ለዝምታ የቸገረ ነገር /ሰአሊ በቀለ መኮንን/

ለዝምታ የቸገረ ነገር /ሰአሊ በቀለ መኮንን/

በዚህ ሰሞን አቤቱታ ከበዛባቸው ቦታዎች እንደ ግብር መክፈያ ደጃፎች በእንባ የረጠበ ያለ አይመስለኝም። በግብር መወዛገብ ከተጀመረ ከረመ። እንደብዙዎች እኔም በቅርብ ርቀት ስኖረውም ስታዘበውም ሰነበትኩ። ግን እያደር የእንባው ብዛት ለዝምታ የቸገረ ነገር ሆነና ያጋጠመኝንም ሆነ ቢሆን የሚሻለውን ለማለት ተገደድኩ።

ካገራችንና ከዓለም ታሪክ ሁሉ የምናውቀው፤ ግብር በአንድ አገር መንግስት የመኖሩ ወይም ቢያንስ ገዢና ተገዢው ተለይቶ በሆነ ደረጃ ስርዓት የመኖሩ መተማመኛ ዘዴ ሆኖ ማገልገሉን ነው። ምንም እንኩዋ ግብር መገበር በኢትዮጵያ የመሳፍንትም ሆነ የነገስታት ዘመን የራሱ መልክ የነበረው ስርዓት ይሁን እንጂ ከናካቴው ዛሬ አዲስ የመጣ እንግዳ ነገር ግን አይደለም። ምናልባትም በዘመናዊ መልክ ግብርን ለአገር ልማት በጊዜው የመክፈልም ሆነ ባግባቡ ሰብስቦ ባግባቡ ተግባር ላይ የማዋል ስርዓት ኖሮ አያውቅ ይሆናል። ከፋይ መክፈል የሚገባውን ያህል መክፈል በሚገባው ወቅት ሲከፍል አይታወቅም። ሰብሳቢም በወቅቱ የሚሰበሰብበት አቅምና ስርዓት ዘርግቶ የሰበሰበውንም ሳያባክንና ሳይሰርቅ በእምነትና በብቃት ልማት ላይ ሲያውል አይስተዋልም። በዚህ የረዥም ዘመን አለመተማመን ላይ የተመሰረተ የተዳዳሪና ያስተዳዳሪ ግንኙነት የተነሳ ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ስታጣ ኖራለች። አብዛኛው ያለመልማት ችግር በሙሉ በዚህ ስርዐት ላይ የተንጠለጠለ ነው። ያለመልማት በቁሳቁስና በመሰረተ ልማት ብቻ ሳይሆን በመላ አስተዳደራዊ ግንኙነትና አስተሳሰብ ጭምር ነው። የዚህ ጥፋትም ዋነኛ ችግር አጠቃላይ ያስተዳደር ባህል ጉዳይ ይሁን እንጂ በመሰረቱ የባህሉ አብቃይና አሳዳጊዎች ራሳቸው ከፋይና ሰብሳቢዎቹ መሆናቸው ግልፅ ነው።

ከዚህ ሁዋላ ቀርነት ለመውጣት ለቆረጠ ደግሞ፤ ዞሮ ዞሮ ችግሩን ከሆነ ቦታ በሆነ ዘዴ ማስተካከል መጀመር የግድ ይሆናል። እንደምናውቀው የኛም የግብር አከፋፈል ስርዓት በአዲስ መልክ ታውጆ ስራው ሲጀምር እንደብዙ ሌሎች እርምጃዎች ጨከን መረር ብሎ እንደተጀመረ እናስታውሳለን። ፈረንጆቹ አግሬሲቭ እንደሚሉት ዓይነት። ብዙ ጊዜ የዚህ ጨከን መረር የማድረግ ሰበብ ሲነገር እንደምንሰማው “ካለንበት ማጥ ለመውጣት የዛሬዎቹ ሰዎች መስዋዕት መሆን አለብን። ድህነታችን ጊዜ የሚሰጥ አይደለም “ ወዘተ የሚል ነው። ወዲህም ደግሞ“ ጨከን ብሎ መጀመሩ እያደር ሰለሚለመድ እድገታችንን ያፋጥነዋል” የሚልም አለበት። አባባሉ በቁሙ ችግር የለበትም ማለት እንችላለን። ወደ መሬት ሲወርድ ግን በመጠራጠር መንፈስ ተወጥሮ ገና ከጥልቅ አለመተማመን ባልወጣ ግንኙነት መካከል አኩል ተሰውተን አኩል መጠቀሙን ባንጠላም ማን ብቻውን መስዋዕት ሆኖ ነው ለማን ምቹ ስርዓት የሚፈጥረው የሚል ተጨማሪ ጥያቄን በጉምጉምታ ሲፈጥር ተሰምቱዋል። የዚህ ምክንያቱ ነባሩ ጥርጣሬ ብቻ አይመስለኝም። መስዋዕትነቱን ወዶም ተገዶም ከተቀላቀለው ጎን ለጎን ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ከመስዋዕትነቱ የሚጠቀም እንጂ ከመዋጮው ነፃ የሆነ ወገን ባደባባይ ተሰልፎ ስለሚታይ ነው።

እውነት ለመናገር ምንም ነገር በማናቸውም ደረጃ ሲጀመር አንከን ስለማያጣው ፈጥኖ ትችት ለመሰንዘር አስቸጋሪ ይሆናል። በርግጥ እያደር እርምጃውን እያዩ ወጪውን ከቀሪው እያመዛዘኑ መፍረድን ይጠይቃል። ብዙ አገሮች ብዙ ዓይነት ስርዓቶችን ሲተክሉ የየራሳቸውን መስዋዕትነት ከፍለውበታል። ነገር ግን የኪሳራቸው መጠን የተለያየ ነው። ትልቁ የአንድ ስርዓት ስኬትም በተቻለ መጠን ባነሰ ኪሳራ ተፈላጊውን ውጤት በማምጣቱ የሚመዘን ይመስለኛል።

በመሰረቱ ቀድሞ የነበረው በከፋይና በሰብሳቢ መካከል ያለው አለመተማመን ዛሬ ከዘመናት በሁዋላ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። በምትኩ መተማመንን ለመፍጠር ዓይን አይቶ ልብ የሚፈርደው ስንት ስራ ተሰርቱዋል? ስንትስ መተማመንን የሚሸረሽር አካሄድ ተተክሉአል? ብሎ መጠየቅ ግድ ይሆናል። እርግጥ ነው ብዙ ዘመናት ያልነበሩ አያሌ የልማት ስራዎች ባጭር ጊዜ ተከናውነው ታይተዋል። የዚያኑ ያህል ቀድሞ ባልነበሩ መጠን አያሌ ጨካኝና ደፋር ሌቦች ተፈልፍለዋል። በዚህ ወቅት ያገራችን ሰው ልማቱም ሌቦቹም በእኩል ቁጥር ከደጁ የቆሙለትና የቆሙበት ግብር ከፋይ መሆኑን ስንት የበላይ አስተዳዳሪ ያውቅ ይሆን?። ከላይ እንደተጠቀሰው የተበላሸ የግብር ታሪክ ያለው አገር በቁርጠኝነት ለመሻሻል ምንም ይሁን ምን ከሆነ ቦታ እርምጃውን መጀመር አለበት ብለናል። በዚሁ ስሌት እኛም ከሆነ ስፍራ ጀምረን ጥቂት ዓመታት መጉዋዝ ችለናል። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ካመታት ጉዞ በሁዋላ ካለፈው ሁሉ ተምሮ ከንግዲህ ደግሞ በዘለቄታው ለሰብሳቢውም ለከፋዩም በሚበጅና በሚመች የተሻለ መንገድ ተጠናክሮ ለመቀጠል ቆም ብሎ ማስተዋልና መማከር የአባት ነበር።

ነገር ግን ሲጀመር ከነበረው ከረር መረር ያለ እርምጃ በሁዋላ አሁን የሆነውና እየሆነ ያለው ግን ወደ ተሻለ ጥቅምና ምቾት የሚያመራ ሳይሆን ይልቁንም የሀገሪቱንም ጥቅም የከፋዩንም ክብር የሚገፍ ውጥረት የነገሰበትና መልሶ ወደ ቀድሞው አለመተማመን የሚከትት መሆኑ አሳዛኝ ያደርገዋል። ሁሌም ሁሉን ነገር ባለጉዳዩን አግልሎ ከላይ በሚወርድ ትዕዛዝ ብቻ ሁሉንም ማዋከብ የዕለትን እንጂ የዘላለምን ችግር አይፈታም። በተለይ በዘለቄታ የሚያገለግል ስርዓት በመትከል ሂደት።

በመሰረቱ ይሄ የምናውቀው ቤተሰባችን ዘመዳችን ጎረቤታችን የሆነ ከፋዩ ህዝብ እንኩዋንስ በሚታመን ማስረጃና በትዕግስት አስተምረውት ቀርቶ በማይረባ የሽንገላ ሰላምታ ሲደልሉትም ምስጢሩን ዘርግፎ የሚሰጥ ስጉ ህዝብ ነው። ምናልባት የሚጠብቀው ቅድመ ሁኔታ ቢኖር ሁሌም ክብሩ እንዳይዋረድበት ብቻ ይሆናል። ይህንን የግብር ስርዓት ለማሻሻል በተሞከረበት የስራ መነሳሳት ዘመን ሁሉ ይህ ቀላል ብልሀት በግብር ሰብሳቢው በኩል ሲሞከር አይቼ አላውቅም። የግብራችን አሰባሰብ ስርዓት የልቅሶ ሜዳ የሆነበት አንዱና ትልቁ ምክንያት ይሄ ነው ብዬ እከራከራለሁ። ይህንን ደፍሬ የምልበትን ምክንያት ባጭሩ ላስረዳ፡።

እስከ 2007 ዓ/ም ድረስ ከመምህርነቴ በተጉዋዳኝ በሙያዬ ስራ መስራት ፈለግሁና ማንም ሳይጠይቀኝ የንግድ ፈቃድ አወጣሁ። እግረ መንገዴን ላገሬ ጥቂት ገንዘብ እንኩዋ አዋጣለሁ በሚል። ከዋናው ስራዬ ይልቅ የግብር መክፈሉን ስርዓት ለመፈፀም እንደ ቁም እስረኛ በየሶስት ወሩ ያለውን ስቃይ ንቀት መንጉዋጠጥና እንግልት መቁዋቁዋም ባለመቻሌ ፈቃዱን ለመመለስ ተገደድኩ።

ያየሁት የቁም እስረኛ አበሳ በግብር አከፋፈል የመጀመሪያ ዓመታት በግብር ከፋይ ብቻ ሳይሆን በግብር ሰብሳቢም ላይ ሊፈጠር የሚችል በሁለቱም ወገን የጀማሪዎች ችግር ነው ተብሎ ይታለፍ እንበል። ሆኖም ከዓመታት ልምድ በሁዋላ በቀጣዩ ጊዜ እየተሻሻለ ስርዓቱ ለሁሉም ምቹ እየሆነ መሄድ ሲገባው፤ ጭርሱን ግብር ከፋዮች ሁሉ ሌቦችና አጭበርባሪዎች፤ ግብር ሰብሳቢዎች ግን በሙሉ ተቆጣጣሪዎችና ያገሩ ተቆርቁዋሪዎች ያደረገ ስርዓት ሲፈጠር ባይኔ በብረቱ ተመለከትኩ።

በተለይ የንግድ ፈቃዴን ለመመለስ በግብር አስፈፃሚዎች ፊት በቆምኩባቸው ቀናት ሁሉ ሰለ ግብር መስሪያ ቤት ያረጋገጥኩት ነገር ቢኖር፤ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያገራችን ሰው እንደውሻ ተስተናግዶ ሰብዓዊ ክብሩ የሚዋረድበት ስፍራ መሆኑን ነው። ከተወሰኑ ዓመታት ሙከራ፡ በሁዋላ ተንገዳግዶ ተመልሶ ደህና ቦታ ይይዛል ብዬ ተስፋ ያደረግሁበት መስሪያ ቤትና፡ ስርዓት የዚህ ዓይነት የዜጎች ማዋረጃ ጣቢያ ይሆናል ብዬ አስቤም አልሜም አላውቅም ነበር። በራሴ ላይ በመድረሱ ግን የበሽታውን ሰንኮፍ ለማስተዋል ችያለሁ።

እንግዲህ ግብር የሚፈለገው ለልማት ነው። ልማት የሚውለው ለሰው ልጅ ጥቅም ነው ። የሰውን ልጅ በማዋረድ የሚሰበሰብ ገንዘብ የውርደቱን ማስታወሻ እንጂ የምቾቱን ህንፃ ይገነባል ብዬ ለማሰብ እቸገራለሁ። ስለዚህ ማንነቴ ግድ ሳይሰጣቸው ላገሬ መዋጮ ላቀብል የቀረብኩትን ሰው በጠራራ ሰልፍ እያንቃቁ ባልታረመ አንደበት ለሚያዋርዱኝ ሰዎች ገንዘብ ልከፍል ቀርቶ ከፊታቸው ላልቆም ወስኜ በህግ አግባብ እስከወዲያኛው ተለያየን። ያንን ቀን ሳስብ ያለማጋነን በካንሰር ተይዤ የዳንኩበት ቀን ያህል ይሰማኛል። ልባርጉ በጁ ያለች ገንዘብ ንግዱንም ለመቀጠል ከንግዱም ለመለየት እንዳታስችለው በሁለቱ መሀል ቅርቃር እንዲገባ፡የተደረገ ብዙሀን ታችኛው ነጋዴ ምን ቢያደርግ ከዚህ ይገላገል ይሆን ? ይህ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚገባው እዚያው ዘግናኝ ደጃፍ ላይ ተዋርዶ ለቀመሰው ብቻ ነው።

ዛሬ እየሆነ ካለው ስንነሳ፤ አስቀድሞ ግብር በጭፍን መገመትን ያመጣው ሰበብ፤ መረጃ ይሸሸጋል ከሚል ከነባሩ ያለመተማመን ስጋት በመነሳት መሆኑን ከባለስልጣናቱ ቃለ ምልልስ ሰምተናል። መልሱ ባጭር ሲነገር ከፋይ፤ አጭበርባሪ፤ ሰብሳቢ ደግሞ ያገር ጥቅም ተቆጣጣሪ ነው ማለት ነው ። በኔ ድምዳሜ ይህ የችግሩ መሰረታዊ ምንጭ የስብራቱ ሁሉ መጀመሪያ ነው። እኔ የማውቀው የኢትዮጵያ ፖሊሲ ሁሉ የሚጀምረው ባለጉዳይን ህዝብ ያገሩ ተሳታፊ የጥቅሙ ተቆጣጣሪ እንጂ ራሱን ሌባና አጭበርባሪ ነው ይገለል በማለት አይደለም (ቢያንስ በወረቀት ላይ)። ይልቅስ በኢትዮጵያ ሁኔታ ከኢትዮጵያውን ስለ ልቡና በመነሳት ያለዚህ ሁሉ ግርግርና፡ አውጫጭኝ አያሌ አዎንታዊ መንገዶችን ተከትሎ ውጤታማ ስራ መስራት በተቻለ ነበር። ለምሳሌ፤ የከፋዩን ሰብዓዊ ክብር ለድርድር ሳያቀርቡ በዜግነቱ ተንከባክቦ መብትና፡ግዴታውን በጥሞና እያስረዱ ያለ መስቀለኛ ምርመራ በፊት በር ቀርበው መረጃዎቹን በሙሉ በሃላፊነት ራሱ እንዲሰጥ፤ የሰጠውም መረጃ በየጊዜው እንደየሁኔታው እንዲሻሻልና እንዲስተካከል ስለ ትክክለኝነቱም ሆነ ስለ መዛባቱ ሁሌም ተጠያቂነቱ የርሱ መሆኑን በማስጠንቀቅ እንደራሱ ጉዳይ ሊተውለት ይገባ ነበር።

ይህ አካሄድ የሃላፊነት ስሜትን ከማሳደሩ በላይ “ ለካስ በሀገሬ እንደዚህ አከበራለሁ ፤ ታዲያ፡ከኔ የጎደለው ምንድነው “ የሚለውን ዘላቂ ጥያቄ ለመመለስ የሚያበረታታ ነበር ። ተፈላጊውም ግብ የዚህ ሀገራዊ ስርዓት ዘላቂ ጥያቄን መመለስ እንጂ ለዛሬ ሪፖርት የሚሆን ብዙ ገንዘብ መሰብሰብ መቻል አይደለም።

አሁን እየሆነ ያለው ግን ከፋዩን ሁሉ አንደ ወንጀል ተጠርጣሪ በመስቀለኛ ጥያቄ የሚያዋክቡ፤ ገሚሶቹ በጉቦ ጥማት ቀንዳቸው የቆመ፤ ገሚሶቹ እንደ ባዕዳን ጭካኔያቸው ከፊታቸው ላይ የሚንቀለቀል፤ ተሞልተው የመጡትን እንጂ የሚያዩትን የማያምኑ ፤የማይሰሙ፤ ግብረሃይሎች በማሰማራት ከፋዩን የማይመለከተው ጥያቄ ጭምር እየጠየቁ ባገሩ ጉዳይ የመገለልና የባዕድነት ስሜት እስኪሰማው ግብሩን ለበላተኛ የመክፈል የዱሮ ስሜት እንዲያገረሽበት ተደረገ። ይብስ ብሎ ይህንን አሰራር ዜጋው በልቅሶ ሲያማርር ሹመኞቹ በሚዲያ እየቀረቡ እንደሰለጠነ ዘዴ ፈጠጥ ብለው ሲከላከሉ አንዳንዴ ከማናደድ አልፎ ያስቃል።

ይሁንና በዚህ ጭፍን ግምታቸው መነሻነት ከፋዩ በየቢሮው እየቀረበ እየተብጠለጠለ የተመደበበትን እንዲከፍል ማስፈራራትና፡ ማስጠንቀቅ ቀጠለ። (በነገራችን ላይ ካገኘሁዋቸው ሰዎች አንድ ሰው ብቻ የቦሌ ክፍለ ከተማ የሰው ክብር በመጠበቅ ትንሽ ሻል ይላል ማለቱን አስታውሳለሁ።)

ይህ ሁሉ ሲሆን ዛሬ በዚህ ሰዓት ስለሚሰበሰበው ሳንቲም እንጂ ስለ ዘላቂ የሀገርና የዜጋ ግንኙነት ስለ ዘላቂ የስርዓት ተከላ ለሴኮንዶች መታሰቡን እርግጠኛ አይደለሁም ። አሁን ይህ ሂደት ብዙ ምስቅልቅል ክፈጠረ በሁዋላ ለሚቀርቡ ወቀሳዎች የሚዘጋጁት መልሶች አንዳንዴ ጭራሽ የሀገሩ ባለቤት ለሆነ ዜጋ የሚሰጡ አይመስሉም። “ ግብር ከመደብንበት ህዝብ ከመቶ አርባው ፐርሰንት ብቻ ነው ቅር ያለው” ብሎ የሚመልስ ባለስልጣን ቁጥሩ ላይ አልዋሸም ብንል እንኩዋ፤ ግብርና፡ግብር ከፋይ ዜጎችና መብታቸው ለአንድ ሀገር ያለው መሰረታዊ ትርጉም ገብቶታል ወይም ግድ ይሰጠዋል ለማለት ይቸግራል። ግብር ከፋዮች “ ሰብዓዊ ክብራችን ይገፈፋል እንገለመጣለን እንሰደባለን እንሽሙዋጠጣለን “ እያሉ ሲያለቅሱ “ ችግሩ የሰራተኞች ማነስ ስለሆነ ቁጥር እንጨምራለን “ ሲሉ ያላገጡት ባለስልጣ የመለሱትን ሳዳምጥ ጉዳዩ ጨርሶ የግብር ስለመሆኑ መጠራጠር ጀመርኩ ። ቁጥር እንጨምራለን ማለት ተሰብስበው እንዲሳደቡ እናደርጋለን ማለት ነው? ወይስ…..?

ካፈርኩ አይመልሰኝ ወይም እኔ ያልኩት ብቻ ነው ልክ ከሚል መነሻ ለተፈጠረው ችግር ሁሉ የሚደረደሩ የቀዳዳ መወተፊያ፡ መልሶች ሁሉ ሆድ ይፍጀው እያለ ራሱ ውስጥ ተደብቆ በቅኔ መንፈስ ለኖረ ህዝብ ዝም ማሰኚያ፡ እንጂ ከቶም ማሳመኛ ሊሆኑ አይችሉም።

ስርዓት መትከል ከስራዎች ሁሉ የከበደ ስራ እንደሆነ እንኩዋን በመንግስት ደረጃ ትንሽ መስሪያ ቤት ያስተዳደረም ቢሆን ለመገመት አይሳነውም። ሆኖም ስራው ያሻውን ያህል ቢከብድም ፤ ሁሉን በሆደ ሰፊነት ይዞ ሀላፊነቱን ራሱ እንዲወጣ የፈጀውን ጊዜ ፈጅቶ ህዝቡን ማላመድ ነው ልማትን ማፋጠን። ይህ ሁሉ ሀተታዬ ሌባና አጭበርባሪ የለም ሁሉ ንፁህ ነው ለማለት አይደለም። ሌባማ አገር ገንብተው በጠገቡት ቱጃሮችም መሀል አለ። እያልኩ ያለሁት ግን አጭበርባሪ የሚስተናገድበት የህግ መስመር እያለ ድፍን አገር እንደሌባ የሚዋረድበት አግባብ አይበጅም ነው። ህጋዊውን በክብር ማስተናገድ ግድ እንደሆነ ሁሉ ህገወጡንም ከነክብሩ የሚቀጡበት ህግ ያላት አገር መሰለችኝ ኢትዮጵያ። ህግ ተላላፊ ደግሞ ቁጥሩ ብዙ አይደለም። ዘላቂ ስርዓት ሁሉ በረዥም ሂደት ውስጥ እየጠራ ባስተማማኝ ይተከላል እንጂ በጥቂት ወንጀለኛ ሰበብ መላ ያገሩ ህዝብ ክብርና ማረግ አየተገፈፈ በዘመቻ ነገር ይቃናል ማለት በጉልበቱ የሚያስብ ሰው መንገድ ብቻ ነው።
በማጠቃለያዬ፤ ከክፍያዎች ሁሉ በፊት የሰው ክብር መቅደሙን እናረጋግጥ። ሁሉም ነገር ያለ ሰው ከንቱ ነውና።

ክብሩን ከነሃላፊነቱ ከሰጡት ኢትዮጵያዊ እንኩዋን ደጁ ላይ ለቆመ የምድር መንግስት አይቶት ለማያውቀው የሰማዩ ዙፋንም በፍቅርና በውዴታ ስንት አስራት ሲከፍል የኖረ ህዝብ ነው።

LEAVE A REPLY