“አግባው ሰጠኝ ህይወቴ አደጋ ውስጥ ነው” አለ

“አግባው ሰጠኝ ህይወቴ አደጋ ውስጥ ነው” አለ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ በ1997 ዓ.ም የፓርላማ ተወካይ የነበረ እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ መስራችና የምክር ቤት አባሉ አቶ አግባው ሰጠኝ “በሽብር ተጠርጥረሃል” ተብሎ ጥቅምት 2007 ከሰሜን ጎንድር ተይዞ ወደ ማዕከላዊ ተጋዘ። በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን መዝገብ 16 ሰዎች የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ለሁለት ዓመታት በተለያየ ስቃይ ካለፉ በሗላ አግበውን ጨምሮ 9 ተከሳሾች ነጻ ተባሉ።
ይሁን እንጂ አግባው “ነጻ” ቢባልም በቂሊንጦ ቃጠሎ እጅህ አለበት በማለት ሌላ “የሽብር ክስ” ተመሰረተበት።የተለያዩ የማሰቃያ ተግባርም ተደረገበት።

አግባው ከዚህ ቀደም በ”ዝዋይ እስር ቤት የተፈጸመበትን ድብደባና የማሰቃየት ተግባር” በህክምና ምርመራ እንዲ ረጋገጥለት ለፍ/ቤቱ አቤቱታ ባቀረበው መሰረት ማረሚያ ቤቱ በትናንትናው ዕለት ለችሎቱ መልስ ሰጥቷል። መልሱም በአንድ በኩል አግባው “ሊያመልጥ እንደሞከረ የሚገልፅ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የእርስ በእረስ ጠብ እንደነበርና አግባውም በጠቡ ተጎድቶ ሊሆን ይችላል።”በማለት ለማስተባበል ተሞክሯል።አግባው ሰጠኝ ከአቅማችን በላይ ነውም ብለዋል።

አግባው ነሐሴ 1/2009 በዋለው ችሎት ልብሱን አውልቆ የደረሰበትን ጉዳት ለማሳየት ቢሞክርም በዳኞች ተከልክሎ ሳያሳይ ቀርቷል። አግባው ሰጠኝ በቂሊንጦ ቃጠሎ የተጠረጠሩ ሰዎች የታሰሩበት ዞን 5 ታሰሮ የነበር ሲሆን ከዝዋይ መልስ ይቅርታ ጠይቀው ከአንድ ሺህ በላይ እስረኛ ወደ ሚታሰርበት ዞን 2 አዘዋውረውታል። ይሁን እንጂ የማረሚያ ቤቱ አስተዳድር ይቅርታ ከጠየቁ በሗላ “ከአቅማችን በላይ ነው” ብለው ለፍርድ ቤቱ መልስ መስጠታቸው አስገራሚ ነው ተብሏል። አግባውም ካልቻሉ እነ መቶ አለቃ ማስረሻ የታሰሩበት ዞን 4 ሊያስሩት ይችሉ እንደነበር ተናግሯል።ነገር ግን ወደ ዞን 2 የቀየሩኝ ሊያጠቁኝ አስበው ሊሆን ይችላል በማለት ስጋቱን ገልጿል። ህይወቱ አደጋ ውስጥ እንደሆነና ዋስትናም እንደሌለው ተናግሯል ። ጎንደር ላይ የሆነ ነገር ሲፈጠር እኔ ላይ አይናቸው ይቀላል።አሁንም “ከአቅማችን በላይ ነው” ብለው ለፍ/ቤት መልስ መስጠታቸው ሊያደርጉ ያሰቡት ነገር እንዳለ አመላካች ነው፤ ስለሆነም ህይወቴ አደጋ ውስጥ ነው።ዋስትናም የለኝም ።” በማለት ለችሎቱ ትናንት አስረድቷል።

የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም በአግባው ሰጠኝ ላይ የሚፈጸመው ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር በአስቸኳይ እንዲቆም ለመጠየቅ “ዘመቻ” ለመጀመር ዝግጅት ላይ ናቸው።

LEAVE A REPLY