/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/:- ነሐሴ 28/2008 ዓ.ም በቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ ለጠፋው የሰው ህይወትና ለደረሰው የንብረት ውድመት ተጠያቂዎች ናችሁ በሚል የፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የመሰረተባቸው ተከሳሾች 178 ደረሰ።
ዛሬ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በኤፍሬም ደቢሳ የተከፈተው መዝገብ እንደሚያመለክተው የቂሊንጦን እስር ቤት በማቃጠል ተጠርጥራችሗል ተብለው በሽብር ከተከሰሱት 159 ሰዎች በተጨማሪ ዛሬ ደግሞ 19 ሰዎች ተመስርቶባቸዋል።
በእነ ያሬድ ሁሴን መዝገብ 121 ተከሳሾች፤
በእነ ማስረሻ ሰጤ መዝገብ 38 ተከሳሾች፤
እንዲሁም ዛሬ በእነ ኤፍሬም ደቢሳ 19 ተከሳሾች በድምሩ 178 ሰዎች የጸረ-ሽብር ህጉን 3(1)፣ 3(2) እና 3 (4) ስር የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት በመተላለፍ በሚል የ”ሽብርተኝነት ክስ” ተመስርቶባቸዋል።
በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በርካታ ጋዜጠኞች፣ፖለቲከኞችና የሰብዓዊ መብት ተማጋቾች በሙያቸውንና በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የታሰሩ ንጹሀን ዜጎች የሚበዙበት ሲሆን ነሐሴ /2008 ዓ.ም በተነሳውን ቃጠሎ ተከትሎ በእሳት በመቃጠል እንዲሁም “ሊያመልጡ ሞክረዋል” በሚል በመንግስት ታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት ተደብድበው 67 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታው የሚታወስ ነው።
በሀሰት ክስ ተመስርቶባቸው ለአመታት ፍ/ቤት ሲመላለሱ ከቆዩ በሗላ ነጻ የተባሉ ንጹሀን ዜጎችም በዚሁ ክስ ምክንያት ከእስር ሊለቀቁ አልቻሉም። 66 አመት አዛውንት የሆኑት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩና በ1997 የፓርላ አባል እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ም/ቤት አባል የሆነው አቶ አግባው ሰጠኝን መጥቀስ ይቻላል።