1. የኣገራት ምሥረታ
በዓለም ላይ ያሉ ሀገሮች ዛሬ ያላቸው ዳር ድንበር ተለይቶና ታውቆ ፣ ዓለም ኣቀፍ ሕጋዊ እውቅና ኣግኝተው፣ ሉዓላዊነታቸው ተከብሮና ተጠብቆ በእኩልነት መኖር ከመጀመራቸው በፊት የነበራቸው ዳር ድንበር ይለዋወጥ ግዛታቸውም ይሰፋ ይጠብ ነበር። በሀገሮች መካከል ዝርዝር ልዩነቶች ቢኖሩም የሁሉም ሀገሮች ኣመሰራረት ከኃይል ጋር የተያያዘ መሆኑን ከታሪክ መማር ይቻላል።
የዳር ድንበር መለዋወጥም ሆነ የግዛት መስፋትና መጥበብ እንዲሁ በሰላማዊ መንገድ የመጣ ሳይሆን በተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች በተደረጉ ኣስከፊና ደም ኣፋሳሽ ጦርነቶች ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ብዙ ሕይወት ጠፍቷል ፣ ንብረት ወድሟል ፣ በደልና ሰቆቃ ደርሷል ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተረግጠዋል። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ሀገርም እንደ ሀገር ሕይወትም እንደ ሕይወት መቀጠል ግድ ነውና ያለው ምርጫ በጋራ መኖር ወይም መበታተን ነው። በጋራ መኖርን የመፍትሔ ስልት የመረጡ ሀገሮች ታሪካቸውን በጥሞና መርምረው፣ የደረሰውን በደል ለይተው፣ ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ፣ ሳያጋንኑና ሳያንኳስሱ ታሪካቸውን እንዳለ ተቀብለው፣ በታሪክነቱ በክብር ኣስቀምጠው፣ እንዳስፈላጊነቱም የሰላምና የእርቅ ሥርዓት ዘርግተው ተፈጻሚ ኣደረጉ፤ የወደፊት የጋራ ሕይወታቸው በእኩልነት በነፃነትና በዴሞክራሲ የሚኖሩበትን ሥርዓት ዘርግተው ሰላምን ፈጠሩ፤ ልማትና እድገትን ኣፋጠኑ፤ ዴሞክራሲያዊ ባሕላቸውን ኣዳበሩ።
የኣውሮፓ ሀገሮች በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በኣንጻሩ ግን ካልታከመ የታሪክ ቁስል መላቀቅ የተሳናቸው ኃይሎች ያሉባቸው ሀገሮች ፤ የደረሰባቸውን ወይም የፈጠሩትን በደል ነጋ ጠባ እያነሱ እየጣሉ የግልና የቡድን ፍላጐታቸውን የሚያራምዱ ኃይሎች ያሉባቸው ሀገሮች፤ ዘረኛነት፣ ጠባብነትና ትምክሕተኛነት የተጠናወታቸው ኃይሎች ያሉባቸው ሀገሮች፤ በእኩልነት፣ በነፃነት እና በዴሞክራሲ በጋራ ለመኖር ወደሚያስችል ሥርዓት ለመሸጋገር ፍላጐትና ኣቅም የሌላቸው ኃይሎች ያሉባቸው ሀገሮች፤ ሕዝቦች እስካሁን የተሸከሙት ግፍና በደል ኣልበቃ ያላቸው ይመስል፤ ሰላምና ነፃነት እየናፈቃቸው እያለ ፤ ችግርና ድኅነት እየጠበሳቸው እያለ ፤ ቀሪ ሕይወታቸው በፈላጭ ቆራጭ ኣምባገነን ኣገዛዝ መዳፍ ሥር እንዲገፉ ወይም እንዲፈረካከሱ ይገደዳሉ።
ለዚህ ኣባባል እውነተኛነት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ውስብስብ የፖለቲካ ችግሮች ያሉባቸው ብዙ የኣፍሪካ ኣገሮችን በምሳሌነት መመልከት ይቻላል።
2. የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ እና እንድምታው
የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ የብዙ ሺህ ዓመታት ሂደት ውጤት ስለመሆኑ ከበቂ በላይ መረጃ እያለ፣ ለብዙ ሺህ ዓመታት በተካሄደው የመንግሥት ምሥረታ ከመነሻው እስከ ኤርትራ መገንጠል ድረስ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ሲለዋወጥ፣ የግዛት ክልል ሲሰፋና ሲጠብ እንደነበር በግልጥ እየታወቀ፣ የኣፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የሀገረ መንግሥት ምሥረታው ሂደት አንዱ አካልና የመጨረሻው ምዕራፍ ወይም መቋጫ እንደሆነ ግልፅ ሆኖ እያለ፣ እንደወያኔ የግል የፖለቲካ ኣጀንዳ ያነገቡ እነዚህን እውነታ ገፍትረው እና ክደው ሆነ ብለው የምኒልክን ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደት መነሻና መድረሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ ዓመት ታሪክ ነው ይሉናል።
ትልቁን የሀገርና የሕዝብ ጉዳይ ረግጠው ፣ ወደ “ቆሼ” የፖለቲካ ጥሬ ለቀማ የሚባዝኑትን ታዝበን ፣ የሩቁን የምሥረታ ሂደት ለታሪክ ትተን ፣ የወቅቱ የፖለቲካ ትኩረትና ግለት ወደሆነው ወደ ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደት የመጨረሻ ምዕራፍ እናተኩር። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የተመሰረተችው እንደ ሌሎች ሀገሮች ሁሉ በኃይል ነው። ኣፄዎች ነገስታት ሱልጣኖች ለብዙ ሺህ ዘመናት በገብር ኣልገብርም ፣ በተገዛ ኣልገዛም የሥልጣን ሽሚያ በኢትዮጵያ ላይ ብዙ ጦርነቶች ኣካሂደዋል። በዚህም ብዙ ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ በደልና ሰቆቃ ደርሷል። ከመነሻው ያለማንገራገር እንገዛለን እንገብራለን ያሉ ኣካባቢዎች (ለምሳሌ ወለጋ) ሕይወታቸው ከሞላ ጐደል እንደነበረ ቀጥሏል፤ እምቢ ኣንገዛም ኣንገብርም ያሉ መለስ ብለው ግን እሺ ብለው የተገዙና የገበሩ ኣካባቢዎች (ለምሳሌ ጅማ) የደረሰባቸው በደል የአንድም ነፍስ ዋጋ ብዙ ቢሆነም በአንጻራዊ መለኪያ ያን ያህል የከፋ ኣይደለም ። እምቢ ኣንገዛም ኣንገብርም ብለው ከፍተኛ ተቃውሞ ያካሄዱ ኣካባቢዎች (ለምሳሌ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ኣርሲ፣ ሀረር) ከፍተኛ እልቂትና ውድመት በደልና ሰቆቃ ተፈጽሞባቸዋል።
ከሀገረ መንግሥት ምሥረታ ጋር ተያይዞ የተካሄደው ጦርነት በልግዛ በላስገብር ፍላጐት ላይ ያተኮረ እንጂ በማንነት እና በኣካባቢ ላይ ያነጣጠረ ኣልነበረም። የልግዛ ላስገብር ጦርነት እንዳበቃ ኣሸናፊው መልሶ ተሸናፊውን የኣካባቢው ኣስተዳዳሪ ኣርጐ ይሾመዋል። ገዢዎች በየኣካባቢው የፈፀሙትን ጭካኔ የጀመሩትና የተለማመዱት በየራሳቸው ኣካባቢ ኣንገዛም ኣንገብርም ባሉት ላይ ነው። ዘንድሮም እንደምናየው ወያኔም በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ እየፈጸመ ያለውን ዘረኛና ፋሺስታዊ ግፍ የጀመረውና የተካነው ትግራይን ቤተ ሙከራ በማድረግ ነው።
ኣንገዛም ኣንገብርም ያሉት ኣሸንፈው ቢሆን ኖሮ ሊያስገብሩና ሊገዙ የመጡትን ወደ መጡበት ማባረር ብቻ ሳይሆን በእነሱ ላይ የደረሰውን ዓይነት በደል መልሰው ማድረሳቸው ኣይቀርም ነበር። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ኣህመድ ግራኝ ነው። ኣህመድ ግራኝ ሊያስገብሩና ሊገዙ ወደ ኣካባቢው (ሀረርጌ) የመጡትን ኣሸንፎ እየተከታተለ እስከ ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ዘልቆ ከድል ወንበራ ጋር በደምቢያ መቀመጫውን ኣድርጐ ኢትዮጵያን ለተወሰነ ጊዜ ገዝቷል። ኣህመድ ግራኝ ደምቢያ ድረስ የዘለቀው እቅፍ ኣበባ ሳይሆን ጠመንጃ እና ጥይት ይዞ ነው፤ ጠመንጃ እና ጥይት የሚያደርሰው ለሁሉም ግልፅ ነው።
በአህመድ ግራኝ መልሶ የመግዛትና የማስገበር ጦርነት እንደሌሎች የላስገብርና የልግዛ ጦርነቶች ብዙ ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል ፣ በደልና ሰቆቃም ደርሷል ። ከሀገረ መንግሥት ምሥረታ ጐን ለጐን የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተለያየ ጊዜያት ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እንቅስቃሴ ወይም ፍልሰት ኣድርገዋል። የሕዝብ ፍልሰት ተራ የገበያ ጉዞ ኣይደለም፤ በተደራጀ መልኩ እንደ ኃይል ወይም ሠራዊት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። የሕዝብ ፍልሰት ወደ ሌላ ኣካባቢ በመሄድ ባመዛኙ ነባሩን ኣፈናቅሎ ፣ መሬቱን ቀምቶ፣ ሀብት ንብረቱን ዘርፎ፣ የሚቃወመውን ገድሎ የሚደረግ ሠፈራ ነው። ተወራሪውም ኣቅሙ እስንከሚፈቅድለት ድረስ ተከላክሎ ወራሪውን መመለስ ካቃተውም በተሸናፊነት ኣብሮ መኖር ነው። በኢትዮጵያ የታየው የውስጥ የሕዝብ ፍልሰት ሕይወትን የማጥፋት፣ ንብረትን የማውደም ፣ መሬት የመንጠቅ፣ ሕዝብን የማፈናቀልና የማሰደድ ኣሉታዊ ገፅታው ቢሆንም፣ በኣዎንታዊ ጐኑ ከዚህ ሁሉ በኋላ ሕዝቦችን ኣቀራርቧል፣ ቋንቋና ባሕልን ኣወራርሷል፣ የጋራ ማንነትንና ሥነልቦናን በኣጠቃላይ ኢትዮጵያዊነትን ለማሳደግ የበኩሉን ድርሻ ኣበርክቷል።
ይህ ኢትዮጵያዊነት ነው በተለያዩ ጊዜያትና ምክንያቶች ኢትዮጵያን የወረሩ ኃይሎችን ድባቅ እየመታ የመለሰው። በሀገር ውስጥ እንቅስቃሴ ወይም ፍልሰት ኣብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የዚሁ ሂደት ኣካል ቢሆንም ከግማሽ ምዕተ ዓመት ላላነሰ ጊዜ በኣብዛኛው የኢትዮጵያ ክልሎች በጥልቀትና በስፋት የተካሄደው የኦሮሞ ሕዝብ ፍልሰት ጐልቶ ይነሳል። ፍልሰት በኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብን ኣሰፋፈር በእጅጉ ቀይሮታል ፤ የኦሮሞ ኣሰፋፈርም በኣመዛኙ የግማሽ ምዕተ ዓመት የፍልሰት ሂደት ውጤት እንጂ ጃዋር ሞሓመድ፣ ጸጋዬ ኣራርሳ እና ደጀኔ ጉተማ በኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ እንደገለፁት ኦሮሞ የሰፈረው እግዚኣብሔር በሰጠው መሬት ላይ ኣይደለም።
ዜጐች በየትኛውም የኣገራቸው ክፍል የመንቀሳቀስ፣ የመስራት ፣ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብታቸው የተከበረ ነው። ይኼን ኣክብሮና ተቀብሎ በሰላም ኣብሮ በመኖር ፈንታ ይህ የእነእገሌ መሬት ነው ፣ እነእገሌ መጤ ናቸው ይውጡ ማለት የዜግነትን መብት መግፈፍ ይሆናል። እነ ጃዋር ሞሓመድ ፣ ጸጋዬ ኣራርሳ እና ደጀኔ ጉተማ እግዚኣብሔር ለኦሮሞ በሰጠው መሬት ላይ ሌላው ይጠቀማል ማለቱን የሚገፉበት ከሆነ ሌሎቹ ሰማንያ ኣምስት ብሔረሰቦች እግዚኣብሔር የሰጣቸውን መሬት እስከሚያገኙ ድረስ ሁሉም ከፍልሰት በፊት ወደ ነበረበት ቦታ መመለስ ግድ ሊል ነው። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ውስብስብ የፖለቲካ ሁኔታ በኣንድ በኩል ከኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ፣ በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ሕዝቦች የሀገር ውስጥ ፍልሰት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው።
ይህን እውነታ መቀበል ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን ለመመስረት በጣም ይጠቅማል። ከወያኔ በፊት የነበረውን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት የተደረጉ ውስን እንቅስቃሴዎች ኣካባቢያዊ እና ቡድናዊ ነበሩ። በ1950ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴም ግልፅ መነሻና መድረሻ ባለመያዙ ፤ በጠንካራ ድርጅትና ኣመራር ባለመደገፉ፤ በርዕዮት ዓለም ውዥንብር በመዋጡ፤ መሬት ላራሹና የብሔረሰብ ጥያቄ መፈክር ከማንሳት ባሻገር ያለፈ ውጤት ኣላስመዘገበም። ቀስ በቀስ ሕዝባዊ ትግል እያደገ መጥቶ በ1966 የሕዝብ እምቢታ በተጋጋመበት ወቅት የተሻለ ኣደረጃጀት እና ኣመራር የነበራቸው መኢሶን፣ ኢሕኣፓና ብሔርተኛ ድርጅቶች በየራሳቸው የግልና የቡድን ድብቅ ኣጀንዳ ተጠምደው የሕዝቡን ትግል ወደ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ለማሸጋገር ባለመቻላቸው ደርግ እንዲነጥቀው ኣድርገዋል፤ መልሰውም ራሳቸውን የደርግ ሰለባ ኣድርገዋል። ደርግም በራሱ የግል ኣጀንዳ ተጠምዶ ኣንድ ትውልድ ከመጨፍጨፍ በቀር ኣብዮቱን መጠበቅ ሀገርንም ማስተዳደር ተስኖት በተፈጠረው ክፍተት ወያኔ ሥልጣን ላይ ወጣ።
የ1966 ሕዝባዊ ኣብዮት ለየማኅበረሰቡ ልኂቃን በተለይም ለመኢሶን ፣ ለኢሕፓና ለብሔር ድርጅት ኣባል ልኂቃንና ለደርግ በኢትዮጵያ ላይ ለዘመናት የተከማቸውን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት ወይም ለመቀየር መልካም ኣጋጣሚ ሆኖ ሳለ ኣሁንም በየኪሳቸው ስለያዙት ዘውድ (የኣሰፋ ጫቦ ኣባባል) እና በሕሊናቸው ስለሚያስቡት የፖለቲካ ጥሬ እየተጨነቁ የተፈጠረውን ታሪካዊ ኣጋጣሚ ኣመከኑት፣ ኣከሸፉት። በኢትዮጵያ ላይ ለረጅም ዘመናት የተንሰራፋውን ፈላጭ ቆራጭ ኣገዛዝ ተወት እናድርገውና ፣ በተለይ ከዘመነ መሣፍንት ወዲህ የተፈራረቁትን ኣምባገነን ገዢዎች ስንመለከት ከወያኔ በቀር ሌሎቹ ሁሉንም ያለ ልዩነት ገዝተዋል። ከወያኔ በቀር ሌሎች ገዢዎች የኢትዮጵያን ጥቅም፣ ዳር ድንበርና ሉዓሏዊነት ኣስከብረዋል። ቴዎድሮስ በመቅደላ፣ ዮሓንስ በመተማ፣ ምኒልክ በኣድዋ፣ ኃይለሥላሴ በጣሊያን ወረራ፣ መንግሥቱ በሶማሊያ ወረራ ያሳዩት ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ሕያው ማስረጃዎች ናቸው።
በኢትዮጵያ ላይ የተፈራረቁ ገዢዎች ሁሉ ከተለያየ ማህበረሰብ የመጡና የየራሳቸው ቋንቋ ያላቸው ቢሆንም አማርኛን የአገዛዛቸውና የሥራዓታቸው ማስፈፀሚያ ቋንቋ አድርገው ተጠቅመውበታል፣ እየተጠቀሙበትም ነው፤ አማርኛን የአገዛዛቸው ቋንቋ ያደረጉት አማራ ለምኗቸው ፣ አስገድዷቸው፣ ወይንም ጭኖባቸው ሳይሆን የየራሳቸው ቋንቋ አማርኛ የሚሰጣቸውን አገልግሎት ስለማይሰጣቸው ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ፈልገው፣ ወደውና ፈቅደው መርጠው ነው፤ የየራሳቸው ቋንቋ የየመንግስታቸው የሥራ ቋንቋ መሆን ቢችልማ ኖሮ ትልቁ ራስ ዓሊ በጎንደር ቤተመንግሥት በኦሮምኛ፣ ኣፄ ዮሓንስ በመቀሌ ቤተመንግሥት በትግርኛ፣ መለስ ዜናዊ በምኒልክ ቤተመንግሥት በትግርኛ መክረውና ወስነው በኣማርኛ ባላስፈፀሙ ነበር። ቴዎድሮስና ምኒልክ ቋንቋቸው ኣማርኛ ስለሆነ ለሁሉም የመንግሥት ሥራ በኣማርኛ መጠቀማቸው ግልፅ ነው።
ኃይለሥላሴና መንግሥቱ ኦሮምኛን ለምክክርም ሆነ ለውሳኔ ኣልተጠቀሙበትም፤ ለምክክር፣ ለውሳኔ፣ ለማስፈፀም የተጠቀሙት ኣማርኛን ነው፤ እንግዲህ ገዢዎች ከተለያየ ማህበረሰብ የመጡ፣ ለአገዛዛቸው የየራሳቸውን ቋንቋ ትተው አማርኛን የመረጡ፣ አማርኛ በመላው ኢትዮጵያ በስፋት እንዲዳረስ ያደረጉ መሆናቸው ግልጽ ሆኖ እያለ ብልጣ ብልጥ ፖለቲከኞች ለድብቅ ኣጀንዳቸው ሲሉ የፈጠጠውን እውነት ክደውና አወላግደው አማራ ጨቋኝ፣ የራሱን ቋንቋ በሌሎች ላይ የጫነ ገዢ መደብ አድርገው ይወነጅሉታል ይከሱታል።
በኣማርኛ ፈንታ የመንግሥት የሥራ ቋንቋ እንግሊዘኛ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ብልጣ ብልጥ ፖለቲከኞች ምን ይሉ ነበር? በኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ወዶ ፣ ፈቅዶና ፈልጐ የኢትዮጵያን ጥቅም፣ ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስደፈረ የወያኔ መንግሥት ነው። ወያኔ ለመንግሥት ሥልጣን እንዲበቃ ከሱዳን መንግሥት ለተደረገለት ድጋፍ ከጐንደር እስከ ጋምቤላ ከተዘረጋው ከ1,600ኪ.ሜ. የኢትዮጵያ ድንበር ወደ ውስጥ ከ30 እስከ 60ኪ.ሜ. በመግባት በኣማካኝ 72,000 ካሬ ኪ.ሜ. መሬት ገምሶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳያውቀውና ፓርላማ ሳይመክርበት በድብቅ ለሱዳን መንግሥት በወሮታ ሥጦታ ኣስረክቧል። የወያኔ ወራዳ ተግባር ይቀጥላል፣ በደምህ ደሜ ነው ፀረ-ወያኔ ህዝባዊና አገራዊ ትግል ወያኔ በተወጠረበት ግዜ በአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባህር ዙሪያ እየታየ ያለው የጂዎ ፖለቲካ ለውጥ ከፍተኛ ስጋት ስላሳደረበት ወታደራዊ አቅሙ ስለማያዋጣው ኤርትራ እባክሽ ታቃዋሚዎቼን መርዳት አቁሚ በማለት ወደ መቶ ሺህ ኢትዮጵያውያን ሕይወት የተገበረበትን ባድሜን በእጅ መንሻ ማቅረቡ አይቀርም።
ወያኔ ለሱዳን ያስረከበው መሬት መሀዲስቶች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ ኣፄ ዮሓንስ ከትግራይና ከሌሎች ኣርበኞች ጋር የኣገር መከላከል ጦርነት ሲያደርጉ በጀግንነት የወደቁበትን ፣ ደማቸውን ያፈሰሱበትንና ኣጥንታቸውን የከሰከሱበትን መተማን ይጨምራል። እጅግ ኣስገራሚ፣ ኣሳፋሪና ኣንገት ኣስደፊ የሚያደርገው የኢትዮጵያ መሬት ተገምሶ መሰጠቱ ብቻ ሳይሆን የኣፄ ዮሓንስ እና የትግራይ ኣርበኞች ደምና ኣጥንት ለጥቅም ሲባል ኣብሮ መቸብቸቡ ነው።
ወያኔ ወርቅ ከሆነው ትግሬ መወለዳችን ያኮራናል (መለስ ዜናዊ) ብሎ በኣደባባይ ኣውጆ እኮራበታለሁ እና ኣከብረዋለሁ የሚለውን የኣባቶቹን ፣ የኣያቶቹን እና የቅድመ ኣያቶቹን ደምና ኣጥንት እንደ ተራ ሸቀጥ ኣሳልፎ መስጠቱ ነው። በዚህም ኣሳፋሪ ድርጊቱ ወያኔ የወላጆቹን ደምና ኣጥንት የሸጠ የመጀመሪያው ኣሳፋሪ ልጅ ወይም ትውልድ ያደርገዋል።
እነ ኣፄ ዮሓንስ በደምና ኣጥንታቸው ያስከበሩትን ዛሬ ከነደማቸውና ከነኣጥንታቸው ወያኔ የሸጠውን የኢትዮጵያን መሬት ኢትዮጵያዊያን በደማቸው ያስመልሱታል፣ ያስከብሩታል። ወያኔ የወላጆቹን ደምና ኣጥንት በመሸጡ እንኳን ሊጸጸት፣ ጉዱን ቀጥሎ በሕይወት ያለውን የትግራይን ሕዝብ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵዊነት እየነጠለው ነው። ከመነሻው የወያኔ ሁኔታ ያላማራቸው የትግራይ ሽማግሌዎች በደስታና በሀዘን ኣብረን ከኖርነው ኣማራ ጐረቤታችን ተለያየን፣ እንደወትሮኣችን በኣገራችን ኢትዮጵያ ተንቀሳቅሰን ለመኖር ሰጋን ብለው ለነመለስ ሲነግሯቸው “ይህቺ ባቄላ ካደረች ኣትቆረጠምም”፣ የተነሳንበትንም ዓላማ ያደናቅፋል በማለት የመቀጣጫ እርምጃ ተወሰደባቸው።
ትግሬ ኢትዮጵያዊ ኣይደለም በማለት የብዙ ሺህ ኣመታት ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ኣስወልቆ የወያኔነት ጥብቆ ኣለበሰው ፣ ወያኔነት የትግሬነት፣ ትግሬነትም የወያኔነት መገለጫ ስለሆኑ ወያኔ ከሌለ ትግሬ ኣይኖርም በማለት በሩዋንዳ የቱትሲዎችን መጨፍጨፍ ደጋግሞ ያነሳል፤ በኢትዮጵያዊነት የቀጠሉ ትግሬዎችን “ከሃዲ” በማለት መውጪያ መግቢያ ኣሳጣቸው፣ በኦሮሞና በኣማራ የተነሳውን ፀረ ወያኔ ትግል ምክንያት በማድረግ “ትግሬ ተነጥሎ ተጠቃ” በማለት በዕቅድና በዝግጅት በየኣካባቢው የሚኖሩትን ትግሬዎች ወደ ትግራይ ወሰደ፤ በወያኔው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር በዶ/ር ኣዲሱ ገብረእግዚኣብሔር በኩል ኣሁንም “ትግሬ በትግሬነቱ ተጠቃ” ኣስብሎ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ኣስቀረበ። ወያኔ ይህን ሁሉ የሚያደርገው በኣንድ በኩል የትግራይን ሕዝብ ዋሻውና ምሽጉ ለማድረግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የትግራይ ሕዝብ በፍርሃትና በጭንቀት ወደ ወያኔ እንዲሸጐጥ ለመገፋፋት ነው። ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጨፍጭፏል ፣ ሀብት ንብረቱንም ዘርፎ ወደ ውጭ ኣሽሽቷል፣ ቤተሰቡንም ከሞላ ጐደል ኣውጥቷል፣ እሱም ለሽሽት ኣኰብኩቧል። ወያኔ ኣንድ ማለዳ ተነስቶ እወክልኃለሁ እያልኩ የነገድኩብህ የትግራይ ሕዝብ ዕዳውን ኣንተ ክፈል ብሎ ከመፈርጠጡ በፊት “ላም እሳት ወለደች ፣ እንዳትልሰው ፈጃት፤ እንዳትተወው ልጅ ሆነባት” ሆኖብህ የተሸከምከውን ጉዱን ወያኔን “ጨው ለራስህ ብለህ ጣፍጥ ፣ በቀር ድንጋይ ነህ ተብለህ ትጣላለህ” ብለህ ወያኔ የትግራይን ሕዝብ ኣትወክልም ልትለው ይገባል።
ሌላው የትግራይ አዛኝ ቅቤ አንጓቾች ለከርስና ለኪስ ስትሉ ለወያኔ ያደራችሁ የትግራይ ልሂቃን ናችሁ፡ እናንት የወያኔ ልሂቃን በትግራይ ሕዝብ ስም ነገዳችሁ የትግራይን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ለያችሁ፤ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ዘመታችሁ፣ ወያኔነት፡፡ ወያኔ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሐብት ንብረት ዘርፎና ነቅሎ የትግራይ የልማት ጉዝጓዝ ሲያደርገው ስህተት ነው ለማለት አቅም አጣችሁ፣ ይሉኝታ ቢስነት፡፡ እስካሁን ተዘርፎና ተነቅሎ ወደ ትግራይ የገባው በቂ ስላልሆነ ተጨማሪ ሐብትና ንብረት ካልገባ፤ ወያኔ ለስልጣን በተዋጋበት ግዜ በትግራይ ጉዳት ደርሷል በማለት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንገሥት ልዩ ድጎማ እንዳደረገው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትም ባለመቋጨቱ በትግራይ ላይ ጉዳት ደርሷል ብሎ ፌደራል መንግሥት ካሳ ካልከፈለ፣ በትግራይ መንደሮች የባቡር ሐዲድ ካልተዘረጋ ፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐ/ማሪያም ደሳለኝ ስልጣን ይልቀቅ ብላችሁ ተንጫጫችሁ፣ ስግብግብነት፡፡
ሌሎች ኢትዮጵያውያን የልማት ፕሮጀክት አዘጋጅተው ለመንግስት ሲያቀርቡ ፈቃድ እያስከለከላችሁ ፡ ያስከለከላችሁት ፕሮጀክት ባለቤት ሁናችሁ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ( ልማት) ባንክ የማይመለስ ብር አፍሳችሁ በአፋር ፣ በአዲስ አበባ ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል … ወዘተ ልማታዊ ባለሐብት ሆናችሁ ፤ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች መሬት እየወሰዳችሁ ፎቅ ገነባችሁ መልሳችሁ ሸጣችሁ ለውጣችሁ በውጭ ሐገር ሐብት እና ንብረት አፈራችሁ፤ ራስ ወዳድነት። ለነፃነትና ለፍትህ አደአባባይ የወጡ ኢትዮጵያውያን ጭንቅላት በአልሞ ተኳሽ አጋዚ ሠራዊት ሲቦደስ፣ በፌደራል ፖሊስና መከላከያ ሠራዊት ሬሳቸው ሲረፈረፍ፣ የብዙዎች ደብዛ ሲጠፋ፣ በሞቱ ልጆቻቸው ሬሣ ላይ እናቶች ተገደው ተቀምጠው እንባቸው ሲፈስ፣ በወያኔ ማጎሪያ እሥር ቤት ሰቆቃና ጩኸት ሞልቶ ሲፈስ ፡ የወያኔ ትግራይ ልሂቃን ይኽን ሁሉ እያያችሁና እየሰማቹህ እንደ ሰባዊ ፍጡር እንኳን ሀዘንና ፀፀት ለመግለጽ ህሊና አጣችሁ፣ ሞራለቢስነት።
የወያኔ ልሂቃን፤ ነገ ሌላ ቀን ነው፣ የሠራችሁት መዘዘ ብዙ አሳፋሪ ጥቁር የታሪክ ጠባሳ በትውልድ፣ በዘመድ አዝማድ፣ በወላጅ፣ በልጅና ልጅ ልጅ በቁጭትና በፀፀት ይታሰባል ፣ፍትህም በአደባባይ ይጠየቃል፣ ወያኔ የትግራይ ሕዝብ ዕዳውን ይክፈል ብሎ ሲፈረጥጥ ፡ እናንተም ተጎልታችሁ ከመቅረታችሁ በፊት ፈጣሪ ህሊናውን ከሰጣችሁ የትግራይን ሕዝብ በተለይ ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ባጠቃላይ ይቅር በሉን ብላችሁ ወደ ሕዝብ ተቀላቀሉ።
3. ደምህ ደሜ ነው ፣ ፀረ ወያኔ ሕዝባዊ ትግል ፋሺስቶች ፣
ዘረኞችና ኣምባገነኖች ድብቅ ኣላማቸውን ለማሳካት ተንደርድረው በሕዝብ ውስጥ ይመሽጋሉ፤ የሕዝብ ብሶት ነው የሚሉትን ያራግባሉ ፤ ሀሳባቸውን የተቀበለውን በሰላም ሌላውን በግድ ከጀርባቸው ያሰልፋሉ። ወያኔም ሥልጣን ለመያዝ ትግሬ ያባቶቹን የመንግሥት ሥልጣን በምኒልክና በሸዋ መሳፍንት ተነጠቀ፤ የበላይነቱን ኣጣ፤ ማንነቱንና ታሪካዊ ቦታውን ተቀማ፤ ወያኔ ልጁም ወደ ታሪካዊ ቦታውና ክብሩ ይመልሰዋል በማለት ወደ ጫካ ገባ፤ በለስ ቀንቶትም ለሥልጣን በቃ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሠረቱ ሰውን ያምናል ቃሉንም ይጠብቃል። ወያኔ ኣዲስ ኣበባ ገብቶ ሥልጣን ሲይዝ፣ ጥርጣሬና ስጋት ቢኖርም፣ መቼም ከደርግ የባሰ ኣይሆንም፣ ሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ እስከሚደርስለት ወራሪ ጠላትን እየመከተ የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት እየጠበቀ የኖረው የትግራይ ሕዝብ ልጅ ነው በማለት በኢትዮጵያዊነቱ ቢቀበለውም የወያኔ ጉዞ ግን በፍጹም የተለየ ሆነበት፣ ወያኔ በዘር ተሰባስቦ፣ በዘር ተደራጅቶ ፣ ዘረኛ ፖሊሲ ቀርፆ፣ ዘረኛ የማስፈፀሚያ ስልት ነድፎ ኢትዮጵያን የግሉ ኣድርጐ ለመግዛት የተነሳበትን ዓላማ ለማስፈፀም የቋጠረውን ቂም በቀል፣ ያናወዘውን ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት፣ የተጋተውን ዘረኛነት እና ጥላቻ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጭኖ ከ1983ዓ.ም. ጀምሮ በፈላጭ ቆራጭነት ኢትዮጵያን በብቸኝነት እየገዛ ነው። ከሁሉም በፊት ወያኔ ፣ ሁሉም ነገር ለወያኔ በሚለው ዘረኛ እና ስግብግብ መመሪያው መሠረት በኣምሳሉ በፈጠራቸው ዘራፊ ድርጅቶች ፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ኣማካኝነት ያለ ሃፍረትና ያለ ይሉኝታ የሀገሪቱን ሀብት ዘረፈ ፣ ሕዝቡን ከመሬቱና ከቤቱ ኣፈናቀለ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በኣስከፊ ሁኔታ ረገጠ።
ሚሊተሪውና ደህነንቱን፣ ፖሊሱንና ቢሮክራሲውን ሙሉ ለሙሉ በኣባላቱ ተቆጣጥሮ ለኣገዛዙ እንቅፋት የሆኑትን ጨፈጨፈ፣ ኣሰረ ፣ ኣሰቃየ፣ ደብዛቸውን ኣጠፋ ፣ ተቋማትን ኣፈረሰ፣ ታሪክን ደመሰሰ።
ከኣሜሪካ፣ ከእንግሊዝና ከኣውሮፓ ሕብረት የሚያገኘውን የባጀት ድጐማ ፤ ከልማትና ረድዔት ድርጅቶች የሚያሰባስበውን ድጋፍ ፤ ከተለያዩ ሀገሮች የሚያገኘውን ግዙፍ ብድር በብር እያተመ ከፍሎ የውጪ ምንዛሪውን ወደ ውጪ በማሸሽ ላይ ነው። በዚህም ሂደት ያልተደረሰበትን ትተን ወደ 36 ቢሊዮን ዶላር በውጪ ሀገር እንዳስቀመጠ ግልፅ ሆኗል። በዚህም ኢትዮጵያን ልትወጣ ወደማትችለው ዕዳ ከቷታል።ለዘመናት መፍትሔ ያጣውን የብሔር ጥያቄ ፈትቻለሁ በማለት ወያኔ ኢትዮጵያን በቋንቋ ሸንሽኖ፣ የክልሎችን ኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥልጣን ቀምቶና በራሱ በወያኔ እጅ ኣስገብቶ የብሔረሰቦች ቀን ብሎ ባወጀው ዓመታዊ በዓል የባሕል ልብሳችሁን ለብሳችሁ በቋንቋችሁ ዝፈኑ፣ ተደሰቱ፣ ኣማራን ገዢ መደብና ጨቋኝ እያላችሁ ኣውግዙ በማለት የጐሳ ኣፓርታይድን እያጠናከረ ነው። ጉድና ጅራት ወደኋላ ነው እንደሚባለው ወያኔ የበግ ለምድ ለብሶና ተለሳልሶ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ቀስ በቀስ ለምዱን ኣውልቆ ፈሺስታዊነቱንና ዘረኛነቱን፣ ስግብግብነቱንና ራስወዳድነቱን፣ ቂመኛነቱንና ተበቃይነቱን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በደም ጅረት ተገበረው። ይባስ ብሎ ተብቶና ተኩራርቶ ጀግንነቱንና ታላቅነቱን ለማሳየት “ተሀምበሌ ተሀምበሌ ከወያኔ ዘሎ ዝከበሬ” በማለት ነጠላ ዘፈን ሲለቅ የኢትዮጵያ ሕዝብም እርስ በእርሱ “ደምህ ደሜ ነው ተባብሎ” ፀረ ወያኔ ሕዝባዊ ትግሉን ኣፋፈመ። ወያኔ እያደረሰ ያለው በደል ሕዝቡ ከሚሸከመው በላይ በመሆኑ ቁጣና ኣመፅን ኣስከተለ፤ በየኣካባቢው የሚካሄደውን የተበታተነ ትግል ወደ ሕዝባዊ ትግል ኣሳደገ ኣሸጋገረ፤ በኦሮሞ፣ በኣማራ፣ በኮንሶና በሌሎች ኣካባቢዎች የተቀጣጠለው ኣመፅና ትግል ለወያኔ የእግር እሳት ሆነ። ሕዝባዊ ትግሉን ይበልጥ ያሳደገው፣ ያስተሳሰረውና ሕዝባዊና ሀገራዊ ባሕሪ የሰጠው የሚፈሰው የኦሮሞ ደም የኛም ደም ነው፣ በቀለ ገርባ የኛም መሪ ነው ብሎ ለተላለፈው የኣማራ ኣጋርነት ድምጽ የኣማራው ደም የኛም ደም ነው፣ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ የኛም መሪ ነው ፣ የወልቃይት ጥያቄ የኛም ጥያቄ ነው የሚለው የኦሮሞ ቅጽበታዊ ምላሽ ነው።
ወያኔ እሳትና ጭድ ኣድርጌያቸዋለሁ የሚላቸው ኦሮሞና ኣማራ ባልተጠበቀ ፍጥነትና ጥንካሬ ኣሸዋና ሲሚንቶ (የዶ/ር ዲማ ነገዎ ኣባባል) ሆኖ ሲያያቸው፤ የነፃነት ቻርተራቸውን በደማቸውና በኣጥንታቸው መጻፋቸውን ሲመለከት፤ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ገንብተው በነፃነት እና በእኩልነት በጋራ ለመኖር ያላቸውን ቁርጠኝነት ሲገነዘብ እጢው ዱብ ኣለ።
በኣንፃሩ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ የፖለቲካ ሰዎች፣ ድርጅቶችና ኣክቲቪስቶች ፈጣን ምላሻቸው ድጋፍ ቢሆንም በቀጣይነት ያሳዩኣቸው እንቅስቃሴዎችና የወሰዷቸው እርምጃዎች የተፈጠረውን ኣንድነትና የጋራ ትግል የተጠበቀውን ያህል የሚያፋጥንና የሚያጠናክር ሆኖ ኣልታየም።ለትግሉ ኣለመፋጠን እንደዋና ምክንያት ሆኖ የሚቀርበው ኣንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ድርጅቶችና ኣክቲቪስቶች ከሕዝብ እና ከሀገር ፍላጐት በላይ የየራሳቸውን ድብቅ የግልና የቡድን ኣጀንዳ በማስቀደማቸው ነው። የሚያስገርመው ይኼን የሚያደርጉት ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም ፍላጐት ቁመናል እያሉ ነው። በየኪስ ያሉ ዘውዶችና በሕሊና የሚታለሙ የፖለቲካ ጥሬዎችን እርግፍ ኣድርጐ መተው ካልተቻለ ችግሩ እየተባባሰ ይቀጥላል። 4. ድኅረ ወያኔ ኢትዮጵያ ኣቋሞች ከወያኔ በኋላ ኢትዮጵያን የሁሉም የጋራ ቤት ኣድርጐ ማዋቀርና ለሁሉም የሚሆን የፖለቲካ ሥርዓት መዘርጋት እንዴት ይቻላል? በኣጠቃላይ ድኅረ ወያኔ ኢትዮጵያ ምን ትምሰል በሚለው ጥያቄ ላይ በዋናነት ኣራት ኣቋሞች ተንፀባርቀዋል፣ እንመልከታቸው።
ኣቋም ኣንድ ፡-ኣንድ ሀገር ፣ ኣንድ ሕዝብ ፣ ኣንድ ቋንቋ ፣ ኣንድ ሰንደቅ ኣላማ የኣቋም ኣንድ መሠረታዊ ኣስተሳሰብ ድኅረ ወያኔ ኢትዮጵያ ኣንድ ሀገር ፣ ኣንድ ሕዝብ ፣ ኣንድ ቋንቋ፣ ኣንድ ሰንደቅ ዓላማ፣ በሚል እሳቤ ትመሥረት የሚል ይመስላል። ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ የሆነ ነገር ባይኖርም ኣንድ ሀገር ኖሮን፣ ኣንድ ሕዝብ ሆነን ፣ ኣንድ ቋንቋ ተናግረን ፣ ኣንድ ሰንደቅ ዓላማ ኣንግበን ኣብረን እንኑር ማለት ሊሆን ይችላል። ኣንድ ሀገር፣ ኣንድ ሕዝብ፣ ኣንድ ቋንቋ፣ ኣንድ ሰንደቅ ዓላማ ለመፍጠር እንደ ሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ረጅም ጊዜ የሚሻ ሰፊና ፍትሓዊ የፖለቲካ ሥርዓት መደላድል ይፈልጋል።
ሕዝብ ወዶና ፈቅዶ ኣብሮ ለመኖር ከወሰነ ኣንድ ሀገር መኖር የግድ ይላል። በኛ ተጨባጭ ሁኔታ ኢትዮጵያ ማለት ስለሆነ፣ ኣንድ ሀገር የሚለውን መልስ ኣገኘ ማለት ይሆናል። በኣንድ ሀገር ኢትዮጵያ ኣብሮ ለመኖር የወሰነ ሁሉ የኢትዮጵያ ዜጋ ሆነ ማለት ነው። ዜግነት ለማኅበረሰብ ፣ ለቡድን ፣ ለእምነት … ወ.ዘ.ተ. ሳይሆን የሚሰጠው ለግለሰብ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው እንደ ኣንድ ሕዝብ ሆነው ስለሚኖሩ ኣንድ ሕዝብ የሚለውን መልስ ኣገኘ ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያዊያን እንደ ኣንድ ሕዝብ የሚኖሩት ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መሥርተው እንደመሆኑ መለያቸው የሚሆን ዓለም ኣቀፍ እውቅና ያለው ሕጋዊ ሰንደቅ ዓላማ ይኖራቸዋል፣ በዚህም ኣንድ ሰንደቅ ዓላማ የሚለው መልስ ኣገኘ ማለት ነው። ፌደራላዊ መንግሥት የሥራ ወይም ኦፊሺያል ቋንቋ ያስፈልገዋል፣ እስከዛሬ የታወቀው የሥራ ቋንቋ ኣማርኛ ሲሆን ዛሬ በኢትዮጵያ ባለው ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ተጨማሪ ቋንቋ ማሰብ ይቻላል፣ በዚህም ሆነ በዚያ የሥራ ቋንቋ ይኖራል ማለት ነው።
በሕግ የተወሰነ ሥልጣን ኖሯቸው እራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ የፌደራል መንግሥት ኣባል ወይም ኣካል የሆኑ ኣሀዶች ይኖራሉ። እነዚህ ኣሀዶች በቋንቋቸው ይጠቀማሉ፣ በመላው የኢትዮጵያ ግዛት ክልል ሁሉ ሕጋዊ ተቀባይነት ካለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በተጨማሪ ኣሀዶች ያስፈልገናል ቢሉ ችግር ኣይታየኝም። ስለ ባንዲራ ኣጠቃቀም ስፖርትን ምሳሌ በማድረግ ግንዛቤዬን ላካፍል፣ የእግር ኳስ ተወዳዳሪዎች እውቅና ያለው የየክለባቸው ኣርማ ይኖራቸዋል ፣ ውድድር ለማድረግ ሜዳ ሲገናኙ የኣርማ ልውውጥ ያደርጋሉ ፤ የእግር ኳስ ክለቦች ኣርማ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ይታወቃል፤ የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ቡድን በዓለም ኣቀፍ ደረጃ ሲወዳደር ግን ይዞት የሚሄደው የየክለቦችን ኣርማ ሰብስቦ ሳይሆን ኣንድ ሀገራዊ ኣርማ ይዞ ነው። ኣንድ ሀገር፣ ኣንድ ሕዝብ ፣ ኣንድ ቋንቋ ፣ ኣንድ ሰንደቅ ዓላማ፣ ሊኖር የሚያስችል ሀሳብ ተነሳ እንጂ ሀሳቡ እውን ወይም ተግባራዊ የሚሆንበት መሰረት ግን ኣልተመለከተም።
ሕዝብ ፈቅዶና ፈልጐ በኣንድ ሀገር እንደ ኣንድ ሕዝብ የመግባቢያ ቋንቋ ኖሮት ኣንድ ሰንደቅ ዓላማ ኣንግቦ የሚኖረው ከሁሉም በፊትና በላይ ሁሉንም በነፃነትና በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል ፍትሓዊ እና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፣ የኤኮኖሚና የማኅበራዊ ሥርዓት መኖር ሲረጋገጥ ብቻ ነው። ይህ በሁሉም ተቀባይነት ያለው የፖለቲካ ሥርዓት የሕዝቡን ኣንድነትና እምነት ያጠናክራል፣ ተስፋና ሕልም ያለመልማል ፣ ዕድገትና ብልፅግና ያመጣል ፣ ዴሞክራሲን ያዳብራል ፣ በሕዝቦች መካከል ሰላምና መግባባት ይፈጥራል። ቋንቋ ፣ ባሕልና ሃይማኖት በኣንድ ሀገር ፖለቲካ ላይ የሚኖራቸው ሚና በጥሞና ሊታይ ይገባል። ኣንድ ቋንቋና ባሕል ባለበት ሀገር ሰላም ፣ ዕድገትና ዴሞክራሲ ጤናማ ነው፣ ብዙ ቋንቋና ባሕል ባለበት ሀገር ሰላም፣ ዕድገትና ዴሞክራሲ ይታወካል የሚል ኣባባል ይሰማል። የኣንድ ሀገር ሰላም፣ ዕድገትና ዴሞክራሲ ጤናማ መሆን ወይም መታወክ በቋንቋና ባሕል ማነስና መብዛት የሚወሰን ሳይሆን በነፃነትና በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት መኖር ኣለመኖር ነው። የኣንድ ቋንቋና ባሕል መኖር ለሰላም ፣ ለዕድገትና ለዴሞክራሲ ዋስትና መሆን ቢችል ኖሮ ለምሳሌ ኣንድ ቋንቋ ፣ ኣንድ ባሕልና ኣንድ ሃይማኖት ያላት ሱማሊያ ዛሬ የደረሰባት ችግር እና ሰቆቃ ባልተፈጠረባት ነበር፣ ሶማሊያም እንደ ሀገር በቀጠለች ነበር ፤ እንዲሁም ኣንድ ቋንቋ፣ ባሕልና ሃይማኖት ያለባት ሩዋንዳ በዘር ማፅዳት ጭፍጨፋ በመቶ ቀን ወደ ኣንድ ሚሊዮን የሚደርስ ሕይወት ባልተቀጠፈ ነበር። በኣንፃሩ ብዙ ቋንቋና ባሕል ለሰላም፣ ለዕድገትና ለዴሞክራሲ እንቅፋት ቢሆን ኖሮ ለምሳሌ ብዙ ቋንቋ በሚነገርባት ፣ ብዙ ባሕል በሚንፀባረቅባትና፣ ብዙ ሃይማኖት በሚሰበክባት ኣሜሪካ በሰላሟ፣ በዕድገቷ እና በዴሞክራሲዋ ላይ የከፋ ፈተና በተጋረጠባት ነበር።
ከዚህ መረዳት የሚቻለው ቋንቋ፣ ባሕል ፣ ሃይማኖት … ወ.ዘ.ተ. የየራሳቸው ውስን ግብዓት ሊኖራቸው ቢችልም ትልቁ ትኩረት መሆን ያለበት ሁሉም በነፃነት እና በእኩልነት ለመኖር ወደሚያስችል ፍትሓዊ እና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት መዘርጋቱ ላይ ነው። ይህ ከሆነ ለኣንድነት ጽኑ መሠረት የሆኑት የሕግ የበላይነት ፣ ነፃነት ፣ እኩልነት ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ያለ ልዩነት ለሁሉም በእኩልነት ተደራሽ መብቶች ይሆናሉ።
ኣቋም ሁለት ፡-
በኣንዲት ኢትዮጵያ በነፃነት፣ በእኩልነትና በዴሞክራሲ ኣብሮ መኖር ኣንድነቷ እና ሉዓላዊነቷ በተጠበቀባትና በተከበረባት ኢትዮጵያ ፍትሓዊ እና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት መስርቶ ኣብሮ መኖር የሚል ነው። የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነትና ወሳኝነት ተቀብሎ እና ኣክብሮ ፌደራላዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መስርቶ ፣ የጋራና የወል መብት ኣክብሮ በኢትዮጵያ ኣብሮ መኖር ይቻላል በሚል እምነትና ስምምነት ሦሥት የብሔር ድርጅቶች (የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ፣ የኣፋር ሕዝብ ፓርቲ ፣ የሲዳማ ኣርነት ንቅናቄ) እና ኣርበኞች ግንቦት ሰባት የኢትዮጵያ ኣገራዊ ንቅናቄ መሥርተው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ይህ ግንዛቤ የተወሰደው ሀገራዊ ንቅናቄው በየጊዜው በሚሰጠው መግለጫ ነው። (ስሕተት ከሆነ ይታረም)
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ በኢትዮጵያ ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ፣ ጠቃሚ መነሻ የፖለቲካ መፍትሔ ያቀረበ ፣ ደምህ ዴሜ ነው ብሎ የተቀጣጠለውን ትግል ኣንድነት እና ትብብር ያጠናከረ፣ በነፃነት፣ በእኩልነትና በዴሞክራሲ ኣብሮ ለመኖር በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ፍላጐት ያበረታታ ኣቋም ተደርጐ በሀገር ውስጥ ይነገራል። ከሕዝብ የታየው ድጋፍ ሀገራዊ ንቅናቄው ዓላማውን በስፋት እንዲያደርስ፣ ተመሳሳይና ተቀራራቢ ኣቋም ያላቸውን የንቅናቄው ኣካል እንዲያደርግ፣ የራቀ ኣቋም ያላቸውን ለማቅረብ እንዲጥር ተጨማሪ ኃይል ይሆናል የሚል ኣስተሳሰብ ይሰማል።
ኣቋም ሦሥት ፡-
ኦሮሞን ነፃ ለማውጣት ኢትዮጵያን ማፈራረስ ኣቋም ሦሥት ኢትዮጵያን በማፈራረስ ኦሮሚያን ነፃ ማውጣት የሚል ነው። ይህ ኣቋም የታወጀው በኦቦ ሊበን ዋቆ ሲሆን ኣቋሙ የግላቸው ብቻ ይሁን የፓርቲያቸውም ጭምር ግልፅ ኣይደለም። ያም ሆነ ይህ ኣቋሙ ኣንዱን ኣፍርሶ ሌላውን መገንባት ነው። ማፍረስ ከባድ ነው ምክንያቱም ሲያፈርሱ መፍረስ ኣለና። ኢትዮጵያን ማፈራረስ እኮ ኦሮሞን ማፈራረስ ነው የሚለው የህዝብ ብዛት እንጂልሽ ሆኗል ።
ኢትዮጵያ ፈርሳ ነፃ ትሁን የተባለችው ኦሮሚያ ኢትዮጵያን ከሁለት (ሰሜንና ደቡብ) ከፍላ ኢትዮጵያን መኃል ለመኃል ኣቆራርጣ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ተዘርግታለች፣ ኦሮሚያ ከትግራይ በቀር ከሁሉም ክልሎች ጋር በድንበር ትነካካለች ፣ ከዚህም የተነሳ ከኣንዳንድ ክልሎች ጋር ግጭት ውስጥ ናት ፣ ወያኔም ግጭቱ እንዲባባስ ማድረግ ያለበትን ሁሉ እያደረገ ነው። ዛሬ ከኦብነግና ከኦቦ ሊበን ደጋፊዎች በቀር ሁሉም ኢትዮጵያን የጋራ ቤታችን ናት፣ ለሁላችንም እንድትሆን ኣድርገን እናዋቅራት፣ እናደራጃት እያሉ ነው።
በዚህ ሁኔታ ነው ኢትዮጵያ ትፈራርስ፣ ኦሮሚያም ነፃ ትሁን የተባለው፤ ለመሆኑ ኦሮሞ የሰራውን ቤት ያፈርሳል ወይ? ይፍረስ የሚሉ ካሉ የጋራ ቤታችን ናት የሚሉት ዝም ብለው ይመለከታሉ ወይ? እንደታሰበው ተሳክቶ ኦሮሚያ ነፃ ብትሆን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ጋር በድንበር የምትነካካው ኦሮሚያ፣ ኢትዮጵያን መኃል ለመኃል ሰንጥቃ እንደ ወሽመጥ የገባችው ኦሮሚያ ፣ የሰራነውን ቤት ኣናፈርስም የሚል ኦሮሞ የሚኖርባት ኦሮሚያ ፣ የባሕል፣ የቋንቋና የኣካባቢ ልዩነት የሚታይባት ኦሮሚያ ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ኣሻራ ያላት ኦሮሚያ ፣ እስልምናና የኦሮሞ ብሔርተኝነት የተጣረዘባት ኦሮሚያ ፣ (ኣቶ ዩሱፍ ያሲን “ኢትዮጵያዊነት ፡ ኣሰባሳቢ ማንነት በኣንድ ሀገር ልጅነት” በሚለው መጽሓፋቸው ፈጣሪ ኣንድን ኦሮሞ የሚጠይቀው ለኦሮሞ ወንድምህ ምን ኣደረግክለት ብሎ ሳይሆን ለሙስሊሙ ወንድምህ ምን ኣደረግክለት ብሎ ነው ያሉትን ልብ ይሏል)፣ እንደ ኣንድ ነፃ ሀገር ትቀጥላለች ብሎ ማሰብ ይቻላል ወይ? የሚለው ሰከን ተብሎ ካልታየ ኢትዮጵያን ከማፈራረስ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ቂም፣ ጥላቻና እልቂት ከሚታሰበው በላይ ይሆናል።
ይህ የመከራ ደመና ወያኔ ለ25 ዓመታት ሊያሳካው ላልቻለው የመከፋፈል ሙከራ መልካም ገፀ-በረከት ይሆናል። የሱማሌ ፣ የኤርትራና የደቡብ ሱዳን ልኂቃን ዛሬ ሀገራችሁ ያለበትን ሁኔታ ዓለም ይገነዘባል። በሀገራችሁ ጉዳይ ላይ እንድትገቡ ምን ኣነሳሳችሁ? ምን ዓላማና ግብ ኣነገባችሁ? ወደ ሥልጣን ከወጣችሁ በኋላ ለሀገራችሁ ምን ለውጥ ኣመጣችሁ? ሕዝቡ ሰላምና ነፃነት፣ ልማትና እድገት ኣገኘ ወይ? በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስንት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተደረገ? ወይንስ በሕዝብ ስም ሥልጣን ላይ ቂብ ብላችሁ ድብቅ ኣላማችሁን እየፈፀማችሁ ነወይ? ለማንኛውም ጥቂት የኢትዮጵያ ልኂቃን እናንተ ወደ ኣለፋችሁበት መንገድ ልንገባ ነው እያሉ ነውና ቂጥኛም ከውርዴ እንደሚባለው ለነዚህ ልኂቃን ግፉበት ይቅርባችሁ የምትሉትን ልምድ ኣካፍሏቸው። ኣቋም ኣራት ፡- ትኩረት በልዩነት ትኩረት በልዩነት ኣቋም በልዩነት ላይ ያተኩራል ፣ ልዩነትን ያጐላል ፣ ያገናል ፤ ለምን በልዩነት ላይ እንደሚተኮር፣ ልዩነት ለምን እደሚጐላ እና እንደሚገን የተሰጠ ማብራሪያ ፣ የተቀመጠ ዓላማና ግብ የለም። ትኩረት በልዩነት ኣቋምን የሚያራምዱት የተወሰኑ የኦሮሞ ልኂቃን ሲሆኑ ኣጀንዳቸውም ኦሮሞና ከኦሮሞ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው።
እነዚህ ልኂቃን እየተሰባሰቡ በተለያየ ጊዜና በተለያየ መድረክ ስለ ኦሮሞና ከኦሮሞ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ መግለጫ፣ ትንታኔና ተረክ ያቀርባሉ። የሚያቀርቡትም እንደግለሰብ ሁነው ሳይሆን ተቋማዊ እና ድርጅታዊ ቁመና እንዳላቸው ሁነው ኣንድ ወጥ የጋራ ኣቋም ይዘው ነው። የተደራጁ ናቸው እንዳይባል ይፋ ስያሜ ወይም መጠሪያ ይኑራቸው ኣይኑራቸው የታወቀ ነገር የለም። በዚህ ሁኔታ እነሱን ከሌላው ትኩረት በልዩነት ኣቋምን ከማይደግፈው ኦሮሞ ለመለየት ሲባል በዚህ ጽሑፍ “የልዩነት ልኂቃን” ብሎ መጥራቱ ተመራጭ ሁኗል።
የልዩነት ልኂቃን መግለጫ፣ ትንታኔና ኣቋም በኦሮሞ ላይ ያተኮረ ሆኖ ኣቀራረባቸውም ፕሮፌሰራዊ ፣ ኣካዳሚያዊ ፣ ፍልስፍናዊ ፣ ፖለቲካዊና ፕሮፖጋንዳዊ ስለሆነ የግልፅነት፣ የተኣማኒነትና የሚዛናዊነት ጥያቄዎች ይነሳሉ። የልዩነት ልኂቃን ራዕይ ሰንቀው ፣ ዓላማና ግብ ኣስቀምጠው በይፋ ኣንደነ ኦቦ ሊበን ወደ ሕዝብ ስላልቀረቡ በይሆናል ኣስተያየት ከመስጠት ይልቅ ከሚያነሷቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል ኦሮሞ ብቻ ተበደለ ፣ የኦሮሞ ታሪክ ጠለሸ ፣ ኦሮሞ እንደ ቁመናው ተጠቃሚ ኣልሆነም እያሉ ትኩረት ሰጥተው በተደጋጋሚ የሚያነሷቸውን ሦሥት ጉዳዮች መመልከቱ የተሻለ ግንዛቤ ሊሰጥ ይችላል።
4.1 – ኦሮሞ ብቻ ተበደለ በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደት የተደረጉ ጦርነቶች በሃይማኖት ፣ በዘርና በኣካባቢ ላይ ያነጣጠሩ ሳይሆኑ ኣልገዛም ኣልገብርም ባሉ ላይ ሁሉ የተደረጉ ጦርነቶች ናቸው። ገዢዎች በልግዛ ላስገብር ፍላጐታቸው ላይ ከየትኛውም ኣቅጣጫ ፣ ከራሳቸው ቤተሰብ ጨምሮ ፣ በሚነሳባቸው ተቃውሞ ምንም ዓይነት ርህራሄ ኣይኖራቸውም ( በነገራችን ላይ ገዢዎች ለሥልጣናቸው ያሰጋሉ የሚሏቸውን ቤተሰቦቻቸውን በኣምባ ላይ ነው በጥበቃ የሚያኖሯቸው) በልግዛ ላስገብር በሚካሄደው ጦርነት የሚደርሰው እልቂት በደልና ሰቆቃ መጠን ኣልገብርም ኣልገዛም እምቢተኝነት ተቃውሞ ጥንካሬ ጋር የተያያዘ ነው። እምቢተኝነቱና ተቃውሞው ጠንካራና ረዥም ከሆነ የሚደርሰውም እልቂት በደልና ሰቆቃ ያንኑ ያህል የከፋ ነው። በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደት እልቂት ፣ በደልና ሰቆቃ በሁሉም ቦታ የደረሰ መሆኑ እየታወቀ ፣ የልዩነት ልኂቃን በሌላው የደረሰውን በመተው፣ የፈለጉትን በማጉላት ያልፈለጉትን በማንኳሰስ በኦሮሞ ላይ ብቻ ደረሰ ስለሚሉት ይናገራሉ ፣ ይጽፋሉ።
እንዲያውም በኣኖሌ የበደል መታሰቢያ ሓውልት እንዲቆም ተደርጓል። ኣቶ ጁነዲን ሳዶ ከሲሳይ ኣጌና ጋር በኣደረጉት ቃለ ምልልስ የኣኖሌ ሓውልት ትንሹ የበደል መግለጫ ነው ብለውታል። ኣቶ ጁነዲን ዛሬ የሚክዱት ፣ ትናንት ግን የሚያውቁትና የተወኑበት የወያኔ የእሳትና ጭድ ከፋፍለህ ግዛው የፖለቲካ ጨዋታ ሳይረሳ፣ ታሪክና እውነት ሳይጋነኑና ሳይንኳሰሱ እንደወረዱ መቀመጥ ይኖርባቸዋል። ሌሎቹ በደል ደረሰብን የሚሉ ሁሉ በየቦታቸው የበደል መታሰቢያ ሓውልት እናቁም ቢሉ ፣ ሀገራዊ መፍትሔ ካልታሰበ በቀር ኢትዮጵያ የበደል መታሰቢያ ሓውልት ሀገር ልትሆን ነው።
በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደት ስለደረሰ በደል ሲነሳ የኣንዱን ኣካባቢ ትቶ የሌላውን ነጥሎና ኣጉልቶ ማቅረቡ ብዙ ጥያቄ ያስነሳል። ለምሳሌ ሆዳቸው እየተቀደደ ካልተወለዱ ልጆቻቸው ጋር በየሜዳው የተጣሉት የደቡብ ኢትዮጵያ እናቶች ታሪክ ፣ እንደ እንስሳ ታርደው ቆዳቸው የተገፈፉት ደቂቀ እስጢፋኖሶች ታሪክ፣ በቴዎድሮስ ዘመን በጦርነት ከተማረኩ በኋላ በደባርቅ የተጨፈጨፉት ሰባት ሺህ ወታደሮች ታሪክ፣ ወደ ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የኦሮሞ ፍልሰት ጊዜ ስለተቆለለው ለቆጠራ ያታከተ የጭንቅላት ክምር ታሪክ በአህመድ ግራኝ የመልሶ የማስገበርና የመግዛት ጦርነት ግዜ ስለጠፋው ሕይወት ፣ ስለወደመው ንብረት፣ ስለደረሰው በደልና ሰቆቃ ታሪክ ፣አጼ ዮሐንስ በጎጃምና በወሎ ህዝብ ላይ ያደረሱት ጭፍጨፋ ያቃጠሉት ቤት ያነደዱት አዝመራ ታሪክ፤ አንዳንድ አባገዳዎች በሌሎች ላይ ያደረሱት እጅግ የከፋ ጭካኔ ታሪክ ከኦሮሞ እጅ፣ እግርና ጡት መቆረጥ ታሪክ ጋር ኣብሮ ቢቀርብ ኖሮ፤ እንዲሁም ኦሮሞ በወለጋ ከመስፈሩ በፊት የነበሩ ነዋሪዎች መፈናቀልና መሰደድ ታሪክ እና በኦሮሞ ፍልሰት ዘመን በየኣካባቢው የነዋሪዎች መፈናቀልና መሰደድ ታሪክ ከኦሮሞ ከፊንፊኔ መፈናቀልና መሰደድ ታሪክ ጋር ኣብሮ ቀርቦ ቢሆን ኖሮ የልዩነት ልኂቃን ኣባባልን ከኣድሏዊነትና ወገንተኛነት ባሻገር የተሟላ፣ ተኣማኒ፣ ሚዛናዊና ሙያዊ ባደረገው ነበር። በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ የመጨረሻው ምዕራፍ በተለይም ከዘመነ መሳፍንት ወዲህ በነበሩ ኣገዛዞች ኦሮሞ ተገለለ፣ ተገፋ ፣ ተገቢ ሥፍራውን ኣጣ ፣ የበታች ተደረገ የሚል ቅሬታ ከኣንዳንድ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ይቀርባል።
ፈላጭ ቆራጭ ኣምባገነኖች ባህሪያቸው ስላልሆነ በኦሮሞ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ዘረኛ ፖሊሲ እየተገበሩ ለሌላው ነፃነትና ዴሞክራሲ ፈቀዱ ብሎ ማሰብ የፖለቲካ የዋህነት ነው፣ ምክንያቱም ከዘረኛው ወያኔ በቀር ሌሎቹ ገዢዎች ሁሉንም በእኩልነት ደፍጥጠው ነው የገዙት። በየሰበብ ኣስባቡ ምክንያት እየመዘዙ ኦሮሞን ተገዥ ፣ ሌላውን ገዥ ኣድርጐ ለማቅረብ የሚደረገውን ትርፍ የለሽ የፖለቲካ ጨዋታ ባዶነት ለማሳየት ሀዘንሽ ቅጥ ኣጣ ከቤትሽ ኣልወጣ እንዳይሆን እንጂ ከትልቁ ራስ ዓሊ እስከ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ኣገዛዝ ድረስ ከቁንጮ እስከግርጌ የነበሩትን ባለሥልጣናት ማንነት፣ ሚናና ድርሻ መረጃ እየነቀሱ በዝርዝር ማቅረብ በተቻለ ነበር፣ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስላልሆነ እንጂ። በማኅበረሰብ፣ በቡድንና በግለሰብ ላይ የሚደርስ መገለል፣ መገፋት፣ ተገቢ ቦታን ማጣትና የበታች መደረግ የሕግ የበላይነት ፣ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት መፋለስ ውጤት በመሆኑ የተዛባው ሊስተካከል ይገባል። ግልፅ መሆን ያለበት የተዛባውን ማስተካከል ማለት ግን ሲገፋ የነበረው ይግፋ፣ ሲገለል የነበረው ያግልል ፣ የበታች የነበረው የበላይ ይሁን ማለት ኣይደለም ፤ ሰው ሁሉ እኩል በመሆኑ ሁሉም በነፃነትና በእኩልነት ይኑር ማለት ነው። ሕዝባዊነት የጐደላቸው ፖለቲከኞች በሕዝብ ስም ተነስተው ሕዝብን መናጆ ኣድርገው የፖለቲካ ጥሬ መለቃቀም የተለመደ ሆኗል። የምር ለሕዝብ የሚታሰብ ከሆነ የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነትና ወሳኝነት ተቀብሎ፣ በነፃነትና በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል የፖለቲካ ሥርዓት መሥርቶ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ጨዋታ መግባት ብቻ ነው፣ የእናቴ ቀሚስ ኣወላደፈኝ ሳይባል።
ይህ ካልሆነ በሀገርና በሕዝብ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለማሳየት ወያኔንና ኦነግን በምሳሌነት ወስዶ መመልከት ይቻላል። ከደርግ መውደቅ ጋር ተያይዞ ወያኔና ኦነግ ኢትዮጵያን እንግዛ ተባብለው ወደ ኣዲስ ኣበባ ሲመጡ እያንዳንዳቸው በየሕሊናቸው ያንሰላስሉ የነበረው ለዘመናት የሕዝብ ብሶት የሆነውን የዴሞክራሲ ጥያቄ መመለስ ሳይሆን ስለ ፖለቲካ ጥሬ ድርሻቸው ነበር። “… ሲሰርቁ ሳይሆን የሚጣሉት ሲከፋፈሉ ነው” እንደሚባለው ስለ ሽግግሩ ቻርተር መነጋገር እንደጀመሩ በፖለቲካ ጥሬ ድርሻ ተጣሉ ፣ ጉልቤው ወያኔ የፖለቲካ ጥሬውን ጠቅልሎ ወሰደ፣ ኣቅመ ቢሱ ኦነግ 30ሺህ ወታደሮቹን ገብሮ፣ በተለይ እወክለዋለሁ የሚለውን ኦሮሞ፣ በኣጠቃላይ ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለወያኔ ፋስ ዳርጐ በቦሌ ወደ ስደት ተመለሰ፣ በዚህም የሕዝብ የዘመናት ፖለቲካ መከራ እንዲሁም የወያኔ ኣገዛዝ እድሜ ተራዘመ። በዚህ ኣጋጣሚ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት የኣንዳንድ የኣማራ ፖለቲከኞች ኣቋምና ኣመለካከት ነው።
ኣንድ ኢትዮጵያ ማለታቸው መልካም ነገር ቢሆንም የኢትዮጵያ ብቸኛ ኣሳቢና ተቆርቋሪ ኣድርገው ራሳቸውን መመልከታቸውንና ድኅረ ወያኔ ኢትዮጵያ እነሱ በሚያስቡት መንገድ ብቻ ትዋቀር፣ ትደራጅና ትተዳደር ማለት ጠቃሚ ፖለቲካ ኣይደለም።
በነፃነትና በእኩልነት ኣብረን እንኖራለን የሚሉት ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በጋራ ቤታቸው ያገባቸዋል፣ የመፍትሔ ኣካልም ናቸው በማለት ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ ጋር በጋራ የጋራ ቤትን ለማደራጀት በቂ ትኩረትና ፍላጐት ኣለማሳየታቸው እነርሱም የሕዝብን የፖለቲካ ችግር እንዲሁም የወያኔን ኣገዛዝ ዕድሜ በማራዘም ትልቅ ድርሻ እያበረከቱ መሆናቸው ግልጽ ሊሆን ይገባል። በዚህም ሆነ በዚያ እራሳቸውን ከሀገርና ከሕዝብ በላይ ያደረጉ ፣ የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጐት ብቻ የሚያሳድዱ በታሪክም በትውልድም ተጠያቂ ናቸውና ወደ ሕሊናቸው ተመልሰው የሀገርና የሕዝብ ወገንተኛነታቸውን በማረጋገጥ ታላቅነታቸውን ያሳዩ።
4.2 – የኦሮሞ ታሪክ ጠለሸ ብዙ ሺህ ዓመታት የወሰደው የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ሂደትና ውጤት፤ በየጊዜውና በየኣቅጣጫው የተካሄደው የሕዝብ የውስጥ እንቅስቃሴ ወይም ፍልሰት ውጤትና ኣንድምታ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ከፈላጭ ቆራጭ ኣምባገነኖች የደረሰበት በደልና ሰቆቃ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈላጭ ቆራጭ ኣምባገነኖችን በላዩ ላይ ተሸክሞ እንኳን የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ለማስከበር ያሳየው ቁርጠኝነትና ጽናት፤ በውጭ ወራሪዎች ላይ ያሳየው ጀግንነት፣ የከፈለው መስዋእትነትና ያስመዘገበው ድል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመከራም ሆነ በደስታ ሕይወቱ ያዳበረው የጋራ ባሕል፣ ኣንድነት፣ ኣብሮነት፣ መግባባት ፣ ሥነልቦናና ኢትዮጵያዊ ማንነት ባጭሩ ኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያዊያን የጋራ ታሪክ መገለጫዎች ናቸው።
በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ሀገር ባለሙያዎች ጽፈዋል፣ ኣስተምረዋል፣ ቃለ ምልልስም ኣድርገዋል። ከእነዚህም መካከል በቅርቡ በኢሳት ቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ያደረጉት ዶ/ር ኃይሌ ላሬቦ ይገኙበታል። ዶ/ር ኃይሌ ላሬቦ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ከኢሳት ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ የኦሮሞን ታሪክ ኣጠልሽተዋል በማለት ዶ/ር ሕዝቅኤል ጋቢሳ ፣ ዶ/ር ኣባስ ሀጂ እና ኣቶ ኢታና ሀብቴ ቅሬታቸውንና ተቃውሟቸውን ኣሰምተዋል።
በተጨማሪ ዶ/ር ሕዝቅኤል ይቅርታ ካልተጠየቀ ብለው ማስፈራሪያ ሰጥተዋል። በዚህ ኣጋጣሚ የኣዲስ ኣበባ ማስተር ፕላን እንዳይተገበር እንቅፋት የሚሆኑትን ልክ እናስገባቸዋለን ያለው ኣባይ ፀሓዬ እንዲሁም ወልቃይቶች እኛ ኣማራ እንጂ ትግሬ ኣይደለንም ሲሉ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን ያለው ኣባይ ወልዱ ትዝ ኣሉኝ። ኣቶ ኢታና ሀብቴም ኢሳት የግንቦት 7 ልሳን ነው ብለዋል ፤ ያሉሽ ኣሉሽማ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ የእስላማዊ ኦሮሚያ መንግሥት ኣፈቀላጤ ፣ የሽብርተኞችና የኣክራሪዎች ልሳን ነው ይባላል እኮ።
ለኦሮሞ ታሪክ መጠልሸት እንደ ምክንያት የተነሱት ጦርነቱ ወደ 30 ደቂቃ ወረደ ፣ የሞተው ሰው ብዛት ወደ መቶዎች ዝቅ ኣለ የሚሉ ናቸው። ጦርነቱ 30 ደቂቃም ፈጀ 30 ዓመት ፤ በመቶዎች ሞቱ በሺህዎች የልግዛ ላስገብር ጦርነት ተካሂዷል ፤ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል ፣ በደልና እልቂት ደርሷል ስለሆነም መሠረታዊ ጉዳዩን ኣይለውጠውም። የመረጃ ግድፈት ካለ በመረጃ ማስተካከል እንጂ የስሜት ጦርነት ኣውጆ ነገሩን ማጋጋል ፋይዳው ግልፅ ኣይደለም።
የሁለቱም ውዝግብ መስተናገድ የነበረበት ዳኝነትን ለተመልካች እና ለኣድማጭ ትቶ በማንነት ላይ በማነጣጠር ሳይሆን በመረጃና በሙያዊ ሥነምግባር መሠረት ሊሆን ይገባል።
ታሪክ በተለያዩ ሰዎች ሊጻፍ ይችላል። የታሪክ ባለሙያዎች በመካከላቸው የእውቀትና የምርምር ብቃት ልዩነት ቢኖርም ጽሑፋቸው ከሞላ ጐደል በመረጃ ላይ ይመሰረታል ፤ ለፖለቲከኞች ታሪክ መጻፍ ማለት የራሳቸውን ፍላጐት ፣ ምኞትና ድብቅ ኣጀንዳ የሆነውን ጉዳያቸውን በሕዝብ ስም ደርሰው መልሰው ሕዝብ ላይ መጫን ማለት ነው። ከዚህ የተነሳ እውነትነትና ሚዛናዊነት ፖለቲከኞችን ብዙም ኣያስጨንቅም። እንደፈለጉ ያጋንኑታል ፣ ያሳንሱታል ፣ ይንዱታል ፣ ጥላሸት ይቀቡታል ፣ ያንሸዋርሩታል። የንጉሡን የዕለት ውሎ በመከታተል የሚጻፍ ታሪክ ይዘቱ በዋናነት ከንጉሡና ከሥርዓቱ ፍላጐት ውጭ ኣይሆንም። ልብ ወለድ ታሪክ የሚጽፉም ኣሉ፣ ተግባራቸውም እንደሚፈለገው ታሪክን ኳኩለውና ኣስውበው (በኮለኔሉ የተጻፈው የመለስ ታሪክ) ኣንኳሰውና ኣጠልሽተው በመጻፍ ክፍያቸውን መውሰድ ብቻ ነው። የወያኔ ታሪክ ፀሓፊዎች ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው።
ዶ/ር ኃይሌ ላሬቦና በዶ/ር ኃይሌ ላሬቦ ቃለ መጠይቅ ላይ ተቃውሞ ያቀረቡ ምሁራን እራሳቸውን ከየትኛው የታሪክ ጸሓፊ ጋር እንደሚመድቡ ራሳቸውን ይጠይቁ። በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እንደ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ ኦሮሞም የራሱ ኣሻራ ፣ ያውም ትልቅ ፣ ኣለው። ይህን ኣሻራ መሰረዝ መደለዝ ፣ መፋቅ ወይም ኣለመቀበል የኢትዮጵያን ታሪክ መካድ ብቻ ሳይሆን ራስንም መካድ ነው። በዚህም የሚደፋ ዘውድና የሚለቀም የፖለቲካ ጥሬ ኣይኖርም። የማንኛውንም ማኅበረሰብ የታሪክ ኣሻራ መፋቅ የኢትዮጵያን ታሪክ ማጠልሸት ነው። ጥላሸቱንም የማንሳት ኃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት እና ግዴታ ነው።
4.3 – ኦሮሞ እንደ ቁመናው ተጠቃሚ ኣልሆነም እንደ ቁመና ተጠቃሚ መሆን ምን ማለት ይሆን? መለኪያና መስፈርቱስ ምንድን ነው? ግልጽ ባለመሆኑ ከልዩነት ልኂቃን ጀርባ ያለውን ለማወቅ በይሆናል ከመዳከር ዛሬ ወያኔ በምን ቁመናው በኢትዮጵያ ላይ ብቸኛ ተጠቃሚ ለመሆን ቻለ የሚለውን መመልከቱ በልዩነት ልኂቃን ኣእምሮ የሚርመሰመሰውን ለመረዳት ያግዝ ይሆናል። ወያኔ በቁጥር(ብዛት) ቁመና ብቸኛ ተጠቃሚ ሆነ እንዳይባል እወክለዋለሁ የሚለው 5% የሆነው ማኅበረሰብ ይህን ቁመና የመፍጠር ኣቅም የለውም ፤ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በነፃና ፍትሓዊ ምርጫ ቁመና ብቸኛ ተጠቃሚ ሆነ እንዳይባል በዝረራ የተሸነፈበት የ1997 ምርጫ ቋሚ ምስክር ነው ፤ ወያኔን ብቸኛ ተጠቃሚ ያደረገው ቁመና ወታደራዊ የበላይነቱ ብቻ ነው።
ወታደራዊ ቁመናው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰጥ ለጥ ኣድርጐ ለመግዛት ኣስችሎታል። ኦሮሞን በየትኛው ቁመና ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቧል? ቁጥሩ (ብዛቱ) ወደ 35% ስለደረሰ 35% የፖለቲካ ፣ የማህበራዊና ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በኮታ ይገባዋል ማለት ይሆን? በምርጫም ቢሆን 35% ስለሚያገኝ 35% ተጠቃሚነቱ ይጠበቃል ማለት ይሆን? (መራጭ ግለሰብ እንጂ ማኅበረሰብ በጅምላ እንዳልሆነ ይታወቅ) ቀሪው ቁመና ወታደራዊ የበላይነት ሲሆን በዚህ ረገድ ምን ዓይነት ዝግጁነት ይኖር ይሆን? የልዩነት ልኂቃን ኦሮሞን ብቸኛ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችለው ቁመና ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ እንደሆነ እንቅስቃሴያቸው ኣመላካች ነው። ከወያኔ በኋላ ተራው የኦሮሞ ነው በሚል ይመስላል የልዩነት ልኂቃን ወያኔ ወደ ሥልጣን ለመውጣት ያደረጋቸውን ሁሉ እየተገበሩ ነው። እንደውም ወያኔ የኦሮሞን የመግዛት ልብ ያንጠለጠለ መስሎት በአንድ በኩል አዎን ቀጥሎ የመግዛት ተራ የኦሮሞ ነው ፣ ኢትዮጵያን ተከፋፍለን እንገዛለን እያለ በሌላ በኩል ሰጥ ለበጥ ብለው አልገዛም ያሉት ማረን ፣ አትሂድብን፣ አንተው ግዛን የሚሉት መስሎት ሥጋትና ጭንቅ ውስጥ ለማስገባት ለኦሮሞ አስረክቤአችሁ እሄዳለሁ በማለት ግራ ቀኙን በማተራመስ ላይ ነው ፤ በአዲስ አበባ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም አጀንዳ ሤራ እና ብሔረሰቦችን በድንበር እና በመሬት በማጋጨት ተንኮል በደምህ ደሜ ነው ፀረ ወያኔ ሕዝባዊ ትግል ወደ መቃብር የገባበትን እሳትና ጭድ ከፋፍለህ ግዛው ያፖለቲካ ጨዋታን ነፍስ ዘርቶና በጥልቀት አድሶ ለመመለስ በመሯሯጥ ላይ ነው።
ወያኔ አልሞትኩም ብየ አልዋሽም ሆነብህ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ ፤ ምንም አደረክ ምን እንደማይሳካልህ ደምህ ደሜ ነው ቃል ኪዳን ከወያኔ እና ከእባብ ቀድሞ ወያኔን እንደሆነ እየመረረህም ቢሆን አውቀኸዋል ፤ የሚበጅህ ከወያኔነት ወደ ኢትዮጵያዊነት ተመልሰህ ከህዝብ ጋር መሆን ነው ። የወያኔ መንገድ ለራሱ ለወያኔም ኣልጠቀመውም፤ ዘረኝነት፣ ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት ወደ ገደል ኣፋፍ ኣድርሰውታል፤ እድሜውን ያራዘመ መስሎት ኣሁንም ጭፍጨፋውን ቀጥሏል፤ ዛሬ የሚያፈሰው ደም ነገ በይፋ ይፋረደዋል። የልዩነት ልኂቃንም ይህን ሁሉ እያዩ የወያኔን መንገድ ምርጫቸው ካደረጉ የሚጠብቃቸውም ግልፅ ነው። ለማንኛውም እያደረጉ ያሉትን እንመልከት ፤ ወያኔ በመጀመሪያ የወያኔን የነፃነት ቻርተር (ዘረኝነት) ፃፈ ፤ የልዩነት ልኂቃንም የኦሮሞን የነፃነት ቻርተር በመጻፍ ላይ ናቸው ፣ ይዘቱ ቻርተሩ ተጽፎ ሲያልቅ ይታወቃል። ወያኔ ከጐንደር፣ ከወሎና ከኣፋር መሬት ቦጭቆ የወያኔን ካርታ ሰራ ፤ የልዩነት ልኂቃንም የኦሮሞን ካርታ እያዘጋጁ ነው ይባላል፤ ኦሮሚያ ከትግራይ በቀር ከሌሎች ክልሎች ጋር በድንበር ተነካኪ በመሆኑ እንዲሁም ጐጃምና ወሎ ኦሮሞ ናቸው የሚለው ኣባባል በካርታ ዝግጅቱ ላይ የሚኖረው እንደምታ ከዝግጅቱ በኋላ የሚታወቅ ይሆናል።
ወያኔ ወልቃይቴን ትግሬ እንጂ ኣማራ ኣይደለም በማለት ማንነትን የመወሰን ሥልጣን ወሰደ ፤ የልዩነት ልኂቃንም ዲባባ ሁሉ ኦሮሞ ኣይደለም (ደጀኔ ጉተማ ፣ ጃዋር ሞሓመድ፣ ጸጋዬ ኣራርሳ በኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ) ይህ ኣባባል የኦሮሞ ማንነትን ግለሰቡ ሳይሆን እንደ ወያኔ የሚወስን የልዩነት ልኂቃን ኃይል ይኖራል ማለት ነው። ወያኔ ትግሬ የሆነው ሁሉ ማሰብ ያለበት እንደ ወያኔ እንጂ እንደ ኢትዮጵያዊ ኣይደለም ብሎ ትግሬን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን እንደለየው የልዩነት ልኂቃንም ኦሮሞ እንደ ኦሮሞ እንጂ እንደ ኢትዮጵያዊ እንዳያስብ በየመድረኩ ኦሮሞና ኦሮሞነትን ብቻ ማፋፋም እና ማጥመቅን ተያይዞታል። የልዩነት ልኂቃን ሁለት ያልፈፀሟቸው ጉዳዮች ቀርተዋል ኣንዱ ወያኔን ለሥልጣን ያበቃው ዓይነት ወታደራዊ ኃይል ማዘጋጀት ሲሆን ሌላው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ተቋማትን በመዝረፍ ሀብት ኣከማችቶ ወደ ኢንዶውመትመለወጥ።
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ምን እየታሰበ እንደሆነ ግልፅ ማድረግ ይችላሉ። ኣንድ የኦሮሞ ኣክቲቪስት የልዩነት ልኂቃን እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን እንዳሳሰበ ተረድቷል መሰል ከመሳይ መኮንን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ኦሮሞ ፈፅሞ ኣይገነጠልም ፤ ኣሁን ቤቱን እያደራጀ ነው ፤ ኣደራጅቶ ሲጨርስ ሁሉንም ይጋብዛል በማለት ለማረጋጋት ሞክሯል። (ውድ አክቲቪስት፡ እንያ ህይወታችሁን የታደጉዋችሁ እናት ከመሞታቸው በፊት ነገሩኝ ያልከው ማተብህ ይሁን) ነገር ግን የጋራ ቤት መሰራት ያለበት በጋራ ነው እንጂ ኣንዱ ሠሪ ሌላው ተመልካች ፣ ኣንዱ ጋባዥ ሌላው ተጋባዥ መሆን የለበትም።
ሰማንያ ኣምስት የነፃነት ቻርተር ጽፎ ፤ ሰማንያ ኣምስት ካርታ ኣዘጋጅቶ ፤ እነዚህን ኣገጣጥሞ ኢትዮጵያን እንመሰርታለን ከሆነ ሃሳቡ የኣቶ ዩሱፍ ያሲን “ኢትዮጵያዊነት ፤ ኣሰባሳቢ ማንነት ባንድ ኣገር ልጅነት” ሙጫ (ኢትዮጵያዊ ዜግነት ሙጫ) ያልተጣበቀ ሀገር መልሶ የእንቧይ ካብ መሆኑ ኣይቀርም። ድብቅ ኣጀንዳ የሌላቸው እና በራሳቸው የተማመኑ ከላይ ከኣንድ እስከ ሦሥት ኣቋማቸውን በይፋ የገለፁ የፖለቲካ ኃይሎች ለሕዝብ ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን ኣቋም ሕዝብ ይፍረድ ብለው በልበ ሙሉነት በይፋ ኣቅርበዋል።
እናንተም የልዩነት ልኂቃን ሕዝብ ይፍረድ የምትሉ ከሆነ ኦሮሞ በደሉ የሚካስበትን ፣ የጠለሸው ታሪኩ የሚፀዳበትን እና እንደቁመናው ተጠቃሚ የሚሆንበትን እቅድ ኣቅርቡለት ፣ የወደፊት ሕይወቱን የሚመራበትን ዓላማና ግብ ኣስቀምጡለት። የፖለቲካ ድርጅቶችና ልኂቃን ትልቁ ፈተና የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነትና ወሳኝነት ኣለመቀበል ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጐት መልሰው በሕዝብ ላይ መጫናቸው ነው።
ይኼን ሁሉ ተሻግሮ ከሕዝብ በላይ ዳኛ የለም ብሎ ሃሳብን በይፋ ማቅረብ ከተቻለ ለድብቅ የፖለቲካ ኣጀንዳ ስኬት ሕዝብ ወደማያባራ እልቂት ፣ በደልና ሰቆቃ ኣይማገድም ማለት ነው። ግድያ ፣ እስራት ፣ ደብዛ ማጥፋት ፣ በደልና ሰቆቃ በሀገር ውስጥ ያለ ቢሆንም የሀገር ቤቱ ስቃይ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ስቃይ ጭምር ነውና የምታደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ነፃነትን የሚያቀርብ ስቃይን የሚያርቅ ሊሆን ይገባል። ከላይ የተጠቀሱትን በቅንነት ማድረግ ከተቻለ ተጠቃሚው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጐጂው ወያኔ ስለመሆኑ ብዥታ ሊኖር ኣይገባም።
ከመቶ ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ የሚኖርባት አገር ኢትዮጵያ ፣ ወደ ሰማንያ ኣምስት ብሔረሰቦችን ያቀፈች አገር ኢትዮጵያ ፣ ወደብ ኣልባ ትልቅና ታላቅ አገር ኢትዮጵያ ፤ የግብፅና የሱዳን ሕልውና መሠረት ዓባይ ወንዝ መነሻ አገር ኢትዮጵያ ፤ ውስብስብ እና ያልተረጋጋ ፖለቲካ የሚታይበት የኣፍሪካ ቀንድ ኣካል አገር ኢትዮጵያ ፤ ከስድስት ሀገሮች የተጐራበተች አገር ኢትዮጵያ ፤ የአፍሪካ ህብረት መዲና የሆነች አገር ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢና ከዚያም ያለፈና የተሻገረ የጂኦ- ፖለቲካ ውዝግብ ትኩረት ሆናለች። ያንዣበበባትን የጂኦ-ፖለቲካ ፈተና ለማለፍ በጥሞና የታሰበበትና በጥልቀት የተጠና የውጪ ግንኙነት የፖለቲካ ስትራቴጂ ነድፎ በጥንቃቄ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፣ በብቃት ለመሻገርም ኢትዮጵያን ለዘመናት ያመሳትን፣ ዛሬም እልባት ያልተገኘለትን፣ ኢትዮጵያን ለማዳከምና ሕዝቦችን ለማበጣበጥ የኣካባቢና ሌሎች ተዋንያን እንደ ቤንዚን የሚያርከፈክፉትን የውስጥ የፖለቲካ ጥያቄ ለሁሉም በሚያመች መንገድ መፍታቱ እጅግ ኣስፈላጊ ነው።
የሁሉም ማኅበረሰብ ፖለቲከኞች የወቅቱ ትልቁ ፈተና የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ጥያቄ መፍታት መቻል ኣለመቻል ነው። ኢትዮጵያን፣ በየማኅበረሰባችን የዘውድ መድፊያ ዙፋን ያገኘን መስሎን፣ ወደ ትናንሽ መንደር ብንበጣጥሳት የበጣጠስነው ኃይላችንን ፣ ጉልበታችንንና ታላቅነታችንን ስለሆነ ኣቅመ ቢስ ሆነን በኣካባቢ እና በሌሎች ተዋንያን እንሰለቀጣለን። የየማኅበረሰቡ ፖለቲከኞች ከግለሰብና ከቡድን ፍላጐት በላይ ተሻግረን ለሀገርና ለሕዝብ ፍላጐት ቅድሚያ ሰጥተን የሚቃጣብንን የውጭ ጥቃት በጋራ እንቋቋማለን የሚል እምነት ኣለኝ ፣ ካልሆነ ለማንኛቸንም ኣይበጅ።
5.ማጠቃለያ
ፀረ ወያኔ ትግል በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር እየተካሄደ ነው፣ የሀገር ውስጥ ትግል ተስፋፍቷል ፣ ሀገራዊ ሆኗል ፣ በደምና በኣጥንት የኢትዮጵያ የነፃነት ቻርተር ተጽፏል ፣ በድኅረ ወያኔ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስርተው በእኩልነትና በነፃነት ኢትዮጵያን የጋራ ቤታቸው ለማድረግ ያላቸውን ፍላጐት ገልፀዋል ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ላሉ የፖለቲካ ኣክቲቪስቶች፣ ድርጅቶች ፣ ኃይሎችና የነፃነት ኣርበኞች ተባባሪ ደጋፊና ኣጋር እንዲሆኗቸው ጥሪ ኣድርገዋል። በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በነፃነት ኣርበኞች መካከል ቅንጅት፣ ትብብርና መደጋገፍ ኣለ። በኣክቲቪስቶች በፖለቲካ ድርጅቶች እና ኃይሎች መካከል በወደፊቷ ኢትዮጵያ ላይ ልዩነት ቢታይም ወያኔን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ግን ተመሳሳይ ኣቋም ይታያል።
የሀገር ውስጡ ትግል ሀገራዊ ባሕሪ ቢይዝም የድርጅትና የኣመራር ድጋፍ ይፈልጋል። ኣሁንም ትግሉ በተደራጀና በተቀናጀ ኣመራር ሳይሆን በተበታተነ መልኩ በጐበዝ ኣለቃ ይመራል ፣ በቂ ትጥቅና ስንቅ ይፈልጋል ይህን ሁሉ የሚያደራጅ የሚመራና የሚያንቀሳቅስ ኣካል ያስፈልጋል። ልኂቃን በየራሳቸው ያለውን ፍላጐት ትተው የሕዝብን ትግል ለማደራጀት ለማጠናከርና ለመምራት ሙሉ ኃላፊነት መውሰድ ይኖርባቸዋል። ከመነሻው ይኼን ማድረግ ካልተቻለ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ትግሉም ኣላማውን ሊስት ይችላል። ኢትዮጵያዊያን እስክ ዛሬ በደል የደረሰባቸው በገዢዎች ነው።
ኢትዮጵያዊያን እስከ ኣሁን ድረስ በዘር ፣ በሃይማኖት ፣ በመሬት ብቻ …. ግጭት ኣድርገው ኣያውቁም። በሕዝቦች መካከል ግጭት የተጀመረውና እየተስፋፋ የመጣው በወያኔ ኣገዛዝ ነው። ግጭቱም እንዲስፋፋ ወያኔ ኣስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ነው። ሕዝቦች በገዢዎች የሚደርስባቸውን በደል በጋራ ትግል ማስወገድ ይችላሉ። በሕዝቦች መካከል በሚደረግ ግጭት ተያይዞ የሚመጣ ችግር ግን ለመገመት የሚያስቸግር እጅግ የከፋ ነው። ለማስቆም ቢቻልም እጅግ ኣስከፊና ዘግናኝ ዋጋ ኣስከፍሎ ነው። ለዚህም ነው ወደ ሕዝብ ለሕዝብ ግጭት የሚያመሩ ሁኔታዎች እንዳይበቅሉ ፣ እንዳያድጉና እንዳይሰራጩ ብርቱ ጥረት መደረግ ያለበት። ልኂቃን በዚህ ጉዳይ ላይ ልዩ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ምክንያቱም ከተሰራጨ ጐርፍ ነው ፣ ሰደድ እሳት ነው ፣ ሁሉንም ጠራርጎ ይወስዳል ይለበልባል።
ዛሬ በየመን፣ በደቡብ ሱዳንና በሱማሊያ የሚታየው ችግር ሕዝብ በሰላም እና በነፃነት መኖር ያልቻለበት ፣ ሕፃናት እናቶች እና ኣባቶች በጥይት ፣ በረሀብ እና በበሽታ የሚረግፉበትና የሚሰቃዩበት ከሥልጣን ሽሚያ ጋር ተያይዞ በመጣ ጣጣ ነው። የሥልጣን ተቀናቃኞች ከመሳሪያ ትግል ኣሳልፈው ወደ ዘር ግጭት ስላሸጋገሩት አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ ተፈጥሮአል። ሳይማር ያስተማረ ወላጅ ዳቦ፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ሲመኝ የተረፈው መከራና ሰቆቃ ነው። የህዝብና የስልጣን ተቀናቃኞች ፍላጎት ተጣጥሞ ቢሆን ኖሮ የህዝብን የስልጣን ባለቤትነትና ወሳኝነት ተቀብሎ በነፃና ፍትሀዊ ምርጫ ለስልጣን በቅቶ የተፈለገውን ሰላም፣ እድገት እና ዲሞክራሲ ለህዝብ ማበርከት በተቻለ ነበር። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቀናቃኞች በየመን በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን እየደረሰ ያለው ኢትዮጵያን እንዳይገጥማት መነሻቹህ የራሳችሁ ሳይሆን የህዝብ ፍላጎት ሊሆን ይገባል።
ሰው የሚያጭደው የዘራውን ነው። ጥላቻን ፣ ቂም በቀልን፣ ዘረኝነትን፣ ልዩነትን፣ ስግብግብነትን፣ ራስ ወዳድነትን የሚዘራ የሚያጭደው እልቂትን ፣ በደልንና ሰቆቃን እንጂ ሠላምና ነፃነትን፣ እድገትና ብልፅግናን፣ ዴሞክራሲያዊ ባሕልን ኣይደለም። እኛ ኢትዮጵያዊያን መማር ከፈለግን ዓለም ሁሉ የመማሪያ መድረክ ነው። የምናጭደውም የዘራነውን ነው።
እንደ ደቡብ ሱዳን ሶማሊያ እና ሶሪያ እንሁን ካልን ምን መዝራት እንዳለብን ግልፅ ነው። በሌሎች የደረሰው መከራ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እንዲደርስ ኣንፈልግም የምንል ከሆነ ፣ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትን እና ወሳኝነትን እንቀበላለን የምንል ከሆነ ፣ ኢትዮጵያ በልፅጋ ማየት የምንፈልግ ከሆነ ፣ ኢትዮጵያዊያን በሰላም እና በነፃነት በእኩልነት እንዲኖሩ የምንፈልግ ከሆነ ፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያዊያን በሀገር ውስጥ የመሰረቱት ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ የፈጠረው ኣጋጣሚ እንደ 1966 ታሪካዊ ኣጋጣሚ ኣይመክንም ፣ ኣይሰናከልም፣ ኣይከሽፍም የምንል ከሆነ፣ ከወያኔ በኋላ የመግዛቱ ተራ የኛ ነው ከሚል ቅዠት የምንወጣ ከሆነ ፣ በደልና ሰቆቃ በቢሾፍቱ ኢሬቻ በዓል ጭፍጨፋ ይብቃ የምንል ከሆነ፣ ዘውዳቸን ከኪሳችን ፣ የፖለቲካ ጥሬያችን ከሕሊናችን እናውጣ ፣ ልዩነትን ማጉላትና ማግነን እናቁም፣ ከታሪክ እስረኛነት እንውጣ፣ የጋራ ታሪካችን እንደወረደ ተቀብለን በክብር እናስቀምጥ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሓዊ ሥርዓት መስርተን በነፃነት እና በእኩልነት በጋራ የምንኖርበት ኢትዮጵያን ለመመስረት ወደሚያስችለን ምክክርና ውይይት እንግባ። ይህን ማድረግ ካልቻልን ኣሸናፊም ተሸናፊም ኣይኖርም፣ ነፃነትም ሰላምም ኣይኖርም፣ የሚኖረው የማያባራ እልቂት እና ሰቆቃ ነው።
ልኂቃን ቢያንስ ለመጡበት ማኅበረሰብ ደህንነት ያስባሉ፣ የመጡበት ማኅበረሰብ ሰላም የሚያገኘው ሌላውም ማኅበረሰብ ሰላም ሲያገኝ ብቻ መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ነው።
አዲስ ጀምበር