አቶ ማሙሸት አማረ የሽብርተኝነት ክስ ተመሰረተባቸው

አቶ ማሙሸት አማረ የሽብርተኝነት ክስ ተመሰረተባቸው

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦  የቀድሞው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ማሙሸት አማረ ዛሬ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የሽብር ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በአቶ ማሙሸት የመሰረተባቸው ክስም “የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ቁጥር 652/ 2001 አንቀፅ 4 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ፤በማሴር፣ መዘጋጀትና ማቀድ” በማለት የሽብርተኝነት ክስ መስርቶባቸዋል።

አቶ ማሙሸት አማረ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ተነስቶ የነበረውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ወደ ሁሉም የሀገሪቱ ክፍል እንዲስፋፋ አባላትን በመመልመል፣ ሀገር ውስጥና ውጭ ሀገር ከሚገኙ ግለሰቦች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በጎጃምና ጎንደር የነበረውን እንቅስቃሴ በማቀናጀትና በመምራት ተንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለግንቦት ሰባት አባላትን መልምሎ ወደ ኤርትራ በመላክ፣ መንግስትን በትጥቅ ትግል ለመጣል በሰሜን ሸዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በማመቻቸት፣ አባላትን በማሰልጠንና በማስታጠቅ ተንቀሳቅሰዋል የሚል ዝርዝር ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

አቶ ማሙሸት አማረ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ በመሰረቱት የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት(መአህድ) ፓርቲ ገና በ16 አመታቸው አባል በመሆን ለሀገራቸው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመስረት ከፍተኛ መስዕዋትነት የከፈሉ ሰው ናቸው። አቶ ማሙሸት አይ ኤስ የተባለ የሽብር ቡድን 30 ኢትዮጵያዊያንን በሜዲትራሊያን ባህር መሰዋቱን ተክትሎ “ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም መንግስት ድርጊቱን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ ሰልፈኛውን ለተቃዉሞ አነሳስተሀል በማለት የተመሰረተባቸውን ክስ በነጻ ቢሰናበቱም ከመጋቢት 2009 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ።አቶ ማሙሸት የክስ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ለነሐሴ 1/2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

አቶ ማሙሸት አማረ መአህድ/መኢአድ ፓርቲን ከአባልነት ጀምሮ በስራ አስፈጻሚነት፣በምክር ቤት አባልነትና በፕሬዚደንት አገልግለዋል። ያሁኑን ሳይጨምርም ህወሓት/ኢህአዴግ በድምሩ 14 ዓመታት በግፍ መታሰራቸውን ከእራሳቸው አንደበት አረጋግጠናል።

LEAVE A REPLY