38 የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቅ ደብዳቤ...

38 የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለህብረቱ አስገቡ

ደብዳቤው ለአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ለሆኑት ለወ/ሮ ፌደሪካ ሞጋህሪኒ ገቢ ተደርጓል።
/Ethiopia Nege News/:- በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ድምፃቸውን በማሰማት የሚታወቁት አና ጎሜዥን ጨምሮ 38 የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት ለህብረቱ በጋራ ያስገቡት ደብዳቤ “የኢትዮጵያ መንግስት” በህዝብ ላይ ያደረሰውን የመብት ረገጣ የሚዘረዝርና አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ህብረቱን የሚጠይቅ ነው።

እ.ኤ.አ 2016 በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች በተደረጉት ህዝባዊ ተቃውሞዎች ወቅት የመንግስት የፀጥታ ኋይሎች በሰላማዊ ሰልፎች ላይ ግድያ እስራትና የወሲብ ጥቃት ስለማድረሳቸው በደብዳቤው ተዘርዝሯል። በፖለቲከኞችና ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይም ያለ ምንም ህጋዊ መሰረት እስራት እንደተፈጸመና መቀጠሉንም የሚጠቅስ ነው። ለአብነትም ከሶስት አመት በፊት ከየመን ታፍነው ተወስደው በኢትዮጵያ እስር ቤት እየማቀቁ ያሉትን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ዋና ፀሀፊ የነበሩትን አቶ አዳርጋቸው ፅጌን ደብዳቤው ጠቅሷል።

የፓርላማ አባላቱ ባለፈው ዓመት በሀገሪቱ የተከሰተውን ህዛባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች የተወሰዱ እርምጃዎች በገልተኛ አካላት እንዲጣራና ጥፋተኛ የሆነው አካል ተጠያቂ እንዲደረግ ህብረቱ ድጋፍና ግፊት እንዲያደርግ በጋራ ጠይቀዋል።

ይህን ደብዳቤ(ዘገባ) ይዞት የወጣው ያልተወከሉ ሀገራት ህዝቦች ተቋም(UNREPRESENTED NATIONS AND PEOPLES ORGANIZATION) የተባለ አለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት 38ቱን የፓርላማ አባላት የወሰዱትን እርምጃ አድንቆ፤ እንዲህ ያለው እርምጃ በኦሮሚያ፣ ኦጋዴንና አማራ ክልሎች በተቃዋሚዎችና የሰብአዊ መብት ጠባቂዎች ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ለመከታተል ቁርጠኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብሏል።

የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ እርዳታ የሚያደርግ የአውሮፓ ሀገራት ማህበር ሲሆን አሁን አሁን የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎቹ ላይ በሚያደርሰው የሰብዓዊ መበት ጥሰት ምክንያት ህብረቱ በተደጋጋሚ በግለጫዎችንና የመፍትሔ ሀሳቦችን ማውጣቱ ይታወቃል።

LEAVE A REPLY