በኦሮሚያ ለ5 ቀናት የተጠራው የስራ ማቆም አድማ ዛሬ ተጀምሯል።
/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ በኦሮሚያ ክልል ለ5 ቀናት የተጠራው “ከቤት ያለመውጣት የስራ ማቆም አድማ” በተለያዩ ከተሞች ተጀምሯል። የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፤ ከአቅማችን በላይ የተጣለብን ግብር ይቀነስልን የሚሉና ሌሎች የመብት ጥያቄዎችን በማንሳት በአምቦ፣ ጊንጭ፣ ነቀምት፣ ጅማ፣ ሰንዳፋ፣ ሰበታ፣ ሊሙ፣ አርሲ፣ በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ባሌና ሌሎች ከተሞችም የስራ ማቆም አድማው እየተካሄደ ነው።
የንግድ ድርጅቶች ተዘግተዋል፤ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል፤ በወያኔ ባለስልጣናት ንብረቶች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። አድማውን በመጣስ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሞከሩ ተሽከርካሪዎች ላይም እርምጃ ተወስዶባቸዋል። የአግአዚ ወታደሮች ወጣቶችን እያሰሩ መሆናቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል።
በተለይ በጫት ንግድ የሚታወቁ ከተሞች አካባቢ ጸጥታ የሰፈነ ሲሆን አድማው በመላው ኢትዮጵያ እንዲካሄድና ዘላቂ ወደሆነ መፍትሄ የምታመራ ሃገር ለመገንባት የሚቻልበትን መስመር ይዘረጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሆኗል፡፡
የአንዳንድ ተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችና አክቲቪስቶች ሁኔታውን ከግብታዊ እይታ ወጥተው ከአሁን በፊት ከአመት በላይ የዘለቀውን ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ የነበሩ ስህተቶችን በአትኩሮት በማጤን ለሃገራዊ ራዕይ እንዲነሱ ጥሪ የቀርቧል፡፡
ጥሪውን ያቀረቡት ወገኖች እንደሚሉት ይህ እንቅስቃሴ ከስሜታዊ ጉዞ ከጸዳና ይህንን አስከፊ አገዛዝ በህዝባዊ እምቢተኝነት ፍጻሜውን ለማየት የሚያስችል የተባበረ ኢትዮጵያዊ እንቅስቃሴ እንዲሆን መስመር ካልተዘረጋ አካባቢ ተኮር በሆነ እንቅስቃሴ የህዝብን ትግል በማምከን የሚታወቀው ህወሃት መራሹ መንግስት አሁንም ህዝብን ከህዝብ በማጋጨትና በማፈራራት እንዳያዳፍነው እንደሚሰጉ በተለይ ለኢትዮጰያ ነገ ገልጸዋል፡፡
የተጀመረው የህዝብ ትግል በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እንዲስፋፋ ማድረግ የዜግነት ግዴታ ነው የሚሉት እነኝህ ወገኖች የአዲስ አበባን ህዝብ የዚህ ትግል አብይ ተካፋይ ካላደረገና አንዳንድ ጽንፈኞች በሚያራግቡት አካባቢ ተኮር ፖለቲካ ህዝቡ ከመፈራራት ነጻ ሆኖ አዲስ አበባ የመዲናነት ሚናዋን እንድትጎናጸፍ መሰራት አንዳለበት አስምረውበታል፡፡