ሪፖርተር:- በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ኦሮሚፋ እንደ አንድ ትምህርት እንዲሰጥ ጠይቀዋል
የኦሕዴድ የፓርላማ አባላት ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ አዋጅ አስገዳጅ እንዲሆን ጠየቁ፡፡
የረቂቅ አዋጅ የተለየዩ አንቀጾች የኦሮሚያን ጥቅም የሚያስከብሩ ሳይሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የሚመስሉ አንቀጾችን የያዘ በመሆኑ አስገዳጅ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡
‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ማንነት የሚያንፀባርቅ አሻራ በከተማው ውስጥ በቋሚነት እንዲኖር ከክልሉ ሕዝብ ጋር በተያያዙ ታሪካዊ ክስተቶች ስም መታሰቢያዎች እንዲኖሩ አመቺ የሆኑ እንደ አደባባዮች፣ ጎዳናዎች፣ ሠፈሮችና የመሳሰሉት ቦታዎች እንደ አስፈላጊነቱ በቀድሞ የኦሮሞ ስማቸው እንዲጠሩ ይደረጋል፤›› የሚለውን የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 6(2) አስገዳጅ መሆን አለበት ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በረቂቁ የተቀመጡትን የኦሮሞ ልዩ ጥቅሞች ለኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ለማቅረብ እንዲቻል አፋን ኦሮሞ በከተማ አስተዳደሩ የሥራ ቋንቋ ሆኗል መባሉን የኦሕዴድ የፓርላማ አባላት ያደነቁ ቢሆንም፣ የሥራ ቋንቋ እስከሆነ ድረስ እንደ አማርኛ በሁሉም የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል በከተማዋ በመንግሥት የሚሠራጩ የመገናኛ ብዙኃን በአፋን ኦሮሞ ጭምር የሚጠቀሙበት ሁኔታ ይኖራል የሚለውን የረቂቁን አንቀጽ 6(5) አስገዳጅ አይደለም ብለዋል፡፡
ከአካባቢ ብክለት የሚጠብቅ መብትን አስመልክቶ በተቀመጠው የረቂቁ አንቀጽ ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ካሳ እንዲያገኙ ቢደነገግም፣ ጉዳቱን ባደረሰው ላይ ቅጣት እንዲጥል ጠይቀዋል፡፡
ረቂቁ በሰጠው ትርጓሜ የአዲስ አበባ ከተማ ወሰን ማለት የከተማው አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚያደርገው ስምምነት ተወስኖ ምልክት የተደረገበት ወሰን እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ማለት ፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የምክር ቤቱ አባል አድሃኖ ኃይሌ (ዶ/ር) ይህ ዞን የት ድረስ እንደሆነ በአዋጁ እንዲካተት ጠይቀዋል፡፡ ፓርላማው የዘንድሮው የሥራ ዘመኑን በዚህ ሳምንት የሚያጠናቅቅ በመሆኑ፣ ረቂቁ በጥድፊያ እንዳይፀድቅ ሥጋት የገባቸው የኦሕዴድ አባላት ጥያቄ ያነሱ ቢሆንም፣ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ በዚህ ዓመት እንደማይፀድቅ አረጋግጠዋል፡፡