/ETHIOPIA Nege News/:- የአማራ ክልል መንግስት ለኢትዮጵያ መብራት ሀይል ባለስልጣን ባቀረበው ሪፖርት ላይ እንደገለፀው ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ በክልሉ አንድም የሐይል ማመንጫም ሆነ የሐይል ማከፋፈያ ማሻሻያ(Electric substation) ስራ አለመደረጉን ገልጿል።
በክልሉ 25 የሚሆኑ የሐይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች(Substation) ያሉ ቢሆንም አብዛኛዎቹ በደርግ ጊዜ የተሰሩ በመሆናቸው በከፍተኛ ደረጃ ያረጁ ናቸው ተብሏል። የሐይል መጠኑም 66 ኪሎ ቮልት ሲሆን አነስተኛ የሐይል መጠንና ባረጁ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ዘመኑ የሚጠይቀውን የሐይል አቅርቦት ህብረተሰቡን ማስተናገድ እንዳልተቻለ የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን የክልሉን መንግስት ር/መስተዳድር ልዩ አማካሪ የሆኑትን አቶ ለማ ጥሩነህን ጠቅሶ ዘግቧል።
በክልሉ በሐይል አቅርቦት ምክንያት ፋብሪካ መገንባት አለመቻሉንና የተገነቡትም ቢሆን ስራ መስራት አለመቻላቸውን ገልፀው ባለሀብቶችን ወደ ክልሉ መጥተው መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ለማድረግም የሐይል አቅርቦት አለመኖር እንቅፋት እንደሆነበት የክልሉ መንግስት አስረድቷል።
በአማራ ክልል አዳዲሶቹን ጨምሮ አስር ዩንቨርሲቲዎች ያሉ ሲሆን በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
አቤቱታውን የሰሙት የኢትዮጵያ መብራት ሐይል ሀላፊ የሆኑት ኢንጂንየር አዜብ አስናቀ የሰጡት አስተያየት “የረካ ደበኛን መያዝ ማለት ለአንድ የስራ ሀላፊ ትልቅ ስኬት ነው።እኛ ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ አይደለንም።ችግሩን ለመፍታት ሁሉም የመስሪያ ቤቱ አባላት የተቻለውን ያህል እየሰራ ነው።” ብለዋል።
የአማራ ክልል ንግድ ቢሮ በበኩሉ የኢትዮጵያ መብራት ሐይል የክልሉን ችግር አፅንዖት ሰጥቶ እንዲፈታ ጠይቋል። ይህ ካልሆነ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲውቅልን የሚያደርግ ስራ መስራት አለብን በማለት በምሬት ገልፀዋል።
በአማራ ክልል እ.ኤ.አ 1953 የተገነበው እድሜ ጠገቡ {ጢስ አባይ} የሐይል ማመንጫ ጣቢያ 12MW ሲያመነጭ፤ እ.ኤ.አ በ2010 ግንባታው የተጠናቀቀው ጣና በለስ(Beles Power Station) 460MW ሐይል የሚያመነጭ ቢሆንም ክልሉ ተጠቃሚ ሳይሆን አብላጫው የኤሌክትሪክ ሐይል ለትግራይ ክልል የሚሔድ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
በአሁኑ ሰዓት በመላ ሀገሪቱ 3715MW የሐይል አቅርቦት ያለ ሲሆን የአባይ ግድብን{ህዳሴ ግድብ} ጨምሮ 8950MW በመገንባት ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። የተጀመሩት ሁሉም የሐይል ማመንጫ ጣቢያዎች ቢጠናቀቁ፤ በድምሩ 12665MW ይሆናል።ይህ ደግሞ በኤክትሪክ ሐይል ሀብት ከአፍሪካ አንደኛ በመሆን ከጥቂት አመታት በሗላ ለአውሮፓ ሀገራት ሳይቀር የኤሌክትሪክ ሐይል በመሸጥ ገቢ አገኛለሁ ለሚለው የኢህአዴግ መንግስት የግብፅን የኤሌክትሪክ ሐይል መጠን ግማሽ እንኳን እንደማይሆን መረጃዎች ያሳያሉ።