለሉ አለያም ለማሸለብ (hybernate) ያሰቡ ይመስላል።
እንደሚገመተው አቶ መርሻ በ80ዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል የሚገኙ አዛውንትና አክራሪ ግራ-ዘመም ፖለቲከኛ ናቸው። በዚህ ዕድሜአቸው ዘመኑ የወለደውን የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ሃሳባቸውን ማስተላለፍ መሞከራቸው ያስመሰግናቸዋል። ከ66ቱ አብዮት ጀምሮ እስካሁን ቀንደኛ የኢሃፓ አባል ብቻ ሳይሆኑ ከፍተኛ የአመራር አካል በመሆን ድርጅቱን ያገለገሉ መሆኑን ከሰዎችም ከርሳቸውም ሰምተናል።
ያ-ትውልድ የፈፀመውን አሉታዊና አውንታዊ የፖለቲካ ክስተቶች ካሠቡ፣ ከተገበሩ እና ካስተገበሩ የኢሃፓ አባላት መካከል ቀዳሚ ተዋናኝ እንደነበሩ ለማወቅ ነቢይ መሆንን አይጠይቀም። በመሆኑም ካካበቱት ልምድ ተነስተው ያሁኑን ትውልድ ለመምከርና እና ለማስተማር መከጀላቸው ተገቢ ነው። ምክንያቱም ግለሰቡ የመረጃ፤ የልምድ እና የተመክሮ ቤተመዘክር ናቸውና። በግልፅ፤ በድፍረት፤ በቆራጥነት፤ በእውነት ከተናገሩ ለዚህ ትውልድ ብዙ ትምህርት እና ምክር ሊሰጡ ይችላሉ። ይህ ሰፊ ኑዛዜ አዘል ምክር እና ተመክሯቸው (lessons learned) ዘግይቶ የመጣ ቢሆንም እንዲሁ ከሚቀር ዝግይቶ መደረጉ (better late than never) መልካም ነው።
ቁምነገሩ ተመክሯቸውን እና ልምዳቸውን ለኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል እና ተስፍ ሲሉ (ለድርጅታቸው ሳይሆን) ያለማወላወል ሊነግሩን እና ሊአጋሩን ይችሉ ይሆን ወይ ነው። በተለይ እርሳቸውም ሆነ የሚመሩት ድርጅት በታሪክ አጋጣሚ ታሪካዊ ስህተት ሠርቶ ነበር ይሉ ይሆን የሚለው ለሁላችንም የሚሊዮን ብር ጥያቄ ይሆናል። ምንያቱም በልምዳችንም ሆነ በባህላችን እኔ ልክ ነኝ የሚል አባዜ የተጠናወተን፤ ይቅርታ ተሳስቸ ነበር ማለትን እንደውርደት እና እንደሽንፈት ስለምንቆጥር በግልጽ ይነግሩናል የሚል የሞኝ ተስፍ አንይዝም። በተለይ አክራሪ ፖለቲከኞች እና አምባገነኖች ይቅርባይነትን እና ተሳስቻለሁ ማለትን እንደክሽፈት፤ ፍርሃት፤ ውርደት ስለሚአስቡት የሚአደርጉት አይመስልም። የአክራሪ ፖለቲከኞች በሐሪ የሚአስተምረንም ይህኑ ሐቅ ነው። ምሳሌ ለመጥቀስ ካስፈለገ መኢሶን፣ ህውሃት፤ ኢሃፓ፤ ፖልፖት፤ ማኦኢዝም፤ አፓርታይድ ወዘተ በዚህ አቋማቸው የተካኑ ምስክሮች ናቸው።
ሆኖም አቶ መርሻ በቁሰ-አካል ፍልስፍና፤ በሒስ እና ግለ-ሒስ የሚአምኑ የግራ ፖለቲካ አቀንቃኝ ስለሆኑ በድፍረት ይናገራሉ ብለን ግን ተስፍ እንሰንቃለን። ስለሆነም የጥርጣሬ ስብዕናን (the benefit of the doubt) ሳልነፍግ ጽሑፋቸውን እና ሰፊ ኑዛዜአቸውን በጥሞና አንብቤአለሁ። ከዚህ በተጨማሪም ዕድሜ እየገፋ ወደ ላይኛው ቤታችን የመሄጃ ጊዜ ሲቀርብ እውነት ተናግሮ መሸኘትን ሰዎች ሁሉ ይወዳሉ። ለምሳሌ በቅርቡ አንድ የMI-5 የደህንነት ሰው በሞት አልጋው ላይ ሆኖ ልዕልት ዳያናን እና ሌሎች አራት ታዋቂ ግለሰቦችን በእንግሊዝ ልዑላን ቤተሰብ ትዕዛዝ ግድያውን እንደፈጸመ ተናዟል። አበው ሲተርቱ እውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ማድር ይላሉ። መርሻም እውነቱን ተናግረው እየመሸ ባለው የግዜ ቤት ሄደው ያድራሉ ብለን እየጠበቅን እረዥም ጽሑፋቸውን እንድታነቡላቸው እመክራለሁ።
በጽሑፋቸው ያ-ትውልድ ያደረገውን ስህተት የ21ኛው ክፈለ ዘመን ኢትዮጵያዊ ወጣት እና ትውልድ እናዳይደግም በማሳሰቢያ መልክ አጽኖዖት ሰጠው ምክር አዘል ማሳሰቢያ ሰጠዋል። የፀረ-ካፒታሊስትና የፀረ-ኢምፔሪያሊስት ቋንቋቸውን እና እምነታቸውን አንፀባርቀዋል። ለኢትዮጵያ ፖለቲካያዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ፀጥታዊ እና ማህበራዊ ቀውስ የምዕራቡን ዓለም እና ኢምፔሪያሊዝምን ተጠያቂ አድርገዋል። ሶስተኛው ዓለም ኢትዮጵያን ጨምሮ ማለታቸው ነው የኒዎ-ሊበራሊዝም ፍልስፍና ባነሆለለው የተማረ ወይም የተመለመለ አገልጋይ (petty bourgeois) የሆነ ክፍል መሣሪያነት በምእራቡ ዓለም ተመዝብሯል ይሉናል። እርግጥ የምዕራቡ ዓለም በሶስተኛው ዓለም ላይ የማይናቅ ተጽዕኖ እንዳደረገ የማንስማማበት አመክንዮ አይኖርም።
በአንፃሩ መርሻ ጥብቅና የቆሙለት ምሥራቃዊው ዓለም (Eastern World) በርሳቸው ቋንቋ የላባደሩ ዓለም (ህብረተሰብአዊነት እና ኮሙኒስም) ከምዕራቡ ዓለም ባልተናነሰ ደረጃ ለሃገራችንና ለሶስተኛው ዓለም የፖለቲካ ችግር እና ቀውስ አስተዋጾ ማድረጉን ሳይገልጹ በለሆሳስ አልፈውታል። ሶስተኛው ዓለም በተለይም ኢትዮጵያ አክራሪ የግራ ፖለቲካ ፍልስፍና ባነሆለለው የተማረ ወይም የተመለመለ አገልጋይ (revolutionary)የሆነ ክፍል መሣሪያነት በአብዮት ስም ሕዝባችን ፍዳ እንዳየ እንዴት ሊገልጹና ሊአስተምሩን አልከጀላቸውም። አብዮት ልጆችቿን ትበላለች ብለው እነመርሻ እንደሰበኩት ሁሉ አሁን ደግሞ የዚያ ግራ ዘመም ፖለቲካ ቅሪት አገሪቱንም ጨርሶ ሊበላት መቃረቡስ ለምን አልታያቸውም።
መርሻ አያይዘውም ጥቂት የተደራጁ አላዋቂዎች ወይንም መሃይሞች፣ የዕምነት አክራሪዎች፣ የተለያዩ አጋጣሚዎችን ተጠቅመው የአንድ ሀገርን መንግሥታዊ ሥልጣን ከጨበጡ፣ አዛዥና ናዛዥ፣ ፈላጭና ቆራጭ ሆነው የሚያዙትን ሃይል ለዚያው፣ ካላዋቂነት የያዙትን ዕምነትና መመሪያቸውን ለመተግበር በማሰማራት ከፍተኛ ጥፋት ሊያደርሱ ይችላሉ ይላሉ። እውነት ብለዋል። በኢትዮጵያ አብዮት ታሪክ እና ዘመንም የሆነው ይኸው ነው። ጥቂት የተደራጁ አላዋቂ አክራሪ የግራ ፖለቲካ አቀንቃኞች ኢሃፓ፤ መኢሶን፤ ሕውሃት፤ ሻቢያ ወዘተ በሃገራችን እና በሕዝባችን ላይ ያደረሱት ጥፋት እና እልቂት በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ይህን ሐቅ ደፍረው ለመናገር ለምን አልቻሉም ወይም ሳይፈልጉ ቀሩ። ለዚህ ምክንያቱ አንድ እና አንድ ነው። ዓለም የወዛደሮች ትሆናለች ለሚለው መርህ አቀንቃኝ ስለሆኑ ይህን ማውገዝ አላስፈለጋቸው ይሆናል።
መርሻን የመሰሉ የወዛደሩ አምባገነን መሪዎች እና ጠበቆች ደግሞ ለዚህ አጋርነታቸውን ማሳየት ስለሚጠበቅባቸው ሳይኮንኑት፤ በተመክሮነትም ሳይገልጹልን አልፈዋል። የአይጥ ምስክሩ ድምቢጥ ሆኖባቸው ስለሆነ አንታዘባቸውም። ነገር ግን ለማስተማርና ለመምከር የከጀሉትን ያህል ግን በዚህ እረገደ ትምህርትና ተመክሮ ሳይሰጡን እናዳለፉ ግን ይወቁት።
ሆኖም ከምዕራቡና ከምስራቁ ዓለም በበለጠ በሃገራችን ፖለቲካ ትልቁን ሚና እና ተጽዕኖ ያደረገው የዛትውልድ ለመሆኑ መቀበል ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። አሁንም እያደረገ ይገኛል። ከአቶ መርሻም በድርጅት አባልነታቸውና እንደ አንድ ፖለቲካ አዋቂነታቸው የበለጠ እንጠብቃለን። ይህን ከተቀበልን ደግሞ ያትውልድ የሰራቸውን በጎና መጥፎ ተግባሮችን ነቅሰን መነጋገር ይኖርብናል። ይህ ሲሆን ነው አዲሱን ትውልድ መምከርና ማስተማር የምንችለው። በደፈናው ያትውልድ ስህተት አድርጓል ወይም አድርገናል ብሎ በማድበስበ ማለፍ ሃላፊነት የጎደለው ኢትዮጵያዊነት ነው። ከተጠያቂነት እንደመሸሽም ይቆጠራል። በሽታውን የደበቀ ፈውስ አያገኝምና።
ሐቅ መናገር እና ስህተት አድርገናል ወይም አድርጌአለሁ ማለት ውርደት ሳይሆን አዋቂነት እና አስተዋይነት ነው። በርሳቸው የፍልስፍና አስተሳሰብ እና ክህሎትም አንፃር ቁስ አካላዊ (dialectical) ነው። በድርጅታቸው ለተደረጉ በጎ ምግባሮች ምስጋናን ከአክብሮት ጋር መለገሰ ከኢትዮጵያ ሕዝብ እና ከወጣቱ ትውልድ የሚጠበቅ ሲሆን ለተደረጉ ስህተቶች ደግሞ ሃላፊነትን ወስዶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ ከአቶ መርሻ እና ድርጅታቸው ይጠበቃል።
ለዚህም ነው አቶ መርሻ የመሩትና እየመሩት ያለው ድርጅት ኢሃፓ ያከናወኑትን በጎ ጎኖችና የተፈጸሙ ጥፋቶችንና ቀውሶችን በነቂስ ዘርዝሮ ለዚህ ትውልድ ማስረዳት አስፈላጊ የሚሆነው። ያ-ትውልድ ያስመዘገባቸው ደግ ነገሮችና ያደረጋቸው የስትራተጅም ሆነ የፍልስፍና ስህተቶች ካሉ በማያሻማ ሁኔት ቢገለጹ ለትምህርትነት ይበጃል። አቶ መርሻ አስራ አምስት ገጽ ጽሁፍ ሲአዘጋጁ ይህንን በግልጽ ሳይመዘግቡ አልፈውታል። ምነልባት በቀጣይ ጽሑፋቸው እንደጲላጦስ ከደሙ ንፁሕ ነኝ ሳይሉ ያቀርቡት እንደሆን ወደፊት የምናየው ይሆናል። ይህን ካላደረጉ ግን ዳዋ መቸበቸብ ወይም የጓሮ እስክስታ (bit around the bush) እንጅ ትምህርት እና ተመክሮ እንደምስጠት አይሆንም።
የአየር ንብረት መዛባት (climate change) በሰው ዘር ላይ ያስከተለውን እና ሊአስከትል የሚችልውን ቀውስ በቁንጽል ለመዘርዘር ከመሞከር እና የዓለማችን ከባቢ አየር ባለሙያ (environmental scientist) መስሎ ለመታየት ከመጣር የሚአውቁትን የነጭ ሽብር ታሪክን ስህተቶችና ተመክሮዎች ቢጠቅሱ ወጣቱ ትውልድ ከሳቸውና ከድርጅታቸው ብዙ በተማረ ነበር። ጥርሳቸው እስኪወልቅ፤ የፀጉር ቀለማቸው እስኪለቅ ከተካኑበት የነጭ ሽብር ፖለቲካ ላይ ያለውን ተመክሮ ቁልጭ አድርገው ቢአስተምሩን ምንኛ ባከበርናቸው ነበር። በዚህ ረገድ የትግል አጋራቸው የነበረችው ሕይወት ተፈራ ማማ በሰማይ (Tour In The Sky) በተሰኘው መጽሃፏ በግልጽ እንዳስቀመጠችው መርሻም በግልጽ ቢነግሩን ትልቅ ከበሬታን ያገኙ ነበር። ክብር ለሕይወት ተፈራ ይድረስ።
በቅርቡ አቶ ዓቻምየለህ የተባሉ ፀሐፊ ‘እስኪ ዶሴው ይውጣ’ በሚል ርዕስ ተከታታይ ጽሑፎች የኢሃፓን ተመክሮና ስህተት ቁልጭ አድርገው በማስረጃ አስነብበውናል። ፀሐፊው የኢሃፓ ልሳን የሆነውን ዴሞክራሲያን እትሞች በማጣቀስ ባቀረቡት ጽሁፍ ዓይን ያፈጠጡ ሐቆችን እና ስህተቶችን አብራርተዋል። አቶ አቻምየለህ የዚህ ትውልድ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ከእኛ ትውልድ ምን ተመክሮ እንዳገኙ ተናግረዋል። እኔ እስከማውቀው የኒህን ሰው ጽሁፍ የሚአስተባብል ከኢሃፓዎች እና ድርጅታቸው አንድም ማስተባበያ አልተሰማም። በአቶ ዓቻምየለህ አመለካከት፤ አጻጻፍ እና አነጋገር ኢሃፓ የኤርትራን የነፃነት ጥያቄ በአቅዋም ደረጃ እንደ ደገፈ፤ የሶማሊያ ወረራን በተመለከት ኢሃፓ የሁለት አምባ ገነኖች ጦርነት ስለሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደርግን እንዳይደግፍ እንደቀሰቀሱ፤ ዓማራው ትምክህተኛ ስለሆነ ኢሃፓ ይህን ህብረተሰብ እንደሚዋጋው በልሳኑ ማወጁን ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል። በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር ጊዜም ኢሃፓ ከደርግ እኩል ተጠያቂ እንደሆነ አብራርቷል። የኤርትራን ነፃ መውጣት፤ የአፋር፤ ኦሮሞ እና ሌሎች ብሔሮች ከፈለጉ መገንጠል እንደሚችሉ በልሳናቻው ወስነዋል። ይህ ሁሉ ብሔር ተገንጥሎ ምን ዓይነት አገር ሊቀራቸው፤ ሥልጣን ቢይዙስ ምን ዓይነት አገር ሊአስተዳድሩ ይችሉ እንደነበር የሚአውቁት መርሻና ጟዶቹ ብቻ ናቸው። ይህ ነው ሐቁ እና ከዚያ ትውልድ የተገኘው ገሃድ ትምህርት እና ተመክሮ። አሁን ወያኔ አገር ገነጠለ አስገነጠለ እያለ ኢሃፓ በመርሻ በኩል የሚወቅሰው ለምን እንደሆነ ሊገባን አይችልም። ይህን ካላችሁ ደግሞ እስኪ ያትውልድ የያዛቸው አቋሞች ስህተት ነበሩ ብላችሁ መርሻዎች በአደባባይ አውጁ።
የኢትዮጵያን ሕዝብም ይቅርታ ጠይቁ። ይህን ስታደርጉ ነው ንስሐ ገባችሁ፤ ለዚህ ትውልድም ትምህርት እና ተምክሮ ሰጣችሁ የሚባለው። አይዞዎት በድፍረት ይናገሩ፤ ምንም የሚሆኑት ነገር አይኖርም። የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርባይነት እና የሃያሉ እግዚአብሔርን መሃሪነት ለአንዴም እንኳን ቢሆን እያሰቡ ይንገሩን፤ ያጫውቱን።
ሌላ ያ-ትውልድ በዚህ ትውልድ ወቅት የሰራውን አንድ ሱህተት ለናሙና እንጥቀስ። እርስዎ እንዳሉት በ1997 ዓ.ም. ፌድራላዊ ምርጫ ህወሐት ኢሐአዴግ በቅንጅት መሸነፉን አልቀበልም እንዳለ ጠቅሰዋል። ትክከል ነው። ግን ከመጀሚሪያው ቅንጅት እንዳያሸንፍ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ ቅስቀሳ እና ተቃውሞ ያደረገ እርስዎ እና ድርጅትዎ አልነበሩምን። ከብርሃኑ ነጋ ጋር በነበራችሁ ታሪካዊ አንባጓሮ ምክንያት በጅምላ አልተቃውማችሁትምን። በዚህ እና ከዚያ በፊት በነበራችሁ ቁርሾ ምክንያት አሁንስ ቢሆን አርበኞች ግንቦት ሰባትን ዓይንህ ላፈር የምትሉት በዚህ ቂምበቀል አይደለምን። መርሻ ህብረት፤ አንድነት እያሉ በመግለጫ የሚአላዝኑትን በተግባር መተርጎም ለምን አቃተዎት። ለርስዎ ከአንድነት ይልቅ የቂም በቀል ፖለቲካ፤ ከይቅርታ በበለጠ አካኪ ዘራፍነትን አይደለም እንዴ ለዚህ ትውልድ ያስተማራችሁት። ከብርሃኑ እና ከግንቦት ሰባት ጋር አንድነት ከመፍጠር ከሕውሃት ጋር መስራትን እንመርጣለን አላላችሁም። እናንተ ብርሃኑ እና አንዳርጋቸው አዲስ አበባ ገብተው ከወያኔ ጋር ስለሠሩ በየአደባባዩ ስታወግዙ፤ ስታጥላሉ፤ ቁምስቅላቸው ስታሳጧአቸው አልነበረም። ዛሬ በሕውሃት በኩል ምን ተቀየረና ነው አሁን አገር ቤት ገብታችሁ ከመንግሥት ጋር መሥራት የፈለጋችሁት። የተለወጠ ነገር ኖሮ ሳይሆን ብርሃኑን ለመቃወም ሲባል ብቻ የተደረገው የእርስዎ ስትራተጂካዊ ለውጥ ነው። ሐቁ ይሄ ብቻ ነው ሌላውን ይተወት።
ስለዚህ ለአቶ መርሻ እና ቡድናቸው የምንሰጠው አንድ ተምክሮ ቢኖር ወያኔ ከርስዎ እና ከቡድንዎ ጋር ከሚሰራ ከብርሃኑ እና አንዳርጋቸው ጋር እርቀ ሰላም ፈጥሮ አብሮ መስራትን እንደሚመርጥ ነው። ለምን ቢባል እናንተ ለሥልጣን የምትቋምጡ አደገኞች፤ አንዳርጋቸዎች ደግሞ ለሃገር እድገት እና ሰላም የሚሰሩ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉና።
እውነቱን እንነጋገር ከተባል ያትውልድ አነሳሱ ለኢትዮጵያ ትንሳኤ ብዙ አልሞና ሰንቆ የተነሳ ነበር። በዚህ ምክንያት የምሁሩን፤ የወታደሩን፤ የወጣቱን፤ የአርሶአደሩን ቀልብ ስቦ የነበረ ድርጅት ነው። ለዚህም ነው አብዛኛው ወጣት በጥለቀት በማያውቀው የማርክሲዝም ፍልስፍና አብዶ ሕይወቱን የገበረው። ወጣቱም ኢሃፓን የሚአሽከረክረው ኢትዮጵያዊነት እንጅ ጠባቦች ሕወሃቶችና የኤርትራ ሻቢያዎች መሆናቸውን አልተረዳም ነበር።
ሐቁ ይውጣ ከተባለ ኢሃፓን የመሩት እነመርሻ ሳይሆኑ ዘረኞች የሆኑ ሕውሃቶችና ተገንጣይ ሻቢያዎች ነበሩ። መርሻን የመሰሉ አጃቢዎች ግን አሽቃባጮች እንጅ ወሳኝ (core) መሪዎች አልነበሩም። ኤርትራዊያን እና ተጋሩ ሕዝባዊውን ዓላማ መጠቀሚያ እንዳደርጟችሁ አሁን ጉዱ ፍጥጥ ብሎ ወጧል። የተገኘውም ትምህርትና ተመክሮ ይሀው ስለሆነ አቶ መርሻ ሊቀበሉት ይገባል። ይህን እና ይህን የመሰለውን የስህተት ሃቅ ነው ለዚህ ወጣት ፤ ለዚህ ትውልድ ማስተማር ያለብን። ሾላ በድፍኑ ወጣቱትውልድ ከእኛ ስህተት ይማር ብሎ ማላዘን ፍች የለውም። ወጣቱን ሊአስተምረው የሚችል እና እኛ ያደረግነውን ስህተት እንዳይደግም መምከር የምንችለው ሐቁን አውጥተን መንገርና ማስተማር ስንችል ብቻ ነው። አራት ነጥብ።
ይህች አገር እና ሕዝቧ አሁን ለደረሱበት ውድቀት መንገድ የጠረገው ያትውልድ መሆኑ ይሰመርበት። አለባብሰው ቢአርሱ ባረም ይመለሱ ነውና ሾላ በድፍኑ አዲሱ ትውልድ ከዚያ ትውልድ ስህተት ይማር ብሎ አድበስብሶ ማለፍ ማስተማር ሳይሆን ወይ ማምታታት አለያም ሐቁን ላለመናገር የተደረገ አጉል ብልጣብልጥነት መሆኑን አቶ መርሻ ሊገነዘቡት ይገባል።
በመጨረሻም መርሻ ዮሴፍ ትህትና በተላበሰ መልኩ የመጨርሻ ኑዛዜአቸውን ለግሰውናል። አስራ አምስት ገጽ፤ ሰባት ሺህ ቃላት፤ ሰላሳ ሽህ ሆህያትን ተጠቅመው ዕራያቸውን ተናግረዋል። የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ወጣት እና ኢትዮጵያዊ ትውልድ ግን ምን ትምህርት እና ተመክሮ እንዳገኘበት አቻምየለህን የመሰሉ የዛሬው ዘመን ወጣቶች ፍርዱን ይስጡበት።
ከአብዮት ጀምሮ እስካሁን የተደረጉትን የፖለቲካ እንቶ ፈንቶዎች በሚገባ የሚአውቁ ለመሆኑ ጥርጥር ስሌለለን ከኑዛዜ በፊት ኢትዮጵያ፤ ዕውነት ፤ ተመክሮ እና ትምህርት ቢቀድም ፀሐፊውን ብዙ ባስከበራቸው ነበር። ለማንኛውም ሕይወት የማያቋርጥ ትምህርት ቤት ናትና አሁንም አልመሸም። ወደ ማይቀረው ዓለም ከመሄድዎ በፊት ሐቁን አስተምረው በማለፍ ነፍስዎን ለንስሐ ያብቋት። ኢትዮጵያን፤ ሕዝቧን እና አዲሱን የኢትዮጵያ ትውልድም ተመክሮዎን፤ ልምድዎን እና ዕውቀትዎን ስለእውነት ብለው በማካፋል አገርዎን ይታደጟት። ያምሆኖ ግን በጥቅሉም ቢሆን ተሳስተን ነበር ማለት በመቻልዎ ምስጋናየ ከአድንቆትጋር ይድረስዎት። ለውደፊቱም እውነቱን ለመናገር እንዲችሉ እግዚአብሐር ድፍረቱን እና ተመክሮ ይስጥዎት።
ቸር ይግጠመን።
አቢቹ ነጋ
ሰኔ 23 ቀን 2009 ዓ.ም.