/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አወቃቀር ፈርሶ በአዲስ መልክ ሊዋቀር እንደሆነ ባለስልጣናቱ ገለጹ። አዲሱ አወቃቀርም 9ኙ ክልሎችና ሁለቱን የከተማ መስተዳድሮች መሰረት ያደረገ እንደሚሆንም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከአራት ዓመት በፊት ሲቋቋም ማኔጅመንቱ ለህንድ ኩባንያ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም የተሻለ ውጤት አለማምጣቱ በሌላ አዲስ አደረጃጀት እንዲተካ ምክኒያት መሆኑ ታውቋል።
ሪፖርተር ጋዜጣ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ መንግስቴ እንዳሉት “ሀይል የማከፋፈል ሥራው በአገር አቀፍ ደረጃ በዘጠኙም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ይደረጋል” ብለዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሀገር ደረጃ 15 ዲስትሪክቶች ቢኖሩትም ሰባቱ በአንድ ክልል ውስጥ ናቸው። ይህም ለሁሉም ለክልሎች በፍትሃዊነት እንደማይሰራጭ አመላካች ነው ተብሏል። በየክልሎቹ አዲስ የሚዋቀረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠሪነቱም ለክልሎች እንደሚሆን ተጠቁሟል።
በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት በአዲስ አበባ ለንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት እንቅፋት እንደሆነበት የአዲስ አባባ የንጹህ ውሀ መጠጥ አቅርቦት ባለስልጣን ሲያማርር ቆይቷል። ኢትዮ-ቴሌኮምም በመብራት መቆራረት ምክንያት ጥራት ያለው አገልግሎት ለደበኞቸ እንዳላቀርብ አድርጎኛል በማለት ስሞታ ማሰማቱ የሚታወስ ነው።
የአማራ ክልል መንግስትም በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ በደል እየደረሰብኝ ነው በማለት ቅሬታውን አሰምቷል። በአማራ ክልል ያሉ የኃይል ማስተላለፊያዎችና ትራንስፎርመሮች በደርግ ዘመን የተገነቡና ያረጁ በመሆናቸው ዘመኑ የሚጠይቀውን የ“ሀይል” አቅርቦት ለህዝብ ለማዳረስ አልቻልኩም በማለት አማሯል። ከ197 በላይ የሚሆኑ ፋብሪካዎች ግንባታቸውን ጨርሰው የሀይል አቅርቦት ማግኘት ባለመቻላቸው ወደ ሥራ አለመግባታቸውንም ክልሉ መግለጹ አይዘነጋም፡፡