/ያሬድ ከፍያለው/
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማያም ደሳለኝ ስልጣን በያዙ ሰሞን በተከታታይ መስዋዓት ለመሆን መዘጋጀታቸውን ይገልጹ እንደነበር አስታውሳለሁ። አሁንም አልፎ አልፎ ሲናገሩት ይሰማል። እኛ ደግሞ እሳቸውም ሆነ ሌሎች የህወሀት ፈረሶች በሚሊዮን ብሮች በሚሸጥ V8 ተሽከርካሪ እየተንቀሳቀሱ፣ ሚሊዮን ብሮች እየከፈሉ ልጆቻቸውን በውጭ ሃገራት እያስተማሩ እንዲሁም ሆድ ቁርጠት ሲያማቸው በህዝብ ገንዘብ አውሮፓ ለህክምና እየተሄዱ ምንድን ነው መስዋዓትነት እያልን ሲገርመን ነበር። ነገሩ የገባን ዘግይቶ ነው። ለካ መስዋዓትነት የሚባለው በህወሃትን ፖለቲካ ቁማር ሰለባ መሆን ኖሮአል። በቅርቡ የህወሀት መንግስት በዘረፋ ላይ ተሰማርተዋል በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር አዋልኳቸው ያላቸውን የመንግስት ባለስልጣናትና የክፍል ሃላፊዎች፣ ደላሎችና ነጋዴዎች ቁጥር በቀናት ልዩነቶች እየቆጠበ ሲነግረን ተመልክተናል። የሚሰጡ መግለጫዎች እርስ በእርስ የሚጣረሱ መሆናቸውን ስናይ ሚስጥሩ ምን ይሆን የሚል ጥርጣሬ ይሰፍርብናል።
በመጀመርያ ደረጃ በቀናት ልዩነት ሰዎችን በቡድን በቡድን ተጠያቂ ማድረጉ ለምን አስፈለገ፣ ሁለተኛ መንግስት ለዓመታት በከፍተኛ አመራሬ ውስጥ ሙስና እንዳለ መረጃ አለኝ ማስረጃ ግን የለኝም ሲል ለዓመታት ቆይቶ አሁን አንበሳ መሆኑ ምን ተገኝቶ ነው። ሶስተኛ በመጀመሪያው ቀን ጋዜጣዊ መግለጫ የክፍል ሀላፊ ዳይሬክተሮች እንጂ ሚኒስትሮች ሙስና ውስጥ የሚገቡበት እድል የለም ተብሎ በቀጣይ ሶስት ሹመኛ ከፍተኛ አመራሮች መታሰራቸው የጥርጣሬያችን ምንጮች ናቸው። የሀገሪቱ የሙስና ደረጃ ላይ ከሚሰጡ ትንተናዎች እንደምናየው በስኳር ኮርፖሬሽን የሀብት ብክነት ውስጥ ከአቶ አባይ ጸሀዬ ቀድሞ ተጠያቂ ሊሆን የሚገባ ሰው እንደሌለ እንረዳለን። እሳቸው ብቻ ሳይሆን ሚስታቸውም የተነከረችበት ጉዳይ ነው። ሆኖም ምክትል ዳይሬክተሮች ሰለባ ሆነዋል። የእስሩ መለኪያ ምን ይሆን?
በዚህ ጽሁፍ አቅራቢ እምነት የህወሀት መንግስት የሀገሪቱ ሁሉም ባለስልጣናት የሌብነት ዓይነትና መጠን የያዘ ዝርዝር ቀደም ብሎ ያለው መሆኑን ነው። ህወሀት ዝርዝሩ እንዲዘጋጅ ያደረውና አሰባስቦ ያስቀመጠው ሙስናን ለመከላከል ካለ ጽኑ ፍላጎት ሳይሆን አፈንጋጮችን ለመምታት አሊያም እንደ ሰሞኑ ባለስልጣናት በእሳት ማጥፊያነት ለመወርወር ሰበብ ፍለጋ መሆኑ ካለፉት ስራዎቹ በመነሳት መናገር ይቻላል። ዝርዝሩ ቢታሰሩ በህውሃት ስርዓት ላይ የሚያስከትሉት ጥቅምና ጉዳት ከግምት ያስገባ ትንተናም የያዘ እንደሚሆን የህውሃትን የሸፍጥ ስራዎችን የገመገመ ዜጋ ለመረዳት አያዳግተውም። ህወሀት የቅርብ ፈረሶቹንም የሚጠራጠር ድርጅት በመሆኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝም የተዘጋጀ ወጥመድ እንደሚኖረው አያጠራጥርም። የደቡብ ክልል ካለው ሶሽዮ ፖለቲካ ሁኔታ አንጻር ህወሃት ከደህዴን በኩል የሚመጡ ሰዎች ላይ ጥገና ለመሆን የሚገደድበት ሁኔታ የለም። ደህዴን እንደ ኦህዴድ በተተኪ ታማኝ ሰዎች እጥረት የተመታ ድርጅት እይደለም። ይሀ ደግሞ ከሰዎቹ ልዩ ባህርይ የመጣ አይደለም። በደቡብ ክልል ያለው ሶሽዮ ፖለቲካል ሁኔታ የፈጠረው መልካም አጋጣሚ እንጂ። ምናልባት ልዩነቱ አመራር ቢቀየር የታዛዥነት መጠን መለያየት ብቻ ይሆናል። ብአዴንም በተመሳሳይ የተሻለ የታማኝ ሰዎች ምንጭ ነው። ከኦህዴድ ሲነጻጸር። ስለዚህ አቶ ህይለማርያም ትርፍና ኪሳራቸው ሲሰላ ከኦህዴድ እና ብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ያነሰ ኪሳራ የሚያመጡ ሰው ናቸው።
ስለዚህ አቶ ሀይለማርያም የሚነገራቸውን ካልሰሙ ወይም የህውሃትን የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት ለማስተጓጎል ከሞከሩ የህወሀት ጥርስ ውስጥ የመግባት እድላቸው ሰፊ ነው። በቀላሉ በሌላ ይተካሉ። እንደ ኦህዴድ ሲቀጥልም እንደ ብኣዴን ሰዎች እየተቆጣና እየመከረ ከሳቸው ጋር የሚቆይበት አንዳች ምክንያት እይኖርም። ከአባዱላ ገመዳ ወይም ሁሉም የኦህዴድ እና ብአዴን ስራ አስፈጻሚዎች ጋር ሲነጻጸር እሳቸው ለመጠቃት ቅርብ ናቸው። ትንሽ ያለመታዘዝ ከታየባቸው የከፍተኛ ሙስና ዶክመንተሪ ፊልም ተዘጋጅቶላቸው ሊወረወሩ ይችላሉ። ትንሽ እንኳን የህዝቡን ጩሀት ካረገበ በሚል። ከሆነ የሚሆነው እንዲህ ነው። ህወሀት በራሳቸው ክልላዊ ድርጅት በኩል ይመጣባቸዋል። ውክልናቸውን ያስነሳል። ከዛ ቀሪውን ስራ እሱ ይሰራል። የዚህን ያህል ምስኪን ሰው ናቸው፤ አቶ ሀይለማርያም።