አቻምየለህ ታምሩ ለዶክተር ጸጋየ አራርሳ መልስ ሰጠ

አቻምየለህ ታምሩ ለዶክተር ጸጋየ አራርሳ መልስ ሰጠ

የጸጋዬ አራርሳ ነገር

ወያኔ ባወጀው የአዲስ አበባ የጠብ አጀንዳ ዙሪያ ምንም ነገር ላለማለት ወስኛለሁ። ምንም ነገር ላለማለት የወሰንሁበት ምክንያትም ወያኔ ያዘጋጀልንን ጦርነት ላለመዋጋት ስል ነው። ሆኖም ግን አዲስ አበባን አስመልክቶ የአውስትራሊያው የኦሮሞ ብሔርተኛ ጸጋዬ አራርሳ በአዲስ ስታንታድር መጽሔት ላይ “COMMENTARY: THE INTEREST THAT IS NOT SO SPECIAL: ADDIS ABEBA, OROMIA, AND ETHIOPIA (http://addisstandard.com/the-interest-that-is-not-so-speci…/)” በሚል ርዕስ ባሳተመውና ትናንትና ዛሬ ብዙ ሰው እየተቀባበለ ሼር ሲያደርገው በዋለው አርቲክል ላይ ጸጋዬ ከኦሮሞ በስተቀር ያለውን የአዲስ አበባ ኗሪ መጤና እንግዳ ለማድረግ የሄደበት ርቀት ዝም ብዬ እንዳላልፍ አድርጎኛል።

ጸጋዬ አራርሳን ባወቅሁባቸው ያለፉት ሁለት አመታት ውስጥ በሚጽፈው አርቲክልም ሆነ በሚሰጠው ቃለ ምልልስ ውስጥ ከኦሮሞ ውጭ ያለውን የአዲስ አበባን ነዋሪ እንግዳ[guest] ወይንም መጤ ሳያደርግ፤ ኦሮሞን ደግሞ ብቸኛ የአዲስ አበባ ባለቤት፣ አስተናጋጅ [host] እና ታሪካዊ የምድሪቷ ራስ እንደሆነ ሳይናገር ንግግሩንና ጽሁፉን የቋጨበት ወቅትና ኩነት ትዝ አይለኝም። የጸጋዬንና የርዕዮታለም አጋሮቹን የመነቸከ የኢትዮጵያን አገረ መንግስት አመሰራረት ትርክት ላደመጠ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው መኖር የጀመረው ንጉስ ምኒልክ የሸዋ ንጉስ ከሆኑ በኋላ ቢመስለው አይፈረድበትም።

ከታች የታተሙት ገጾች ጸጋዬ አራርሳ አዲስ ስታንዳርድ ላይ ባቀረበው ጽሁፉ ውስጥ ኦሮሞ የአዲስ አበባ ታሪካዊ ባለቤትና ምድሩ ላይ የበቀለ [indigenous] መሆኑን ለማሳየት ካቀረበው ጸሐፊ ከሻለቃ ዊሊያም ሀሪስ መጽሐፍ የተወሰዱ ናቸው። ሆኖም ግን የሀሪስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝው ታሪክ ጸጋዬ በኩሸት የነገረን የኦሮሞ የአዲስ አበባ ታሪካዊ ባለቤትነትን የሚያሳይ ሳይሆን ተቃራኒውን ማለትም ኦሮሞ የአዲስ አበባ ታሪካዊ ባለቤት እንዳልሆነና እንዴውም የአዲስ አበባ መጤ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። የኔ ጽሁፍ አላማ ማንም ፊደል የቆጠረ ሁሉ የሀሪስን መጽሐፍ አንብቦ ሊያረጋግጠው የሚችለውን እውነታ [በመጽሐፉ የሰፈረውን ማለቴ ነው] ለዘረኝነት ጥማቱ ማርኪያ ሲል ጸጋዬ አራርሳ ጠምዝዞ ያቀረበውን ድፍረት የተሞላበት ውሸት ማጋለጥ ነው። ከዚህ ውጭ ጽሁፌ የጸጋዬ አይነት አላማ እንደሌለው አንባቢዎቼ እንዲያውቁልኝ እሻለሁ።

ጸጋዬ አራርሳ ባሳተመው የአዲስ ስታንዳርድ ጽሁፉ የአዲስ አበባን ኗሪዎች ታሪክ ሲያስቀምጥ «A cursory glance at writings by William Harris, Alexander Bulatovich, and even Evelyn Waugh, indicates that the State operated in Addis Abeba as an occupying force of settler colonialists bent on pushing out and displacing the indigenous Oromo peoples» ብሏል። ይህ የጸጋዬ ትርክት እውነትነው አለውን? እስቲ የሚቀጥሉትን አንቀጾች እንመልከት። በመጀመሪያ የጸጋዬን ምንጭ ማንነት እንግለጥ።

ጸጋዬ የጠቀሰው ሻለቃ ዊሊያም ሀሪስ በንጉስ ሳህለ ሥላሴ ዘመን ኢትዮጵያን የጎበኘና ንጉስ ሳህለ ሥላሴ ወደ ጉራጌ ምድር ሲሄዱ አብሯቸው የተጓዘ የእንግሊዝ መንግሥት ልኡካን ቡድን መሪ ነው። ዊሊያም ሀሪስ ከጉብኝቱ በኋላ አገሩ ተመልሶ ባዘጋጀው «የኢትዮጵያ ደጋ አገር» ወይንም በእንግሊዝኛው «The Highlands Of Ethiopia» መጽሐፉ ስለ ከንጉሱ ጋር ስለነበረው ጉዟቸው በስፋት ያወራል።

ሻለቃ ሀሪስ በጉዞ ማስታወሻው እንደነገረን ሳህለ ሥላሴ ወደ ጉራጌ ሲጓዙ በፍልውሀ በኩል ተሻግረው እንደሄዱ፤ ሲመለሱ ደግሞ በእንጦጦ ዞረው ወደ አንኮበር እንደገቡ፤ በየመንገዳቸው ኦሮሞዎችን እንዳገኙና ግብር ያስገቡላቸው እንደነበር ያትታል።

ጸጋዬ አራርሳ አዲስ አበባን ዋና ከተማ አድርጎ እንደገና የተመሰረተውን የኢትዮጵያ መንግስት «an occupying force of settler colonialists bent on pushing out and displacing the indigenous Oromo peoples» ሲል ሀሪስ ያልጻፈውን ቢጠቅስም፤ የጸጋዬ ዋና ምንጭ ዊሊያም ሀሪስ ግን «The Highlands Of Ethiopia» በሚል በጻፈው መጽሐፍ ገጽ 234 ላይ «Thus affairs continued until the sixteenth century, when the invasion of Mohammad Graan led to the total dismemberment of the Ethiopic empire ; and Shoa, among other of the richest provinces, was overrun and colonized by the Galla hordes. Libne Dengel, the emperor of Gondar, fell by the hand of the Moslem conqueror.» ሲል ጽፏል። ጸጋዬ አራርሳ ግን በአዲስ ስታንዳርድ የጻፈው ዊሊያም ሀሪስ ኦሮሞ ወራሪና ቅኝ ገዢ ነው ያለውን አበሻ ለሚላቸው ገልብጦ በመስጠት ነው። ከፍ ሲል ከቀረበው የሀሪስ ሀተታ የምስረዳው የሸዋና የተቀሩት ሀብታም የኢትዮጵያ ክፈለ ሀገሮች ወራሪና ቅኝ ገዢ ኦሮሞ እንደሆነ እንጂ ጸጋየ እንዳለው ከኦሮሞ ውጭ የሆነው አበሻ በተለይም አማራ አይደለም።

ምን ይሄ ብቻ! ደፋሩ ጸጋዬ ከኦሮሞ በስተቀር ያለውን የአዲስ አበባ ኗሪ «መጤ፣ ወራሪ፣ ሰፋሪና ቅኝ ገዢ» አድርጎ ለማሳየት የተጠቀመበት የዊሊያም ሀሪስ መጽሐፉ በገጽ 244 ላይ ስለ ኦሮሞ «But the glory had departed from the house of Ethiopia, her power had been prostrated before the mighty conqueror and his wild band ; and the Galla hordes, pouring flagrante hello into the richest provinces, from southern Central Africa, reerected heathen shrines during the reign of anarchy, and rose and flourished on her ruins.» የተባለውን እሱ በአዲስ ስታንዳድር ላይ ባወጣው ጽሁፍ ለኦሮሞ የተባለውን ገልብጦ የሌለ ተረክ ይነግረናል።

ባጭሩ ጸጋዬ አራርሳ ከኦሮሞ ውጭ ያለው የአዲስ አበባ ነዋሪ «an occupying force of settler colonialists bent on pushing out and displacing the indigenous Oromo peoples» ሲል ሀሪስን አጣቅሶ ያቀረበው ክስ መሰረት የሌለው የጸጋዬ የራሱ ፈጠራ ነው። እንዴውም በተቃራዊው ጸጋዬ ከኦሮሞ ውጭ የሆነውን የአዲስ አበባን ነዋሪ «an occupying force of settler colonialists bent on pushing out and displacing the indigenous Oromo peoples» ለማለት በማስረጃነት የተጠቀመበት የዊሊያም ሀሪስ መጽሐፉ ሸዋን ጨምሮ ለም የሆኑ የኢትዮጵያ ክፍለ አገሮችን ወራሪና ቅኝ ገዢ የሚለው ኦሮሞን ነው።

ከዊሊያም ሀሪስ በተጨማሪ በዘመኑ ሸዋን የጎበኙ ሌሎች የውጭ አገር ተጓዦችም ማስታወሻቸውን ትተው አልፈዋል። ለምሳሌ የኦሮሞ ብሔርተኛ ነን የሚሉ ግለሰቦች በብዛት የሚጠቅሱት ዮዋን ክራምፍ አንዱ ነው። JOURNALS OF THE Rev. Messrs. ISENBEEG AND KRAPF, MISSIONARIES OF THE CHURCH MISSIONARY SOCIETY, DETAILING THEIR PROCEEDINGS IN THE KINGDOM OF SHOA, AND JOURNEYS IN OTHER PARTS OF ABYSSINIA, IN THE YEARS 18-39, 1840, 1841, AND 1842 በሚል በቀረበ መጽሐፍ ላይ የሰፈረው የዮዋን ክራምፍ ማስታወሻ እንደሚያስረዳው ጸጋዬ አማራ እንደወረረው ሊነግረን ወደሚፈልገው ወደ አዲስ አበባ ወይንም ወደ ሸዋ ምድር ብቻ ሳይሆን የአቢሲኒያ ምድር ወደ ሆነው ወደ ባሌም ኦሮሞዎች የገቡት ግራኝ አሕመድ አቢሲኒያን ወርሮ ሕዝቦቿን ከገደለና ኗሪዎችን ካፈናቀለ በኋላ እ.ኤ.አ በ1559 ዓ.ም. እንደሆነ ይነግረናል።

ይህንን ከፍ ብሎ የቀረበውን ታሪክ ዮዋን ክራምፕ እንዲህ ሲል ያስቀምጠዋል፤ «Adjoining to and south-eastward of Efat is the district of Gan, and adjoining and eastward of it again is Bali, a small kingdom, through which the Gallas first rushed into Abyssinia in 1559, Bali is west south-west of Zeilah, and south-west of Mocawa. Fattigar, once a considerable province, lies to the southward and south-westward of Gan and Bali of the ancient Mahomedans.» ከዚህ የምንረዳው ጸጋዬ «an occupying force of settler colonialists bent on pushing out and displacing the indigenous people» ሲል ያቀረበው ተረክ [narrative] የሚገልጸውና ወራሪው ኦሮሞ እንጂ ጸጋዬ እንዳለው ከኦሮሞ ውጭ የሆነው የአዲስ አበባ ኗሪ አይደለም።

ከዚህ በተጨማሪ ዮዋን ክራፕፍ ንጉሱ በሌላ ጊዜ ወደ ጉራጌና አካባቢው ሲጓዝ አብሯቸው ተጉዞ ኖሮ በጉዟቸው የሚያገኟቸው ኦሮሞዎች ንጉሱ ፊት እየቀረቡ ግብር ያስገቡ እንደነበር፣ ንጉሱም በኦሮምኛ እንደሚያነጋግሯቸው፤ ሹመትና ሽልማት እየሰጡ በአካባቢው በሰፈሩ ኦሮሞዎች መሀል አልፈው ጉራጌ እንደደረሱ ያወሳል። ከጉራጌ ጉዞ በኋላ በእንጦጦ ዞረው ወደ አንኮበር እንደተመሰሉ፤ እንጦጦ ላይ በግራኝ ወረራ የፈረሰ የቤተ ክርስቲያን ቅሪት እንዳለና በዚሁ የግራኝ ወረራ ወቅት የፈረሰችና የበርካታ አቢሲኒያ ነገስታት መናገሻ ሆና ታገለግል የነበረች ከተማ እንጦጦ ተራራ ላይ እንደነበረችና ከመፍረሷ በፊት ዓፄ ልብነ ድንግል ለመጨረሻ ጊዜ በዋና ከተማነት ይገለገልባት እንደነበር ይተርካል።

የጸጋዬን ተረክ [narrative] መሰረት አልባነት ለማስረገጥ እሱ ራሱ በጽሁፉ ካቀረባቸው የውጭ አገር ጎብኝዎች በተጨማሪ የግራኝ አሕመድ ወረራን የከበተውን የአረብ ፋቂህን መጽሐፍ Futuh Al-Habasha: The Conquest of Abyssinia [16 century]፣ የበርሙዴዝን «The Portuguese expedition to Abyssinia in 1541-1543»፣ ወዘተ ማቅረብም ይቻላል።

እንግዲህ! ይህ ሁሉ ማስረጃ ከፊታችን ተቀምጦ ነው የሕግ ባለሙያው ጸጋዬ አራርሳ የልብነ ድንግልን ልጆች ያያታቸው ዋና ከተማ ለነበረችው ለእንጦጦና አዲስ አበባ ዙሪያ መጤና የዋና ከተማችን እንግዳ አድርጎ ሊያቀርባቸው የፈልገው። ጸጋዬ በአዲስ ስታንዳርድ መጽሔት ያቀረበው ድፍረት የተሞላበት ጽሁፍ ዊሊያም ሀሪስ በሳህለ ሥላሴ ዘመን በፍል ውሀ በኩል አድርገው ወደ ጉራጌ ሲሄዱ ኦሮሞዎችን አገኘን ያለውን ትርክት አዛብቶ በማቅረብ ከሸዋ አልፈው ወደ አያቶቻቸው ርስት ወደ ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ የትውልድ ምድር ወደ ፈጠጋር[ሐረርጌ አዋሳኝ] ሳህለ ሥላሴ ያደረጉትን ጉዞ ጠምዝዞ ኦሮሞዎችን ብቸኛ የአዲስ አበባ ባለቤቶች፤ በግራኝ ወረራ ምክንያት የሞቱና ከርስታቸው የተፈናቀሉትን ደግሞ ለአዲስ አበባ እንግዳና መጤ አድርጎ አቃርኖ ማቅረቡ የምሁር ዋነኛ ባህሪ ማለትም integrityን የሌለው መሆኑን ከማሳየቱ ባለፈ ታሪካዊ እውነታውን አይለውጠውም።

ከግራኝ ወረራ በኋላ በየዘመኑ የነገሱት የኢትዮጵያ ነገስታት ሁሉ በየዘመናቸው ፈርሳ የነበረችውን የአያቶቻቸውን አገር አንድ ለማድረግ ሲጥሩ የነበሩት በግራኝ አህመድ ወረራ የተበታተኑትን የኢትዮጵያ ክፍለ አገሮች እንደበፊቱ አንድ ለማድረግ እንጂ ጸጋዬ ሊነግረን እንደሚፈልገው ቅኝ ግዛት ፍለጋና ለወረራ አልነበረ። የእንግሊዙ ዊሊያም ሀሪስና የፈረንሳዩ ቴዎፍሎስ ሌፌቭር የሚነግሩን ይህንን ሀቅ ነው። ኢትዮጵያ [በካርታም ላይ ቢሆን] እስካለች ድረስ አዲስ አበባ የመላው አትዮጵያዊያን፣ የአፍሪካዊያንና የዓለም ከተማ ነች፤ ከኦሮሞ ጀምሮ የመላው አትዮጵያዊ ከተማ ሆና ትኖራለች።

LEAVE A REPLY