ግሸን መድሀት ቤትና የዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ ውዝግብ መቋጫ

ግሸን መድሀት ቤትና የዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ ውዝግብ መቋጫ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ ዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ ቀደም ሲል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ነሐሴ 4 2017 ባወጣው የምርመራ ዘገባ ከስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይንም ዶፒንግ ጋር በተያያዘ በአለም አቀፉ የፀረ ዶፒንግ ኤጀንሲ በወጣው የተከለከሉ መድኃኒቶችና ዘዴዎች ዝርዝር ውስጥ በቀዳሚነት የተካተተውና /EPO/ የተባለው መድኃኒት ስቴዲየም አካባቢ በሚገኘው የ“ግሸን ፋርማሲ” ያለምንም የሐኪም ትዕዛዝ በቀላሉ እንደሚሸጥና ስፖርተኞችም በቀላሉ እየገዙ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ መግለፁ ይታወሳል፡፡

በዚህም መድኃኒቱ በጋዜጣው ላይ በተጠቀሰው የግሸን ፋርማሲ ውስጥ እንደሚገኝ በፍተሻ ማረጋገጥ እንዲሁም የዘ-ጋርዲያን ጋዜጠኞች በላኩት ደረሰኝ መሠረት መድኃኒቱን ከፋርማሲ መግዛታቸው ማወቅ ተችሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በጋዜጣው ላይ ፎቶግራፋቸው የታተሙ መድኃኒቶችን መለያ ቀጥር በመመርመር ፋርማሲው በደረሰኝ ያስገባቸውን መድኃኒቶች ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መሸጡን የአዲስ አበባ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምርመራ በማካሄድ ደርሸበታለሁ ብሏል፡፡

በዚህም መሠረት ፋርማሲው ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ስታዲየም የሚገኘው የግሸን ፋርማሲ ለሦስት ተከታታይ ወራት እንዲዘጋና አገልግሎት እንዳይሰጥ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡የቅርንጫፍ መድኃኒት ቤት ኃላፊም የሙያ ፈቃዳቸው ለ6 ወራት እንዲታገድ ተደርጓል።

በወቅቱ ዘ-ጋርዲያን ይህንን ዘገባ ይዞ ሲወጣ የፋርማሲዉ ሀላፊዎች መድሐኒቱን እንዳልሸጡ በሚዲያ ወጥተው ማስተባበላቸው ይታወሳል። ይህንን መሰል አስነዋሪ ተግባር ለፈጸሙና ሀገራችን በአትሌቲክሱ ዘርፍ ያላትን አለም አቀፋዊ መልካም ስም ላጎደፉ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተጣለባቸው ቅጣት አጥጋቢ አለመሆኑን አስተያየት ሰጭዎች እየገለጹ ነው።

LEAVE A REPLY