የመጨረሻዎቹ ሳምንት መጀመሪያ በዝዋይ እስር ቤት ከጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጋር
ከሁለት አመት ከአስራ አንድ ወር በፊት በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በ16ኛው የፍትህ አዳራሽ ውስጥ ዳኛው የበላዮቻቸውን ውሳኔ ሲያነቡ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የ3 አመት እስራት መወሰኑን ሲናገሩ ተመስገን ፊት ላይ የታየው ነገር እና ፍርዱን ከተናገሩ ከ6 ደቂቃ በኃላ ተመስገን በወታደሮች ታጅቦ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ወዳለው በተለምዶ አንበሳ ቤት ወደሚባለው ሲወስዱት ፍርድ ቤት ውስጥ የነበረው ሰውና ወጪ ሆኖ ሲጠብቅ የነበረው ህዝብ ጠብ-መንጃ የያዙትን ወታደሮች ከቆብ ሳይቆጥር በጭብጨባና በጩኸት ከተመስገን ጋር አብርው እንደሆኑና የቆመለትን አላማ እንደሚደግፉ ሲያሳዩ ጋዜጠኛ ተመስገን ፊት ላይ የታየው ነገር ብርታቱና ፈገግታው አንድ ሳይቀንስ ዛሬም ከሁለት አመት ከአስራ አንድ ወር በኃላ በነበሩበት እንዳሉ ናቸው። ያኔ ተመስገንን ያየው ዛሬም ቢያየው ከነበረበት የመንፋስ ልዕልና ከፍ ብሎ ነው የሚያገኘው።
ዛሬ መስከረም 2/2010ዓም ዝዋይ እስር ቤት ስሄድ ተመስገን ስለቆመለት ፍትህ ይከበር ስላለው መብት ስለከፈለው ዋጋ እያሰብኩኝ ነው የደረስኩት።
የተለመደውን አታካች ፍተሻ ከአንድም ሁለት ቦታ አልፌ ተመሰገን መጠበቅ ያዝኩ ከጎኔ እናቴ የቋጠረችውን ስንቅ ተመለከትኩ። እናቴም አሰብኩ። እናቴ የተመስገን የፍርድ ቀን ጀሞ ከሚገኘው ቤታችን በለሊት ተነስታ አቢዮት አደባባይን አቋርጣ ሰመአቱ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ተገኝታለች። ተመስገን ከታሰረ ጀምሮ የምግብ ፍላጎቷ የጠፋው እናታችን የዛን ዕለት ሙሉ ቀን ቤተ ክርስተከያን ውስጥ እየጠበቀችን እህል ባይኖ አልዞረም ነበር የናት ሆዱስ እንዴት እሺ ይላታል። የተመስገንን የፍድድ ነገር ወደ አመሻሹ ላይ ስትሰማ ቀና ብላ “ምነው አምላኬ” በሚል ሁኔታ ወደ ሰማይ ተመልክታ ቆየች። የግዷን ከተቀመጠችበት ተነስታ ከቤተክርስቲያኑ እየወጣች መለስ ብላ የእስጢናፋስን ምስል ተመለከተች።
ምስሉ ላይ እስጢፋኖስን በድንጋይ ሲወግሩት ይታያለደ። ላፍታ ትንፋሿን ሰብስባ ተመለከተች አይኖቿ እንባ አቀሩ ከአይኖቿ እንባም ፈሰስ። ከራሷ ጋር አወራች። አለሰማዋትም ግን መስሉን እያየች ስለነበረ እንዲህ ያለች መሰለኝ “ሰመአቱ እስጢፋኖስም ሰማአት የሆነው ለእምነቱ ነው ልጄም ሰመአት የሆነው ለሀገሩ ነው” ያለች መሰለኝ። እናቴ የወገቧን መቀነት እያጠባበቀች ወታ ሄደች። ይህው 2 አመት ከ11ወሯ እናቴ መቀነቷን እንዳጠበቀች ነው። ወግ ልምዱስ የሚለው “የወንድ ልጅ እናት ተጠቂ በገመድ” አይደል።
እናቴ ከልጇ እስር በኃላ እርጀናዋ ቢጠናም ህመሞ ቢብስም መንፈሶ ግን አልተፈታም። “ከዚህ በኃላ ልጄ የኔ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ልጅ” ነው ካለች በኃላ እሷም የኢትዮጵያ እናት ሆና ድካሞን ወጥ አደርጋ ይህው ስንቅ እየቋጠረች ስትልክ 2 አመት ከ11 ወር ሆናት።
ከሃሳቤ ስመለስ ስቀመጥ ሁለት ወታደሮች ብቻ የነበሩት ስድስት ሆነው ተመስገንም ከፊትና ከኃላ በወታደሮች ተከቦ እየመጣ አየሁት። ከተቀመጠኩበት ተነሳው ተመስገንን ተመለከትኩት እርምጃው ፈገግታው ፊቱ ላይ ጎልቶ የሚታየው ጥንካሬው ከ2 አመት ከ11 ወር በፊት በከፍተኛው ፍርድ ቤት በወታደሮች ተከቦ ሲሄድ ከነበር ልዩነቱ የቦታ ብቻ ሆኖ ታየኝ። ከመነሻውስ “ለሀገሬ ስል ጉዞዬ እስከ ቀራኒዮ ነው” ብሎ የተነሳሁን ሆኖ እያሳየንስ አይደል። ተመስገን ለቆመለት አላማ ቆሞ የተገኘ ብርቱ ሰው ነው።
ከአንድ አመት በፊት መንግስት ያቀረበለትን “አመክሮ” አለቀበለም በዚህ መንግስት ለመገምገም ህሊናዬ አይፈቅድልኝም በማለት የመንግስትን አመክሮውን አለመቀበሉ ይታወሳል።
ተመስገን ዛሬም የሀገሩ ጉዳይ ጠልቆ ይሰማዋል ተመስገን በፊትም የሀገሩ ጉዳይ ጠልቆ ይማው ነበር ተመስገን ነገም የሀገሩ ጉዳይ ጠልቆ የሚሰማው ለሀገሩ መሆን የሚገባውን ሁሉ በደስታ እየሆነላት ያለ የኢትዮጵያ ብርቱ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መንግስት የፈረደበትን ሙሉ በሙሉ የእስራት ግዜ ሊጨርስ 30 ቀናት ብቻ ቀርተውታል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለሀገርክ ያደረከው የምታደርገው ነገር ሁሉ በዚህኛው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለዘላለም በኢትዮጵያ ላይ ፃንቶ ይቆያል።
ታሪኩ ደሳለኝ
ዝዋይ
መስከረም 2/2010ዓ.ም