የኢትዮጵያ ሶሺዮ ፖለቲካ ጉዞ፣ ተግዳሮቶቹና የመፍትሄ ኣሳብ /ገለታው ዘለቀ/

የኢትዮጵያ ሶሺዮ ፖለቲካ ጉዞ፣ ተግዳሮቶቹና የመፍትሄ ኣሳብ /ገለታው ዘለቀ/

ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባት ምቹ የሆነ የሶሺዩ ፖለቲካ ሥርዓት ወደ መፍጠር

/ለአራተኛው የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንፈረንስ የቀረበ ጽሁፍ/

መስከረም 2017
ዋሽንግተን DC.
የተባበረችው አሜሪካ

ቢጋር

I. ረቂቅ

II. የኢትዮጵያ ሶሺዮ ፖለቲካ ጉዞ

III. የኢትዮጵያ ሶሺዮ ፖለቲካ ተግዳሮቶች

3.1.ማህበራዊ ተግዳሮቶች

3.1.1. የሶሺዮ ፖለቲካችንን መሸርሸሩ

3.1.2. የግትርነትና ጽንፈኝነት ባህርያት መዳበሩ

3.2. ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች

3.2.1. ብዙሃን ይግዛ

3.2.2. ለማንነት ድምጽ በሃይል መጋለጥ

3.2.3. የማንነት ግጭት

3.2.4. የቡድንና የግለሰብ መብት እንዲጋጩ ማድረጉ

3.2.5. የፖለቲካ ስልጣን ቀመር ችግር

3.2.6. የጋራ መሪ እንዳናፈራ ማድረግ

3.2.7. ሁለት ኣይነት ኣርበኞች መፍጠሩ

3.3. ኢኮኖሚያዊ ችግሮች

3.3.1. የሃብት ክምችት ተስፋ መሆኑ ቀርቶ የግጭት መንስዔ ይሆናል

3.3.2. በብሄራዊ ሃብትና በብሄር ሃብት መሃል ግልጽነት ኣይኖርም

3.3.3. ያልተመጣጠነ እድገት ያመጣል

3.3.4. ሙስናን ያዳብራል

3.3.5. ለኮሚዩኒቲ ሞቢላይዜሽን የሚሆን ሃይል ያሳጣል
IV. ምን ይሻላል? የመውጫ ኣሳብ (EXIT)

4.1. የዓለም ማህበራዊ ፖለቲካ ንድፈ ሃቦችና ሞዴሎች ቅኝት

4.1.1. ሜልቲንግ ፓት

4.1.2. ካልቸራል ሞዛይክ

4.1.3. ብዝሃነት

4.1.4. ህገ-መንግስታዊ ኣርበኝነት

V. የመፍትሄ ኣሳብ

5.1.በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ኣንድነት ፍሬም ወርክ

5.1.1. የንድፈ ሃሳብ ይዘቶች

5.1.1.1. ኣዲስ ኪዳን

5.1.1.2. ሄራ

5.1.1.3. የሃገር ኣስተዳደር ቅርጽ

5.1.1.4. የቋንቋ ማኔጅመንትና ኣጠቃቀም

5.1.2. የአዲሱ ቃል ኪዳን ዋስትናዎችና ተግዳሮቶች

VI. መደምደሚያ

I. ረቂቅ

የሰው ልጅ ማህበራዊና ግላዊ ተፈጥሮ ስላለው ለማህበራዊ ኑሮውና ለግላዊ ኑሮው የተለያዩ ጠገጎችን እያበጀ ይኖራል። እነዚህ የሚሰራቸው ጠገጎች ለግል ህይወቱም ሆነ ለማህበራዊ ህይወቱ ወሳኝ ናቸው። ሰው የዚህን ዓለም ኑሮውን ለመግፋት ከሚያስችሉት መሳሪያዎች ኣንዱ እነዚህ ጠገጎቹ ናቸው። የሰው ልጅ በህይወቱ የሚፈጥራቸው እነዚህ ጠገጎች ሃይማኖታዊ ወይም ባህላዊ ወይም ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትርፍ ያስገኙለታል። ታዲያ ይህ የሰው ልጅ በዓለም ላይ ከሚፈጥራቸው ጠገጎች መሃል ከፍተኛውና ጠንካራው ሃገር የሚባለው ጠገጉ ነው። በርግጥ ከዚህ ኣልፎ ዛሬ ጊዜ ሌላ ከፍ ያለ የጋራ የዓለም ጠገግ ህዝቦች ኣበጅተው ስያሜውን ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ብለውታል። ነገር ግን የሰው ልጅ ከቀን ተቀን ህይወቱ ጋር በጣም የተሳሰረው ጠገግ አገር ሲሆን ለዚህ ጠገግ የተለያዩ ስምምነቶችን ኣስፍሮ በዚህ ጥግ ስር ይኖራል። ሃገር የሚባለው ጠገግ ጠባብ ኣይደለም። የሰው ልጅ በዚህ ጠገግ ስር ብዙ መለስተኛ ጠገጎችን ሊፈጥር ይችላል። ለምሳሌ የባህል የሃይማኖት ወይም ሌላ ዓላማ ያለውን ጠገግ በዚህ ሰፊ ጠገግ ውስጥ ሊሰራ ይችላል። ሃገር የሚባለው ጠገግ እነዚህን ሁሉ ኣቅፎ መያዝ የሚችል ሰፊ ኣዳራሽና ከፍ ያለ ጠገግ ነው። እንደ ብሄር የሃይማኖት ስብስብ ያሉ ጠገጎች በተፈጥሯቸው ልዩነትን በውስጣቸው ኣይዙም። ልዩ ልዩ ቡድኖችን ኣቅፎ በውስጣቸው ለማስኖር የሚያስችል ተፈጥሮ የላቸውም። ከነዚህ ስብስቦች ከቡድናቸው ስምምነት ወይም ደንብ ውጭ የሆነ ቡድን ቢመጣ በውስጣቸው ያለ ቅራኔ ሊኖር ኣይችልም። በመሆኑም ነው ኣገር የሚባለው መዋቅር ከነዚህ የቡድን ጥጋጥጎች ተላቆ ሁሉን ማቀፍ የሚችል ጠገግ ሆኖ በዘመናዊቷ ዓለም የተሰራው።

ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ኢትዮጵያም በውስጧ ብዙ ቡድኖችን የያዘች ሰፊ ጠገጋችን ናት። ይሁን እንጂ በተለይ ባለፉት ሃምሳ ኣመታት ግድም በውስጧ ያሉትን ሌሎች ጠገጎች በተለይም ብሄርን ለማስተናገድ ይመረጣል ተብሎ የሃገራችንን የፖለቲካ ሲስተም የተቆጣጠረውን የብሄር ፖለቲካ እያካሄድን ነው። በዓንድ ሃገር በተለይም ብዙህ በሆኑ ህዝቦች ውስጥ በተለይ የፖለቲካው ለሂቅ የሚከተለው የሶሺዮ ፖለቲካ ፍልስፍና የዚያን ሃገር የፖለቲካ ውቅር በቀጥታ ተጽእኖ ይፈጥርበታል። ሃገር መስርተን እየኖርን ያለን ብዙ ብሄሮች ስለዚህ ስብስብ ያለን ፍልስፍናና ይህን ስብስብ ልናስተናግድበት የምንፈልገው መንገድ የሃገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ህይወት ሁሉ ይለውጣል። ዛሬ በዚህ ጽሁፍ ስር በጥልቀት የምናየው ጉዳይም ይሄው የኢትዮጵያ የሶሺዮ ፖለቲካ ፍልስፍናና ያመጣውን ተጽእኖ እንዲሁም ይህንን ተከትሎ ከመጣው ችግር የመውጫውን መንገድ ነው። በአንድ ሃገር ውስጥ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለመገንባትም ይሁን ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባት የሶሺዮ ፖለቲካ ኣመለካከታችን ወሳኝ ነው። የዚህ ጽሁፍ ዓላማም ለዴሞክራሲ ስርዓት የሚሆን ምቹ እርሻን ለመፍጠር የተሻለ የሶሺዮ ፖለቲካ ኣስተሳሰባና ሲስተም ለማሳየት ነው። ይህ ሲስተም በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ኣንድነት የተሰኘ ፍሬም ወርክ ሲሆን በውስጡ የአዲስ ቃል ኪዳን ጥሪ፣ የህገመንግስት ለውጥ፣ የመንግስት ኣወቃቀርና የቋንቋ ማኔጅመንትና ኣጠቃቀምን የሚመለከት ይሆናል። ፍሬም ወርኩ በነዚህ ኣራት ጉዳዮች ላይ የሚሰጠው ኣሳብና ሲስተም የተባበረች ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ ኣማራጭ ሲስተም ይሆናል።

II. የኢትዮጵያ ሶሺዮ ፖለቲካ ጉዞ

የኢትዮጵያ ሶሺዮ ፖለቲካ ፍልስፍና በጋራ በምንፈጥረው ጠገግ ውስጥ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ህይወታችንን ተጽእኖ ይፈጥርበታል በሚለው ከተስማማን የኢትዮጵያን ሶሺዮ ፖለቲካ ጉዞ ኣጥንቶና መርምሮ የተሻለ ኣመለካከትና ሲስተምን ማምጣት የግድ ይለናል። በዚሁ መሰረት በዚህ ክፍል ውስጥ የኢትዮጵያን ሶሺዮ ፖለቲካ ጉዞ በጥቂቱ እናያለን።

ዘመናዊት ኢትዮጵያ ዘመናዊ ኣስተዳደር ማካሄድ ከጀመረችበት ጊዜ ኣንስቶ ኢትዮጵያ በተወሰነ የባህል ምስለት ውስጥ ኣልፋለች። የዘመናዊት ኢትዮጵያ መሃንዲሶች የሚባሉት ኣጼ ቴዎድሮስ ኣጼ ዮሃንስና ኣጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን ዘመናዊ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ የባህል ምስለት በተለያየ ደረጃ ተካሂዷል። በርግጥ በኢትዮጵያ ምድር ይህ የባህል ምስለት የተካሄደው በኣማራና በሌሎች ብሄሮች መካከል ብቻ ሳይሆን ቀደም ብሎ በኦሮሞ ብሄር መስፋፋት ጊዜም የባህል ምስለቶች ተካሂደዋል። ደቡብ ኣካባቢ ያሉትን እንደ ጌዲኦ ቡርጂ ኮንሶ የመሳሰሉትን ህዝቦች ብናይ የኦሮሞ ባህልና ቋንቋ ተጽእኖዎችን እናያለን። የጌዲኦ ህዝብ የገዳ ስርዓትን የሚከተል ህዝብ ነው። ኮንሶ የኦሮሞን ሃይማኖት የሚከተል ነው። በርግጥ ስለ ምስለት ስናወራ ቡድን የሚባለው በተለይም ብሄር በአንድ ቀን እንደ ኣዳምና ሄዋን ተፈጥሮ ምድር ላይ የተገኘ ኣይደለም። ብሄር የሚፈጠረው በመስፋፋት ምናልባትም በምስለት ነው። ስለሆነም ምስለቱን ጠለቅ ብለን እንይ ካልን ዛሬ ምስለት ተካሂዶብናል የምንል ብሄሮች እኛም ራሳችን በምስለት ውስጥ ኣልፈን ይሆናል እዚህ የደረስነው። የሆነ ሆኖ ግን ኣዲሲቷ ኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስትን ስታጠናክር በዚይን ወቅት የነበሩ ቡድኖችን ስታሰባስብ የሰሜኑ ባህል በተለይም በከተሞች ኣካባቢ ተጽእኖ ፈጥሮ ቆይቷል። ዓለምም ለነገሩ በኣብዛኛው የተፈጠረችው እንደዚህ ነው። የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያ ምስለት ባየለበት መንግስት ስር ለብዙ ዓመታት ኖረች። በዚያን ጊዜ የነበረው የሶሺዮ ፖለቲካ ኣስተሳሰብ ኣንድን ሃይማኖትና ባህል በመጫን ላይ ያተኮረ ነበር ማለት ይቻላል። ይህ ሁኔታ ብዙ ዓመት ከቆየ በሁዋላ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የዓለምን የሶሺዮ ፖለቲካ ኣስተሳሰብና ኣተያይ የሚቀይር ኣንድ ፍልስፍና ብቅ ኣለ። የማርክሲስት ሌኒኒስት ኣስተምህሮ የዓለምን ወጣቶች ልብ ለተወሰነ ጊዜ ገዝቶ ነበር። ይህ ኣስተሳሰብ ከያዛቸው ትምህርቶች መካከል የብሄሮች ነጻነት፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና የራስን እድል በራስ እስከመወሰን ድረስ መሄድ የፍትህ ጥግ መስሎ ታየ። ያለፈውን ስርዓት ማንነትን የደፈጠጠ በመሆኑ በቀል ተያዘበት። በመሆኑም የብሄሮች ጥያቄ በዘመናዊት ዓለም የፖለቲካ መለዮ ለብሶ እሳት ጎርሶ መጣ። ቀላል የማይባሉ የኢትዮጵያ ተማሪዎችም በኣስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ በዚህ ትምህርት ከነፉ። የብሄሮች ጥያቄ መነሳቱ ሳይሆን የከፋው ብሄር የሚባለውን ስብስብ ወይም ጠገግ እንደ ሰው ልጆች ጠገግ የመጨረሻ ቅንጣት ወይም የማምለጫ ኣለት ተደርጎ መወሰዱ ነበር። በዚህ ጠገግ ስር ፍትህ የማይጎድልበት ይመስል፣ በዚህ ጠገግ ስር የማይርበው ይመስል፣ የማይጠማው ይመስል፣ ክፉ የማያገኘው ይመስል፣ ብሄር የሰው ልጆች የመጨረሻ ዞሮ መግቢያ፣ ተገንጥሎ ማረፊያ ጎጆ ተደርጎ በሶሺዮ ፖለቲካ ፈላስፎች ታየ። ኢትዮጵያም ይህንን ትምህርት መከተል ስትጀምር በሳህን በሳህን ለየብቻችን ፖለቲካንና ኢኮኖሚን እንድንጫወት ተደረገ። ኢትዮጵያ በምስለት ውስጥ ኣልፋልች ብሎ ቂም ይዞ የተነሳው ኣዲሱ የማህበረ ፖለቲካ ኣስተሳሰብ ስልጣን ሲይዝ ብሄሮች ያገግሙ ዘንድና ጠገጋቸውን ይጠግኑ ዘንድ የፖለቲካ ማልያ እንዲለብሱ የሚያደርግ ፍልስፍና ነው። ነገር ግን ይህ የሶሺዮ ፖለቲካ ኣስተሳሰብ የገጠመው ችግር ኣንደኛ ኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ በምስለት ውስጥ በማለፏ ወደ ሁዋላ ተመልሳ በየቤታችን እንደር የማትልበት ደረጃ ላይ መድረሷ ነው። ትልቁ ግጭት ይሄ ነው። እነዚህ ቡድኖች ለምእተ ዓመት ኣብረው ሲኖሩ እየተጋቡ የፈጠሩት ቅይጥ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ብሄሮች በብዛት ወደ ሶስተኛ ወይም ሁለተኛ ደረጃ የሚሆን ነው። ይህ ኣካል ሃገሪቱን የማትከፋፈል የማድረግ ሃይል በውስጡ ይዟል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለረጅም ዘመን ኣብረው ከመኖራቸውና ብሄሮች ራሳቸው ሲስፋፉ ሲነቃነቁ በመኖራቸው የውስጥ ድንበር ኣፍርሰዋል። በዓሁኑ ሰዓት ይህ መንግስት ዘጠኝ ክልል ያደረጋት ኢትዮጵያ ስትፈጠር ዘጠኝ ኣይደለችም። ቡድኖች መሬታቸው ወሰኑ እስኪጣፋቸው ሃገር ሲመሰርቱም ሲስፋፉም ቆይተዋል። ሌላው ሶስተኛው ችግር ደግሞ እነዚህ ቡድኖች በጋራ ዘመናቸው የሰሩት ብዙ ታሪክ ኣላቸው። ይህም አዲሱን ሶሺዮ ፖለቲካ የሚቃረን ሃይል ነው። በሌላ በኩል የዓለምን ኣፈጣጠር ስናይ ዛሬ ከሞላ ጎደል የተረጋጋችው ዓለም ስትፈጠር በዚሁ በምስለት ጎዳና መሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ለብቻዋ የመጣባት ችግር ባለመሆኑና ከሰው ልጆች ንቃተ ህሊና እድገት ጋር አብሮ መታየት ስላለበት ኢትዮጵያን እንደገና ወደ ሁዋላ መልሶ የተከፋፈለች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለማድረግ የዓለም ሶሺዮ ፖለቲካም በተቃርኖ የቆመ ሃይል ነው። በጋራ ያፈራነው ሃብትና እሴቶቻችንም ይህን ኣዲስ የሶሺዮ ፖለቲካ የሚቃረኑ ወይም በተቃራኒ የሚስቡ ሃይሎች ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህን ሃይሎች ሁሉ እንደ ጠባብ ወይም እንደ ትምክህት እያየ ኣዲሱ የሶሺዮ ፖለቲካ ኣሳብ ስራውን ቀጠለ። በመሆኑም ሃገሪቱ የብሄር ፌደራሊዝምን በመመስረት የሶሺዮ ፖለቲካ ጉዞዋን ከምስለት ወደ ልዩነት ወሰደው። ጉዟችን ከምስለት ወደ ልዩነት ነው ማለት ነው።

image
ለመሆኑ ከምስለትና ከልዩነት የቱ ይከፋል?

በመሰረቱ በዘመናዊ የሶሺዮ ፖለቲካ ኣስተሳሰብ ስንመለከተው ሁለቱም ተገቢ ኣይደሉም። ምስለትም ልዩነትም ኣደጋዎችን ይዘዋል። ይሁን እንጂ ከሁለት ጥሩ ካልሆኑ ነገሮች ኣንዱን ምረጡ ብንባል ግን የትኛው ይሻላል? ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው። ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያ ሶሺዮ ፖለቲካ ጉዞው ከምስለት ወደ ልዩነት መምጣቱ ያመጣውን ችግርና ያዘለውን ኣደጋ የበለጠ በምናብ ስለሚያሳይ ነው።

ምስለት ማለት በግድ እኔን ምሰል ማለት ነው። በቅኝ ግዛት ጊዜ ፈረንሳዩች እንግሊዞች ይህን ተጠቅመውበታል። እኔን ምሰል ማለት እኔ የምናገረውን ቋንቋ ቋንቋህ ኣድርግ፣ እኔ እንደምጨፍረው ጨፍር፣ እኔ የምበላውን ኣይነት ብላ፣ እኔ እንደማስበው ኣስብ ወዘተ ነው። በብዙ ቅኝ ግዛት ኣገሮችም ይህ ሆኗል። በሌላ በኩል ልዩነትን ስናይ ደግሞ እኔ የምለብሰውን ዓይነት ኣትልበስ፣ እኔ በምሄድበት ኣትሂድ፣ የእኔን ኣጨፋፈር ኣትጨፍር ወዘተ ነው። ይህ ልዩነትን መሰረት ያደረገ ኣገዛዝ ሲነሳ ደቡብ ኣፍሪካ ትጠቀሳለች። እንግዲህ ታዲያ ከምስለትና ከልዩነት የቱ ይሻላል የቱ ይከፋል? ካልን ምስለት ይሻላል፣ ልዩነት ይከፋል ማለት እንችላለን። እንዲህም በመሆኑ የኢትዮጵያ ሶሺዮ ፖለቲካ ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ መምጣቱን ያመላክተናል። ወደ ባሰ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የከተተንም ለዚህ ነው። ፍልስፍናው ራሱ ብዙ እምቅ ችግሮችን በመያዙ ነው።

ሶሺዮ ፖለቲካችን ከድጡ ወደ ማጡ ከመምጣቱም በላይ ጠቅላላ የዴሞክራሲ ባህልን የሚይጠፋና የከፋ ችግር ውስጥ የሚከተን ሆኖ ያታያል። የዚህን የልዩነት ወይም የብሄር ፖለቲካ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር በሚገባ በመተንተን ማየት ችግሩን በሚገባ ለመመርመርና ኣማራጭ መፍትሄውን ለመፈለግ ስለሚረዳ በተጨባጭ ያሉትን ችግሮች ዝቅ ሲል አንድ ሁለት እያልን እንመልከት።

III. የኢትዮጵያ ሶሺዮ ፖለቲካ ተግዳሮቶች

3.1. ማህበራዊ ተግዳሮቶች

3.1.1.ማህበራዊ ካፒታላችንን መሸርሸሩ

የመተማመን መትነን (Trust evaporation) እና

የማህበራዊ ድር መጎዳት (broken social networks)

በማህበራዊ ካፒታል ንድፈ ኣሳብ ውስጥ ሁለት ጉልህ ጉዳዮች ይጠቀሳሉ። እነዚህም መተማመንና ኔትወርክ ሲሆኑ ኖርሞችንም ያጠቃልላል። ፖለቲካችን ብሄር ተኮር ሲሆንና “የራስ በራስ (self) ” ጨዋታ ሲመጣ የቡድኖች ኣባላት ኦፖርቹኒስቲክ ጸባይ እንዲያዳብሩ ማድረጉ ኣይቀርም። በተለይ ደግሞ ስልጣን ላይ ያለው ብሄር ጠመንጃና ደህንነቱን ስለተቆጣጠረው ”የኔ” ለሚለው ቡድን የሚያደላ ሊሆን ይችላል ብለው ሰዎች እንዲጠረጥሩ ማድረጉ ኣይቀርም። ይሄ የሶሺዮ ፖለቲካው ራሱ የሚፈጥረው ከባቢ ነው። በዚህ መሰረት የሃገራችንን መተማመን በሶስትኣቅጣጫዎች ብናይ ጥሩ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ግን ማህበራዊ ሃብት እንዴሌሎቹ ሃብቶች ሃብት ነው። የሚያድግ ለኑሮ ኢንቨስት የምናደርገው ሃይል በመሆኑ ካፒታል ነው። ከዚህ ሃብት ውስጥ የመተማመን ካፒታላችንን በሶስት ኣቅጣጫ ስንፈትሽ ኣንደኛ ብሄር ዘለል (cross cultural trust) መተማመናችንን የሚሸረሽር ሁኔታ ተፈጥሯል። ቡድን ከቡድን ሊተማመን የማይችልበትን የሶሺዮ ፖለቲካ መዋቅር ነው የምንከተለው። የአንድ ብሄር ቡድን ኣባላት ከሌላው ብሄር ጋር ያላቸው እምነት መውረዱን ማየት ይቻላል። በየዩኒቨርሲቲው ብንሄድ በተማሪዎች ዶርም በአጠቃላይ ካምፓስ ህይወት ውስጥ የብሄር ዘለል መተማመን ደረጃችን ወርዶ እናያለን። በኣጠቃላይ ስናይ የዚህች ኣገር እጣ ፈንታ በአንድ ብሄር ላይ ብቻ እስኪወድቅ ሃገሪቱ የመገንጠል መብትን ተቀብላላች። ለምሳሌ ኦሮሞ መገንጠል ቢያምረው ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ማለት ነው። ሁለተኛው የመተማመን መመልከቻ ኣውድ ደግሞ ቀጥታ ሲሆን ይህም በመንግስትና በዜጎች መካከል የሚኖረው መተማመን ነው።

በተግባር እንደሚታየው ኦህዴድ ብአዴን የመሳሰሉት ድርጅቶች በገዛ ብሄራቸው ኣባላት በጥርጣሬ የሚታዩ ናቸው። ለህወሃት ኣጀንዳ መሳሪያ ተደርገው ይታያሉ። ጥቅም ኣስጠባቂ ተቆርቋሪ ሳይሆኑ የመበዝበዣ መሳሪያ ተደርገው ይታያሉና በሃይል በመረረ ሁኔታ ይጠላሉ። በሌላ በኩል በብሄር ፖለቲካ ጊዜ የአንድነታችን መገለጫዎችና የጋራችን ቤቶች የሚባሉት የፌደራል ተቋማትም እንዲሁ በአንድ ሃይለኛ ዘውግ በህወሃት ተጠልፈዋል ተብሎ ይታመናል። ዘውጎች በፍርድ ቤት ላይ በምርጫ ቦርድ ላይ ያላቸው መታመን ሲበዛ ወርዷል። ዘ ፈንድ ፎር ፒስ የተባለው ተቋም ባጠናው ጥናት ላይ የኢትዮጵያውያን ስቴት ለጂትሜሲ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል። በዚህ ዓመት በወጣው ሪፖርት ላይ እንደሚያሳየው ዴንማርክ 0.9 ኖርዌይ 0.8 ስዊድን 1.0 ያስመዘገቡ ሲሆን ጋና 4.2 ኣስመዝግባለች። በአንጻሩ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው 8.2 ሲሆን ይህ እጅግ የወረደ ኣሳሳቢ ውጤት የሚያሳየው በመንግስትና በህዝብ መሃል ያለው መተማመን መትነኑን ነው። በሶስተኛ ደረጃ ያለው መተማመን መለኪያ ደግሞ የዜጎች(interpersonal trust) ሲሆን ይህ የመተማመን ሃብታችንም ያለቅጥ በፍጥነት እንዲወርድ ካደረጉት ምክኛቶች ኣንዱ የሶሺዮ ፖለቲካችን መንሻፈፍ ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያውያንን የያዛቸው ሃይማኖትና ባህል ካልሆነ ኣገሪቱ ዜጎቿችን ኣንድ ለኣምስት ጠርንፋ በያዘችበት ኣገር የዜጎች መታመን ማረፊያው ኣንጨቆረር ነው። በአጠቃላይ በሃገራችን ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ የመታመን መትነን(trust evaporation) ይታያል። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ማህበረሰብን እንደ ማህበረሰብ ኣጣብቆ የሚይዘው ዋና ሃይል መተማመን ሲሆን መተማመን ከዚህ መሃል መትነን ሲጀምር ያ ማህበረሰብ ሰላም ያጣል፣ ለመፍረስም ያዘመመ ይሆናል።

ስለማህበራዊ ሃብት ስናወራ ኣንዱ ትልቁ የማህበራዊ ሃብት ዓለባ(element) ኔትወርክ በመሆኑ በዚህ ደረጃም የሃገራችንን ወቅታዊ ይዞታ መቃኘት ተገቢ ነው። የብሄር ፌደራል ስርዓት ሲመጣና ልዩነት እየጎላ ኣንድነት እየኮሰሰ ሲሄድ የሚፈጠረው ነገር ግንኙነት እየቀነሰ መሄዱ ነው። በተለይ ወደ ጎን ከሚያያይዘን መሳሪያ መሃል ኣንዱ ቋንቋ ሲሆን ዛሬ ኣዲሱ ትውልድ ኣማራውና ኦሮሞው ለመግባባት ይቸገር ጀምሯል።የፌደራል ስርዓቱ ግንኙነትን መልቲ ካልቸራሊዝምን የሚገድብ በመሆኑ በሃገሪቱ ያለው የብሄሮች መስተጋብር ቀንሷል ማለት ይቻላል። ብሄሮች በመሬት ኣንድነትና በኢኮኖሚ በፖለቲካ ስለተበጣጠሱ ግንኙነታቸው ቀንሷል። ይህም የሃገርን ማህበራዊ ሃብት ይጎዳል።

3.1.2.የግትርነትና ጽንፈኝነትን ባህርያት ማዳበር

የዚህ ሶሺዮ ፖለቲካ ችግር በሃገራችን ውስጥ ጽንፈኛ ኣስተሳሰብን ማዳበሩ ነው። በዜጎች መሃከል የሚደረገው ክርክርና ውይይት ሁሉ ከብሄር ማንነት ጋር ቶሎ ስለሚያያዝ ኣምክህኖታዊና ሳይንሳዊ ውይይት እየጠፋ ይሄዳል። መደገፍና መቃወም ግትር ይሆናሉ። ይሄ የሶሺዮ ፖለቲካው የሚፈጥረው ድባብ ነው።

አንድ ማህበረሰብ ማህበራዊ ሃብትን ለማፍራት ብዙ ጊዜ ይወስዱበታል። ሲጠፉና ሲፈርሱ ደግሞ ለመገንባት ከባድ ነው። በመሆኑም በዚህ ደረጃ ኣገራችን የገጠማት ተግዳሮት ኣደገኛ ነው። ማህበራዊ ሃብታችን ፈርሶ ድንገት በሆነ ክስተት ሃብታም ብንሆን እንኳን ያንን ሃብት አንጠቀምበትም።

3.2. ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች

ፖለቲካ የአስተዳደርን ጥበብ የሚያጠና ሳይንስ ነው ይባላል። ታዲያ በአንድ የፖለቲካ ጠገግ ስር መኖር ያማራቸው ቡድኖች ኣብረው ሲኖሩ የሚኖራቸው የሶሺዮ ፖለቲካ ኣቅጣጫ ፖለቲካዊ ህይወታቸውን በጣም ይወስነዋል። በተለይ እነዚህ ብዙ ህዝቦች ኣብረው ሲኖሩ ለህይወታቸው ዋስትና የሚመርጡት ዴሞክራሲን በመሆኑ የሚከተሉት የሶሺዮ ፖለቲካ ሳይንስ ወደ ዴሞክራሲ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጉልህ ሚና ኣለው።

በዚህ መሰረት ሃገራችን ኢትዮጵያ የምትከተለው የማህበረ ፖለትካ ፍልስፍና በፖለቲካ ህይወታችን ላይ ያመጣውን ተጽእኖ መመርመር ያስፈልጋልና ዝቅ ሲል ይህንን ጉዳይ እንመልከት::

3.2.1.ብዙሃን ይግዛ (Majority rule)

የዘውግ ፖለቲካ ኣንዱ ዋና ችግር ይሄ ነው። በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰማኒያ ሁለት በላይ በብዛታቸው እጅግ የተለያዩ ቡድኖች ባሉበት ኣገር የፕራይሞር ዲያሊዝም ፍልስፍና የሆነውን የብሄር ፖለቲካ ስንከተል የሚያጋጨን ከዴሞክራሲ መርህ ጋር ከማጆሪቲ ሩል ጋር ነው። በዴሞክራሲ ጊዜ በተለይም በምርጫ ጊዜ ማጆሪቲ ሩል ፍትሃዊ ተደርጎ በዴሞክራሲ ኣሳብ ይታያል። በምርጫ ጊዜ ብቻም ሳይሆን በተለያዩ ውሳኔውች ጊዜም ይህ ጽንሰ ሃሳብ ፍትሃዊ ነው። ይህ ኣሳብ በብሄር ፖለቲካ ውስጥ ግን ችግሮች ይገጥሙታል:: ከችግሮቹ ኣንዱ ዘውጎች ቁጥራቸውን ይዘው በመምጣት የፌደራሉን ስልጣን በቡድን ቁጥር ለመቃረጥ ይመኛሉ። ኦሮሞው ኣማራው ብዙ በመሆኑ ዋና ዋና ስልጣኖችን ይመኛል። ዴሞክራሲ በተፈጥሮው በግለሰቦች ነጻነት ላይ ኣተኩሮ ቡድኖችን መንከባከብ ሲሆን የብሄር ፖለቲካ ዘውግን ጠቅልሎ እንደ ኣንድ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ስለሚያየው ይህ ችግር እንዲፈጠር ያደርጋል። ሃገራችን ከዚህ ካልወጣች የዚህ ችግር ሰላባ ሆነን ስለምንኖር ወደ ዴሞክራሲ እንዳናድግ ያደርገናል።

3.2.2.ለማንነት ድምጽ በሃይል መጋለጥ (Identity vote)

ኣንዱ ዴሞክራሲን ከሚያቀጭጭበት መንገድ ዜጎችን ለማንነት ድምጽ ማጋለጡ ነው። እንደ ኣዲስ ኣበባ ያሉ ከተሞች መሪዎቻቸውን ለመ ምረጥ ሲወጡ የተወዳዳሪን ችሎታ ከማየት ዘውግን የመፈለግ ኣዝማሚያ ይፈጠራል:: ይህ ነገር ደግሞ እያደገና ኔትወርክ እየፈጠረ ሊሄድ ይችላል። ይህ በራሱ የዴሞክራሲን መርህ ያጠፋብናል። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማለት በኣሳብ መካከል ፍክክርና ሙግት ተደርጎ የማረከንን መደገፍ እንጂ የደም ሃረግን እያየን እንድንከተል ኣይደለም። ይህ ችግር የሚታየው በምርጫ ወቅት ብቻ ሳይሆን ሙስናን ስንዋጋ ሁሉ ኮታ ውስጥ እንድንገባ ያደርጋል። ስራ ስንቀጠር ኣድልዎን ያሰፋል። በዚህና በመሳሰሉት ሁነታዎች ዴሞክራሲን ይዋጋብናል።

3.2.3.የማንነት ግጭት

ሌላው ኣደገኛ ነገር ደግሞ ዜጎችን በኣካባቢያዊ ማንነታቸውና በብሄራዊ ማንነታቸው መሃል ግጭትን መፍጠሩ ነው። ይህ ግጭት በሁለት መንገድ ይገለጻል። ኣንድ በግል ህይወት ሁለት ከሌሎች ጋር በምናደርገው መስተጋብር ጊዜ። ዜጎች ብዙ ማንነት ያላቸው ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ፍክክር ውስጥ የገቡት የብሄር ማንነትና ብሄራዊ ማንነት ጉዳይ ናቸው። እነዚህን ሁለት ማንነቶች ሳይጋጩ የሚያኖር ጠገግ መሆን ኣለበት ኣገር። ኢትዮጵያ ውስጥ ልእልና ያገኘው የሶሺዮ ፖለቲካ ጉዳይ የፈጠረው ነገር እነዚህን ማንነቶች እርስ በርስ እንዲታገሉ ያደርጋል። ብሄራዊ ማንነት በተፈጥሮው የሚለብሰው ነገር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ነው። በአንጻሩ ብሄር እነዚህን ልብሶች ማሰፋት ሲጀምርና ፖለቲካዊ ጉዳይን ኢኮኖሚን ከብሄራዊ ማንነት ጋር መጋፈፍ ሲጀምር ያን ጊዜ ሁለቱ ማንነቶች እንደ ባላንጣ ይተያያሉ። የረጋ ኣገር ኣንመሰርትም። ኣካባቢያዊ ማንነት ብሄራዊ ማንነትን ኣንተ እኮ የኔ ጥርቅም ውጤት ነህ ከፈለኩ በማንኛውም ጊዜ ላፈርስህ እችላለሁ ብሎ ተወጣጥሮ ኣፍጦ ይመጣል። ብሄራዊ ማንነት በበኩሉ እነዚህ ልብሶች የእኔ ናቸው ፖለቲካዊ ማንነትንና ኢኮኖሚን ኣትግፈፈኝ ይላል። በእኔ ጥግ ስር ሆነህ ባህልህንና ቋንቋህን እየካደምክ ኑር ለመልካም አስተዳደር ፍላጎትህ የዴሞክራሲን መርሆዎች ተቀበል ይላል። በዚህ ጊዜ ግጭት ይፈጠራል። ከብሄራዊ ማንነትና ከብሄር ማንነቴ የቱ ይበልጣል? እያልን አተካራ ውስጥ እንገባለን። ገብተናልም። አካባቢያዊ ማንነታቸው ያሸነፋቸው ኣንድ ጥግ ይዘው ብሄራዊ ማንነት ያሸነፋቸው ኣንድ ጥግ ይዘው የሃገሪቱን ፖለቲካ በሁለት ጽንፎች ሲጓተቱ ይኖራሉ። ይህ ችግር ውጥረትን እያሰፋ ልዩነትን እያሰፋ ኣገር ያፈርሳል።

3.2.4.የቡድንና የግለሰብ መብት እንዲረማመሩ ያደርጋል

የሶሺዮ ፖለቲካችን ሲንሻፈፍ የሚመጣው ችግር ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንት ችግር እያለባት ከቡድንና ከግለሰብ መብት የቱ ይቀድማል? እያልን እንድንነታረክ ማድረጉ ነው። አንዱ የግለሰብ መብት ከተከበረ የቡድንም ተከበረ ማለት ነው ይላል። ሌላው የቡድን መብት ቅድሚያ ይሻል ይልና ዜጎችን በቁና እያፈሰ እንከባከባለሁ ይላል። ይህ ቡድን ራሱ በሰፋው ቁና በተለያየ ምክኛት ያልሰፈሩ ዜጎች ህይወት ምንም ኣያስጨንቀውም። የግለሰቦች መብት በዚያ ቡድን ስም ቢጨፈለቁ ብዙ ግድ ኣይለውም። ዴሞክራሲ ሁለቱንም የሚንከባከብ የኣስተዳደር ጥበብ ነው። ዋናው ጉዳይ የቡድን መብት የሚባሉት ምን ምን ናቸው? የግለሰብ የሚባለሉት ምን ምን ናቸው? የሚለውን መለየቱ ነው። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ሁዋላ በመፍትሄ ኣሳባችን ላይ እናነሳለን።

3.2.5.የፖለቲካ ስልጣን ቀመር ችግር

ሌላው ችግር ዘውግን የስልጣን መወጣጫ ካደረግን የሚገጥመን ችግር የጋራ የምንላቸው ተቋማት ኣካባቢ ተገቢ የስልጣን ቀመር ማሳጣቱ ነው። ከሰማኒያ በላይ ለሆኑ ብሄሮች በምን ቀመር ነው ከፍተኛውን የስራ ኣስፈጻሚ ስልጣን የምናካፍለው? የሚል ጥያቄ ይነሳል። ስልጣን በጎሳ መካፈሉ ራሱ የዴሞክራሲ ኣስተሳሰብ ባይሆንም ነገር ግን ስልጣን እኩል ተካፍለን ትንሽ እንዳንረጋጋ ተፈጥሯችን ለቀመር ኣይመችም። ቤልጂየም ከፍተኛውን የስራ ኣስፈጻሚ ማለትም የሚንስትሮች ምክርቤትን ያዋቀረችው ሰባት ከደች ተናጋሪዎች ሰባት ከፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ኣድርጋ ነው። ቤልጂየም የሪሶርስ ችግር የሌለባት በመሆኑና ህዝቡ የነቃ በመሆኑ የስልጣን ክፍፍሉ እኩል በመሆኑ የማንነት ፖለቲካ ችግር ጎልቶ ኣልታየም። ወደ ሃገራችን ስንመጣ ግን ለቀመር ኣስቸጋሪ ነው ያለን ተፈጥሮ። ዜጎች በየቀያቸው የየራሳቸውን ብሄር ተወላጆች ተሹመው ቢያዩም ትልቁ ሪሶርስና የፖለቲካ ሃይል ተሰብስቦ ወዳለበት የፌደራል ተቋማት ኣካባቢ የወንዛቸውን ሰው ማየት ይመኛሉ። ይህ ስሜት በብሄር ፖለቲካ ድባብ ውስጥ ከባድ በመሆኑ ሃገሪቱን ኣለመረጋጋት ውስጥ ይከታታል።

3.2.6.የጋራ መሪ እንዳናፈራ ያደርገናል

አንዱ ትልቅ ችግር በየፖለቲካ ፓርቲው የሚያድጉ መሪዎች በዚህ የብሄር ፖለቲካ ድባብ ውስጥ ሲቆዩ በውስጣቸው ኣካባቢያዊ ማንነትን ኣሳድገው ስለሚመጡ ለሁላችን የሚሁኑ ኣባቶችን እንዳናፈራ ያደርገናል። የምንመርጣቸው መሪዎች በመጀመሪያ ለራሳቸው ብሄር ኣድልዎ ላለማድረጋቸው ዋስትና እናጣለን። ሲስተሙ ምቹ ስለሚሆን ስልጣን ላይ ያሉ መሪዎች የአካባቢ ኔትወርክ ፈጥረው ኣድልዎ ፈጻሚ እንዲሆኑ ያደርግብናል። የፖለቲካ መሪዎቻችንን ተክለሰውነት ደባል ስለሚያደርገው የጋራ መሪ ጥም ያደርቀናል።

3.2.7.ሁለት ዓይነት አርበኞች መፈጠራቸው

ሌላው ትልቅ ችግር ደግሞ የያዝነው የሶሺዮ ፖለቲካ ድባብ የብሄር አርበኞችን የሚያበዛ መሆኑ ነው። በርግጥ የብሄር አርበኝነት በራሱ ችግር አይሆንም። ነገር ግን አርበኝነቱ የሚገለጸው በፖለቲካም በኢኮኖሚም፣ በግዛትም፣ በታሪክም ሲሆን ጤነኛ ኣርበኝነት ኣይሆንም። እነዚህ ኣርበኞች ደግሞ የአንድነት ሃይል ነን ከሚሉ ብሄራዊ ኣርበኝነት ስሜት ከያዛቸው ጋር ይጋጫሉ። ከፍ ሲል ሁለቱ ማንነቶች ካልነው ኣሳብ ጋር ይዛመዳል። በአንድ የፖለቲካ ጠገግ ስር እነዚህ ሁለት ኣርበኝነቶች እየበዙ ሲሄዱ የሃገሪቱን የለሂቃን ክፍፍል በሃይል ይመታዋል። በዛሬው ጊዜ ኢትዮጵያ በለሂቅ ክፍፍል ከፍተኛ ችግር ላይ ናት። ፌይልድ ስቴት ኢንዴክስ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በለሂቃን ክፍፍል ከስምንት ነጥብ በላይ ኣስመዝግባለች። እጅግ ኣስፈሪ ውጤት ነው።

3.3. ኢኮኖሚያዊ ችግሮች

ሶሺዮ ፖለቲካችን ሲበላሽ የማህበረ ኢኮኖሚ ህይወታችን በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻችንን ሁሉ ተጽእኖ ይፈጥርባቸዋል። በብሄር ፖለቲካ ጊዜ ሊመጡ ከሚችሉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።

3.3.1.የሃብት ክምችት ተስፋ መሆኑ ቀርቶ የግጭት መንስዔ ይሆናል

አገሮች ወደ ኢኮኖሚ ጥርመሳ ሲያመሩ ሃብት በተወሰነ ቦታ ለተወሰነ ጊዜ እንዲጠራቀም ያደርጋሉ። በርግጥ ይህ ሃብት ሲያፈራ ተመጣጣኝ ስርጭት ይደረጋል። እስከዚያው ግን ሃገሪቱ ለመስፈንጠር እንድትችል ጥሪት ለመያዝ ደፋ ቀና ማለቷ ኣይቀርም። ደቡብ ኮርያና ቻይና እንደዚህ ነው ያደጉት። ደቡብ ኮርያ በኣስራ ዘጠኝ ሰባዎቹ ጊዜ እንደነ ሂወንዴ በመሳሰሉ ግዙፍ የንግድ ተቋማት ላይ ያላትን ኣፍሳለች። ዜጎች ያላቸውን ጉልበትና ገንዘብ መስዋእት ኣድርገዋል። ሴቶች ጌጦቻቸውን ሳይቀር ሰውተዋል። ዓለምም በተለይም የተባበረችው ኣሜሪካ፣ ኣውሮፓውያን፣ ካናዳና አውስትሬሊያም ደግፈዋቸዋል። ከተወሰነ ጊዜ በሁዋላ ጥሪታቸው ሲያፈራ ዜጎች ሁሉ ከፍሬው ያገኙ ዘንድ የሃብት ስርጭት ስራ ሰርተዋል:: ኣሁንም እየሰሩ ነው። በኢትይዮጵያ ሁኔታ እንዲህ ኣይነቱን ያልተመጣነ እድገት ተገን ኣድርጉ ለመስፈንጠር ( unbalanced growth strategy) ኢትዮጵያ ምቹ የሆነ የፖለቲካ ከባቢ ውስጥ ኣይደለችም። የነኮርያና ደቡብ ምስራቅ እስያ ኣገሮች ወደ እድገት ሲገቡ ሃብትን ኣንድ ቦታ ሰብስበው ቢስፈነጠሩና ዛሬ ልማታዊ መንግስት ብንላቸው በወቅቱ ከፍተኛ የሆነ የብሄራዊነት ስሜት ኣንዱ ሃይላቸው ነበር። ሃገርን መውደድ ለኮሚኒቲ ሞቢላይዜሽን ስራና የሚጠራቀመውን ሃብት ዜጎች በጥርጣሬ እንዳያዩ ኣድርጓቸዋል። የሚጠራቀመውን ሃብት ተስፋ ኣድርገው ቆይተዋል። ኢትዮጵያ ከፈጠረችው የብሄር ኢኮኖሚ ግንባታ ኣንጻርና በህገ መንግስቷ ላይ ካስቀመጠችው የብሄር የመገንጠል መብት ኣንጻር የሃብት ክምችት ተስፋ መሆኑ ቀሮ ለግጭት መንስዔ ይሆናል። ለዚህ ነው ዛሬ እነ ኤፈርት በያዙት ሃብት ዙሪያ ኢትዮጵያውያን ሲጠረጥሩ ሲነታረኩ የሚታዩት። ይህ ሃብት ኣፍርቶ ይንቆረቆራል ብለው ተስፋ እንዳያደርጉ ያደረገው የፖለይቲካው ተፈጥሮ ነው።

3.3.2.የብሄራዊ ሃብትና የብሄር ሃብት መካከል ግልጽነት ኣይኖርም

ብሄሮች የተፈሮ ሃብትንና ኢኮኖሚን ሲከፋፈሉ በአጠቃቀሙ ዘንድ ግልጽነት ይጠፋል። በመሬት ኣጠቃቀመቸው ዙሪያ በተፈጥሮ ሃብት የማዘዝ ደረጃቸው ዙሪያ ብዙ ጥያቄዎች እየተመዘዙ ቢወጡም ምላሽ ግን ኣያገኙም። የልዩ ጥቅም ጥያቄዎች ፍትሃቸውን ይበላዋል።

3.3.3.ያልተመጠተነ እድገትን ያመጣል

በአንድ ሃገር ውስጥ ኢኮኖሚ በቡድን ሲያዝ ያልተመጣጠነ እድገት በቡድኖች መካከል መኖሩ ኣይቀርም። እንደ ህወሃት ኣይነቱ ስልጣኑን ተገን ኣድርጎ ንግዱ ትርፋማ ሲሆን እነ ኣፋርና ቤንሽንጉል በዜሮ ወጥተዋል። ይህ ችግር ከፍተኛ የእድገት ልዩነትን በአንድ ሃገር ይፈጥራል።

3.3.4.ሙስናን ያዳብራል

ህወሃት በዚህ የፖለቲካ መሰረቱና በዚህ የፖለቲካ ስተሳሰቡ ስልጣን ላይ እቆያለሁ ብሎ የሚያስበው የብዙሃንን ፈቃድ በማግኘት ኣይደለም። ነገር ግን ከየብሄሩ የተወሰኑ ጥቅመኞችን በመመልመልና በሙስና ነው ስርዓቱን ማዋቀር የሚችለው። ሙስና የስርዓቱ የሲስተሙ ህልውና ነው። በርግጥ ሙስናው በገንዘብ ብቻ ባይገለጽም ነገር ግን ዋናው የመንግስት መሰረት ሙስና እንዲሆን ያደርገዋል። ለዚህም ነው ዛሬ ሃገራችን ውስጥ ድርጅታዊ ምዝበራ በሰፊው የተንሰራፋው። የሙስና ኔትወርክ ጠንካራ የሆነበት ምክኛት አንዱ የስርዓቱ ህይወት በመሆኑ ነው። በብሄር ላይ ተመስርቶ በኣንስተኛ ቁጥር ባለው ማህበራዊ መሰረት ህወሃት ስልጣን ላይ እንደማይቆይ ስለሚያወቅ ሙስናን ኣማራጭ ኣድርጎ ስለሚኖር ነው ዛሬ ሙስና የሃገራችን ዋና ችግር የሆነው።

3.3.5.ለኮሚኒቲ ሞቢላይዜሽን የሚሆንን ሃይል ያሳጣል

ከፍ ሲል እንዳልነው እንደነ ኮርያ ያሉ ሃገሮች ሴማእል ኡንዶንግ የተባለውን የኮሚኒቲ ልማት እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ኣንዱ ሃይላቸው ብሄራዊነትን ማራገብ ነበር። በብሄር ከተበጣጠሰች የዛሬዮቱ ኢትዮጵያ ይህን የህብረተሰብ ሃይል ተጠቅሞ የልማት ስራዎችን መስራት ለማይቻል ለኢኮኖሚ ጥርመሳችን ጉልህ ችግሮችን ይዟል::

IIII. ምን ይሻላል? የመውጫ ኣሳብ (Exit)

ከፍ ሲል የሶሺዮ ፖለቲካችን ችግር ውስጥ በመውደቁ በዚህ ሳቢያ እንዴት መላ ህይወታችንን እንዳወሳሰበው ተመልክተናል። ችግርን መለየቱ ኣንድ ነገር ሆኖ ነገር ግን ታዲያ ለችግሩ ኣማራጭ መፍትሄ ማምጣቱ ደግሞ ተገቢ ነው። ለችግር መፍትሄ ስናፈላልግና የተሻለ ሶሺዮ ፖለቲካ ስርዓት ስንፈልግ ከዓለም ተመክሮ መማር መልካም ቢሆንም ነገር ግን ኮርጀን ሙሉ በሙሉ ገልብጠን ተግባራዊ ለማድረግ መሞከራችን ሁል ጊዜ ሳንካ ኣለው። በመሆኑም የዓለምን የሶሺዮ ፖለቲካ ኣተያዮችና ንድፈ ሃሳቦች ጥቂት እናይና በመቀጠል የራሳችን ለራሳችን ወደ ሆነው የሶሺዮ ፖለቲካ ንድፈ ሃሳብ እናልፋለን። እንግዲህ ብዙ ማንነት ይዘን በአንድ ጠገግ ስር መኖር ያማረን ህዝቦች እኛ ብቻ ኣይደለንም። እጅግ ብዙው የዓለም ህዝብ ብዙ ማንነቶችን ይዞ በአንድ ጠገግ ስር ረግቶ ይኖራል። ለመሆኑ ዓለም ይህን ልዩነቱን ወዴት እያደረገው? ይህን ማንነቱን ምን እያደረገው ነው በአንድ የፖለቲካ ጠገግ ስር ረግቶ የሚኖረው? የሚለውን ለመመለስ የሚከተሉትን የሶሺዮ ፖለቲካዎች ንድፈ ሃሳቦች እንቃኝ። በአንድም በሌላም መንገድ የዓለምን ሶሺዮ ፖለቲካ የተቆጣጥሩት ኣሳቦች የሚከተሉት ናቸው።

4.1.የዓለም የማህበራዊ ፖለቲካ ንድፈ ሃሳቦችና ሞዴሎች ቅኝት

4.1.1. ሜልቲንግ ፓት (Melting pot)

image
ሜልቲንግ ፖት ዘይቤያዊ አገላለጽ ነው። አሳቡ የሚያበረታታው ስደተኞች (Immigrants) ከሚኖሩበት አገር ባህልና ቋንቋ ጋር መስለው እንዲኖሩ ነው። ስደተኛ ተቀባዩ ማህበረሰብ ቀድሞ በሰራው የጋራ እሴት ውስጥ ፈጥኖ ጠልቆ መግባት ማለት ነው ሜልቲንግ ፖት ማለት። የተዘለሉበትን አገር ህዝብ ባህልህ ባህሌ፣ ቋንቋህ ቋንቋየ ብሎ ባለው የተዋሃደ ማህበረሰብ ውስጥ መስሎ መኖር ሲሆን የዚህ ቲየሪ ዓላማ ብዙህነትን ፈጭቶና አቅልጦ አንድ ነጠላ ህዝብ አድርጎ የማውጣት የሶሺዮ ፖለቲካ ኤንጂነሪንግ ነው። ይህ ቲየሪ በጽናት ያመነው ነገር ሆሞጂንየስ መሆን የአንድነትና የጥንካሬ ጉልበት አድርጎ ነው። አንድ ነጠላ ባህል ፈጥሮ ስደተኞች ሲመጡ በዚያ ጋን ውስጥ እንዲገቡ እየገፉ ብዙህ ባህሎች እንዳይፈጠሩ እያደረጉ ቀድሞ የተፈጠረን ባህል ጠብቆ የማቆያ ዘዴ ነው። ይህ ቲየሪ በአብዛኛው ተግባራዊ የሚሆነው ብዙ ሰው ወደ ሚፈልስባቸው አገሮች በተለይም አሜሪካ ፣ ካናዳና ሌሎች አገሮችም ነበር።

ሜልቲንግ ፖት ቲየሪ ከክፉ ልብ የሚመነጭ ሳይሆን ወደዚህ አሳብ ያመጣው የአንድነት ትርጉም፣ የብሄራዊ ማንነት ትርጉምና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮችን ለማስተካከል ነው። ብሄራዊ ማንነት የሚባለውን ነገር ብዙህነት ያጠፋዋል በተጨማሪም ብዙ ሆኖ አንድነት ወይም አንድ ወጥ የሆነ ብሄራዊ ማንነት አይኖርምና ባህሎችና ዘሮች እየተዋሃዱ አንድ አካል መፍጠር አለባቸው ከሚል ነው። ስደተኞች ወደነዚህ አገሮች በየጊዜው እየፈለሱ የየራሳቸውን ባህል እየጠበቁ ከሄዱ ብሄራዊ ማንነት እየኮሰሰ ቡድነኝነት ሊያብብ ይችላል :: ይህ ቡድነኝነት ደግሞ የፖለቲካ መልክ ይዞ ሊነሳና የሃገሪቱን ፍትህ ሊጎዳብን ይችላል ከሚል ነው። በተለይ እንደ አሜሪካና ካናዳ ያሉ አገሮች በሰፊው ከመላው ዓለም ሰው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ስለሚተምባቸው ይህ እጅግ ብዙ ህዝብና እጅግ ብዙ ቡድን የሃገሪቱን ብሄራዊ ማንነት ስንገነባ ምን ሊፈጥር ይችላል ከሚል ስጋትም ነው። ሜልቲንግ ፖት ሊፈታው ያሰበው ማህበራዊ ችግር አንዱ ከፍ ሲል እንዳልነው የተግባቦትን ችግር መፍታት ብሎም ተግባቦትን ከፍ ማድረግ ሲሆን ሌላው ብሄራዊ አንድነትን ማጉላት በተጨማሪም ባህላዊ ቡድነኝነትን ተገን አድርገው ሊከሰቱ የሚችሉ እምቅ ግጭቶችን መቀነስ ነው።

በርግጥ ይህ ቲየሪ ተግባራዊ ቢሆን ሄዶ ሄዶ የሚፈጥረው ማህበረሰብ ተፈጥሮአዊ ሆሞጂንየስ ማህበረሰብ ሳይሆን “አርቲፊሺያል” የሆነ ወይም የተሰራ ሆሞጂንየስ ማህበረሰብ ነው ማለት ነው። ቲየሪው ግቡን ከመታ የሚፈጠረው ማህበረሰብ ቀልጦ የተሰራ ይሆናል ማለት ነው።

ወደ ፍልስፍናዊ መሰረቱ እንሂድና ፍጹም ውህደት አንድነትን ያመጣል የሚለው አሳብ የመጣው ባህልን አንድ ዋና የአንድነት ኢለመንት አድርጎ ከማሰብ የመጣ እምነት ይመስላል። አገሮች ይህን ቲየሪ ተግባራዊ ማድረግ ከፈለጉ የተለያዩ ፖሊሲዎችን እየቀረጹ ስደተኞች ወደ አገራቸው ሲገቡ ባህል እንዳያስገቡ ወይም የነሱን ባህልና ቋንቋ ለማስተማር ወይም ለማስረጽ ሳይሞክሩ ዘለው ወደ ነበረው ባህል በመግባት የጋራውን ባህል እንዲያጠናክሩ ነው። ይህ ግን በተግባር ሙሉ በሙሉ የሚገጥም አይደለም በርግጥ።

ይህ ቲየሪ ኮሙኒኬሽንን ከፍ ሊያደርግ ቢችልም፣ የብሄራዊ ስሜት ቢያጎለብትም፣ ለማንነት ድምጽ እድል ቢያጠብም ነቀፌታዎችም አሉት። አንደኛው ጉዳይ ስደተኛውን በፖሊሲ ወይም እድሎችን በማጥበብ ቶሎ እንዲዋሃድ ማድረጉ በራሱ በዘዴ የተሞላ አስገዳጅ ውህደት እንደተደረገ ያስቆጥራል።
በሌላ በኩል የሚቀርብበት ትችት ደግሞ አለ። ለምንድነው ብሄራዊ ማንነትን ከባህል ጋር የምናያይዘው? ለምን ሌላ ማንነት በጃችን ሰርተን ያንን ማንነት የጋራ አድርገን አንሾምም የሚል ነው። ከዚህ በተጨማሪ በዜጎች ዘንድ የባህል አንድነት ስሜት መፍጠሩና ባለብዙህ ባህል የሚሆኑበትን ሁኔታ መስበክ አይሻልም ወይ የሚል ነው። ባለ ብዙህ ባህል መሆን በራሱ ከብሄራዊ አንድነት ጋር የሚጋጭ አይደለም። ይህንን ብዙህ ሃብት ዜጎች የሚያዩበትን መንገድ በማረቅ እንደ አንድ የጋራ ሃብት አድርገው ነው ሊያስቡ የሚገባው ። ብዙ ባህል መኖር የሃብትና የብልጽግና ምልክት ነው። ቁም ነገሩ ይህንን ሃብት ማስተዳደሩና የዜጎችን ስምምነት ማስተካከሉ ላይ ነው።

ባህል ስንል ታለንት፣ እውቀት፣ ስኪል ማለታችንም ነው። በመሆኑም ስደተኞች ወደ ስደተኞች ወደ ኣንድ ሃገር ሲሄዱ ያላቸውን ታለንት ጥለው ዘፋኞች አንድ ዓይነት ዘፈን እንዲዘፍኑ፣ የምግብ አሰራሩ ተመሳሳይ እንዲሆን፣ የባህል ጥበብ ችሎታ ያለው ያንን ጥሎ ወደ ካናዳ፣ አርጀንቲና ወይም ሌላ ተቀባይ አገር ሲሄድ ያንኑ አገር መስሎ እንዲኖር ከማድረግ ይልቅ ስደተኛው ባህሉን በአንድ በኩል እንደጠበቀ በሌላ በኩል ግን ከሌሎች ባህሎችም እንዲለምድ፣ እንዲቀምስ፣ ባለ ብዙህ ባህል ስሜት ኖሮት እንዲኖር ማድረጉ ብልጽግና ይመስላል። ይህ አይነቱ አቀራረብ አገሮችን የባህል ጥበቦችን አቅርቦት ስለሚያሰፋላቸው ለቫራይቲስ ጥሩ ነው።

በሜልቲንግ ፖት ጊዜ ስደተኞች ወይም ቡድኖች ቋንቋቸውን ጥለው አንድ ቋንቋ መናገራቸው ብሄራዊ ማንነትን ያጎላልኛል ከሚልና ከነባሩ ህዝብ ዘንድ የሚመጣውን የስደተኞች አልግባባ አሉ ሮሮ ለመቀነስ ይመስላል። በርግጥ አንድ ቋንቋ በሚነገርበት አገር ያሉ ህዝቦች አንድ ነጠላ ህዝብ ባለበት አገር ያሉ ህዝቦች ፍትህና ሰላም ካጡ ብሄራዊ ክብራቸውን ያጣሉ፣ ብሄራዊ ማንነታቸውንም አጥብቀው አይዙም። ይሄ የሚያሳየው የሰው ልጅ ብሄራዊ አንድነቱን የበለጠ የሚወደው በህግ ፊት እኩልነቱን ሲያይ ነው።

በመሆኑም ምንም እንኳን የሜልቲንግ ፖት አሳብ ቸር ሆኖ የምበላውን እየበላህ ኑር፣ የምጠጣውን እየጠጣህ አብረኸኝ ኑር፣ የምለብሰውን ልበስ ወዘተ. ቢሆንም የሚያስበውን ብሄራዊ አንድነት ግን አይፈጥርም። ርግጥ ነው በቋንቋ በኩል ተግባቦትን ይጨምራል። በርግጥ ቋንቋን በተመለከተ ዜጎች ባይልንጉዋል እንዲሆኑ ከማበረታታት በተጨማሪ ኦፊሺያል ቋንቋ ወይም የጎንዮሽ ቋንቋ ላይ ጠንካራ ፖሊሲ መንደፉና ማስለመዱ ከብሄራዊ ማንነት ጋር ይያያዛል አይያያዝም ሳይሆን ተግባቦትን ይጨምራል አይጨምርም በሚለው አቅጣጫ ነው መታየት ያለበት። እንግሊዘኛን መናገር የአሜሪካ ብሄራዊ ማንነት መገለጫ አይሆንም። ምክንያቱም ዓለም ሁሉ እየተናገረው ነውና። ቸሩዋ እንግሊዝም ይህን ቋንቋ ለዓለም ህዝቦች ያስረከበች ይመስለኛል። በመሆኑም የአሜሪካ ብሄራዊ ማንነት ሊያያዝ የሚችለው ከቋንቋና ከባህል ጋር ሳይሆን ከተፈጥሮዋ ከዜግነት ጋር ከግዛት ጋር ከባንዲራና ከብሄራዊ መዝሙር፣ከህገ መንግስት፣ ከዜግነት ቃል ኪዳን ወዘተ ጋር ነው ። በአጠቃላይ እነዚህን ሁሉ ቋጥሮ የሚይዘው ደግሞ አሜሪካዊ የሚለው የባለቤትነት ማንነት ይሆናል።

ሜልቲንግ ፓት ስለ ሃይማኖት የሚያነሳው የለም። በዚህ በሃይማኖት ጉዳይ ላይ በሚገባ እምነቱን አለመግለጹ ቲየሪውን ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል። እንደሚታወቀው የሚፈልሱ ሰዎች ይዘውት ከሚንቀሳቀሱት ማንነት መካከል አንዱ ሃይማኖታዊ ማንነታቸው ነው። ታዲያ ቲየሪውን ጥያቄ ውስጥ ከሚከቱት መካከል አንዱና ዋናው ጉዳይ በዛ የሚለው የሰው ልጆች ባህል አንድም ከሃይማኖቱ መርሆዎችና ልምዶች የሚመነጭ ነው ወይም ባህሉ በሃይማኖቱ ተጽእኖ ውስጥ የወደቀ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ሃይማኖታዊ ማንነት ምን ይሁን በሜልቲንግ ፓት ቲየሪ የሚለው ጉዳይ ይነሳል። ሃይማኖታዊ ማንነት ከባህላዊ ማንነት ይልቅ ጠንካራ መሰረት ያለው ነው። የአመጋገብ ባህልን የአለባበስ ባህልንም ሊጫን ይችላል። በመሆኑም ሃይማኖታዊ ማንነትን ሜልቲንግ ፖት እንዴት አድርጎ ሊያየው እንደሚችል መገለጽ ነበረበት።

ዋናው ጉዳይ ሜልቲንግ ፖት ቲየሪ ባህልንና ቋንቋን ዘርን በአንድ ማሰሮ ውስጥ አስገብቶ አንድ አዲስ ነገር ለመፍጠር ከመሞከር ይልቅ ከማንነቶች ውስጥ ሊቀልጡ የሚገባቸውንና በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ማሰሮው ሳይገቡ ራሳቸውን ጠብቀው የሚኖሩ ማንነቶችን ቢለይ ጥሩ ይመስላል። ከባህላዊ ፖለቲካ ማንነት ጋር የተያያዙትን ወደ ማሰሮው ከቶ ሌሎች ማንነቶችን ግን ተከባብረው ከህግ በታች እንዲኖሩ እሴት እንዲለዋወጡ ማስተማሩ ይሻል ነበር ብለው የሚያስቡ ምሁራን ሊኖሩ ይችላሉ።

አንዱ የተቀባይ ኣገሮች ወይም ብዝሃነትን የሚፈሩ ስጋት ተመሳሳይ ባህል ያላቸው ቡድኖች መደራጀት ሲጀምሩ ይህ ድርጅት ፖለቲካዊ ይዘት ውስጥ እንዳይገባ ነው። ይሄ ያለ ጥርጥር የፖለቲካ ቅርጽ ያለውን ብሄራዊ አንድነት ይጎዳል። በምርጫ ጊዜም ማህበሩ በሚያምነው ተመራጭ ወይም እጩ ላይ አባላትን የመግፋት ነገር ሊመጣ ይችላል። የግለሰቦችን መብት አሳልፎ መስጠት ሊመጣ ይችላል። በዘር ወይም በባህላዊ ማንነት ወይም በመልክዓ ምድር ላይ የሚመሰረቱ ማህበራት በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ተሳትፎ ማድረጋቸው ፖለቲካዊ ቅርጽ የሚይዘውን ብሄራዊ ማንነት ይከፋፍላል።

በሌላ በኩል ስለ ብሄራዊ ማንነት ስናወራ ማንነት አንጻራዊ ነው። ብዙ ጊዜ ይህቺ ዓለም የምትጠይቀው ማንነት ከዜግነት አኳያ ነው። በአብዛኛው የዓለም ጥያቄ ከማንነት አንጻር ሲታይ ከዜግነት ጋር የተያያዘ ከሆነ ዜግነት የብሄራዊ ማንነት ዋና መገለጫ በመሆኑ ያ ሊበቃ ይችላል። ከዚህ በላይ ግን የሜልቲንግ ፖት አንዱ ጭንቀቱ የሃገሮችን መንፈሳዊ ምንነት ከመጠበቅ አንጻርም ሊሆን ይችላል። የአንድን አገር መንፈሳዊ ዳራ ሳይለወጥ ለማቆየት ይረዳል ከሚል ሊሆን ይችላል። ይህ ጉዳይ ደግሞ የሃገሮች መንፈሳዊ ዳራ (spiritual realm) ነው።

በአጠቃላይ ሜልቲንግ ፖት ዋናው የተፈጠረበት አጀንዳ ከውጭ የተለያዩ ማንነቶችን ይዘው የሚመጡ ስደተኞችን እንዴት እናስተናግድ? ከሚል የመጣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እሳቤ ሲሆን በሆነ የታሪክ አጋጣሚ ለተገናኙና በተፈጥሮ ብዙህ ለሆኑ አገሮች ይህ ፍልስፍና ችግር ፈቺ አይሆንም። በስደተኞች ደረጃ እርግጥ ነው በተለይ የስደተኛው ቁጥር አንዳንድ እያለ የሚንጠባጠብ ከሆነና አናሳ ቁጥር ካለው ከመዋሃድ ሌላ እድል የለውም። በዛ ባለ ቁጥር ግን በስምምነት ላይ የተመሰረት ባህላዊ ምስለት (conventional cultural assimilation) የሚሻል ይመስላል። በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ምስለት ማለት ስደተኞች በሁለት አቅጣጫ እንዲያድጉ የሚያደርግ ነው። አንዱ የገቡበትን ማህበረሰብ ባህል እንዲለምዱ፣ እንዲቀምሱ የሚያበረታታ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የራሳቸውን ባህል እንዲያቀምሱ ማበረታታት ነው። በስምምነት ላይ የተመሰረት ባህላዊ ምስለት እንደ ቡፌ ሊመሰል ይችላል። ሁሉም የእጁን ጥበብ በገበታ ላይ አውጥቶ ያስተናግዳል። አንድ ቡፌ ሆኖ ግን ሁሉም የተሳተፈበት ነው። በአመጋገብ ወቅት ሰው የፈለገውን ያነሳል። ያመነበትን ይጣፍጣል ያለውን ይመገባል። ሁሉንም ላይበላ ይችላል። በስምምነት ላይ በተመሰረተ ምስለት ጊዜ ከዚያም ከዚህም ተጋጭቶና ቀልጦ የሚፈጠር አዳዲስ ባህልም ብቅ ሊል ይችላል። ባህሎች ወደ ጎን ሲነካኩ የሚፈጥሩት አዲስ ባህል ይኖራል። ያለውን እየጠበቁ፣ አዲሱንም እየተደሰቱ፣ የሚመጣውን እየተቀበሉ የመኖር ስምምነት ነው በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ምስለት እምነት።

አሜሪካ በዚህ የተሻለችና ምሳሌ ትመስላለች። በመሆኑም ከሜልቲንግ ፖት ይልቅ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ምስለት ይሻል ይመስለናል። የሆነ ሆኖ መነሻችን ሜልቲንግ ፖት ሲሆን ይህ ቲየሪ የኢትዮጵያን ማህበራዊ ፖለቲካ አይፈታም። በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ምስለት ወደ ባህላዊ ቡድኖች የባህል አንድነት አድጎ መፍትሄ ያመጣል የሚል እምነት ያለኝ ሲሆን ወደ ኋላ በዚህ ላይ እንወያያለን።

ብዙህ የሆኑ አገራት በተለይም ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ስለ ሜልቲንግ ፖት ማውራት የሚያስችል ከባቢ የላትም። ከሁሉም በላይ ተፈጥሮዋን ያገናዘበ፣ ለሰላምና ለልማት የሚመች የተሻለ ምክር ያስፈልገናል። በሌላ በኩል ሜልቲንግ ፖት ከፍ ሲል እንዳልነው የብሄሮችን ብሄር ዘለል ጋብቻ ያበረታታል። ይህ ግን አስቸጋሪ ጉዳይ ነው። ጋብቻ የግለሰቦች ምርጫ ነው። በህግ ብሄርን ከብሄር የሚያጋባ ወይም እንዳይጋቡ የሚያደርግ ፖሊሲ ማውጣት በዚህ ዘመን አይቻልም። በመሆኑም ቲየሪው ይህን ጉዳይ ጨምሮ ወደ ወደ ማሰሮ የሚከተው ከሆነ ተግባራዊ ሳይሆን አሳባዊ የሆነ ነገር ብቻ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን እንደ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ሰው ስናስብ እንደ ሰለጠነ ሰው ስናስብ ጋብቻና ፍቅር የግለሰቦች ምርጫ ነው። ምርጫቸውን እናከብራለን።

በሌላ በኩል ሜልቲንግ ፖትን የምንረዳው የተለያየ የቆዳ ቀለም ያላቸው በአንድ የፖለቲካ ቅርጽ ባለው አገራዊ ማንነት ስር ተሰባስበው ተቻችለውና ተከባብረው መኖራቸውን ለማሳየት ከሆነ እኔ እደግፈዋለሁ። ሜልቲንግ ፖትን ለረጅም ጊዜ እንዲገባኝ የምፈልገውም በዚህ መንገድ ነበር። በርግጥ የ2008 እ. አ. አ. ብሄራዊ ምርጫም ይህንን ያሳያል ብየ ጽፌም አውቃለሁ። ይህን ችሎታ ሜልቲንግ ፖት ብንለው ይሻላል። ነጩ ጥቁሩ ሌላውም የሰው ዘር ፕሬዚደንት ኦባማን በአብላጫ ድምጽ መምረጡ የሚያሳየው አሜሪካ ወደ ተሻለ ማህበራዊ ፖለቲካ ምህዳር መሻገሩዋን ነው። ይህ ችሎታ ሜልቲንግ ፖት ብለው ወይም ሜልቲንግ ፖት በዚህ መንገድ ተሻሽሎ ከቀረበ የሚደገፍ ነው ።

4.1.2.Cultural mosaic theory (Salad Bowl Theory)

ይህ ቲየሪ በካናዳ Cultural mosaic በመባል የሚታወቅ ሲሆን በአሜሪካ ደግሞ salad bowl ቲየሪ በመባል ይታወቃል። ይህ ጽንሰ ሃሳብ ከስሙ እንደምንረዳው በጣም በቀላሉና ስእላዊ በሆነ መንገድ የተገለጸ ሲሆን ዓላማው እነዚህ በባህል የተለያዩ ቡድኖች ከልዩነት ጋር አብረው መኖር መቻላቸውን ለማሳየት የቀረበ አሳብ ነው። የተለያዩ ባህላዊ ቡድኖችን ኑሮ ለማሳየት የሚሞክር ነው። አገላለጹ ምናባዊና ቀላል በመሆኑ ቶሎ ብንረዳውም ወደ ተግባር ሲገባ የሚነሱ ብዙ ጥያቄዎችን መመለስ ይጠበቅበታል። የጽንሰ ሃሳቡ መሰረቱ የሚደገፍ ነው። ልዩነትን፣ ብዙነትን መልቲ ካልቸራሊዝምን አይፈራም። አይፈራም ብቻ ሳይሆን እንደ ሃብት ማየቱ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይ ያደርገዋል።

ይህ ቲየሪ ባህላዊ ማንነትን ከብሄራዊ ማንነት ጋር ለማያያዝ አይሞክርም። ባህላዊ ማንነትን ለየባለ ባህሎቹ የተወ ሲሆን ምን አልባት ብሄራዊ ማንነትን የሚያየው ከዜግነት አንጻር ነው ማለት ነው። ዜግነት ዋና ጥላ ሆኖ በዜግነት የሚገኙ መብቶች ሁሉ የአንድነት መገለጫ ሆነው በፖለቲካ ጠገግ ውስጥ ያሉ ቡድኖች ሁሉ የራሳቸውን ባህል እየካደሙ ይኑሩ የሚል ነው። በአብዛኛው ለቀጥታ እድገት የተጨነቀ ሲሆን በዚህ ቲየሪ በሚገባ እንደገና ሊታይ የሚገባው ተዋረዳዊ ስለሆነው ግንኙነት ነው። የሰው ልጅ በአንድ የፖለቲካ ጠገግ ውስጥ ሲኖር በአንድ መልክዓ ምድራዊና አስተዳደራዊ ክልል ውስጥ ሲኖር እሴት መጋባቱ አይቀሬ ነውና ይህንን እውነት ተገንዝቦ ተዋረዳዊ የቡድኖችን እሴት መጋባት ጉዳይ መተንተን ያስፈልጋል። አሜሪካ የሳላድ ቦልን ቲየሪ ሙሉ በሙሉ ብትቀበልና በፖለቲካ ፖሊሲዋ ብታስገባ የስደተኞች አሰፋፈርን ጉዳይ ልታስብበት ነው ማለት ነው። ይህ ማለት በብሄራቸው መልክዓ ምድራዊ አሰፋፈር ለማድረግ ልትገደድ ነው። ይህ አይነቱ አሰፋፈር ደግሞ ወደ ራስ ማስተዳደር ሊያመራ ይችል ይሆናል።
የሳላድ ቦል እሳቤ ባህላዊ ማንነትን ከስቴት ማንነት የመነጠሉ ስራ ለብዙህ ሃገራት ብሄራዊ ማንነት ጥሩ ምሳሌን ይሰጣል። የሜልቲንግ ፖት ትልቁ ችግር ባህላቸውን መጠበቅ የሚፈልጉትን መብት መጋፋቱ ሲሆን ሳላድ ቦል መብትን አክብሩዋል ይሁን እንጂ ወደ ጎን ደግሞ ከዚህኛውም ከዚያኛውም የሚማሩ ባለ ብዙህ ባህል መሆን የሚፈልጉትን ሊያበረታታ ይገባዋል። ስለ ባህል ስናወራ ዋናው ጉዳይ የሰባዊ መብት ጉዳይ በመሆኑ ዜጎች ወደ ጎንም ወደ ላይም ባህልን የሚያሳድጉበትን መንገድ ማሳየትና ይህን በመንግስት ተቀባይነት እንዳለው መስበኩና ለዚህም የሚሆኑ ፖሊሲዎችን መቅረጽ ተገቢ ይመስላል።

ሳላድ ቦል ከፖለቲካ አንጻር የተሻለ አማራጭ ሆኖ ከተገኘ ከፍ ሲል እንዳልነው ለምሳሌ አሜሪካንን እንደ ቦል ብንቆጥር በውስጥ የሚኖሩት ቡድኖች ለዚህ የሚመች መልክዓ ምድራዊ አሰፋፈርን ይጠይቃል። በሌላ በኩል የተባበረችው አሜሪካ በዳይቨርሲቲ ቪዛ ሎተሪዋ ከመልክዓ ምድር አንጻር ስታሰባጥር ይታያል። ይሄ የሚያሳየው የባህል መካፈልን አጥብቃ ታምንበታለች ማለት ነው:: ሳላድ ቦልን ወደ ኢትዮጵያ በቀጥታ እናምጣው ብንል ወደ ብሄር ፌደራሊዝም የሚያመራ ይሆናል። ምን አልባት ፖለቲካውን ከማንነት ፖለቲካ አውጥተን በአንድ ብሄራዊ ፖለቲካዊ ማንነት ጥላ ስር አድርገን ግን ፌደራሊዝሙን በቋንቋ ላይ እንድናደርግ ይገፋናል። ከፍ ሲል እንዳልነው በተለይ የተለያዩ ብሄሮች ላሏት ሃገር ኢትዮጵያ ይህ ቲየሪ ተመራጭ ከማይሆንበት መንገድ መካከል ለተዋረዳዊ ግንኙነት ባለመጨነቁ የሃገራችንን ትስስር አያጠነክረውም። ከዚህ በላይ የቡድኖች አቀማመጥ፣ ብዛት፣ እንዲሁም ደግሞ የተቀየጠው ማህበረሰብ መብዛት፣ የተለየ መልክዓ ምድር የሌላቸውና የተበተኑ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ቡድኖች የሚያቅፍ አይደለም። ከሁሉ በላይ የብሄራዊ ስሜትን ለማዳበር አይጠቅመንም። ከዚህ ቲየሪ በባህሎች መካከል ሊኖር የሚገባን መከባበርና አብሮ መኖርን (coexistence) እንወስዳለን።

4.1.3.ብዝሃነት (Pluralism)

ብዙህነት (Pluralism) ከመነሻው አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ባህላዊ ቡድኖች በብዙሃን በተደጋጋሚ ሲዋጡ የመታየቱ ጉዳይ ያሳሰበው ፍልስፍና ነው። በመሆኑም እነዚህ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ባህላዊ ስብስቦች በብዙሃኑ መካከል በጽናት መቆም እንዲችሉ፣ ማንነታቸውን ባህላቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ የሚያበረታታና የሚታገል አስተምህሮ ነው። ባህሎች ሁሉ እኩል ናቸው ከሚል ሁሉ ከሚቀበለው የሞራል ትምህርት ጀምሮ በተግባር እነዚህ ዝቅተኛ ተዋንያን ያላቸው ቡድኖች መኖር እንዲችሉ ማገዝንም ያጠቃልልና ለጋራ ህልውና በጋራ መስራትን የሚጠቁም ነው።። መልቲ ካልቸራሊዝምና ብዙነት የሚጋሩት ጉዳይ በባህል ቡድኖች መካከል መከባበር እንዲኖር መስበክ ብቻ ሳይሆን ሃገራዊ ብሄራዊ ማንነትን ከአንድ ነጠላ ባህላዊ ማንነት አውጥቶ ብዙነትን እንደ አንድ የጋራ ማንነት መገላጫ ወይም ባህላዊ ማንነትን ከብሄራዊ ማንነት መገለጫ ማላቀቅ ነው።

በብዙነት የሚያምኑ ሰዎች በባህላዊ ቡድን ብዙነት ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ብዙነትን፣የሃይል ብዙነትንም ያምናሉ። መድብለ ፓርቲ ስርዓትን ብቻ ሳይሆን ስልጣንን ወደ ተለያዩ ሲቪክ፣ የሙያ ወዘተ ድርጅቶች ማውረድና ማካፈልን የሚያበረታታ እምነት ነው። በፖሊሲ ቀረጻ ጊዜ ዝንባሌ ያላቸው ቡድኖች ምክራቸው ተሰሚነት እንዲያገኝ የሚያሳስብ ነው። ብዙሆች በሃይል ስርጭት የሚያምኑ ሲሆን ከዚህ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የሚመነጨው አንዱ ሌላው እምነት ደግሞ ባህላዊ ብዙህነት ነው። ከፍ ሲል እንዳልነው ባህላዊ ብዙነትን ከሚፈታተኑ ጉዳዮች መካከል ዋናው ደግሞ ገዛፋው ቡድን አነስተኛውን ሲውጠው ማየት ነው። ይህንን መጠበቅና ብዙነትን ማበረታታት ከሰባዊ መብት ስጦታው በተጨማሪ ለሁለንተናዊ እድገትም ጠቃሚ እንደሆነ ስለተደረሰበት ነው።

ብዙነት የማህበረሰባዊ ፖለቲካ ሳይንስ ዋና ጉዳይ የሆነውን ማን ይግዛ? (Who rule?) የሚለውን ጥያቄ የሚያየው ብዙ ይግዛ (let many rule) በሚል ነው። ብዙ ሲገዛ የተሻለ ጥራት ያለው ውሳኔ ይኖራል፣ የተሻለ ፍትህ ይበየናል፣ ልማት ይፋጠናል፣ ሰስቴነብሊቲን ያመጣል። በርግጥም ይህ አቀራረብ የዓለምን ህዝብ የሳበና በአጠቃላይ እምነቱ በብዙሃን ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የቻለ አሳብ ነው። የጥቂት ሌሂቃንን አመራር በመቃወም በፖሊሲና በውሳኔ አሰጣጥ ዙሪያ ብዙዎች ዝንባሌ ያላቸው መሳተፋቸው የሃገርን ፍትህ ያሳልጣል። በርግጥም ኦሊጋርኬያዊ ስርዓትን አምባገነናዊነትን የሚዋጉ ህዝቦች ብዙነትን ከመፈለግ ነው።

ብዙነት ቀድሞ የታሰበው ከፖለቲካዊ አገዛዝ ማን ይግዛ? ጥያቄ የመጣ ቢሆንም ይህ አስተሳሰብ ቀስ እያለ ወደ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ብዙነትም ተሸጋግሯል። በጣም ዳይቨርስ የሆኑ ህዝቦችን አብረው እንዲኖሩ የሚረዳ ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ መከባበርን እኩልነትንና በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ አንዱ አንዱን ሳይጫነው የሚኖርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ምርጥ የፖለቲካና የባህል አቀራረብ ነው ይባላል። አገሮች በአንድም በሌላም መንገድ ይህን ትምህርት ያራምዳሉ። በሌላ በኩል ሃይማኖታዊ ብዙነትን የሚያራምዱ ሃይሎች ደግሞ እንዲሁ በሃይማኖቶች መካከል ተቻችሎ መኖርን፣ አብሮ ለመኖር አብሮ ማሰብንና መስራትን፣ የሃይማኖት ዲያሎጎችን የሚያበረታታ ነው።

መልቲ ካልቸራሊዝምም ይሁን ብዙነህት በአብሮ መኖርና አብሮ ለመኖር አብሮ መስራትን ቢያበረታቱም፣ ርስ በርስ አክብሮትን ቢሰብኩም የባህላዊ ሬለቲቪዝምን አስተምህሮ የሚቀበሉ አይደሉም። ብዙነት ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸው የባህል ቡድኖች እንዳይዋጡ ሲደክም ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ባህላዊ አንጻራውያን (cultural relativst) አይደለም። ካልቸራል ሞዛይክ ግን ወደ ካልቸራል ሬለቲቪስቶች የተጠጋ አመለካከት አለው ።

ብዙሆች ባህላዊ ቡድኖች በጉርብትና ሲኖሩ ወይም በአንድ ላይ ተጠጋግተው ሲኖሩ በአንዳንድ ባህሎች ላይ ትችት ወይም ተቃውሞ ሊያሰሙ ይችላሉ። ይህ ተቃውሞ አንዱ ባህላዊ ልማድ ለአንዱ ትክክል ሆኖ ለሌላው ትክክል ስላልሆነ አይደለም። በዚህ ደረጃ በቀጠነ መልክ አይታይም። ይልቁን ባህላዊ ልማዱ ከዓጠቃላይ የሰባዊ መብት አንጻር ጫፍ የወጣ ባህርይ ካለውና ለጋራ ኑሮ ጠንቅ ከሆነ ብዙሃን ይቃወሙታል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ባህሎች የሚከወኑት ጫት በመቃም ወይም ሌላ አደንዛዥ እጽ በመውሰድ ቢሆን ፕሉራሊስቶች ይህንን ድርጊት ሊቃወሙ ይችላሉ። ይህን የሚያደርግ ባህላዊ ቡድንም እንዲያስተካክል ይመከራል ወይም ይወገዳል። የህጻናት ጋብቻ ባህላቸው የሆነ ቡድኖች እና ሌሎችም ከሰባዊ መብት አንጻር የማይሄዱትን ብዙሆች አይቀበሉትም።

ስለ ሃይማኖታዊ ብዙህነት ስናወራም ብዙሆች ምንም እንኳን በሃይማኖታዊ ልዩነት ቢያምኑም፣ ለአንዱ ትክክል የሆነው ለሌላው በስነምግባር ትክክል ባይሆንም አብረው እንዲኖሩ የሚያበረታታ ቢሆንም ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነትን፣ ኢሰባዊ የሆኑ ሃይማኖታዊ ድርጊቶችን ያወግዛል።

በአጠቃላይ አብሮ ለመኖር የመቻቻሉ ጉዳይ ገደብ ያለው ሲሆን ይህ ገደብ ግን ልበ ሰፊ ነው። ትልቁ የሁሉንም ቡድኖች ትክክል መሆንና ያለ መሆን የሚፈርደው የሰባዊ መብት አለማቀፋዊ ኖርም ይመስላል። በዚህ ከባቢ ስር ትናንሽ የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የአጨፋፈር፣ ወዘተ ባህሎችን ልዩነት ያከብራል።

ፕሉራሊዝምን በሙሉ ልብ የተቀበለ መንግስት ከሞራል አኳያ ብቻ ሳይሆን በተግባር ይህንን አሳብ ተግባራዊ ለማድረግ የቡድኖችን አሰፋፈር የሚጠይቅ የቦታ ጉዳይ አያስነሳም ወይ? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። ነው ወይስ በአጋጣሚ የተገኘውን ቡድን ተከባብሮ እንዲኖር መምከር ብቻ ነው የሚል ነገር ይጨመራል። የሚመስለው የሁለተኛውን ነው። ባህል በአብዛኛው የቡድን ስራ በመሆኑ ቡድኖች ደግሞ በአንድ የተወሰነ አካባቢ ተጠጋግተው ካልተገኙ ባህል አለ ለማለት አይቻልም። ይሁን እንጂ የሚመስለው ስደተኛ የሚቀበሉ ሃገራት በአጋጣሚ ቡድኖች በአንድ አካባቢ ሲገኙና አነስተኛ ቁጥር ያለው ቡድን ሲያቆሙ ያ ቡድን እንዲኖር ጥረት ይደረጋል ማለት ነው። በርግጥም ከዚህ ሌላ ያለው አማራጭ ማለትም ሁሉንም ብሄር በየ ብሄሩ የተለያየ ቦታ ማስፈር አስቸርጋሪ ስለሚሆን በፈቃዳቸው የተመሰረቱትን ቡድኖች መጠበቁ ጥበብ ይሆናል።

ይህን የብዙህነት ትምህርት ተገቢውን የሞራል ስንቅ በመሰነቁ ደረጃ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ብዙህ ሃገራት ያለው አስተዋጾ በጣም ጉልህ ነው። ብዙ ሰው የሚቀበለው ጉዳይ ነው። ከሁሉ በላይ ለምናመጣው ማንኛውም አይነት የማህበራዊ ፖለቲካ አስተምህሮ መሰረት ይሆናል።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት ይህን የሞራል ጉዳይ በልባቸው ከያዙ በኋላ ወደ ተግባር ለመግባት ከራሳቸው ተፈጥሮ ጋር ማገናዘብና የተሻለ ሲስተም መቅረጽ ያሻል። ቅድም እንደተነጋገርነው የብዙነት ምንጩ ከፖለቲካ ብዙነት አስተሳሰብ ነው። በመሆኑም ፖለቲካን የበላይ አድርጎ ባህልን ደግሞ በፖለቲካ ስር የሚተዳደር አድርጎ እንዲያየው አድርጎታል። ባህሎችን የሚያደራጀው፣ የሚንከባከበው የፖለቲካ ስልጣን ያለው መንግስት ነው። የመንግስት ዘርፍ የባህል አሳላፊነትን ስራ እንዲሰራ የሚያበረታታ ነው። መንግስት በየጊዜው ፖሊሲ እያወጣ እያደራጀ፣ ፌስቲቫሎች እንዲካሄዱ እያደረገ፣ ሙዚየሞችን እያደራጀ ባህልን ሊንከባከበው ይፈልጋል።
በሌላ በኩል ብዙነት የማንነት ፖለቲካን የሚቀበል አይደለም። ባህላዊ ብዙነት ሲል በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩትን እኩል የመኖር መብት እንዳላቸው ከማሳየት በላይ በማንነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴን የሚያበረታታ አይደለም። አንዳንድ የግዛት ብዙሃን (territorial pluralists) አማኞች ወደዚያ ያደላ አሳብ ቢኖራቸውም በአጠቃላይ በመንግስት እንክብካቤ ስር ብዙ ባህሎች እንዲኖሩ የሚያበረታታ ነው። ይሄ ጉዳይ በተለይ ፖለቲካዊ ማንነትና ባህላዊ ማንነት ተጣብቆ ለመጣባቸው ወገኖች ከባድ ነው። ስለ ብዙነት ሲያስቡ ስለ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ ስለ ፖለቲካ አሰላለፍ መናገራቸው ነው። ይህ ጉዳይ ቸር የነበረውን የብዙነትን መንፈስ የሚያበላሽ ይመስለኛል። ብዙነት በተፈጥሮው ከቸርነት ከመካፈል አብሮ ከመኖር የተቆራኘ ሲሆን በአንጻሩ የብሄር ፖለቲካ እኔነት ይበዛዋል። ራስን በራስ ማስተዳደር፣ የራስን እድል በራስ የመወሰን፣ የራስ ባህል፣ የራስ ቋንቋ (me….me….me…..) ይበዛዋል:: ይሄ ተፈጥሮው አብሮ በመኖር ላይ ሥነ- ልቡናዊና አልፎም ተግባራዊ አሉታዊ ተጽእኖዎች አያመጣም ማለት አይቻልም። ሃገር የሚቆመው በ “እኛ” በጋራ ስሜት ልእልና (national sovereignty) ነው። ይሄ የኔ….. የኔ…. ጉዳይ በርግጥ በአንድ ሃገር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለሃገራቸው ያላቸውን ታማኝነት (loyality) መሻማቱ አይቀርም።

ኢትዮጵያ በተለያየ የቦታ አቀማመጥ የሰፈሩ ብዙ ቡድኖች ያሏት አገር ሆና ግን ደግሞ በአንድ ሃገር ጥላ ስር ወይም በዜግነት ስር ለብዙ ብዙ ዓመታት ኖራለች። ይሁን እንጂ በተለይ ሁዋላ ላይ ከዘውዳዊ አገዛዝ ወደ አዲስ ስርዓት ስትሻገር የባህል ማነጅመንቷ አካባቢ ችግሮች አሉባት። ከዚህም አልፎ ባህላዊ ቡድነኝነትን የፖለቲካ ጥብቆ ልብስ አልብሳው የብሄር ፌደራሊዝምን ተግባራዊ አድርጋ በመኖር ላይ ነች። ኢትዮጵያ ልኳ ያልሆነ የባህል ፖለቲካ ጥብቆ ልብስ አልብሰዋት የእናትነት ግርማዋን እያሳጣት ነው።

መንግስት የብሄር ፖለቲካ ውስጥ የገባነው የማንነት ጥያቄዎችን ለመፍታት ነው ቢልም የማንንት ጥያቄዎች አሁንም ሳይፈቱ ያሉ ሲሆን ከሁሉ በላይ አገሪቱ የስልጣን ክፍፍሉ ሳይመቻት እንዲሁ ትኖራለች።

የዚህ የብሄር ፖለቲካ አንዱ ችግር ለብዙህ የፖለቲካ ስርዓት አለመመቸቱ ነው። ፖለቲካዊ ብዝሃነት ወይም (political pluralism) ተግባራዊ ለማድረግ እውነተኛ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የፖለቲካው አሰላለፍ ራሱ የሚመች አይደለም። የብሄር ፖለቲካ በተፈጥሮው ነጠላ የሆነ የፖለቲካ ስርዓትን የሚደግፍ ዓይነት በመሆኑ ፖለቲካል ፕሉራሊዝም ችግሮች አሉበት። ፖለቲካዊ ብዙህነት ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መኖር ነው። በአንድ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ የተለያየ አይዲዮሎጂ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊቋቋሙ ይችላሉ። እነዚህ ፓርቲዎች ግን አንዱ ለአንዱ የቆመ ሆነው ነው የሚመሰረቱት። በሌላ አነጋገር አንዱ ስለራሱ ብቻ ሳይሆን ስለሌላውም ይኖራል ማለት ነው። አሜሪካ ውስጥ ያሉ ሁለቱ ግዙፍ ፓርቲዎች ማለትም ሪፐብሊካንና ዴሞክራት የሚከራከሩት ለሁለታችንም፣ ለሃገራችንም የሚሆን እኔ የተሻለ አሳብ አለኝ የለም እኔ ነኝ የተሻለ አሳብ ያለኝ በሚል ነው። ሪፐብሊካን አሳባቸው ቢያሸንፍ ዴሞክራቶችም እንዲጠቀሙላቸው ነው። ዴሞክራቶች አሳባቸው ቢያሸንፍ ሁለቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ አገራቸውን እንዲጠቅሙ ነው። በመሆኑም በዴሞክራሲ ጊዜ
ፖለቲካዊ ፕሉራሊዝም ማለት በአሳብ መፋጨት ሆኖ ግን አንዱ ለሁሉም ጥቅም የሚቆምበት የፖለቲካ ባህል ነው። ወደ ብሄር ፖለቲካ ስንመጣ ግን ፖለቲካዊ ብዙህነት ብዙ መሰናክል ይገጥመዋል። አንዱ ችግር በብሄር ላይ የሚቆመው ፖለቲካ የሚኖረው ለሌላው ሳይሆን ለራሱ በልዩነቱ ላይ በመሆኑ የፕሉራሊዝምን እምነት ያበላሸዋል። በብሄር ፖለቲካ ጊዜ አንዱ ቡድን ስለሌላው አይኖርም። ቡድኖች የሚኖሩት ስለራሳቸው ነው። አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ የዚህ ፖለቲካ እምነት ተግባራዊ መገለጫ ነው። አንድ ቡድን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከፈለገ መገንጠል ይችላል ሲባል ለመገንጠል ድምጽ የሚሰጠው ራሱ ነው፣ ከፈለገ ይሄዳል ካልፈለገ ይኖራል። ምክንያቱም የሚኖረው ስለ ራሱ ብቻ ነውና። የኦሮሚያ መገንጠል ሌላውን ብዙ ቡድን ጠቀመ ጎዳ የሚያሳስብ አይሆንም። በዚህ የብሄር ፖለቲካ እምነት ምክንያት ኦሮሚያ መኖር ያለበት ለራሱ ሲል ብቻ ነው። አማራው መገንጠል ቢያምረው የአማራ መገንጠል ለኦሮሞና ለሌሎች ክልሎች ችግር አለው የለውም ብሎ አያስብም ማለት ነው። ብድግ ብሎ በፈለገው ጊዜ ይሄዳል። ይህ ዓይነቱ የፖለቲካ እምነት ጉራጌው ስለ ራሱ ብቻ ሳይሆን ስለ ኦሮሞውም እንዲኖር፣ አደሬው ስለ ራሱ ብቻ ሳይሆን ስለ ኦጋዴኑም እንዲኖር ስለማያበረታታ ሃገር የሚባለውን ትልቅ ማንነት አጥፍቶ ግራ አጋባን። አንዱ ስለ አንዱ ስለማይኖር ራስ፣ ራስ፣ራስ (me… me…. me…) የሚል ስሜትን እያነገሰ “እኛ”ን ጎዳ። ስለ ፕሉራሊዝም ስናወራ አንዱ ትልቁ የፖለቲካ ፕሉራሊዝም ምሰሶ በአንድ ግዙፍ ብሄራዊ ማንነት ስር የተሰባሰቡ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይላት አንዳቸው ስለሌላውም እያሰቡ ለጋራው ቤታቸው መሻሻል የሚሰሩበት ስርዓት ነው። ይሄ ጉዳይ በብሄር ፖለቲካ ጊዜ በጣም አደጋ ላይ ይወድቃል። የብሄር ፖለቲካ በተፈጥሮም የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አራማጅ አይደለም። በተፈጥሮው ነጠላ የፖለቲካ ስርዓት አራማጅ ነው። ብዙ የብሄር ፖለቲካ ፓርቲዎች ተፈጠሩ ማለት መድብለ ፓርቲ ተፈጠረ ማለት አይደለም። ሁሉም የየቡድኑን ፓርቲ ስለመሰረተ እንጂ አገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን በትክክል እየተደሰተችበት አይደለም። መድብለ ፓርቲ ስርዓት በአሳብ የተለያዩ ፓርቲዎች አንዱ ለአንዱ ጭምር

የሚታገልበት ስርዓት ማለት ነው። አንዱ ቡድን ስለሌላው ግድ የሚልበት በአብሮ መኖር (coexistence) አጥብቆ የሚያምን ነው።

4.1.4.የconstitutional patriotism ንድፈ ሃሳብ ታሪካዊ አመጣጥና የፍልስፍና መሰረቶቹ

ነገሩ እንዲህ ነው። ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በምስራቁ ክፍል ያለውን ግዛቷን በቀድሞዋ ሶቪየት ዩኒየን በመነጠቋና ቀጥሎም ቀዝቃዛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ በመጣው የዚህ ዓለም አተያይ ሳቢያ ጀርመን ለሁለት ጽንፍ አመለካከቶች ተዳረገች:: ይህንኑ ቀዝቃዛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ ምእራቡ ክፍል የምእራቡን ዓለም አመለካከት ሲያስተናግድ ምስራቁ ክፍል አጥባቂ የኮሚኒስት ደጋፊ በመሆን በወቅቱ ተፎካካሪ ለነበሩት ሶቪየት ዩኒየንና ምእራባውያን ሁለቱ ጀርመኖች ለሁለቱ ጎራዎች ደጋፊ በመሆናቸው ተለያይተው ለየብቻ ጎጆ ወጥተው መኖር ጀመሩ።

ሁለቱ ጀርመኖች ቋንቋቸው አንድ ይሁን እንጂ ይከተሉት የነበረው የዚህ ዓለም አተያይ ሁለት የተለያዩ ሰዎች እስኪያደርጋቸው ድረስ ልዩነታቸው ሰፋ። ምስራቁ ክፍል የኮሚኒዝምን የህይወት ፍሬዎች እያፈራ ቆየ። በአንጻሩ ምእራቡ የካፒታሊስቱን ፍሬ እያፈራ ቆየ። ሁለቱ ወንድማማቾች ይከተሉት የነበረው የዚህ ዓለም የፖለቲካ ትምህርት በህይወታቸው የተለያየ ፍሬ እንዲያፈሩ ስላደረጋቸው የማንነት ልዩነቶችን አመጡ።

የማርቲን ሉተር ሃይማኖታዊ ሰው መነሻ የነበረችውና የፕሮቴስታንት እምነት መነሻ የሆነችው ምስራቅ ጀርመን ሃይማኖትን አራክሳ የነበረ ሲሆን ሌላው ቀሮቶ አሁን ከተዋሃዱ በሁዋላ በ2012 OSW (Center for Eastern studies) ባደረገው ጥናት ካላት ህዝብ ከሃያ ስድስት በመቶ በታች የሚሆነው ህዝቡዋ ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄድባት አገር ሆና ስትገኝ በአንጻሩ ምእራብ ጀርመናዊያን በግልባጩ ሰባ ሶስት በመቶ የሚሆነው ህዝቡዋ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል። ይህ የሚያሳየው በሃይማኖት ዝንባሌያቸው ምን ያህል ተራርቀው እንደነበር ነው። በአጠቃላይ በዴሞክራሲ አረዳድ፣ በማሀራዊ ሃብት ክፍፍል፣ ወዘተ የተራራቀ መረዳትን ከመያዛቸው የተነሳ ያፈሩት ስብእና ነው የተለያየ ማንነትን ያመጣው።

እንግዲህ ሁዋላ ላይ በአለም ላይ የኮሚኒዝም ስርዓት መንኮታኮት ሲጀምር ምስራቅ ጀርመንም በእጁዋ ያለውን የኮሚኒዝም ፍሬ ለማየት የጽሞና ጊዜ አገኘች መሰለኝ። ለምስራቅ ጀርመን የለውጥ እንቅስቃሴ ያደረገው የውስጡ የህዝቡ በኮሚኒዝም ፍሬ ያለመርካት ዋናው ጉዳይ ሲሆን የሶቪየት ዩኒየኑ መሪ ሚካዔል ጎርቫቾቭ ሁዋላ ላይ ያመጡት የክፍትነት (openness) አሳብና ሶቪየትን እንደገና የማዋቀር ዓላማ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጦች እንደ ውጪያዊ ተጽእኖ የሚታዩ ናቸው።
የምስራቅ ጀርመን ህዝብ በወቅቱ በነበረው አስተዳደር አዝኖ ውስጥ ውስጡን ለለውጥ ራሱን ማዘጋጀት ጀመረ። ሁዋላ ላይ እነዚያ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የፕሮተስታንት እምነት ተከታዮች ቤተክርስቲያን ውስጥ ተሰብስበው አገራችን ውስጥ ምን እየሆነ ነው? የሚል ውይይት ከፍተው መወያየት ጀመሩ። የጽሞና ጊዜ አምጥተው ያለፉበትን የህይወት ልምድ መገምገም ጀመሩ። በርግጥ ባፈሩት ፍሬ አልተደሰቱም ነበርና በቤተክርስቲያን ውስጥ የጀመሩት ተቃውሞ እየሰፋ-እየሰፋ ሄዶ እልፎች ተቀላቀሉት። በየሳምንቱ ሰኞ ሰኞ አንድ አመት የዘለቀ ተቃውሞ ተሰማ።

እኛ ነን ህዝብ ማለት! (We are the people)

እኛ ነን ህዝብ ማለት! (We are the people)

እኛ ነን ህዝብ ማለት! (We are the people)

እያሉ መዘመር ሲጀምሩ በጣም መሰረታዊ የዴሞክራሲ ወይም የህዝቦች ልእልና ጥያቄ ያነሱ መሆኑ ታወቀ። የአንድ ፓርቲ የበላይነትን በመንቀፍ የህዝቦችን የበላይነት ጥያቄ ይዘው ታገሉ። ይህ የሚያሳየው ምስራቅ ጀርመናዊያን ዴሞክራሲን መጠማታቸውን ብቻ ሳይሆን የማንነት ለውጥ ለማምጣት መዘጋጀታቸውንም ነበር።

የለውጡ ግፊት እየበረታ መጣና 1990 የሁለቱ ጀርመኖች ውህደት አሳብ መጣ። የህዝቡ ንቅናቄ ያስደነገጣቸው የምስራቅ ጀርመን መሪዎች የህገ መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ ደፍ ደፍ ሲሉ ውህደቱ ቀደመና ያሻሻሉትን ህገ መንግስት ወዲያ ጥለው ሁለቱ ጀርመኖች እነሆ ለዳግም ውህደት በቁ።

ታዲያ ሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች ያለያያቸውን የበርሊን ግንብ አፍርሰው ይገናኙ እንጂ ባለፈው ግማሽ ምእተ ዓመት የሚጠጋ ጊዜ ያፈሩት የህይወት ፍሬ የተለያዩ አድርጉዋቸው እንደነበረ ዛሬስ ይበልጥ ሳይገነዘቡ አልቀሩም። ለማናቸውም ውህደቱ ተሳካና የተባበረችውን ጀርመን ወጥ በሆነ የፖለቲካ ስርዓት ለመምራት ፖለቲከኞቹ ሲነሱ የብሄራዊ ማንነት ጥያቄ ተነሳ። ምንም እንኳን አንድ ቋንቋ ብንናገርም የተለያየን ሆነናልና ብሄራዊ ማንነታችን እንዴት ሊሆን ነው? ጀርመን ነን ስንል ምን ማለታችን ነው? ምንድነው አዲሱን ማንነታችንን የሚገልጸው? ሁለቱም ጀርመኖች የባህላዊው ብሄራዊ ማንነት (Traditional national identity) አልተመቻቸውምና እንዴትስ ነው ብሄራዊ ማንነታችንን የምንገንባው? የሚሉት ጥያቄዎች በወቅቱ ለነበሩ የጀርመን ፖለቲከኞች መከራከሪያና ዋና የመወያያ ጉዳይ ሆኖ ነበር። በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ሃበርማስ የተባለ ጀርመናዊ የሶሲዮሎጂ ፈላስፋ የህገ መንግስታዊ ቀናዒነትን ንድፈ ሃሳብ ይዞ ብቅ ያለው። እንደ ሃበርማስ እነዚህን የተለያየ ማንነቶች ያዳበሩ ህዝቦች ሊያገናኝ የሚችል፣ በቅድመ ማንነታቸው ወይም (traditional national identity ) ላይ ምቾት ያልተሰማቸው ህዝቦች ዘንድ ሌላ ድህረ ብሄራዊ ማንነት (post national identity) ሊመጣ የሚችለው ጀርመኖች ለህገ-መንግስታቸው ቀናዒ ሲሆኑ ነው። ሑላችን ለህገ-መንግስቱ ተገዢ ስንሆንና ለሊብራል ዴሞክራሲ ህገ-መንግስት እሴቶችና ኖርሞች ታማኝ ስንሆን የሰው መብት ስናከብር ስናስከብር በተቋማት ላይ መታመን ሲኖረን ያ የብሄራዊ ማንነታችን መገለጫ ይሆናል ማለት ነው የሚል ቁም ነገር አመጣ። በመሆኑም ህገ-መንግስታዊ ቀናዒነት (constitutional patriotism) የብሄራዊ ማንነታችንን ጥያቄ የሚፈታው ነው ብሎ ፖለቲከኞችን መጫን ጀመረ።

በወቅቱ የማንነት ጉዳይ ትልቅ ጥያቄ ሆኖባቸው ለነበሩት የጀርመን ፖለቲከኞችና በባህላዊው ማንነት ምቾት ያልተሰማቸው ጀርመኖች አዲስ ሊፈጥሩት ላሰቡት ማንነት ይህ የሃበርማስ አሳብ በርግጥም ልብ አሳራፊ ሆኖ በዚያን ጊዜ ተገኘ።

ለሁለቱ ጀርመኖች የመገናኛ መስመር ህገ-መንግስቱ ሆኖ ሊብራል በሆነ ዴሞክራሲ ውስጥ ብሄራዊ ማንነታቸውን እንዲጥሉ ሃበርማስ መምከሩ በርግጥ ጥበብ የተሞላና ወቅታዊም ነበር ማለት ይቻላል። ይህ የሃበርማስ አሳብ የጀርመንን ፖለቲከኞች ስሜት ያረጋ በመሆኑ እንደዚሁ የተለያየ ማንነትን ይዘው ብሄራዊ ማንነት ለመገንባት የተነሱ አገሮችም ለውስጥ ችግሮቻቸው መፍትሄ ይሰጣል ብለው ሞክረውታል። ቦስኒያ ለዚህ ተጠቃሽ ናት:: ቦስኒያ ውስጥ በተለይ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ ይህ የሃበርማስ አሳብ በጣም የተቀነቀነ ነበር። የአውሮፓ ህብረትም ይህንን የሃበርማስን አሳብ እንደተጠቀመበት ይታያል።

ሃበርማስ ለህገ መንግስቱ ቀናተኛነት ሲል ለፍትህ ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት፣ ለሶሻል ዌልፌር መቆም እንደማለት ሲሆን እነዚህ ማንነቶች በርግጥ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ናቸው። አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት የሃበርማስ አሳብ አንድን የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተነሳ ስለሆነ አገራዊ የሆነ ሰፋ ያለ ሶሊዳሪቲን ለማምጣት በጣም ይቀጥናል ይላሉ። በርግጥም አገር የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ፣ ፖለቲካዊ ይዘት ብቻ እንዳለው አድርጎ ማየቱና ብሄራዊ ማንነትን ከስቴት ጋር ብቻ ማጣበቁ ቀጣይነት ያለው ማህበረሰብ (sustainable community) ለመመስረት አይሳሳም ወይ የሚል ትችትም ሊቀርብበት ችሉዋል ። ያም ሆኖ ግን በወቅቱ የጀርመኖች ልዩነት ፖለቲካ የወለደው በመሆኑ የሃበርማስም አቀራረብ ፖለቲካዊ እንዲሆን ተጽእኖ አድርጎበት ነውና አሳቡ የሞራልና የሲቪሊቲ ጉዳዮችን አንስቶ የሚገጥሙትን የኮሙኒከሽን ችግሮች በትእግስት በማየት ተቻችሎ ለመኖር ጥሩ ምክር ነበር ማለት ይቻላል። ሃበርማስም በወቅቱ ይህንን በሚገባ ያውቃል። የሃበርማስ ትልቅ ስጋት በውህደት ጎዳና ላይ ላለችው ጀርመን ይሄ ማንነት የሚባል ነገር ችግር እንዳይፈጥር ነገሮችን ማርገብ ነበርና በጣም ማስተዋል የተሞላበት አቀራረብ ነበር ማለት ይቻላል።

ነገሩ ግን ሁለቱ ጀርመኖች ወደ ውህደት እየመጡ የነበሩት የማንነት መራራ ጥያቄ ይዘው አልነበረም። ለሁለቱ ህዝቦች ውህደት ትልቅ አስተዋጾ ያደረገው የምስራቅ ጀርመን ህዝብ የማንነት ለውጥ ለማደርግ ፍላጎትና ጥማት በማሳየቱ ወይም እጅ በመስጠቱ ነው። ምእራብ ጀርመን ከነበራት ፖለቲካዊ ማንነት ንቅንቅ ሳትል ምስራቅ ናት ለውጥ እያመጣች ወደ ምእራቡ አሰተሳሰብ መቀላቀል ያማራት። በመሆኑም የሃበርማስ አሳብ የፖለቲከኞቹን ጥያቄ ወዲያ ያርግብ እንጂ ውህደቱን ያሳለጠው ግን አብዛኛው የምስራቁ ህዝብ የማንነት ለውጥ በማምጣቱ ነው። ለዚህ ዋቢ የሚሆነን ጉዳይ ሁለቱ ሃገራት ወደ ውህደት ከመጡ በሁዋላ የጋራ ህገ መንግስት ሲያረቁ የምስራቁን ሀገ-መንግስት ወዲያ ጥለው ከጥቂት ማሻሻያዎች ውጭ ምእራብ ጀርመን ትጠቀምበት የነበረውን ህገ- መንግስት ነው እንዲቀጥል ያደረጉት። ይህ ማለት እነዚህ ህዝቦች ለመዋሃድ መሃከለኛ የሆነ የሁለቱን ቅይጥ ሀገ-መንግስት አላስፈለጋቸውም ነበር ማለት ነው።

ከፍ ሲል እንዳልኩት ምስራቅ ጀርመን የማንነት ለውጥ ለማድረግ በመወሰኑዋ ስትጠላው የነበረውን ያንኑ የምእራቡን አመለካከት እንደገና የህይወቱዋ መሪ ለማድረግ መወሰኑዋ ነው የውህደቱ መሰረት።። መሬት ላይ ያለው ሃቅ ይህ ከሆነ የሃበርማስ ሃሳብ በውስጠ ተዋዋቂ ምስራቅ ጀርመን የጀመረችውን ወደ ምእራቡ አስተሳሰብ የመዋሃድ (assimilation) እንቅስቃሴ ገፍታበት ሁለቱም ህዝቦች ቀድሞ ምእራብ ጀርመን እያሳደገችው የመጣችውን ፖለቲካዊ ማንነት የጋራ ድህረ ብሄራዊ ማንነት መገለጫ እንዲያደርጉት የሚገፋፋ ነው ማለት ይቻላል።

የሆነ ሆኖ ግን የሃበርማስ አሳብ ከፍ ሲል እንዳልኩት በፖለቲካው ለሂቅ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ከስሜት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ጉዳዮችን በማብረድ ለጀርመኖች ውህደት ትልቅ አፋጣኝ ሚና ተጫውቱዋል።

በአንዳንዶች ዘንድ ደግሞ ሃበርማስ ያመጣው ይህ አሳብ አዲስ ተደርጎ አይወሰድም።ቀድሞውንም ቢሆን አገሮች ህገ-መንግስት አውጥተው ሲተዳደሩ እንደ ሃበርማስ Constitutional patriotism ብለው አይሰይሙት እንጂ ዞሮ ዞሮ በውስጠ ተዋዋቂ ያው ለህገ -መንግስቱ ተገዢ በመሆን ህዝቦች በአንድ የፖለቲካ ጥላ ስር ታምነው እንዲኖሩ ነው የሚፈልጉት። በመሆኑም አሳቡ በመጀመሪያ ደረጃ አዲስ አሳብ ሆኖም የቀረበ አይደለም። እንዴውም ሊብራል ዴሞክራሲ የሚባለው አመለካከት ይውጠዋል። ይህ ማለት የ Constitutional patriotism ተግባራዊ ገጽታው ያው ዞሮ ዞሮ ሊብራል ዴሞክራሲ ነው የሚሆነውና ምንም አዲስ ነገር አልመጣም እየተባለ ይተቻል። ቲየርው ይዞ የመጣው ጉዳይ የሞራል፣ የምክር፣ ስሜትን የመቀስቀስ አይነት ነው። ሌላው የሃበርማስን አሳብ ስናይ በርግጥ ህገ-መንግስታዊ ቀናኢነት የሚመጣው በህገ መንግስቱ ላይ በመታመን፣ ተቋማትን በማፍቀር ከሆነ ማፍቀርና መደገፍ ከመነሻነታቸው በላይ ውጤትነታቸው ነው ጎልት የሚታየው። ዜጎች ለህገ-መንግስቱ አርበኞች እንዴት ሊሆኑ ይችላሉ? አርበኛ ለመሆን ውጤት ሊጠብቁ አይችሉም ወይ? የፖለቲካ ተቋማቱን ፍሬ እያዩ ነው እያደር የሚያፈቅሩዋቸው።ሌላው ደግሞ የሃበርማስ አሳብ ጠበብ ያለ የፖለቲካ ማህበረሰብ በመፍጠር ብሄራዊ ማንነትን የመገንባት አሳብ የያዘ በመሆኑ ቁርጠኛ የፖለቲካ መሪዎች ከጠፉና ተቋማት መርከስ ከጀመሩ ዜጎች አርበኛ ስለማይሆኑ አገር ሊፈርስ፣ ብሄራዊ ማንነት ሊደመሰስ ነው ማለት ነው። በርግጥ የሃበርማስ ቲየሪ ቀጭን ቲየሪ (thin theory) ነው የሚሉትም ለዚህ ነው። ወደ ዋናው አሳባችን ስንመጣ የሃበርማስን አስተያየት ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣትበመጀመሪያ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የማንነት ጥያቄ መረዳት ያስፈልጋል።

ጀርመኖች ያነሱት የማንነት ጥያቄ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ሲሆን የኢትዮጵያው ግን የተለየ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የማንነት ጉዳይ የመጣው የባህላዊ ቡድንን ማንነት ለብሶ የመጣ ሲሆን ቡድኖች በራሳቸው አባላት ራስን ማስተዳደር ይችላሉ የሚል አይነት አስተዳደርንና ስተዳደራዊ ችሎታን ከባህላዊ ማንነት ጋር አደባልቆ ብቅ ያለ የማንነት ጥያቄ ነው ያለው። ከዚህ የምንረዳው ሃቅ የኢትዮጵያ የማንነት ፖለቲካ ጥያቄዎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አደባልቆ የመጣ በመሆኑ ችግሩ ሊፈታ የሚችለው በሶሲዮ ፖለቲካል ቲየሪ ነው። ማንነቶችን ማደባለቅና ለብሄራዊ ማንነት የጠራ መልክ ማጣት የኢትዮጵያ ዋና ችግር ነው። እንዲህ ከሆነ ታዲያ የሃበርማስ አሳብ የሚጨነቀው ቨርቲካል ለሆነውና ፖለቲካዊ ለሆነው ማንነት ብቻ በመሆኑ የኢትዮጵያን ሶሺዮ ፖለቲካል ችግር ሊፈታው በጣም ይቀጥናል። ላሉብን ማህበራዊና ፖላቲካዊ ችግሮች የግድ የሶሺዮ ፖለቲክስ ንድፈ ሃሳብ ነው የሚያስፈልገንና የሃበርማስ አሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረው የማንነት ጥያቄ መፍትሄ ሊሰጥ አይችልም። ከዚህ በተጨማሪም ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ ይህን የሃበርማስን አሳብ ይዘን ህገ-መንግስታዊ ታማኝነትን ብናውጅ በርግጥ በራሱ በህገ-መንግስቱ ላይ ሰዎች ጥያቄ አላቸው። አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ ብቻዋን ብዙ ሰው አስኮርፋለች። በዚህ ሁኔታ ህገ-መንግስታዊ አርበኝነትን መፍጠር አንችልም።

ሌላ ምሳሌ እንይ። ካናዳን። ካናዳን ብናይ የኮቤኮችን የቡድን ማንነት ጥያቄ የሃበርማስን ቲየሪ በመጠቀም በሊብራል ዴሞክራሲ ህገ-መንግስት ሊፈታ አልቻለም ወይም ኮቤኮች በዚህ ልባቸው አርፎ አልታየም። ከፍ ሲል እንዳልነው የኮቤኮች ጥያቄ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ጉዳዮችን ይዞ ስለመጣ ሃበርማስ እንደሚለው በሊብራል ህገ-መንግስት የሚፈታ አልሆነም።

ኮቤኮች በርግጥ ካናዳ አገራቸው ባላት ሊብራል ዴሞክራሲ ውስጥ በፖለቲካ የመሳተፍ መብታቸው ተረጋግጧል። የካናዳ ዜጋ የሆነ ሁሉ በሃገሩ ፖለቲካ ለመሳተፍ ይችላል። የመጣበት ዘርና ቀለም ወይም ባህል አይከለክለውም። ስለዚህ የኮቤኮች የውስጥ ጥያቄ የሚመስለኝ የባህልና ቋንቋ ማንነትን ለመጠበቅ ነው። እንዳይዋጡ ከመስጋት ሊሆን ስለሚችል ትክክል ናቸው። ይህን ተገቢ ጥያቄ በቀጥታ የሚመልሰው ባህላዊ መንግስትን ማቋቋም ይመስላል። በሃገራቸው በካናዳ ውስጥ በኢኮኖሚና በፖለቲካ በግዛት ጉዳይ እንደማንኛውም ዜጋ እየተሳተፉ በሌላ በኩል ግን ባህላዊ ማንነታቸውን የሚጠብቅ ጠንካራ አስተዳደር ማቋቋም ይችላሉ። የቋንቋ ትምህርት ቤቶችን ከፍተው ማስተማር፣ ባህላቸውን መጠበቅ ማስተማር መንከባከብ ይችላሉ ይመስለኛል። ይህን በማድረጋቸውም በታላቋ ካናዳ ውስጥ ሳይዋጡ ባህላቸውና ቋንቋቸው ይኖራል።

በሃገራችን ኢትዮጵያ በተለይ በ1960ዎቹ የተነሳው የብሄር ነጻነት ጉዳይ ሲነሳ ድንገት የተደባለቀው የቡድን ማንነትና የፖለቲካ ማንነት እንዲሁም መልኩ የደበዘዘው ብሄራዊ ማንነት ሳይጠራ እስካሁን ቀርቱዋል። ከቀዝቃዛው ጦርነት በሁዋላ የጽንፈኝነት ፖለቲካ የከሰመ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን የራሱዋን አለም ሰርታ አሁንም በቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ ትገኛለች። እጅግ በሰፋና ጽንፈኛ በሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ ያለን በመሆኑ ዴሞክራሲ ሌላው አለም ላይ እያደገ ሲሄድ እኛ ጋር ቁልቁል ሲያድግ ይታያል።

የሃበርማስ አሳብ አንዱ ለኢትዮጵያ የማይሆንበት መንገድ ፖለቲካዊ ብቻ በመሆኑ ሲሆን ከሁሉ በላይ አንድ ቤት ሲሰራ ዋልታና ማገር ያስፈልጋል። ዋልታውንና ማገሩን እንደ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ልንመስለው እንችላለንና የጠነከረች መሰረት ያላትን ኢትዮጵያን ለመገንባት የሃበርማስ አሳብ አይበቃንም ሃበርማስ አሳቡን ያመጣውም ለጀርመን ነው። በመሆኑም እኛው ራሳችን አገር በቀል የሆነ አንድ የሶሺዮ ፖለቲካል ቲየሪ ልናመጣ ያስፈልገናል ከሚል ነው ሁዋላ ላይ በመፍት ሄነት የማቀርበው የ CCU (Conventional cultural unity) አሳብ የቀረበው።

V. የመፍትሄ ኣሳብ
5.1. በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት ፍሬም ወርክ

ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው ሁለት የተራራቁና የተቃረኑ ሶሺዮ ፖለቲካዎች ጽንፈኞች በመሆናቸው ኣንዱ ኣንዱን በመደፍጠጥ ላይ ኖረዋል። ባለፈው ጊዜ ብሄራዊ ኣንድነት ዘውጋዊ ማንነትን እየረመረመ የመጣ ሲሆን በኣሁኑ ሰዓት ደግሞ ዘውጋዊ ማንነት ብሄራዊ ማንነትን አየረመረመ ሲሄድ ይታያል። እነዚህ ማንነቶች ተቻችለው እንደመኖር አንዱ ባንዱ ላይ ተረማምዶ ጠንካራ ሆኖ ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት የሃገሪቱን ሶሺዮ ፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ከቶታል። እነዚህ ሁለት ጽንፈኛ የፖለቲካ ስርአቶች ትልቁ ችግራቸው የቡድኖችን ፈቃድ አለማግኘታቸው ነው። ቡድኖች ያላቸውን ሁሉ መስዋእት ኣድርገው ብሄራዊ ማንነትን አጥብቀው ይዘው አካባቢያዊ ማንነትን ችላ እንዲሉ ኣልተስማሙም። ኣይስማሙምም። ወይም ደግሞ ብሄራዊ ኣንድነታቸው ኮስሶ የአካባቢ ማንነታቸው እንዲጎለብት ኣልተስማሙም። አይስማሙምም። ይህ የሃገሪቱ ሶሺዮ ፖለቲካ እንዲሻሻል ካስፈለገ ኢትዮጵያ የግድ ወደ አዲስ ኪዳን መሻገር ይኖርባታል። የግድ አንድነትንና ልዩነትን ማስትዳደር የሚችል ስርዓት ያሻስታል። ያለፈችበት የህይወት ልምድና አሁን ያለችበት ሁኔታ ተደማምረው ኣዲሱን ህይወቷን እንድትጀምር ለማድረግ ኣዲስ ኪዳን ያሻታል። ይህ የምናስተዋውቀው የአዲስ ኪዳን ፍሬም ወርክ እነዚህ ሁለት ማንነቶች እርስ በርስ ሳይረማረሙና ሳይጋጩ የሚኖሩበትን መላ የሚያመጣ ነው። አዲስ ኪዳን የሚያሰኘን ኢትዮጵያ በማህበራዊ ጉዳዮች በተፈጥሮ ሃብት ጉዳዮች በፓለቲካ አሰላለፍ ጉዳዮች ግራ አጋቢ ምእራፍ ላይ ስለሆነች ነው። ቡድኖች ኪዳን አድሰው በተሻለ ቃል ኪዳንና ውሳኔ የሃገር ዋልታና ማገር የሆኑ ስምምነቶችን ለመጣል ነው። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ይህ የአዲስ ኪዳን ንቅናቄ በአንድ ንድፈ ሃሳብ ተጠቅልሎ የቀረበ ሲሆን ጽንሰ ሃሳቡ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት ይባላል (Conventional Cultural Unity) ወይም CCU ይባላል።። ይህ ሃሳብ የያዛቸው ጭብጦች ኣራት ጉዳዮች አሉ። እነዚህ ኣራት ጉዳዮች አዲሱን የኢትዮጵያን ሶሺዮ ፖለቲካ ቤት ለመስራት ዋልታና ማገር ይሆናሉ።

CCU መሰረቶች

ኪዳን (Covenant)

ሄራ (Basic Law)

ኣስተዳደራዊ መዋቅር

የቋንቋ ማኔጅመንትና ኣጠቃቀም

እነዚህ ከፍ ሲል የተነሱት ኣራት ጉዳዮች አዲሱን የኢትዮጵያን ሶሺዮ ፖለቲካ ቤት እንደገና ለማነጽ የመሰረት ድንጋዮች ዋልታና ማገር ናቸው::

በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ኣንድነት የሚለውን አገር በቀል የሶሺዮ ፖለቲካ ሞዴል ስናስተዋውቅ ይህ ጽንሰ ሃሳብ የሚይዛቸው እነዚህ ከፍ ሲል የተነሱት ጉዳዮች ሲሆኑ እያንዳንዳቸውን ዝቅ ሲል ለማብራራት እንሞክር።

5.1.1.አዲስ ኪዳን

ኪዳን ስንል ህገ-መንግስት ማለታችን ኣይደለም። የቡድኖች ወይም የዘውጎች ኪዳን የምንለው የቡድኖችን ኣዲስ ቃል ኪዳን (Covenant) ነው። ኣዲሲቱ ኢትዮጵያ ኣዲሱን ሶሺዮ ፖለቲካዋን አሃዱ ብላ ከዚህ ብትጀምር እንዳለ የማህበረ ፓለቲካዋን መሰረት ይለውጠዋል ። አዲስ ኪዳን የፖለቲካዋና የኣስተዳደሯ መሰረት ቢሆን ወደ ተሻለና ግልጽ ወደ ሆነ ሶሺዮ ፖለቲካ ለመወርወር የማእዘን ድንጋይም ይሆናታል። ኪዳኑ የሚያስፈልግበት ሌላው ምክንያት ኢትዮጵያን ዘላለማዊ ኣገር ኣድርጎ ከትውልድ ትወልድ የሚተላለፍ ሰነድ ለማውረስ ነው። ይህ ሰነድ መጪውን ትውልድ ግልጽ በሆነ የሶሺዮ ፖለቲካ ሲስተም ውስጥ ስለሚከተው ኢትዮጵያን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሳለፍ ብሎም ደግሞ ኣዲሱን ትውልድ ኣገሪቱ ከገባችበት የብሄር ጥያቄ ኣዙሪት ኣውጥቶ ስለሚያራምድ ነው። ኣጠቃላይ የፖለቲካ መሰረታችንን ግልጽ በሆነ መሰረት ላይ ለመጣል ይህ ኣዲስ የቡድኖች ኪዳን መሰረት ስለሚሆነን ነው። ቡድኖች ኣዲስ ኪዳን ሲያደርጉ ብሄራዊ ፈውስና መግባባትም ስለሚመጣ ነው። ኣዲስ ኪዳን ስንል ታሪክ የለም ማለት ኣይደለም። ኢትዮጵያን ማፈርስና እንደገና መጀመር ኣይደለም። እንደገና ለማነጽ ነው። የተንሻፈፈውን ለማስተካከል፣ የፈረሰውን ለመጠግን ነው። ኢትዮጵያን እንደገና ለማነጽ ስንነሳና የሃገር ቤታችንን ስንሰራ ከላይ ሞገስ የሚሆነንን ኣንድ የቡድኖች ሁሉ ኪዳን እንቅረጽ ከሚል ነው። እንግዲህ ኪዳኑ ቡድኖች ተማምለው የሚያቆሙት ሃውልት የሚያጸድቁት ሰነድ ሲሆን የዚህ ኪዳን ዋና ይዘት ምንድነው? ካልን ዋናው ጥሪ የመስዋእትነት ጥሪ ነው። ይዘቱ መስዋእትነት ነው። እንደሚታወቀው በኣገራችን ታሪክ ውስጥ ዘውጋዊ ማንነት በተደፈጠጠበት ዘመን ባህልና ቋንቋ የሚያድግበት ሁኔታ ኣልነበረም። ኢትዮጵያ ስትመሰረትም በቡድኖች ኪዳን ሳይሆን በሃይል ነበር። አሁን ደግሞ በሃይል ተሰብስበናልና እንደገና አይነት በሃይል ተበታተንን። በዚህ ጊዜ ባህልና ቋንቋ እንዲያድግ ተደረገና ብሄራዊ ማንነት ደግሞ ተደፈጠጠ። ቡድኖች ኢትዮጵያን ተቀራመቱ። መሬት፣ የተፈጥሮ ሃብት፣ ፖለቲካዊ ማንነት፣ ቋንቋና ባህል ሁሉ ለየብቻ ተኮለኮሉና ጨዋታው በየቤትህ እደር ሆነ። በዚህ መሃል የጋራ የምንለው ነገር ከእይታችን ተሰወረ። ኢትዮጵያ ሁሉን ኣጣች። አገር ሊመሰርቱ የሚችሉ ካስማዎችን ሁሉ ነቃቅለን በየብሄሩ በየሰፈሩ ተከልን። ስለዚህም ብሄራዊ ማንነት ኮሰሰ ብቻ ሳይሆን ጨርሶ ጠፋን። በዚህ ያዘኑ ኢትዮጵያውያን ኣያሌ ናቸው። ሁል ጊዜም ያዝናሉ። በመሆኑም ኣዲሱ ኪዳን የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። ቡድኖች ተሰባስበው ተወያይተው ቀላል በሆነ ቋንቋ ኣንድ ኪዳን ይገባሉ። ይህ ኪዳን ደግሞ ያላቸውን ባህል፣ ቋንቋ፣ የተፈጥሮ ሃብት፣ ፖለቲካዊ ማንነት ሁሉ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት እንሰዋለን የሚል ቆራጥ የሃገራችን ከፍተኛ ኪዳን ነው። አንዱ የኪዳኑ መሰረት የኢትዮጵያውያን የቸርነት ባህልም ነው። ሁለተኛው የኪዳኑ መሰረት ይህቺ አገር በሃይል ከተመሰረተች በኋላ ቡድኖች ሁሉ በጋራ የሰሩት ብዙ አለምን ያስደመመ ታሪክ አላቸው ብዙ የጋራ እሴት ገንብተዋል ደማቸውን ተካፍለው ተዋልደዋል። አገራቸውን ኢትዮጵያን ይወዳሉ አንድነትን ይሻሉ የሚል ነው። እንግዲህ ቡድኖች አዲስ ኪዳን ሲገቡ በኪዳኑ ጊዜ ቡድኖች ሁሉ ያላቸውን ሁሉ መስዋእት ካደረጉ በሁዋላ ፖለቲካዊ ማንነትን ኣደባልቀው ይቀጥላሉ። አንድ ሰፊ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ይፈጥራሉ። ነገር ግን ባህላዊ ማንነትን ከመስዋእቱ ኪዳን በሁዋላ ቡድኖች ሁሉ መልሰው የሚወስዱበትንና የሚንከባከቡበትን ረቂቅ ስምምነት ይስማማሉ። ይህ ማለት ቡድኖች ባህላዊ ማንነታቸውን ከፍ ላለው ኢትዮጵያዊነት ቢሰውም ነገር ግን ዘውጋዊ ማንነት የኢትዮጵያ ማንነትም የቡድኖች ማንነትም ሆኖ ዘላለም እንዲኖር የራሱ ኣስተዳደር ይበጅለታል። ፖለቲካዊ ማንነትና ባህላዊ ማንነት ለየብቻ በተለያየ ሲስተም ያድራሉ። ኪዳኑ ሁሉን መስዋእት ኣድርጎ ባህልና ቋንቋን መልሶ ለየቡድኖቹ ያከፋፍላል። ቡድኖች ሁሉ የኢትዮጵያም የነሱም ንብረት የሆነውን ቋንቋና ባህል በሚፈጠረው ሲስተም ዘላላም ሲጠብቁት ይኖራሉ። ይህ ነው የኪዳኑ ዋና መሰረት። የኪዳኑ ዋና ይዘትም ኑ ያለንን መንፈሳዊና ቁሳዊ ባህሎች እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እንሰዋ የሚል ነው።

የኢትዮጵያ አዲስ ኪዳን ዋና ማእከላዊ ይዘት መስዋእትነት ነው። እኛ የኢትዮጵያ ቡድኖች ያለንን ሁሉ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሰውተናል የሚል ኪዳን ማለት ነው። በኣጠቃላይ ኣዲስ ኪዳን የምንለው ሪፈረንደም ኣይደለም። ኑ የፈረሰውን ቅጥራችንን እናድስ ኑ ኣገራችንን እንደገና እናንጽ። ኑ ኣገራችንን ግልጽ በሆነ ስምምነት እናንጻትና ሰነድ ይዘን ኪዳን ገብተን ተማምለን ወደ ፊት እንሂድ የሚል ጥሪ ያዘለ ነው። አዲስ ኪዳን የነፍስን ጽዳት ለማምጣት ለብሄራዊ መግባባት መንገድ ነው። ኣዲስ ኪዳን የምንለውም ያለፈውን ለመርገም ሳይሆን ወደፊት ለመራመድ ለቡድኖች ሁሉ መሳጭ የሚሆን ኪዳን ገብተን ወይም ስምምነት ተፈራርመን የፈረሰውን ቅጥር ኣድሰን ወደ ፊት እንራመድ ማለት ነው። ቡድኖች የሚገቡት ኪዳን ግልጽ ነው። ያለንን ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህል ቋንቋና የተፈጥሮ ሃብት ሁሉ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሰውተን እየተንከባከብን ለመኖር ቃል ገብተናል የሚል ከፍተኛ ኪዳን ነው። ኢትዮጵያውያን ይህን ኪዳን ፈጽመው ሃውልታቸውን ሰርተው ወደ አዲስ ኪዳን ሲገቡ የመስዋእትነትን ሚስጥር ድራማቲክ በሆነ መንገድ ለዓለም ያሳያሉ። የኪዳኑን ማእከላዊ ጉዳይ የሆነውን የዚህን የመስዋእትነት ጉዳይ ሲያሳዩ የፍቅርን ታላቅ ሚስጥር ይገልጻሉ። ቡድኖች ወደ ጎን ለሚኖራቸው መተሳሰርና ህብረት የሚፈጽሙት መስዋእትነትና ወደ ላይ ማለትም በስልጣናትና በህዝቡ መካከል በሚኖረው ግንኙነትም እንዲሁ በቡድኖች የመስዋእቱ ኪዳን ላይ የሚቆመውን መንግስት በመመስረት መስቀለኛ ስርዓት ፈጥረው አዲሲቱን ኢትዮጵያን እንዲገነቡ ነው የCCU ጥሪ።

በአጠቃላይ ይህ ከህገ መንግስት ሰነዱ በላይ የሚውለው የዜጎችና የቡድኖች ኪዳን የሚከተሉት ይዘቶች ቢኖሩት ጥሩ ነው።

የኢትዮጵያውያን ኪዳን
1. እኛ ኢትዮጵያውያን ብሄሮች ያለንን የተፈጥሮ ሃብት ክህሎትና
እውቀት ሁሉ ለኢትዮጵያ ሃገራችን ሰውተናል:: የእኔ የእኔ የምንለው የውስጥ የብሄር ድንበር የለም።
ኢትዮጵያ የእኛ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ናት።
2. እኛ ኢትዮጵያውያን የማትከፋፈል የተባበረች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሳለፍ ቃል
ገብተናል:: በየዘመናቅቱ ታሪክ እየሰሩ አገራችንን ከዚህ ላደረሱ አባቶችና እናቶች ልዩ ክብር አለን። ታሪካቸውንም እንዘክራለን።
3. እኛ ኢትዮጵያውያን ብዝሃነታችንን እንንከባከባለን እናከብራለን;; ትውልዶች ባህላዊ ተቋሞቻችንን እናከብራልን፣ እንጠብቃለን።
4. እኛ ኢትዮጵያውያን ከዓለም ህዝቦች ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በምንገባው ኪዳን መሰረት ለዓለም ሰላምና ልማት በጽናት እንታገላለን።
5. እኛ ኢትዮጵያውያን ለተባበረችው ኢትዮጵያ ልማትና ሰላም ዘወትር ሳንታክት ለመስራት ቃል ገብተናል
6. እኛ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ለመረዳዳት ቃል ገብተናል:: ትውልድ ኣልፎ ትውልድ ሲተካ ቅርስ እየተውን የሚቀጥለው ትውልድ የተሻለ ህይወት እንዲያይ ለማድረግ እንሰራለን። ያሉንን የተፈጥሮ ሃብቶች በትውልዶች መካከል ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንጠቀማለን። እኛ ኢትዮጵያውያን በሃገራችን ኢትዮጵያ ሰማይ ስር ያሉ ግኡዛንና ህያዋን ፍጥረታትን ሁሉ እንንከባከባለን እንጠብቃለን።
7. እኛ ኢትዮጵያውያን ለነጻነት ለፍትህ ለህግ የበላይነት ዘወትር እንተጋለን።
8. እኛ ኢትዮጵያውያን በህግ በምንወስነው የጊዜ ገደብ በአንድ ሰው ለአንድ ድምጽ መርህ መሰረት ተወካዮቻችንን እየመረጥን መንግስት እየመሰረትን ስንኖር መንግስታችን ለሚያወጣቸው የሰላምና የልማት ፖሊሲዎች በንቃት እንሳተፋለን። እኛ የህዝብ ተወካዮች የመረጠንን ህዝብ በታማኝነትና
በትጋት ለማገልገል ቃል ገብተናል።
9. እኛ ኢትዮጵያውያን ለተገፉ መጠጊያ እንሆናቸዋለን። እንግዶችን በፍቅርና
በደስታ እንቀበላለን። ጽንፈኝነትን ሽብርተኝነትን እንዋጋለን:: ለደካሞች ለተጨቆኑ
ሁሉ እንቆማለን።
10. እኛ ኢትዮጵያውያን ይህንን ቃል ኪዳናችንን ለመጠበቅ ዘወትር ዘብ እንቆማለን። አምላካችን እግዚአብሄር ሃገራችንን ይባርክ።

5.1.2.አዲስ ሄራ

ሁለተኛው የዚህ ኣሳብ መሰረት ደግሞ ሄራ ነው። ሄራ የኦሮምኛ ቃል ሲሆን በእንግሊዘኛው constitution የሚለውን ቃል በምልዓት የሚገልጽ ነው። ህግ-መንግስት የሚለው ስያሜ constitution የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ በሙሉ ሃይሉ ኣይገልጸውምና ነው ሄራ የሚለውን የሃገራችንን ቃል የተጠቀምነው። በመሆኑም ከለውጥ ባሻገር ኣገራችን ኢትዮጵያ ከኣዲስ ኪዳኗ በሁዋላ በሰፊው የምታጸድቀው ጉዳይ ሄራችን ነው። ይህ ሰነድ የሃገሪቱ የመውጫና መግቢያ ህግ ነው። የባህልና የመንግስት ኣስተዳደርን ስልጣን የሚወስን ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ ለህዝቦች ልእልናን የሚሰጥ፣ ቼክ እና ባላንስ ያለው፣ የፌደሬሽኑን ጉዳይ ከኪዳኑ ኣንጻር የሚቀርጽ፣ የመንግስትን ስልጣን የሚወስን፣ የሃይላትን ክፍፍል የሚያሳይ ሰነድ ማለት ነው። ኣገሪቱ በኣጠቃላይ የምትቆመው በኪዳኑ ከዚያም በዚህ ሰነድ ላይ ይሆንና ሶስተኛው የCCU ጽንሰ ሃሳብ ይዘት ደግሞ ኣስተዳደራዊ ሲስተሙን በሁለት ክንፍ ማዋቀር ነው።

5.1.3.አዲስ የሃገር ኣስተዳደር ቅርጽ

ኢትዮጵያ ኣዲስ ኪዳን ካደረገች በኋላ የሃገር ኣስተዳደሯን በሁለት ትከፍለዋለች። ኣንደኛው የባህል ኣስተዳደር ሲሆን ሁለተኛው ፖለቲካዊ ስልጣን ያለው ሁል ጊዜም በህዝቦች ተወካዮች የሚመሰረተው ኣስተዳደር ነው። ባህላዊ ኣስተዳደር የምንለው ቡድኖች ሁሉ የባህል ተወካዮቻቸውን ኣዋጥተው የሚመሰርቱት የባህል ኣርበኞች ቤት ይኖራል። ይህ ቤት ወደ ታች ይደራጅና የቡድኖችን ባህልና ቋንቋ ሲንከባከብ ይኖራል። በዚህ መሰረትም ተጨባጭ የሆኑና ያልሆኑ ባህሎችን ይንከባከባል፣ የሰላምና እርቅ ጉዳዮችን ይሰራል፣ ብሄራዊ ሙዚየሞችን ይንከባከባል። የኬር ቴከር ሃላፊነትን ይወስዳል። አስፈላጊ ከሆነ የሃገሪቱን ብሄራዊ ምርጫ ድግስ የሚደግሰው ይሄው አስተዳደር ሊሆን ይችላል። የፍትህ ኣካሉ በሁለቱ ኣስተዳደር የጋራ ተሳትፎ የሚቆም ነጻ የሆነ ተቋም ይሆናል። በሌላ በኩል ያለው ፖለቲካዊ መንግስት ደግሞ የኢኮኖሚ፣ የትምህርት ኣጠቃላይ የሃገሪቱን የውጭ ግንኙነትን ንግድና ልማት በሚመለከት ይመራል። የሁለቱም ኣስተዳደር ስራዎችና ሃላፊነት በሄራው ላይ በግልጽ ስለሚቀመጥ ችግሮች ኣይኖሩም። ይህ ሲስተም ለሃገሪቱ ልማትና ኢኮኖሚም ትልቅ ኣስተዋጾ ይኖረዋል። የባህል ኣስተዳደሩ የራሱ ፌደሬሽን የሚኖረው ሲሆን ፌደሬሽኑ በመሬት ላይ የሚነበብ ኣይሆንም። የባህላዊ ቡድኖች ባሉበት ሁሉ የባህል ፌደሬሽኑ ስራዎቹን ይሰራል። በኣንጻሩ የፖለቲካ ስልጣን ያለው መንግስት ግን መሬት ላይ የሚነበብ ፌደሬሽን ይሰራል። ይህ የፌደራል ኣወቃቀር ደግሞ ከህዝቦች ኪዳን ኣንጻር ይሆናል። ቡድኖች መሬታቸውን መስዋእት ስለሚያደርጉ ፌደራሊዝሙ ለኣስተዳደር ኣመቺነትን መሰረት ያደረግ ይሆናል ማለት ነው።እንግዲህ የኢትዮጵያን ሶሺዮ ፖለቲካ መሰረት በአዲስ ኪዳን ላይ ስናቆም ከዚህ በሁዋላ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችና ህጎች ሁሉ ከፍ ብሎ ከተቀመጠው የቡድኖች ኪዳን የሚቀዳ ይሆናል።አገሪቱ ግልጽ በሆነና በቆረጠ ኪዳን ላይ ስትቆም ከዚያ የሚቀዱ ህጎች ሁሉ ለግጭት መንስዔ ኣይሆኑም። ከሁሉ በላይ በሃገሪቱ ሰላምና ልማት ይሳለጣል።አጠቃላይ ከላይ ያነሳናቸው የ CCU መሰረቶች በስእላዊ መንገድ እንደሚከተለው ሊገለጹ ይችላሉ።

ሄራ ሄራ

ሌላው ስለ ሶሺዮ ፖለቲካችን ጉዳይ ስናነሳ የዘውጎች ዋና መገለጫ የሆነው የቋንቋ ኣያያዛችንና ኣጠቃቀማችን ጉዳይ በዚህ ንድፈ ኣሳብ መሰረት እንዴት ይሆናል? የሚለው ጉዳይ ይታወሳል። በ CCU ንድፈ ኣሳብ መሰረት ኢትዮጵያ ከኪዳኗ የሚቀዳ ኣዲስ የቋንቋ ማኔጅመንትና ኣጠቃቀም ተግባራዊ ታደርጋለች ይህ ኣጠቃቀምና ማኔጅመንት የሚከተለውን ይመስላል::

5.1.4.አዲስ የቋንቋ ማኔጅመንትና ኣጠቃቀም ዘዴ

በቀጥታ ወደ CCU የቋንቋ አጠቃቀም ዘዴ ከማምራታችን በፊት በዚህ በቋንቋ አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ አንዳንድ ምሁራን የተለየ አሳብን እያራመዱ ይገኛሉ። እነዚህ ጥቂት ምሁራን የሚሉት ኢትዮጵያ ከሰማኒያ በላይ ቋንቋዎችን ይዛ መቀጠል የለባትም ነው። እንዴውም ቶሎ ቶሎ ብላ እያረገፈች ሄዳ ሁለትና ሶስት ቋንቋዎች ይበቃሉ ይላሉ። ቋንቋን ከመሳሪያነቱ በላይ ዋጋ አይሰጡትም። የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሁለት ቋንቋዎች ይዘው ሌላውን ማርገፋቸው የሚጠቅመው ለተግባቦት፣ ከዚያም ደግሞ የቋንቋ ልዩነትን ተገን እያደረገ የሚመጣን እምቅ ግጭቶች ይቀንሳል የሚል ስሌትም ያላቸው ይመስላል። ብቻ የቋንቋን ብዛት እንደ ሃብት እንደ በጎ ነገር አያዮትም። የዚህ አሳብ ችግር የኢትዮጵያን ፍላጎት አለመረዳት ነው። ምን አልባት አሳቡ እንደተባለውም ጥሩ ይሆን ይሆናል። ነገር ግን የመፍትሄ አሳቦች ሁሉ መፍትሄ ይሆናሉ ማለት ግን አይደለም። ፍላጎት መታየት አለበት። የኢትዮጵያ ቡድኖች ቋንቋቸው እንዲጠፋ ስምምነት ውስጥ አይገቡም። ቋንቋቸውን ለኢትዮጵያ ሰውተው ግን ተጠብቆ እንዲኖር ነው የሚሹት። እንዴውም ይልቁን በቋንቋቸው በምልአት እንዲጠቀሙ የሚያደርግ ሲስተም ነው የሚሹት። እነዚህ ቋንቋን ቀንሰን እንቀጥል የሚሉ ወገኖች የሜልቲንግ ፓት ትምህርት ተከታይ መሆናቸው ነው። ብዙህነትን ያለ መቀበል አዝማሚያ ይዟቸው ነው። ይህ ግን ችግሮች አሉት። በመሰረቱ ልማት የሚፈጥነውም ቡድኖች በቋንቋቸው ሲጠቀሙ ነው። ቋንቋ ደግሞ አንድ የቡድኖች ትልቅ የፈጠራ ውጤት ነው። ከሁሉ በላይ የዘውጎች ዋና መገለጫ ነው።

ሌላ በኩል የወቅቱን የመንግስትን የቋንቋ አያያዝ በተመለከተ በተለይ ዜጎችን ወደ ጎን በሚያስተሳስረው የማህበር ቋንቋ ላይ አይጨነቅም። ይሄ ደግሞ ሃገራዊ ትስስር እንዳይጠነክር የሚያደርግ ግዙፍ ችግር ነው።

በCCU ማእቀፍ ውስጥ ስንገባና ቡድኖች አዲስ ኪዳን ሲያደርጉ መጀመሪያ ላይ በገባነው ኪዳን መሰረት ቋንቋዎች ሁሉ የኢትዮጵያዊነት ናቸው። አንድ ቡድን የኔ የብቻየ የሚለው ሃብት የለም ማለት ነው። ባህል፣ ታሪክ፣ መልክዓ ምድር፣ ቋንቋ ሁሉ ሃብትነታቸው የኢትዮጵያ ሆኖ ግን ቡድኖች ደግሞ የማሳደግ ሃላፊነት አለባቸው። ከዚህም በላይ ደግሞ የቡድኖች ኪዳን ቀጥታና ተዋረዳዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር መሳሪያ ቋንቋ ነው::

በአጠቃላይ ግን ኢትዮጵያ ኦፊሺያል ቋንቋ እዴት ልትመርጥ ትችላለች? ብሄራዊ ቋንቋስ ሊኖራት አይገባም ወይ? የሚል ጥያቄ ስላለ በሚከተለው ዘዴ ብንጠቀም የተሻለ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ከአለም አሰራር ትንሽ እንማር። አገሮች ሁሉ የተለያየ የቋንቋ አጠቃቀም ፖሊሲዎች አሏቸው። በዚህ ቋንቋ አጠቃቀም ዙሪያ ውይይት ሲነሳ በተደጋጋሚ የሚነሱ ስያሜዎች አሉና በመጀመሪያ ስለነዚህ ስያሜዎች መግለጫዎችን እንመልከት ።

ብሄራዊ ቋንቋ

ብሄራዊ ቋንቋ ሲባል አዘውትሮ የሚሰጠው ትርጉም በአንድ የሃገር ግዛት ውስጥ መግባቢያ ሆኖ ከማገልገሉ ባሻገር የብሄራዊ ማንነት መገለጫ ተደርጎም ይታያል። ለምሳሌ ያህል ስዊዘርላንድን ብንወስድ አራት ቋንቋዎቿ ማለትም ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛና ሮማንኛ ብሄራዊ ቋንቋ ናቸው። በአንጻሩ ብዙ ሃገሮች በዓለም ላይ ብሄራዊ ቋንቋ የላቸውም። ይህ ማለት ብሄራዊ ማንነታቸውን ከቋንቋ ጋር አያጣብቁም ማለት ነው። ቋንቋን እንደ መግባቢያ መሳሪያ ከማየት ውጭ የብሄራዊ ማንነት መገለጫ አድርገው አያራግቡትም። በህገ-መንግስቶቻቸውም ላይ ብሄራዊ ቋንቋ የሚል አያስገቡም። አሜሪካንን ብናይ ብሄራዊ ቋንቋ የምትለው የለም። እንግሊዝ ራሷ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ፈጣሪ ብትሆንም እንግሊዘኛ ብሄራዊ ቋንቋየ ነው ብላ አላወጀችም። በአጠቃላይ ያለው ሰፊ ብያኔ ግን ብሄራዊ ቋንቋ የሚባለው በአንድ ሃገር ውስጥ አብዛኛው ህዝብ የሚናገረው ተደርጎ ይወሰዳል። ይሁን እንጂ በዚህ ዙሪያ ወጥ የሆነ ዩኒቨርሳል ብያኔ አናገኝም።

ኦፊሺያል ቋንቋ

በዓለም ላይ ብዙዎቹ አገራት አንድ ኦፊሺያል ቋንቋ አላቸው። ይህ ቋንቋ የመንግስት ቋንቋ ሲሆን በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ አገልግሎት የሚሰጥበት ቋንቋ ነው። በዓለም ላይ ወደ ሃምሳ አራት አገሮች ኦፊሺያል ቋንቋቸው እንግሊዘኛ ሆኗል።

የስራ ቋንቋ

በአንዳንድ አገሮች ኦፊሺያል ቋንቋ ብሄራዊ ቋንቋና የስራ ቋንቋ የተደባለቀ ትርጉም ነው ያላቸው። በተባበሩት ህዝቦች ድርጅት ውስጥ ግን እነዚህ ሁለት ስያሜዎች የተለያየ ትርጉም አላቸው። በUN ውስጥ ኦፊሺያል ቋንቋ የሚል ደረጃ ያገኙት ቋንቋዎች ስድስት ሲሆኑ እነዚህም ቻይንኛ፣ አረብኛ፣ ሩሲያኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ስፓኒሽና ፈረንሳይኛ ናቸው። እነዚህ ቋንቋዎች ኦፊሺያል ናቸው ማለት በዚህ ድርጅት ውስጥ ስብሰባዎች ሲኖሩ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ናቸው ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪም የድርጅቱ ዶክመንቶች በነዚህ ቋንቋዎች እየተተረጎሙ የሚሰራጭበት አሰራር ነው ያለው። እንግሊዘኛና ፈረንሳይኛ ደግሞ የስራ ቋንቋ ሆነው በሰፊው መስሪያ ቤቱ ይጠቀምባቸዋል::

ዲፋክቶ ቋንቋ

ህጋዊ ባይሆንም በሃገሪቱ ቋንቋው እየተሰራበት ያለ ሲሆን ዲፋክቶ ይባላል።

የማህበር ቋንቋ

ህንድ በነገራችን ላይ የማህበር ቋንቋ የሚባል ያላት ሲሆን ይህ የማህበር ቋንቋዋ ሂንዱ ነው። አንዳንድ አገሮች ብሄራዊ ቋንቋ እንደሚሉት አይነት ነው። ህንድ የራሷ የሆነ ስያሜ ፈጥራ ነው ብሄራዊ ቋንቋ የሚባለውን የህብረት ቋንቋ ያለችው። መስፈርቱ አብዛኛው ሰው ስለሚናገረው ነው። በአጠቃላይ አንዳንድ ሃገሮች ብሄራዊ ቋንቋ የሚባል ያላቸው ሲሆን ሌሎቹ ግን ኦፊሺያል ቋንቋ ነው ያላቸው።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ አማርኛ የፌደራል ቋንቋ ሲሆን ኦፊሺያል ቋንቋም ሆነ ብሄራዊቋንቋ የሚባል ወጥ የሆነ የለንም። ክልሎች በራሳቸው ቋንቋ የሚጠቀሙ ሲሆን አንዳንድ ክልሎች አማርኛን መርጠው እንደሚጠቀሙ ይታወቃል። በኢትዮጵያ ውስጥ የብሄራዊ ቋንቋ ጉዳይና የኦፊሺያል ቋንቋ ጉዳይ ሲነሳ ኦሮምኛ ብዙ ይሰማበታል። ብዙ የኢትዮጵያ ህዝብ ኦሮምኛ ተናጋሪ ሆኖ ሳለ ለምን ኦፊሺያል ቋንቋ ወይም የፌደራል ቋንቋ አይሆንም? የሚል ክስ ይሰማል። በርግጥ ጥያቄው ፍትሃዊ ነው። አሁን ስናስበው ግን ኦሮምኛ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የቋንቋ አጠቃቀማችንን ብናሻሽል አይሻልም ወይ? ሌሎቹስ ብዙ ህዝብ የማይናገራቸው ቋንቋዎች በተሻለ ደረጃ እንዴት መጠቀም እንችላለን? በሚለው ላይ መወያየት ጥሩ ነው። የቋንቋ ጉዳይ ሲነሳ የአንድ የሁለት ቡድንን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁሉን ቡድን ቋንቋዎች ከፍ የሚያደርግ አሰራር በማምጣት የሁሉን ጥያቄ መፍታት መልካም ነው።

ኢትዮጵያ የቋንቋ ሃብቶቹዋን በተሻለና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ትችላለች። ይህ ዘዴ የቋንቋ ሃብቶቿን ለመጠበቅና ጎናዊ የቡድኖችን ግንኙነት ለማዳበር ይረዳታል። በመሆኑም በስባአ ኪዳን መሰረት ኢትዮጵያ ብሄራዊ ማንነቷን ከቋንቋዎቿ ጋር ልታገናኝ ትችላለች። እንዴውም ጥሩ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ሃብቶች ሁሉ በላይኛው ኪዳን ጊዜ ለኢትዮጵያዊነት ስለተሰው የአንድነት መገለጫ ይሆናሉና የሁሉም ቡድኖች ቋንቋዎች በህገ-መንግስት ተመዝግበው የብሄራዊ ቋንቋነት ስያሜ ሊሸለሙ ይገባል። የብሄራዊ ቋንቋነት ስያሜ ጉዳይ የረቀቀ የብሄራዊ ማንነት መገለጫ በመሆኑ ይህን የማንነት ምልክትነት ለምን ለሁሉም ቋንቋዎች አንሰጥም? ይህ ሲምቦሊክ የሆነ አንድነትንና ብዙነትን የሚያሳይ በመሆኑ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋዎቿ ብዙ ቢሆኑ መልካም ነው። ቋንቋዎች ሁሉ የኢትዮጵያ በመሆናቸውና

ለዚህም ስለተስማማን ሁሉም ቋንቋዎች የብሄራዊነት ቋንቋ ደረጃ ሊጎናጸፉ ይችላሉ። በኢትዮጵያ ሁኔታም ብሄራዊ ቋንቋ የሚለው አሳብ በዚህ አቅጣጫ ብያኔ ቢሰጠው ጥሩ ነው። ኢትዮጵያ ባለ ሰማኒያ በላይ ብሄራዊ ቋንቋዎች ያሏት አገር ትባላለች። ይህም ያስከብረናል። የብሄራዊ ቋንቋ ጉዳይና የኦፊሺያል ቋንቋ ጥያቄም አርኪ መልስ ያገኛል። ቋንቋው ከመሳሪያነት አልፎ ፖለቲካዊ አንድምታ ይዞ ለመጣው የብሄራዊ ማንነት ጉዳይም መልስ ይሰጣል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከድህነት ለመላቀቅ ኮሙኒኬሽናችንን ለማስተካከል ቋንቋዎቻችንን በሚገባ መጠቀም ያሻልና ኢትዮጵያ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የህብረት ቋንቋ ቢኖራት መልካም ነው። ይህ ቋንቋ ደግሞ አማርኛ ቢሆን ጥሩ ነው። የህብረት ቋንቋ አማርኛ መሆን ያለበት በጽሁፍ የዳበረ ብዙ ሰው የሚናገረው በመሆኑ ነው። በአንጻሩ ኦሮምኛም አንዱ የህብረት ቋንቋ ሆኖ ከአማርኛ ጎን ለጎን የሚሰራበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንችላለን። ከዚህ በፊት ሌሎች ቋንቋዎች ጨምሮ ለምን ኦፊሺያል አናደርግም ብየ ብዙ አስቤ አውቃለሁ ይሁን እንጂ ሁሉንም ኦፊሺያል ማድረግ እስከቻልን ድረስ፣ ሁሉንም ብሄራዊ ማድረግ እስከቻልን ድረስ የብሄራዊ ቋንቋነት ስታተስ ጉዳይ አሳሳቢ ጥያቄ አይሆንም።

የፌደራሉ ወይም የህብረቱ ቋንቋ በአራቱም ማእዘናት የሚገኙ የመንግስት መስሪያቤቶች አገልግሎት የሚሰጡበት ቋንቋ ይሆናል። የህብረት ቋንቋው ለብቻው እንደ ብሄራዊ ማንነት መገለጫ ግን አይታይም። ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር አብሮ ብሄራዊ ቋንቋ የሚለውን ረቂቅ የፖለቲካና ማህበራዊ ማንነት መገለጫነት ቀድሞ ያገኘ ቢሆንም አሁን በዚህ በማህበር ቋንቋነቱ ግን እንደ መሳሪያ የጋራ መግባቢያ ይታያል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በማዘጋጃ ቤት ወይም በወረዳዎች አካባቢ አንድ ተጨማሪ ኦፊሺያል ቋንቋ ይኖራል። ይህ ማለት እያንዳንዱ ወረዳ ወይም ማዘጋጃ ቤት በአካባቢው የሚነገረውን ቋንቋና የህብረቱን ቋንቋ በአንድነት የኦፊሺያል ቋንቋ ያደርጋል ማለት ነው። በወረዳና ቀበሌ ደረጃ ዜጎች ከሁለት አንዱ ቋንቋ በመረጡት አገልግሎት ያገኛሉ ማለት ነው። በዚህ መሰረት ሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ኦፊሺያል ቋንቋና ብሄራዊ ቋንቋ ይሆናሉ ማለት ነው።ይህ አሰራር የሚኖረው ጠቀሜታ የቋንቋ አሰራራችንን ማሻሻል ብቻ ሳይሆን ቡድኖችን በብሄራዊና በአካባቢ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ፣ የእኩልነት ተምሳሊት ይሆናል። ቡድኖች ይኮራሉ፣ ሃገራቸውን ይወዳሉ። መዋጥ አይሰማቸውም።

ይህ አሰራር ቋንቋዎችን ሁሉ ወደ ቢሮዎች፣ ወደ ሲስተም ስለሚወስዳቸው ከቴክኖሎጂና ከሰዎች ንቃተ ህሊና ጋር እያደጉ እንዲሄዱ ያደርጋል። የመግለጽ ችሎታቸው ይጨምራል። የቃላት ምህዳራቸው ይሰፋል። ሌላው ጉዳይ በተለይ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት አካባቢ ልጆች ትምህርታቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ማድረጉ ለቋንቋው እድገትና ለተማሪዎቹ ትልቅ ሚና ያለው ሲሆን እዚሁ ጋር መረሳት የሌለበት ጉዳይ የማህበሩን ቋንቋም በማካተት ልጆቹ ባለ ሁለት ቋንቋ ባለቤት (bilingual) ሆነው እንዲያድጉ መደረግ አለበት። በሁለቱም ቋንቋዎች የመጻፍ፣ የማንበብ፣ የመናገር፣የማዳመጥ ክህሎቶቻቸው ከፍተኛ እንዲሆን መስራት አስፈላጊያችን ነው። በሌላ በኩል ሁሉንም ያገራችንን ቋንቋዎች ተረባርቦ የጽሁፍ ቋንቋ እንዲኖራቸው ፊደል እንዲቀረጽላቸው ያስፈልጋል። እነዚህ የጽሁፍ ቋንቋ የሌላቸው ቋንቋዎች ማህበረሰብ አባላት የቡድኑን ታሪክ በአብዛኛው ያቆዩት በስነ-ቃል አማካኝነት እየተቀባበሉ ነው። አንዱ ትውልድ ለአንዱ በቃል እያቀበለው የሚቆይ ታሪክ ደግሞ በቅብብሎሹ መሃል መዛባቶች ሊገጥሙት ስለሚችሉ እነዚህን ሰነ-ቃሎች ወደ ጽሁፍ በመቀየር ታሪክን የማቆየት ስራ ለመስራትም ይረዳል።

በሌላ በኩል ስለቋንቋ ስናወራ ኢትዮጵያ ትልቅ ትኩረት ልትሰጥበት የሚገባው ጉዳይ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ጉዳይ ነው። ዓለም በጣም እየተቀራረበች ከመሄዷም በላይ አብዛኛው መረጃ በዓለም መረብ ላይ ያለው በእንግሊዘኛ በመሆኑ ትውልዱ ከአፍ መፍቻው ቋንቋና ከማህበሩ ቋንቋ በተጨማሪ እንግሊዘኛን ጠንክሮ መማር ያስፈልገዋል። አገሪቱ ያላትን ራእይ ለመፈጸም፣ በአለም ኮሙኒኬሽን ጉዳይ ብቁ እንድትሆን ዜጎችን እንግሊዘኛ ማስተማር ተገቢ ነው።

ዛሬ በዓለም ላይ የእንግሊዘኛ ተናጋሪው ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ የመጣ ሲሆን ኢትዮጵያም በዚህ ርምጃ ውስጥ ፈጣን መሆን አለባት። የእንግሊዘኛ አካዳሚዎችን መክፈት፣ የእንግሊዘኛ የማስተማሪያ መሳሪያዎችን፣ ዘዴዎችንና ስርዓተ ትምህርቱን ማስተካከል፣ መምህራንን ብቁ ማድረግ፣ የፒስ ኮር ኣገልግሎቶችን ማስፋትና ማጠናከር በጣም ወሳኝ ነው። ብዙ ጊዜ የእንግሊዘኛ ትምህርት ችግር ሆኖ የሚታየው ራሳቸው አስተማሪዎቹ እንግሊዘኛ በሚገባ መናገር ሳይችሉ ማስተማራቸው ነው። ስለዚህ ኮሌጆች በተለይም የእንግሊዘኛ ቋንቋ አስተማሪዎችን የሚያመርቱቱ በጣም ሊጠነክሩ ይገባል። ለመነሻ ኔቲቭ መምህራንን ጨምረው እንግሊዘኛ ተናጋሪ አስተማሪዎችን ማፍራት ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የብሄራዊ ቋንቋ፣ የኦፊሺያል ቋንቋና የህብረት ቋንቋን በሚመለክት የራሷ የጠራ ትርጓሜና አጠቃቀም ኖሯት የቋንቋ ሃብቶቿን ፍትሃዊ በሆነና ለአገልግሎት በሚመች መንገድ አደራጅታ ልትጠቀም ትችላለች። ይህ ኣሰራር ትንሽ የኢኮኖሚ ዋጋን ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። ነገር ግን ኣንድ ማየት ያለብን ነገር በትምህርት ኣሰጣቱ ሂዳት ቡድኖች ወደ ማህበሩ ቋንቋ ሊያዘነብሉ ይችላሉ። ከዚህ በላይ ግን ዜጎች ሁለት ቋንቋ ተናጋሪ እየሆኑ ሲመጡ ዋጋው እየቀነሰ ይመጣል። ከሁሉ በላይ ግን የቡድኖች መብት ነውና ከሚኖረው ጥቂት የኢኮኖሚ ውድነት በላይ የዘውጎች ህልውና እንዲሁም ዜጎች በቋንቋቸው ፍትህ የማግኘታቸው ነገር ትልቅ ዋጋ ኣለውና ኣገራችን ይህንን የቋንቋ ኣሰራር መጠቀም ኣለባት። ቡድኖች በቋንቋቸው መገልገል ካለመቻላቸው የሚመጣው አንዱ ኪሳራ የኢኮኖሚ ችግር ነው። አምራች ዜጋ ለማፍራት ቋንቋ ወሳኝ ነው። ስለሆነም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ስናየው የቋንቋ ኣጠቃቀማችን በዚህ መንገድ ሲሻሻል ኣገራችን የተሻለ መረጋጋትን ስለምታመጣ በኢኮኖሚያችን ላይ እንዴውም መልካም ተጽእኖ ያመጣል።

የቋንቋ አጠቃቀም ማሳያ
ፌደራል መንግስት
የህብረት ቋንቋ
ክልል ወይም ስቴቶችወይም የመካከለኛ የመንግስት ስልጣን ርከን
የህብረት ቋንቋ +በክልሉ ብዙ ህዝብ የሚናገረው ቋንቋ

በታችኛው የመንግስት የስልጣን ርከን
የህብረት ቋንቋ+ የአካባቢ ቋንቋ
ክልል ወይም ስቴቶችወይም

5.1.2. የአዲሱ ቃል ኪዳን ዋስትናዎችና ተግዳሮቶች

የዋስትና ጥያቄ

በመጀመሪያ ወደ ኪዳኑ ለመግባት ዋስትናዎቻችን ምን ምን ናቸው? በሚለው ላይ እንወያይ። ስለዚህ ስለ ኣዲሱ ኪዳን ወይም በስምምነት ላይ ስለተመሰረተ ባህላዊ ኣንድነት ጉዳይ ስናወራ የሚነሱ ጥያቄዎች ይኖራሉ። ኣንደኛው ጉዳይ የዋስትና ጥያቄ ነው። ቡድኖች ወደዚህ ከፍተኛ ኪዳን ይገቡ ዘንድ የሚነሳው የዋስትና ጥያቄ የሚመነጨው መጀመሪያ ላይ ያነሳነው ጉዳይ ተመልሶ እንዳይመጣ ነው። ይህም የቡድኖች ማንነት እንዳይጨፈለቅና ሁለተኛ ደግሞ በቡድኖች እውቅና ስም ብሄራዊ ማንነታቸው እንዳይጨፈለቅ ነው። በመሆኑም ቡድኖች ኪዳን ሲገቡ ኣንዱ ትልቁ ዋስትናቸው የሚፈጠረው ሲስተም ራሱ ነው። ሲስተሙ ባህላዊ ኣስተዳደርንና ፖለቲካዊ ኣስተዳደርን መለየቱ ሁለቱንም ማንነቶች እየተንከባከቡ ለማኖር ስለሚያስችል ዋስትና ይሆናል። የቡድኖች ሁሉ ቋንቋ ኦፊሺያልና ብሄራዊ መሆኑ አንዱ ዋስትና ነው። የቋንቋው ሲስተም ለቡድኖች መኖር ዋስትና ነው። ቡድኖች ያላቸውን ሁሉ ኣዋጥተው ኣገራቸውን ለመገንባት ዋስትና ሲሹ ይህ ሲስተም ዋስትና ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኪዳኑ ራሱ የቡድኖች ዋስትና ነው። የማይናወጥ ኪዳን ስለሆነ። ሄራው ማለትም መሰረታዊ ህጉ የመሻሻል እድል ኣለው። ኪዳኑ ግን ሃውልት ተቀርጾለት የሚቀመጥ ጉዳይ በመሆኑ ቡድኖች ይህንን ኪዳን እንደ ብሄራዊ ማንነት መገለጫና ዋስትና ያዩታል። በየአመቱም የኢትዮጵያ አዲስ ኪዳን ቀን እየተባለ ይከበራል። ስለዚህ በኣጠቃላይ ዋስትናችን የቋንቋ ኣጠቃቀማችን፣ ኣዲሱ የአገር ኣስተዳደር መዋቅርና ራሱ የምንገባው ኪዳን ይሆናል ማለት ነው።

ያለፈ የታሪክ ትዝታዎች ጉዳይ (Past bad memories)

በዚህ በCCU ኣመለካከት ወደ ኣዲስ ኪዳን ለመግባት ያለፉ የታሪክ ትውስታዎቻችንን ሁሉ በጋራ መግባባት (mutual understanding) ነው የምንፈታው። በመሆኑም ወደ ኣዲስ ኪዳን ለመግባትና ቡድኖች ያላቸውን ሁሉ መስዋእት ለማድረግ ባለፈ ታሪክ ጠባሳዎቻቸው ላይ ከፍ ያለ መረዳት ውስጥ እንዲገቡ ይመክራል። ኣጠቃላይ የአለምን ተመክሮ ማየት፣ ኢትዮጵያን ከዓለም ነጥሎ ኣለማየት፣ እስካሁን ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታት መስማማት ወሳኝ ነው።ከሁሉ በላይ በታሪክ አጻጻፍ በኩል አገራችን ውዝግብ ውስጥ መግባቷንና ታሪክን ለፓለቲካ ፍጆታ ሲባል የተሰሩ ስራዎችን ከግንዛቤ ማስገባት ያስፈልጋል። በተጨማሪም በኣጠቃላይ ስለ ኣለፈ ታሪክ ስናወራ የዓለምን ታሪክ እናያለን። ለምሳሌ ምእራብ ጀርመንና ምስራቅ ጀርመን ልዩነት ሲያምራቸው ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ጀምረው ነበር። አንዱ የጀርመኖችን ፖለቲካ ያራራቀውም ይሄው ነበር።

በተለይ በናዚ ወቅት የተፈጸመውን የሆልኮስት ዘር ማጥፋት ወንጀል በተመለከተ ታሪኩን ሁለቱ ጀርመኖች በተለያየ መረዳት መተርጎም ከመጀመራቸው አልፎ በርሊንና ቦን ሁለት ሙዚየሞች ቆመው የተለያየ ነገር ማስተማር ጀምረው ነበር። ያለፈውን ታሪክ ለማስታወስ የፈለጉበት ሞቲቭና ታሪኩን ወደ ትውልድ ለማሳለፍ የሞከሩበት ዘዴ ይለያይ ነበር።

ባለፈው ጊዜ ዶክተር መረራ ጉዲና ጥሩ ነገር ተናግረዋል። ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ አናውለው ብለዋል። በርግጥ ጀርመን ከታየው በላይ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የታሪክ መሰረት የሚያምስ ሁኔታ ተፈጥሩዋል። ይህ የሆነው የማንነት ፖለቲካን ለማራገብ ታሪክ መሳሪያ ሆኖ በመቅረቡ ነው። በርግጥ አንድ ሃገር ሲቆም ያለፈን ትውስታ ወዴትም አንጥለውም። ነገር ግን ትውስታችንን የምናይበትን መንገድ ማስተካከል አስፈላጊ ነው።

ስባአ አመለካከት በኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት በመመስረቱ ሂደትና ከተመሰረተ በሁዋላ የተፈጸሙ በጎም ሆኑ መጥፎ ታሪኮች ሁሉ የኢትዮጵያ ትውስታዎች ናቸው። ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ትውስ የሚላት ታሪክ ነው። በጎ በጎውን መርጠን የመታሰቢያ ቀን አቁመን የጋራ ታሪካችን እያልን እየሞቅን መጥፎውን ነቅሰን አውጥተን ለአንድ ቡድን አናላክክም። ሁሉም የኢትዮጵያ ታሪክ ነው። የሚያሳዝነው ያሳዝነናል፣ የሚያስደስተው ያስደስተናል። ባለፉት ጊዚያት በግልም ይሁን ቡድንን እየለየ የተፈጸመ በደል ሁሉ የኢትዮጵያ ትውስታ እንጂ ያ በደል የተፈጸመበት ቡደን ቋንቋ ተናጋሪና አባል ብቻ አይደለም። በዳይና ተበዳይ በህይወት የሉም። ይሁንና እኛ ዛሬ ላይ ያለን ዜጎች ህማምንም ደስታንም እንካፈላለን።

ሌላው ታሪክን በሚመለከት የዓለም ህዝብ ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚያያትም መታወቅ አለበት። ከአጠቃላዩ የዓለም ህዝብ ወደ 54.9 በመቶ የሚሆነው የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖተኛ ሲሆን ኢትዮጵያን የሚያያት በረጅም ጊዜ ታሪኳ ነው። ክርስቲያኑ በሃዋርያት ስራ ላይ የተገለጸውን ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ዋቢ በማድረግ ክርስትናን የተቀበለች ከዓለም ቀደምት አገር ናት ብሎ ያከብራታል። በብሉይም ስሙዋ የተጠቀሰ ተስፋ ያላት አገር አድርጎ ስለሚያምን ተስፋዋን ይጠብቃል።። ሙስሊሙ ህበረተሰብ ደግሞ ለመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች መጠጊያ ለመሆን የበቃች አገር ብለው ስለሚያምኑ እንደዚሁ በሙስሊሙ ህዝብም ዘንድ ታዋቂ ናት። ይሄ ከፍተኛ ተጽእኖ ያለው ታሪክ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም ህዝብ እንዲህ እንደሚያያት መገንዘብ ጠቃሚ ነው። ሌላው ያሉን ቁሳዊ ባህሎች እንደ ላሊበላ፣ አክሱም በደቡብና ኦሮሚያ የሚገኙ ሃውልቶች ሁሉ የኢትዮጵያን እድሜ ይናገራሉ። እነዚህ ታሪኮች ሁሉ የጥንታዊቱን ኢትዮጵያን ትውስታ እየሰጡን እንኖራለን። ኢትዮጵያ በረጅም ጊዜ ታሪኳ ስትሰፋና ስትጠብ ብትቆይም ኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያዊነቷ ግን ብዙህ ሺህ ዘመን ታሪክ ያላት ኣገር ናት። በአጠቃላይ በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት ያለፈውን ታሪክ እንደ ወል ታሪክ የሚያይ ይሆንና የሚከተሉትን ጉዳዮች በጥብቅ ይመረምራል። ይህም ታሪኩ ታሪክ ሆኖ መቅረት ብቻ ሳይሆን አሁን ድረስ ይጎተታል ወይ? የሚለውን ያያል። በተለይ መጥፎ የምንለው ታሪክ አሁንም ካለ ይህን ታሪካዊ ዳራ ያለውን ችግር በሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ እና በተለያዩ ማስተካከያ ርምጃዎች ይፈታል።

በአጠቃላይ ያለፈውን ታሪክ የምናስታውሰው የወል ታሪክ አድርገን ሲሆን ይህንን የወል ታሪካችንን እንደ የወልነቱ ስናየው ትውስታችንን በጥሩ ሚዛን ላይ ያስቀምጠዋል። ከዛሬ መቶ አመት በፊት የነበረውን ታሪካችንን ስንተነትን ኢትዮጵያን ለብቻዋ ንጥል አድርገን በዓለም ሳለች ከዓለም አውጥተናት ሳይሆን ከአለም የሰው ልጆች ታሪክ ጋር እያገናዘብን መፍረድ አለብን። ሌላው አሁን ያለንበት ከባቢስ ምን ይመስላል? በምን አይነት የፖለቲካና ማህበራዊ ከባቢ ውስጥ ሆነን ነው ታሪክን የምንተነትነው? ብለንም መጠየቅ አንዱ ለፍርድ በተሻለ የሞራል ደረጃ ላይ የሚያስቀምጠን ነው። ሌላው ማየት ያለብን የትውስታችን ፍላጎት ምንድነው? በታሪክ መረዳታችን ምን ልናደርግበት ነው? ብለን መጠየቅም መልካም ነው። በርግጥ ያለፉ ታሪኮችን አንስተን በቀልን ልናቅድ ነው? ወይስ የተሻለ አሰራር ለማምጣት መልካም እልህ ውስጥ ሊከተን ነው? ብለን መጠየቅ አለብን የሚል ምክር ይህ የባህላዊ ውህደት አሳብ አዝሎአል። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በርግጥ አገሪቱን ወደ ተሻለ ልማትና ሰላም ለመምራት ከፈለጉ መጀመሪያ ማስተካከል ያለባቸው ያለፈ ትውስታን ነው። አሁን የምንመራውና የፖለቲካ ርእዮቶቻችን የቆሙት በባለፈ መጥፎ ትውስታዎች ላይ ነው። ይሄ ደግሞ ሚዛናዊ አይደለም። የብሄር ፌደራሊዝም ያለፈ ትውስታን ለመበቀል የመጣ ፖለቲካ ነው እንጂ ወደፊት ለመራመድ የሚያስችል ኣይደለም። ያለፈ መጥፎ ትውስታዎችን የምናይበትና የምንገመግምበት አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን መለወጥ ያለበት የወደፊቱን አቅጣጫ ለመተለም ያለፈን መጥፎ ትውስታ ሃይል አድርጎ መታጠቁንም ነው። ያለፈው ትውስታ በጎውን የጋራ እንደምንለው ሁሉ ክፋቶችንም የጋራ አድርገን የተሻለ ስርዓት ለመዘርጋት መነሳት ይኖርብናል። ብዙው ጊዜ ያለፈው አይደለም። የሚመጣው ጊዜ ነው ብዙው ጊዜ። ስለዚህ ስባአ ትውስታዎቻችንን ሚዛናዊ እንድናደርግ ነው የሚመክረው። ፖላቲካችንን በመጥፎ ትውስታዎች ላይ ማቆም ጥሩ አይደለም። ከሁሉም በላይ መጥፎ ትውስታዎችን ይዘን ወደ ብሄር ፖለቲካ ስንገባ ደግሞ እነዚህን መጥፎ ትውስታዎች ከአንድ ባህላዊ ቡድን ወይም ብሄር ጋር አጣብቀን እንድናይ ስለሚያደርግ ሊወገዝ ይገባዋል። ፖለቲካ በአብዛኛው በአገር ጥሩ ትዝታዎች ላይ ነው ሊቆም የሚገባው። አንዱ ለሶሻሊዝም ስርዓት መውደቅ ምክንያት የሚመስልው በበቀልና በመጥፎ ትዝታዎች ላይ በመመስረቱ ነው። ዓለም ሁሉ በታሪኩ በውጣ ውረድ ውስጥ አልፏል። አንዱ አንዱን በድሏል። ግን የሆነ ዘመን ላይ አስተዋይ መሪዎች እግዚአብሄር የሰጣቸው ህዝቦች ያለፈ መጥፎ ትውስታን ለበጎ ይለውጣሉ። ይቅርታንና መረዳዳትን ያስቀድሙና የነፍስ ጽዳትን ያመጣሉ። እንዲህ ያደረጉ መሪዎች አገራት በፍጥነት ወደ ዴሞክራሲ አድገው አገራቸውን ሲለውጡ ይታያል። በአንጻሩ በአለፈው መጥፎ ትውስታዎች ዙሪያ ሲዞሩ የሚኖሩ መሪዎችና ፖለቲከኞች በበዙበት አገር ደግሞ እንዲሁ ሲነታረኩ ይኖራሉ። በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን ለመልካም ትውስታዎች መጠበቂያ እየሰራንላቸው መጥፎዎቹን ደግሞ እንዳይደገሙ እየጣርን ሲንከባለሉ ለመጡት ደግሞ መፍትሄ እየሰጠን ካልሄድን ከገባንበት ችግር መቼም አንወጣም።

ብሄራዊ እርቅ በኢትዮጵያ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ብሄራዊ እርቅን የምንረዳው ግን በሌሎች አገር ሲደረግ የሰማነውን በቀጥታ ወስደን አይመስለኝም። በኢትዮጵያ ሁኔታ ብሄራዊ እርቅ ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ መወያየት አለብን ይመስለኛል። በብሄራዊ እርቅ ጊዜ አንዱ የማስታረቂያ ጥበብ ከፍ ሲል ያልነው ታሪክን ደስታንና ህማምን የጋራ አድርጎ ማየት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የዓለምንም ታሪክ መዳሰሱ መልካም ነው።ይህን በተመለከተ ከዚህ በፊት የጻፍኳትን ጦማር ትንሽ ከርክሜ እንደሚከተለው ላቅርብ።

ብሄራዊ እርቅ በአለማችን ታሪክ ውስጥ በብዙ አገሮች የተፈጸመ ሲሆን የእርቁ ትርጓሜና አፈጻጸም እንዲሁም ግቦች ሁሉ ሊለያዩ ይችላሉ። እኛ ኢትዮጵያዊያን ወደ ብሄራዊ እርቅ ለመግባት መጀመሪያ ብሄራዊ እርቅ በኢትዮጵያ ሁኔታ (context) ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ ካልተረዳን ብሄራዊ እርቁ ግቡን ላይመታ ይችላል። ወይም ደግሞ ለብሄራዊ እርቁ ሁሉን ማሳተፍ አንችልም። በመሆኑም ብሄራዊ እርቅ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ጉዳይ አንስተን በሚገባ እንወያይ። ሃሳባችንን ለማፋፋት ብሄራዊ እርቅን ከአንዳንድ ሃገሮች ታሪክ አንጻር በመጀመሪያ እንመልከት።

ለምሳሌ ያህል በአውስትራሊያ ውስጥ የብሄራዊ እርቅ ጉዳይ ተነስቷል። እንደሚታወቀው ከታላቋ ብሪታኒያ የአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ሰፈራ ፕሮግራም በፊት አውስትራሊያ በነባር (indiginious) ህዝቦች የተያዘች አገር እንደነበረች ይታወቃል። በሰፈራው ጊዜ በነባሮቹ ህዝቦች ላይ የመፈናቀል፣ የማንገላታት ወንጀሎች ተፈጽመዋል። ዛሬ የአውስትራሊያ መንግስት ያን የተፈጸመ ታሪካዊ ስህተት አመርቅዞ እንዳይቆይ የወሰደው ርምጃ ብሄራዊ እርቅ ማድረግ ሲሆን ከ 1998 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት የብሄራዊ እርቅ ወይም (National sorry day) አውጆ በየዓመቱ እየታሰበ ይገኛል። የዚህ የይቅርታ ቀን አዋጅ የሚያሳየው ነገር ላለፉት ስህተቶች ሃላፊነት የሚወስድ አካል መገኘቱንና የነበረውን ግፍ እውቅና መስጠት መቻላቸውን ለወደፊቱም እንደዚያ አይነት ግፍ እንዳይፈጸም ዋስትና መስጠታቸውን ነው። የአውስትራሊያ ችግር እንደኛ ላይታይ ይችላል። ይቅርታው ግን ለስንት አመት እንደሚደረግ አይታወቅም። ዋናው ግን በነባሩ ህዝብ ዘንድ የነፍስ ጽዳት ለማምጣት የታሰበ በመሆኑ ብሄራዊ እርቁ ለአውስትራሊያውያን ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። የነበረውን ታሪካዊ ችግር እውቅና ሰጥቶ ይቅርታ ማወጁ የአውስትራሊያን ህዝብና መንግስት ልበሰፊነትና አርቆ አሳቢነት ያሳያል። ነባር ህዝቦችም በዚህ የሚረኩ ይመስለኛል። ከዛ ውጭ አፈታሪክ እንደሚናገረው ራሳቸው ነባር ህዝቦችም ከሌላ ክፍለ ዓለም መጥተው የሰፈሩ ናቸው። ለዚህ ነው በዓለም ላይ ያልተነቃነቀ ህዝብ የለም የሚያስብለን። ርጋታና ወሰን የመጣው የተባበሩት መንግስታት ከተቋቋመ ወዲህ የዓለም ሃገራት ድንበር ጉዳይ ዓለማቀፋዊ ጉዳይ እየሆነ ከመጣ ወዲህ ከቅርብ አስርታት ወዲህ ነው። የነዚህ ነባር የተባሉ ህዝቦች ጥያቄ መሆን ያለበት በሰፈራው ወቅት የነበረው ግፍና በደል ሲሆን ለዛ ደግሞ መንግስት አዘኑን ገልጿል። ይህ ደግሞ የነባሩን ወይም ቀደም ብሎ ወደ አውስታራሊያ ያቀናውን ህዝብ ልብ የሚያሳርፍ ጉዳይ ነው። ችግሮች ተንከባለው እንዳይቀጥሉ ደግሞ እነሆ ዛሬ ተባብረው ዴሞክራሲያዊ መንግስት አቋቁመዋል:: ይቅርታው ግን አንዴ የሚበቃ ይመስላል። ከሁሉ በላይ ግን አሁን የገባኝ ነገር ቢኖር የአውስትራሊያ መንግስት ርህሩህ በመሆኑ እንጂ ባለማችን ታሪክ ውስጥ ባለፈው ስርዓት የተፈጸሙ ሁሉ በወቅቱ የነበሩ ስርዓቶች ችግሮች ነበሩ። ይሄ አለማቀፍ ክስተት ነው። ዓለም በንቅናቄ ወቅት በነበረችበት ጊዜ አጠቃላይ ከባቢው፣ የሰው ልጆች መረዳትና የኮሙኒከሽን ጉዳዮች ተደማምረው ለግፍ አጋልጠዋል። አሁን ያ ጊዜ አልፎ እነሆ የዴሞክራሲና የሰባዊ መብት ዘመን መጥቷል። ደቡብ አፍሪካን ደግሞ እንይ። በደቡብ አፍሪካም እንደዚሁ ታሪካዊ የሆነ ብሄራዊ እርቅ የተካሄደባት አገር ስትሆን ከአፓርታይድ አገዛዝ ለመላቀቅም ሆነ ከተላቀቀች በሁዋላ ደቡብ አፍሪካን በከፍተኛ የመንፈስ ልእልና ሲመራ የነበረው የብሄራዊ እርቅ ስሜት ነው። በደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ እርቅ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱት መካከል ኔልሰን ማንዴላ አውራ ናቸው። በኔልሰን ማንዴላ የተመራው ደቡብ አፍሪካን እንደገና የማነጽ ስራ ሲጀመር አገሪቱ ያለፈችበትን መራራ ችግር ለመፍታት የተጠቀመችው ዘዴ በሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ (Restorative justice) እና ቀስ እያለ በሚያድግ ዴሞክራሲ ቁስልን ማከምና የወደፊቷን የሁሉም የምትሆንን ደቡብ አፍሪካን መገንባት ይመስላል::

ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ እንደተላቀቀች ወደ ሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ (Retributive juctice) አተኩራ ቢሆን ምናልባትም ውጤታማ አትሆንም ነበር። ዋናው ጉዳይ ግን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የአፓርታይድ ገዢዎች ለነበረው ችግር ሃላፊነት የመውሰድና ብሄራዊ እርቅን በሪስቶሬቲቭ ጀስቲስና በዝግ እያለ በሚያድግ ዴሞክራሲ ለመፍታት ፈቃደኛ በመሆናቸው የጥፋትና የሞት መላእክን ከደቡብ አፍሪካ ሊያባርሩት ችለዋል። ታላቁ የብሄራዊ እርቅ መሪ ኔልሰን ማንዴላም በዚህ ረገድ የተጫወቱት ሚና ታሪክ ሁሌ ሲዘክረው ይኖራል። የደቡብ አፍሪካን ችግርም ስናይ በወቅቱ የነበረው ችግር አፓርታይድ ነበር። ጽንፈኞች ይህን ያራምዱ ነበር። ይሁን እንጂ በአብዛኛው የነጩ ማህበረሰብ ልብና ነፍስ ውስጥ ግን አፓርታይድ የተጠላ ነበር። አፓርታይድ ለመውደቁ አንዱ ምክንያትም ከጥቁሮቹ ትግል ጎን ነጩ ህዝብ ለአፓርታይድ ድጋፍ ባለመስጠቱና በመቃወሙ ነው። ስርዓቱና የስርዓቱ አራማጆች ችግር ነበር ዋናው ችግር። ኔልሰን ማንዴላ በቅርብ ይህን በሚገባ የተረዱ ነበሩ። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነጩ ማህበረሰብ በአፓርታይድ አልተጎዳም ወይም አልተሰቃየም ማለት ደጋፊ ነበር ወይም አባሪ ነበር ማለት አይደለም። አሁን ላይ ሆነው ሲያዩ የሁዋላ ትውስታቸውን ሲያዩ ነጩም ጥቁሩም ያን ጊዜ ይኮንኑት ነው የሚመስለኝ።

የሩዋንዳን ጉዳይም እናንሳ። ሩዋንዳ በዚህኛው ክፍለ ዘመን የዓለምን ህዝብ ያስደነገጠ ወንጀልን ካስተናገደች በሁዋላ ወንጀሉ ጋብ ሲል የወደፊት አቅጣጫዋ ግራ ያጋባት አገር ነበረች። ለአንድ መቶ ቀናት በየቀኑ ስምንት ሺህ ሰዎች፣ በየሰዓቱ ከሶስት መቶ ሰላሳ ሰዎች በላይ ያለቁባት ሃገር የወደፊት እጣ ፈንታዋን ለማሰብ በርግጥም እጅግ እጅግ ከባድ ስራ ነበር። ችግሩ እንዴት ይፈታ? በጎሳ ፖለቲካ ወይም ፌደራሊዝም? እንዴት ይፈታ? ምን ይሻላል? በጣም ፈተና ነበረባት::
በርግጥ ሩዋንዳ ያ ወንጀል ጋብ ሲል ለወደፊት እጣፈንታዋ ወዲያው አዋጭ መስመር መስሎ የታያት ብሄራዊ እርቅ ማውረድ ቢሆንም ብሄራዊ እርቁ በሩዋንዳ ሁኔታ ምን መልክ ይያዝ? በምን መልኩ ይፈጸም? የሚሉት ጥያቄዎች ግን በጣም ሊከብዷት የሚችሉ ጉዳዩች ነበሩ። በአንዳንዶች ዘንድ አጥብቆ ይቀነቀን የነበረው ጉዳይ ብሄራዊ እርቁ በሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ አማካኝነት ሊፈጸም ይገባዋል የሚል ነበር። ሁላችን እንደምናውቀው ሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ ማለት ለወንጀለኛው ተገቢውን ቅጣት በመስጠት የተበዳይን ነፍስ ማጽዳት ወይም ማርካት ማለት ሲሆን ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ደግሞ የሚያተኩረው ወንጀለኛውን በመቅጣት ላይ ሳይሆን ተበዳዩን በመካስ ላይ ያተኮረ የፍትህና የእርቅ ማውረጃ ዘዴ ነው። ታዲያ አንዳንድ ሩዋንዳዊያን ሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ ነው ፈውስ የሚያመጣልን ሲሉ በርግጥ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኙ አልቀሩም። ምክንያቱም ወንጀሉ የተፈጸመው በአጭር ጊዜ በመሆኑ፣ ወንጀሉ ግድያ በመሆኑ፣ ገዳይና የሟች ቤተሰብ ጎረቤት በመሆናቸው፣ አሰቃቂ ወንጀል በመሆኑ ሪትሪቢዮቲቭ ጀስቲስ ተገቢነው እንዲሉ የገፋፋቸው ይመስላል። ይሁን እንጂ በአንድ መቶ ቀናት ላለቀው ስምንት መቶ ሺህ ህዝብ ገዳዩችና ለገዳዩቹ ተባባሪዎች ፍርድ ለመስጠት ሩዋንዳ አቅም አልነበራትም። ሩዋንዳ በዚያን ወቅት ላለቁት ስምንት መቶ ሺህ ቱትሲዎችና ለዘብተኞች ወደ አንድ መቶ ሺህ ወንጀለኞችን ለፍርድ አቅርባ መቅጣት ከፈለገች አጠቃላይ የፍርዱ ሂደት ወደ አንድ መቶ አመት ይፈጅባት ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ። ያን ያህል ፍርድቤትም፣ ዳኛም ኢኮኖሚውም የላትም። በድህነት ላይ ነው ይህ ነገር የወደቀባት።

ሪስቶረቲቭ ጀስቲስን ተጠቅማ ችግሯን ለመፍታት ብትሞክር ደግሞ ገዳይና ሟች ጎረቤታም በመሆናቸው፣ የሟች ደም ገና ስላልደረቀ በርግጥ የሃገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ሌላ ችግር ውስጥ መውደቁ ሌላ አሳብን ያመጣባት ትመስላለች። ሩዋንዳ የነበረችበት መስቀለኛ መንገድ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የጣላት በመሆኑ ሁለቱንም የፍትህ አሰጣጥ ዘዴዎች አደባልቃ እንድትሄድ ሳያስገድዳት አልቀረም። በመሆኑም ባህላዊ የጋካካ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም የተወሰነውን ችግር በዚህ በሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ የተወሰነውን ደግሞ ዝግ እያለ በሚያድግ ዴሞክራሲና በሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ይፈታል እያለች እየደለለች ማርገብ ችላለች። ከሁሉ በላይ ግን ሩዋንዳ ወደ ዘጠና በመቶ የሚሆነው ህዝብ ክርስቲያን በመሆኑና አብያተ ክርስቲያናት የሚሰብኩት የይቅርታና የምህረት ትምህርት የሩዋንዳን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጾ ሳያደርግ አልቀረም። የነዚህ አብያተክርስቲያናት የይቅርታ ስብከት ለሩዋንዳ ሃዘንተኞች መጽናናትን ሰጥቷል። በአጠቃላይ የሩዋንዳ ችግር ውስብስብና አስቸጋሪ በመሆኑ ሁለቱም የፍትህ አሰጣጥ ዘዴዎች ተግባር ላይ የዋሉ ይመስላሉ።

ለአብነት በየሃገሩ የተፈጸመውን ወንጀል እያነሳን የተወያየነው ችግር በየቤቱ አለ፣ ይሁን እንጂ ሁሉም ሃገር ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው አገር የቆመው ለማለት ነው። ወደኛው አገር እንመለስና ብሄራዊ እርቅ በኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት።

በኢትዮጵያ ውስጥ ሊኖር የሚችለውን የብሄራዊ እርቅ ይዘት ለማየት መጀመሪያ ስለ አለፈው ታሪካዊ ግድፈቶች ማንሳት ተገቢ ነው። ከፍ ሲል እንዳልነው በአውስትራሊያ ውስጥ ለነበረው ግፍ ሃላፊነት የሚወስድ እውቅና የሚሰጥ አካል ተገኝቱዋል። ወደኛ ሃገር ስንመጣ ላለፉት በደሎች እውቅና ለመስጠትም ሆነ አንድ አካል ለጥፋቱ ሃላፊነት ለመውሰድ የምንችልበት ሁኔታ ጠፍቷል። ይህ የሆነበት ምክንያት ሁሉም የባህል ቡድን በየፊናው ባለፉት ስርዓቶች ተጎድቻለሁ ባይ በመሆኑ ነው።

በአጼ ምኒልክ ጊዜ የጠፉ ጥፋቶች ካሉ ለነዚያ ጥፋቶች የአማራውን ህዝብ ሃላፊነት ውሰድና ይቅርታ በል የሚል አካል ቢነሳ አማራው ለራሱ ተበድያለሁ ባይ ነው። በፊውዳሉ ስርዓት በጭሰኝነት፣ በባርነት መከራየን አይቻለሁ:: በወቅቱ የተጠቀሙት ጥቂት ፊውዳሎች ናቸው:: ተውኝ እባካችሁ ይላል። በአጼ ሃይለስላሴ ዘመንም ቢሆን የወሎ ርሃብ ሲመጣ ሃይለስላሴ ዓለም እንዳይሰማ አድርገው በዚያ ደረጃ ጨክነው አስጨርሰውኝ የለም ወይ? ደርግ አማራ ነው ካላችሁ ደግሞ የጎንደርንና የወሎን ወላድ እምባ አታዩም ወይ? ወዘተ. እያለ እያነባ ባለፉት ስርዓቶች የተጎዳውን ይቆጥራል። ኦሮሞው በበኩሉ በዚህኛውም ባለፈውም መንግስት ተነጥየ ተጎዳሁ፣ ባህሌ፣ ማንነቴ ተጎዳ ብሎ እያነባ ይናገራል፣ ትግሬው በበኩሉ ባለፈውም ሆነ አሁን የተመቸኝ ነገር የለም፣ የውስጥ ችግሬን እኔ ነኝ የማውቀው ተለይቼ ተበድያለሁ እያለ ያነባል፣ የደቡብ ህዝቡ ተበድያለሁ የኔን መከራ ማን ባየው እያለ እያነባ ይናገራል፣ ሱማሌው የኔ መከራ መቼ ነው የሚያቆመው? መከራየን እያየሁ ነው እያለ ያነባል። ጋምቤላው፣ አፋሩ ሁሉም በተናጠልም በቡድንም ተጎድቻለሁ እያለ ያነባል። ታዲያ እንዲህ በሆነባት አገር ብሄራዊ እርቅ ምን መልክ ይኖረዋል የሚለው ጥያቄ ላይ ነው በጥልቀት መወያየት ያለብን።

በመጀመሪያ ግን እኛ ኢትዮጵያዊያን ያለፉ ታሪካዊ ችግሮች አጥንተን መፍትሄ ለመስጠት የታሪክ ተዓማኒነት ችግርም ገጥሞናል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ፖለቲካው ከፋፍሎ የመግዛት ዘዴን የሚጠቀም በመሆኑ አንዳንድ በፈጠራ የሚጻፉ ታሪኮች ያለፈውን ታሪካችንን በሚገባ አይተን ብሄራዊ እርቅ ለማምጣት እንቅፋት ነው። የሆነ ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፈውም ሆነ አሁን ላለው ግፍና በደል አንድ ቡድን እንደ ቡድን ሃላፊነት ወስዶ ይቅርታ የሚልበት ሁኔታ የለም። በደቡብ አፍሪካም ሆነ በአውስትራሊያ ወይም በሌሎች አገሮች እንደተፈጠረው አይነት ሃላፊነት ወስዶ የቡድኖችን እንባ የሚያብስ ጠፋ። በመሆኑም የኢትዮጵያ ምሁራን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ብሄራዊ እርቅ ማለት ምን ማለት እንደሆነና ሁላችንን የሚፈውስ አሳብ በግድ አምጠው ሊወልዱ ይገባል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየው ቡድኖች እንደቡድንም በጅምላም ባለፈው ጊዜ ለደረሰባቸው በደል ሁሉ ያለፈውንና አሁን ያለውን ስርዓት የታሪክ ተጠያቂ ማድረጉ አንዱ የስምምነቱ አሳብ ወለል ቢሆን መልካም ነው። ይሁን እንጂ ላለፉት ችግሮቻችን ቡድኖች እንደ ቡድን ተጎዳሁ የሚሉት ካለ ለዚያ ቡድን ጉዳት እውቅና መስጠት አንዱ የስምምነቱ አካል ሊሆን ይገባል። አንድ ቡድን ተጎዳሁ ተጎድቼ ነበር ሲል የለም ያንተ ጉዳት ትንሽ ነው የኔ ይበልጣል ማለቱ ብሄራዊ ፈውስን አያመጣም። ሰው ህመሙን የሚያውቀው ራሱ ነው። በመሆኑም ቡድኖች የተጎዳነው አለ ሲሉ ማዳመጥና ሃዘንን መጋራት ለችግር እውቅና መስጠት ነው የኢትዮጵያ እርቅ መሰረቱ። ኦሮሞው አጼ ምኒሊክ ጎድተውኛል ካለ ሌላው ብሄር ልክ አይደለም አልጎዱህም ማለቱ ለብሄራዊ እርቁ አይጠቅመንም። አንዱ ዜጋ አጼ ምኒሊክ ካጠፉት ጥፋት ይልቅ የሰሩት ጀብዱ በተለይም ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪ ለመመከት ያደረጉት ተጋድሎ ከበለጠበት ቢወዳቸው ቢፎክርላቸው ሌላው ኢትዮጵያዊ መበሳጨትና ጥል ውስጥ መግባት የለበትም። አንድ መሪ ለአንዱ ኢትዮጵያዊ ተወዶ ለሌላው የሚጠላ ቢሆንም ከዚህ ልዩነታችን ጋር አብረን መኖር እንችላለን። ኢትዮጵያዊ ለመሆን ሁሉ ሰው አጼ ምኒሊክን መውደድ አለበት ማለት አይደለም። ፕሬዚደንት ኦባማንና ፕሬዚደንት ቡሽን የሚወድም የሚጠላም በሰላም እንደሚኖረው እኛም ከልዩነት ጋር መኖርን መልመድ ያስፈልገናል።

አሁን እኛ ጋር ያለው የኮሙኒኬሽን ችግር ይመስላል። የኮሙኒኬሽን ችግሮች ምንጫቸው የእውነት መዛነፍ (distortion of truth) እንዲሁም የማንነት ፖለቲካ ውጤቶች ስለሆኑ ለነዚህ ችግሮች ራስን ሰለባ አለማድረግ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሄራዊ እርቅ ዋናው መሰረት እርስ በርስ መረዳዳት (understanding eachother) ነው ማለት ነው። ያለፈውን ህመማችንን በመደማመጥ ነው ልንፈታው የምንችለው። ችግራችንን ስንገልጥ የለም ያንተ ቁስል ትንሽ ነው የኔ ነው ትልቁና አንተ ስለ ብሶትህ አታንሳ አይባልም። ቢሆን ቢሆን ራስን ከውጭ ወደ ውስጥ ከውስጥ ወደ ውጭ የማየት ልብ ቢኖረን እሱ ነው ያለፈውንና አሁን ድረስ የቀጠለውን ችግራችንን የሚፈታው። በአሁኑ ሰዓት እኔ ኦሮሞ መሆኔ ቀርቶ ትግራይ ሆኘ ብፈጠር ምን ይሰማኝ ነበር? ምን እሆን ነበር? ብሎ ቢያስብ በአንጻሩ የትግራይ ህዝብ ኦሮሞው አማራው ተለይቼ ተጎዳሁ ሲል በአሁኑ ሰዓት እኔ ኦሮሞ ሆኘ ተፈጥሬ ቢሆን ምን ይሰማኝ ነበር? የሚል ከፍ ያለ መረዳት(understanding eachother’s pain and understanding each other’s feelings) በተለይ በሌሂቁ በኩል ቢታይ ነው የብሄራዊ እርቁ መሰረቱ የሚጠብቀው። አንድ ሰው ጉዳቴ ከፍተኛ ነው ሲል የለም ያንተ ትንሽ ነው የኔ ነው ትልቁ ጉዳት ወደ ማለት ማዘንበላችን የኮሙኒኬሽን ችግር ያመጣብናል። እውነቱን እንነጋግር ከተባለ እኛ ኢትዮጵያዊያን ያለፈውን ችግር በብሄራዊ ይቅርታ ለመዝጋት የገጠመን ችግር ይሄው የኮሙኒኬሽን ችግር ነው። ያለመደማመጥና ህመምን ለመካፈል መድረክ ማጣት ትልቅ ችግሮች ሆነዋል። ሌላው ደግሞ ቅድም እንዳልኩት ያለፈውን ችግራችንን በብሄራዊ እርቅ ለመፍታት የነበሩትን በደሎች ወደ መድረክ አምጥቶ እውነትን ለመግለጥ አሁን ያለው መንግስት ታሪክን ስላቆራፈደውና ብርታትንም ሆነ ድካምን ከቡድን ማንነት ጋር እንድናያይዝ የሚገፋ ነገር በመኖሩ በከፍተኛ ሁኔታ እውነትን የማግኘት ችግር ይገጥመናል። በተጨማሪም ኢትዮጵያዊያን አዳዲስ በሚወለዱ ታሪኮች ሳንደነብር ከስሜት በላይ ሆነን እርስ በርስ በመረዳዳትና አለ ለተባለው ችግር እውቅና በመስጠት ነገሩን ማርገብ ይጠበቅብናል። ከሁሉ በላይ ግን ኢትዮጵያ ያለፈውን ችግር ልታይበት የምትችልበት አንድ ሌላ ትልቅ ነገር የዛሬው ይዞታዋ ነው። በፊት የነበሩ ማህበራዊና ፓለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አሁን ድረስ እየተንከባለሉ መጥተው ስለሚገኙ አሁን ያለውን በቡድኖች መካከል ያለውን ክፍተት በሪስቶሬቲቭ ፍትህ ልትፈታው ይገባታል። በትምህርት፣ በፖለቲካ ተሳትፎ በባህልና በቋንቋ አካባቢ ያለውን ችግር ኢትዩጵያ ለመፍታት ስምምነት ውስጥ መግባት አለባት። ይህ ስምምነት ነው አንዱ የብሄራዊ እርቁ ይዘት። ሪስቶሬቲቭ ፍትህ ስንል በማህበራዊ ተቋማት ግንባታ ይሁን ከፍ ሲል በገለጽናቸው ሁኔታዎች የተጎዱ አካባቢዎችን በአፌርማቲቭ አክሽን ዘዴዎች ለመፍታት ስምምነት ላይ መጀመሪያ መድረስ አለብን። ሌላው ጉዳይ ደግሞ ቅድም እንዳልነው ትውስታዎቻችንን የጋራ አድርጎ ማሰቡን አለመርሳት ነው። ክፉውንም ደጉንም የጋራ ታሪክ አድርጎ መቁጠር በጣም ከፍ ያለ መረዳት ነው። በአጼ ምኒሊክ ዘመን የተፈጠሩ መልካም ነገሮችን ስንዘረዝር በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የነበሩትን ቡድኖች ሁሉ ይመለከታል። ቀረጥ የከፈሉና ለመንግስት የገበሩ ሁሉ ታሪካቸው ነው። ልክ እንደዚሁ የተፈጠሩ ስህተቶች ሲታወሱን ደግሞ ቀረጥ የከፈለው ግብር የከፈለው ህዝብ ሁሉ የጋራ ታሪኩ መሆኑን ማሰብ ነው። ጥሩ ጥሩውን እየነቀስን አውጥተን የጋራ ታሪካቸን ነው እያልን መጥፎውን አውጥተን ለአንድ ቡድን ማሸከም ሚዛናዊነት የጎደለው ነው። ለብሄራዊ እርቅ እነዚህ መረዳቶች መሰረት ይሆኑናል። ከሁሉ በላይ ለኮሙኒኬሽን መጠልቀቅ ነው እርቁን ወይም መግባባቱን የሚያፋጥነው። ለኮሙኒኬሽ መጠንቀቅ ማለት አንድ የኦሮሞ ሰው ባለፈው ስርዓት ባህሌ ተጎዳ ብሎ ተክዞ ሲነግረኝ የተጎዳኸው አንተ ብቻ መሰለህ እኔም ነኝ። የኦሮሞ ባህል በመጎዳቱ እኔም ነኝ ያጣሁት ሃገራችን በዚህ ሁኔታ ውስጥ አለፈች ያሳዝናል። አሁን እንዳይደገም መጣር አለብን ብለው አለቀ ማለት ነው።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በስምምነቱዋ ወቅት የምታካትታቸው ጉዳዩች በግልጽ መጀመሪያ መቀመጥ አለባቸው። ቡድኖች እንደ ቡድን ሁሉም ተበድለዋልና ብሄራዊ እርቁ ሁሉንም ሊክስ የሚችልና ኮሙኒኬሽንን የሚያዳብር መሆን አለበት። በዓለማችን የሚነሱ ጦርነቶች አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል ምክንያታዊነት ያላቸው አይደሉም አብዛኛዎቹ ከኮሙኒኬሽን ችግር ጋር የተያያዙ ናቸው መሰለኝ። አንዳንዴ ቡድኖች የተጣሉበትን ሁኔታ በውል ሳያውቁት ብዙ ይዋጉና ብዙ ሰው ካለቀ በሁዋላ ይታረቃሉ። የሚገርመው ሲታረቁና ስሜታቸው ሲረጋ የከፈሉት ዋጋ እንዲሁ ሜዳ ላይ ሆኖ የሚያገኙበት ጊዜ ይኖራል። የባድሜው ጦርነት ምሳሌ ነው። በመሆኑም ብሄራዊ እርቁ በቡድኖች መካከል ያለን ኮሙኒኬሽን ለማስተካከል መላ ሊወልድ ይገባዋል።

ከፍ ሲል እንዳልነው ብሄራዊ እርቅ በኢትዮጵያ የሚኖረው መልክ ሁሉንም በመካስ ላይ ሁሉንም ችግሮች እውቅና በመስጠት ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል። በተለይ ያለፈውን ችግራችንን ለመፍታት ችግሩ ከኮሙኒኬሽንና ከስሜት ሃያልነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ በረጋና በሰከነ መንፈስ ዜጎች ያለፈውን ችግራቸውን በጋራ እውቅና ሰጥተው ሲንከባለል ለመጣው ችግር ደግሞ አፈርማቲቭ አክሽንስና ሌሎች የርስበርስ የመካካሻ ዘዴ ተጠቅመው ፈውስን ማውረድ አለባቸው። ያለፉት ጨቋኞች በግልም በቡድንም እየለዩ ሲጨቁኑን መኖራቸውን የጋራ መረዳት ላይ መድረስ አለብን ።

ስለ ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ስናወራ ለተበደሉ ቡድኖች ሁሉ ትልቁ ካሳ አዲስ የሚፈጠረው የማህበራዊ ፖለቲካ ሲስተም ነው። ይህ ሲስተም ካሳቸው ከሆነ የብሄራዊ እርቁ መሰረት እሱ ነው። CCU አንዱ ትልቁ ፍላጎቱ ሁሉንም የሚክስ ሲስተም ለመፍጠር ነው። በባህል ማንነት የተጎዳነውን ባህላዊ ማንነታችንን የሚንከባከብ ጠገግ መፍጠር፣ የቋንቋ አጠቃቀም ፖሊሲን አውጥቶ ሁሉን ቋንቋዎች ኦፊሺያል ማድረግ፣ ሁሉን ቋንቋዎች ብሄራዊ ቋንቋ ማድረግ ትልቁ ካሳ ነው። በፖለቲካው መስክ ዴሞክራሲን መሰረት አድርገን ጥራት ያላቸውን ተቋማት መገንባት ስንችል ያ ነው የሁሉም ቡድኖች ካሳ።

በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ ውህደት ብሄራዊ እርቅን በኢትዮጵያ የሚያየው እንደዚህ ነው። በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት ብሄራዊ እርቁ ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስን መሰረት ያደረገና በሚያድግ ዴሞክራሲ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል ስምምነት ማለት ነው። ይህ ማለት ግን ሪትሪቢዩቲቭ ጀስቲስ ቦታ የለውም ማለት አይደለም። በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ሙስናና ከፍተኛ ወንጀል እየፈጸሙ ያሉ ሰዎች ይህንን አሳባችንን እያዩ እንደ ጅልነት አይተው ከስልጣን እስኪወርዱ በግፋቸው እንዲቀጥሉ በር አይከፍትም። የብሄራዊ እርቅ ሰነዱ እንደነዚህ አይነት ሰዎችን በቡድን እያየ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ወደ ፍርድ ሊያመጣቸው መቻሉ አያጠያይቅም። እንደ ቡድን እንደ ሃገር ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን ዝግ እያለ ሊሰራጭ በሚችል የሪዲስትሪቢዩሽን ዘዴ ተመጣጣኝ እድገት ለማምጣት መስማማት፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎን ከባህላዊ ውህደት ስምምነት አንጻር አይቶ ከብሄር ፖለቲካ አውጥቶ በአንድ ብሄራዊ ማንነት ስር ለመገንባት መስማማት ፈውስን ለማምጣት ይጠቅማል። ኢትዮጵያ ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ላይ እንድታተኩር የሚያደርጋት ለዘላቂ ሰላምና ልማት አንድነት የሚረዳት ሲሆን ይህ የፍትህ አሰጣጥ ዘዴ በኢትዮጵያ ቡድኖች ዘንድ የተባረከና የሚበረታታ ነው። የኦሮሞ ስርዓትን ብናይ ለሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ ትልቅ ቦታ አለው። ይቅር ማለትን፣ በዳዩን ከመቅጣት ይልቅ ተበዳዩን መካስን ያበረታታል። አማራው አካባቢ ያለውን የሽምግልና ስርዓት ስናይ በአብዛኛው ሪስቶሬቲቭ ጀስቲስ የሚበረታታበት ሁኔታ አለ። በደቡብ፣ በምስራቅ በተለይም በሶማሌ ክልል ይህ የፍትህ ስርዓት ከፍተኛ ተጽእኖ አለው።

የሃይማኖት ዳራችንም ቢሆን ወደ መቶ ፐርሰንት የሚጠጋው ህዝብ ሃይማኖተኛ በሆነበት አገርም ይህ የፍትህ ስርዓት ሊሸከመው የሚችል በተፈጥሮው የተደራጀ ተቋም በመኖሩ ተመራጭ እንዲሆን ያደርገዋል።

ሌላው ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ባለፈው ጊዜ በግድ በሆነ ምስለት ጠፉ የሚባሉ ባህሎች ካሉ እነሱን የማስመለስ (Restoration and revival of cultural heritages) ስራ ለመስራት መስማማቱ ነው አንዱ የእርቁና የካሳው ሰነድ የሚይዘው ጉዳይ። የጠፉና በመጥፋት ላይ ያሉ ጠቃሚ ባህሎች ካሉና ቡድኖች የሚቆጩባቸው ከሆነ የማስመለስ ፖሊሲ አውጥቶ ቡድኖችን ሁሉ አስተባብሮ ለመካስ ኪዳን መግባት። ቡድኖች አጣናቸው የሚሉዋቸውን በሙሉ ለማስመለስ ባይቻልም አብዛኛውን በመመለስ የቡድኖችን ልብ ማሳረፍ ይቻላል።

ሌላው የብሄራዊ እርቁ ሰነድ ሊይዘው የሚገባው ጉዳይ ለወደፊቱዋ ኢትዮጵያ የሚሆን አስተዳደራዊ ባህልን የመገንባት ስምምነት ሲሆን ይህም ዴሞክራሲ ነው። ቡድኖች በመጀመሪያ ዴሞክራሲ ከአሁን በሁዋላ ያስተዳድረን መንግስታት ቢቀያየሩም ዴሞክራሲ ግን የጋራ ባህላችን ይሁን የሚል ስምምነት ውስጥ ሊገቡ ይገባል። ይህ አስተዳደራዊ ባህል የጋራ የሁላቸው በመሆኑ ወደፊት ለህይወታቸው መሪ ይሆናል ማለት ነው።

ሌላው መሰመር ያለበትና የስምምነቱ አንዱ አካል ሊሆን የሚገባው ለመልካም ታሪኮቻችንም እውቅና መስጠት ነው። ኢትዮጵያን የመከራ ቤት ብቻ አድርጎ ከማየት የአፍሪካ መቀመጫ ያደረጋትን የነጻነት ታጋይነቱዋን ማስታወስና ለነዚህ ታሪኮቻችን ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ አስተዋጾ በማድረጋቸው እውቅና ሊሰጡት ይገባል። ይህ አይነቱ ስሜት ሚዛናዊ የሆነ ስሜትን ከመፍጠሩም በላይ አገር አለን ስንል የምንመካባቸው ብዙ አኩሪ ታሪኮች እንዳሉንም ስለሚያደርግ ነው።

በአጠቃላይ ብሄራዊ እርቅን በኢትዮጵያ ጨምቀን ካየነው በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነትን መፍጠር ማለት ነው። ስለዚህ CCU ብሄራዊ እርቅን የሚያየው ለአዲሲቱ የተባበረችው ኢትዮጵያ የምናደርገው የጋራ ስራ ነው።
ስለ ብሄራዊ እርቅ ስናወራ አብዛኛው ጉዳይ ከስሜት ጋር የተያያዘ በመሆኑ አንዱ ሌላው ያለፈውን ጥሩ ያልሆነ ትውስታ ያመጣውን ችግር ለመፍታትና አሁን ያለውን የቅሬታ ችግሮች ለመፍታት ዜጎችና ለሂቃን ከላይ ሆነው እንዲያዩ ነው የሚያስፈልገው። ከላይ ሆነን ስናይ ችግሮቻችን ገዝፈው አይታዩንም። ከላይ ከዓለም ታሪክ፣ ከላይ ከግሎባላይዜሼንና ከዓለም ስላጣኔ፣ ከላይ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከላይ ከአፍሪካ ቀንድ ላይ ቆመን ስናይ ነው የሰከነ መፍትሄ የምናመጣው። ይሄ ጉዳይ በተለይ ለሂቁን ይመለከታል። ትልቁ ችግር ችግሮቻችንን ከስር ከስሩ ስናይ ነው። ከስር ስናይ ገዝፈው ይታዩናል። የብሄር ፖለቲካ አንዱ ትልቁ ችግር ይሄ ነው። ራሱ ተፈጥሮው ከታች ከ DNA እንድንነሳ ከዚያም ቤተሰብ ከዚያም ዘመድ አዝማድ ከዚያም ጎሳ ከዚያ መጨረሻ ላይ ነው አገር ብለን እንድናስብ የሚያደርገን። በብሄር ፖለቲካ ጊዜ የመጨረሻው ታሳቢ አገር ሲሆን የመጀመሪያው ጉዳይ ራስ(self) ነው። ለዚህም ነው እኔ እኔ እኔ (Me… Me…. Me….) የሚበዛበት። የፖለቲካው ተፈጥሮ ከደም ጋር ለተያያዘው ከፍተኛ ዋጋ ሲሰጥ ከደም ብዙ ርቆ ለሚገኘው አገር ለሚባለው ጽንሰ ሃሳብ የሚሰጠው ዋጋ ዝቅ ይላል።

ከላይ ሆነን እንይ ስንል ስለ ፖለቲካ ስናስብ ስለ የፖለቲካ ተሳትፎ ስናወራ ወይም የፖለቲካ ቤት ስንሰራ ከላይ ከብሄራዊ ማንነት ነው መጀመር ያለብን። ከላይ ከኢትዮጵያዊነት የምንጀምረውና በዚህ ጥላ ስር የምናደርገው መሰባሰብ ፍትህን ለማምጣት ዴሞክራሲን ለማምጣት ይረዳናል። በብሄር ፖለቲካ ጊዜ ፍትህን ከሚያቀጭጩ መንስዔዎች መካከል አንዱ የፖለቲካው እምነት በDNA ላይ የቆመ በመሆኑ ነው። ይህ ነገር ሥነ- ህይወታዊ የሆነ ነገር ቢሆንም በዚህ ሥነ- -ህይወት ላይ የፖለቲካ ቤት እንድንሰራበት አይደለም የሚያስፈልገው። የሚያስፈልገው የቤተዘመድ ማህበር ማቋቋም ነው። ወይም ማህበራዊ የሆነ ስራን ለመስራት ነው። የደም ሃረግን ፈልጎ በጎሳ ላይ የሚቆም ፖለቲካ ከዴሞክራሲና ከፍትህ ጋር የማይሄደው ዴምክራሲ በተፈጥሮው የሚያየው ከላይ ስለሆነ ነው። ዴሞክራሲ የመርህ ጉዳይ ነው መሰረቱ። የጎሳ ፖለቲካ ደግሞ በደም ሃረግ ላይ ቆሚያለሁ ለሚለው ቡድን ነው መሰረቱ። ይሀ ተፈጥሮው ነው ከዴሞክራሲ የሚያለያየው። ዴሞክራሲ ልክ እንደ ንስር ነው። ከላይ ሆኖ ወደ ታች ያሉትን የልዩነት ቅንጣቶች ሁሉ አብጠርጥሮ እያየ ይጠብቃል። ንስር በተፈጥሮው ከፍ ብሎ የሚበር ፈጣን ሲሆን ከብዙ ከፍታ ወደ ታች ጥቃቅን ቅንጣቶችን ሁሉ ያያል። ራሱን እያደሰም የሚኖር ልዩ ፍጡር ነው። ዴሞክራሲ እንዲህ ነው። በመርሆዎች ላይ ቆሞ ራሱን እያደሰ ግን ደግሞ ታች ግለሰቦችን እያየ ይጠብቃል። በአንጻሩ የጎሳ ፖለቲካ ደግሞ በመሬት ላይ የሚንደባለል ሲሆን ከፍ ሲል እንዳልኩት ወደ ላይ የሚያየው አገርና ዴሞክራሲ ሩቅ ናቸው። አበሾች ከላይ ሆነን ነው ማየት ያለብን። በዴሞክራሲ ጊዜ ነው ብዙህነት ተግባራዊ የሚሆነው። ዴሞክራሲ ሲገዛ፣በመሰረቱ የልዩነት የመጨረሻ ቅንጣት ያለውም በግለሰብ ደረጃ ሲሆን ከዚያ ከፍ እያለ በቡድን እስከ መለያየት ይደርሳል። ዴሞክራሲ የሚቆመው በዚህ በግለሰቦች በዜግነት መብት ላይ ሲሆን ቤቱን የሚሰራው ከላይ ከብሄራዊ ማንነት ከመርህ አንጻር ነው። በአንጻሩ የብሄር ፖለቲካ ደግሞ በቡድን ላይ ቆሞ እነዚያን የቡድኑን አባላት የሚያያይዝበት ሙጫ የደም ሀረግ ነው። ዴሞክራሲ በአንጻሩ ግለሰቦቹን የሚያያይዘውና የሚያደራጀው በእሴቶች ላይ ነው። ዴሞክራሲ ለእሴቶች ትልቅ ዋጋ ያለው ሲሆን በፍትህ ፊት በዴሞክራሲ ጊዜ የስጋ ወንድሜና ሌላው ኢትዮጵያዊ እኩል ናቸው። ዴሞክራሲ የሚመክረኝ የስጋ ዘመዴን በጓዳ በግል ህይወቴ እንድንከባከብ ሲሆን በአደባባይ በፖለቲካ ጊዜ ግን በብሄራዊ ማንነት ጥላ ስር የተዛመደኝ ሁሉ ወንድሜ እንዲሆን ነው። ይህ ሥነ- ህይወታዊ ያልሆነ ነገር ግን የኪዳን ጉዳይ ነው። ዴሞክራሲ ከዝምድና ኪዳን ይበልጥበታል::

በደም ሃረግ Genealogical DNA ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ በተለይ በድህነት ለምንታወቅ ለኛ፣ ረሃብ ለሚያጠቃን ለኛ ከፍተኛ ችግር ነው። አንድ የፖለቲካ አሳላፊ አንድ የሱ ብሄር አባልና አንድ ከሱ ብሄር ውጭ የሆነ ሰው ተርበው ሲለምኑ ሲያይ ቀድሞ ልቡ የሚነካው ለዚያ ደም አለኝ ለሚለው ሰው ነው። ይህ በራሱ ሳይሆን ችግሩ ይህ ልቡ ያደላለትን ሰው ለመርዳት የሚያስችል የፖለቲካ ስልጣን ሊይዝ ይችላል። በዚህ ጊዜ ይህን ስልጣን መጠቀሚያ አድርጎ አድልዎ እንዲፈጽም የማድረግ ልዩ ጉልበት ስላለው ነው የብሄር ፖለቲካ የሚጠላው። የብሄር ፖለቲካ አድልዎ ለመፈጸም ምቹ ሲስተም ስለሚዘረጋ ነው የምንጠላው። ጨክነን ከላይ እንውጣ፣ ከላይ እንይ እኛ እዚህ ስለ ብሄር ፖለቲካ ስለ ዞንና ቀበሌ መገንጠል ስናወራ የአፍሪካ ህብረት እውን ቢሆንስ? አፍሪካ ብትዋሃድስ። አሁንም ሲዳማን ነጻ ለማውጣት እንታገላለን? አሁንም ጋምቤላን ነጻ ለማውጣት ልንታገል ነው?

አሁንም አፋርን ወይም ኦጋዴንን ነጻ ለማውጣት ልንታገል ነው? የአፍሪካ ቀንድ የሆነ ጥምረት ውስጥ ቢገባስ? በዚህ ከፍታ ላይ ሆነን በዚህ ጉልህ መነጽር ስናይ የኛ የመንደር ፖለቲካ ምን ያህል አንሳ እንደምትታይ ማሰብ ይጠበቅብናል። መገንጠልን መፍትሄ ያደረግን ዞኖችና ክልሎች መገንጠል እውን ቢሆን ተገንጥለን የት ነው የምንሄደው? እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ክፍላተ ሃገራት ይቅርና የአፍሪካ ቀንድ ራሱ በሆነ መንገድ ካልተቀናጀ ከችግር አይወጣም። ለኢኮኖሚ እድገትና ከዚያ ክልል ረሃብን ለማጥፋት መልካም አስተዳደር ለመገንባት ተደጋግፎ ነው ማደግ የሚቻለው። አንዱ አካባቢ ግንጥል ብሎ ብቻውን የተሻለ ህይወት ለመግፋት የሚያስችል ከባቢ የለንም። ይህንን ነው ማሳብ ያለብን። ከሁሉ በላይ አሁን ያለው ትልቅ ችግር የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቱ ያልተሟላባት አገር ናት አገራችን። የከፋ ችግር አለ። በፕላኔት ላይ የመጨረሻ ድሃ ነን። ስለዚህ እባካችን ይህንን ነው ማየት ያለብን። ስለነዚህ ስለ ተቸገሩ ሰዎች ሲባል የፖለቲካ ሰዎች በሆነ ህብረት ውስጥ ገብተውና ተቻችለው ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል። አለበለዚያ ውጭ ያለው ሰው በርገሩን እየገመጠ፣ አገር ቤት ያለው ባለስልጣን በህዝብ ሃብት እየደነሰ የምናደርገው የእልህ ፖለቲካ በመሃል ደሃውን እንጀራ ስላሳጣው ቢያንስ ሃላፊነት የሚሰማው ተቃዋሚ በፍጥነት ወደ አንድ የጋራ አጀንዳ መምጣት አለበት። ኢትዮጵያውያን ለሂቃን ይህን እንደሚያደርጉና የሁላችንን የዜጎችን ጥያቄ እንደሚመልሱ አምናለሁ።

እነዚህ የብሄር ኢንተርፕሩነርስ የሚባሉት በቀላሉ ወደሚፈልጉት ስልጣን የሚያሳልፍ ብቃት ሳይኖራቸው ሲቀር፣ አንዳንድ ጊዜም ለተጠናወታቸው የስልጣን ጥማት ሁኔታዎች አልመች ሲሉ በፍጥነት የሚታያቸው በብሄር ተቆርቋሪነት ስም ብቅ ማለት ነው። ይሄ በጣም አደገኛ ነገር ነው። እነዚህ ሰዎች አንዳንዴም የብሄራቸውን ብዛት እየያዙ ያንን የስልጣን ጥያቄ ማቅረቢያ ያደርጉና በዚያ ትከሻ ላይ የሚፈልጉትን የግል ጥቅም ማግኘት ይሻሉ። የብሄሩ ብዛት አነስተኛ ሲሆን ደግሞ የመገንጠል ጥያቄን ይዘው የሚፈልጉትን ስልጣን ለመያዝ ይሞክራሉ። ግለሰቦች ስልጣን ሲሹ በብዙ መንገድ ይመጣሉ። አንዳንዶች በሃይል፣ በጠብ መንጃ ስልጣን መያዝ ይሻሉ ሁዋላም ዲክቴተር ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ራእያቸውን አሳይተው ህዝብ መርቋቸው እንዲመጡ ይሻሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ ብሄርን፣ ደምን ታከው ወደ ስልጣን መምጣት ይሻሉ። ከነዚህ ሁሉ አደገኛው ጎሳን ለስልጣንና ለግል ፍላጎት መጠቀም ነው። ኢትዮጵያውያን ከእነዚህ መጠበቅ አለባቸው። በጣም አደገኞች ናቸው።ለብሄራዊ መግባባትና እርቁም እንቅፋት ናቸውና መንቃት አለበን።

የፖለቲካ ድርጅቶች

እርግጥ ነው አዲስ ኪዳን የሚገቡት ፓርቲዎች ኣይደሉም። የመጀመሪያውን የኢትዮጵያውያን ኪዳን የሚያቆሙት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ናቸው። የፖለቲካ ቤት የምንሰራው ከዚህ ኪዳን በሁዋላ በዚህ ኪዳን መሰረት ነው። የፖሊሲ የርእዩት ልዩነት ቢኖርም ከኢትዮጵያውያን ኪዳን ስሜት ግን ፈቀቅ ሊል ኣይችልም። ይሁን እንጂ ስለአዲስ ኪዳን ስናወራ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሁሉ ወደዚህ መሰረታዊ ኪድን እንዲያዘነብሉ ጥሪ የማደግ ታሪካዊ ሃላፊነት ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ በአዲሱ ኪዳን ጊዜ እንደ እንቅፋት ሆነው የሚነሱ አንዳንድ የፖለቲካ ሃይላት ይኖራሉ። በተለይም አክራሪ የብሄር እርበኞች ኣካባቢ ያሉ ሃይላት የኪዳኑ ዋና ተግዳሮት ሆነው የሚታዩ ናቸው በአጠቃላይ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ኣሰላለፍ ስናይ ኣጠማመዱ ወጥነት የሌለው የብሄርና ብሄራዊ ፓርቲ ኣንድ ላይ የሚተራመሱበት እርሻ ነው። በዚህ እርሻ ላይ የፖለቲካውን ሜዳ በበላይነት የተቆጣጠረው ብሄር ተኮሩ ሃይል ነው። በሃገሪቱ ውስጥ ካሉት ከመቶ በላይ የሚሆኑ ድርጅቶች መካከል 70% የሚሆኑት በዘውጋቸው የተደራጁ ሃይላት ሲሆኑ 30% የሚሆኑት ደግሞ አገራዊ ፓርቲዎች ናቸው። በርግጥ የዘውጉ ፖለቲካ በሃይል በዚህ ደረጃ የበላይ ቢሆንም በኮንስትቲየንሲ ግን ውጤቱ የተገላቢጦሽ እንደሆነ ይታመናል። የኣስራ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሰባቱ ምርጫ፣ በቅርቡ ኦሮምያና ዓማራ ኣካባቢ የተነሳው ተቃውሞ ማሳያዎች ናቸው። በቅርቡ በነበረው ተቃውሞ ጊዜ ጎንደር የሚፈሰው የኦሮሞ ደም የእኔም ነው ሲል ናዝሬትና ሌሎች የኦሮምያ ኣካባቢ ዓጸፋውን ሲመልሱ የሚያሳየው ሃቅ የደም ፖለቲካ (bloodline politics) መሰረት እንደሌለው ነው። የሆነ ሆኖ እነዚህ በዘውግ ላይ የተደራጁ ሃይላት አገሪቱ ወደ አዲስ ኪዳን ስትገባ ከሚኖራቸው ተጽእኖ ኣንጻር በ 3 ተከፍለው ሊታዩ ይችላሉ::

አንዳንድ የዘውግ ድርጅቶች ብሄራቸው ከኢትዮጵያ ጥላ ስር ሳይጠፋ ነገር ግን ራስን በራስ ማስተዳደር እንዲከበር የሚሹ ናቸው። እነዚህ ሃይላት መስዋእትነትንና መዋጮን ይፈራሉና ለአዲሱ ኪዳን ተግዳሮት ናቸው። ህዝቡ ወደ ኪዳን እንዳይገባ ለማድረግ ከመጣር አልፈው ራሳቸውም እንደዜጋ ወደዚህ ኪዳን ለመግባት የሚደፍሩ ኣይደሉም ፣ሁለተኛው ሃይል አክራሪ ሲሆን እስከ መገንጠል የሚንቀሳቀስ ነው። ይህ ሃይል በከፍተኛ ሁኔታ የአዲስ ኪዳን እንቅፋት ነው። ኣዲስ ኪዳንንን እንደ ጦር ይፈራል። መስዋእትነትን አንድነትን ዓይቀበልም። በቁጥር ግን እጅግ ኣናሳ ነው።

ሶስተኛው የብሄር ተኮር ሃይል ደግሞ ለዘብተኛ ሲሆን ቀን እስኪያልፍ በብሄር ተደራጅቶ የሚንቀሳቀስና ኢትዮጵያውያን ወደ አዲስ ኪዳን ለመግባት ቢነሱ ስጋት የመሆን ደረጃው ዝቅ ያለ ነው። ይህ ሃይል የሚሻው ነገር ዘውጉ ተለይቶ የሚጠቃበት ሁኔታ እንዳይፈጠር እንጂ መገንጠልን ኣይደግፍም። ኣሁን ያለው የዘውግ ፖለቲካ ኣሳስቦት ለዘውጉ ከለላና ድምጽ ለመሆን ቢደራጅም ኢትዮጵያውያን የኔ የኔ የሚለውን ትተው ኣዲስ ኪድን ገብተው ከብሄር ፖለቲካ ወጥተው ወደ እኛ የማህበረ ፖለቲካ ምህዳር ቢገቡ ኣይከፋውም።

የአንድነት ሃይል

አንደኛው ሃይል ጽንፈኛ የሆነ በመሆኑ ምንም እንኳን ስለኢትዮጵያ ኣንድነት የሚያወራ ቢሆንም ነገር ግን በቡድኖች መብት ላይ ያለው ግንዛቤ በጣም ዝቅ ያለ ነው። ሊያያት የሚፈልጋት ኢትዮጵያ በአንድነት ያበደች አገር ሆኖ ነገር ግን የብሄርን ጥያቄ ዝቅ ኣድርጎ የሚያይ በመሆኑ ኣዲስ ኪዳን ደግሞ የግልንም የቡድንንም መብት ለማስከበር የተነሳ በመሆኑ በዚህ ጽንሰ ሃሳብ ኣካባቢ የከረረ ተቃዋሚ ይሆናል ተብሎ ባይታሰብም የተወሰኑ ማንገራገሮችን በማስሳየት ተግዳሮት ሊሆን ይችላል። ሌላው የአንድነት ሃይል ደግሞ ምክኛታዊ የሆነ ዴሞክራሲን ኣጥብቆ የሚሻ፣ ብዝሃነትን የሚቀበል የማንነት ጉዳይም የሚያሳስበው ሃይል የዚህ ኪዳን ኧርሊ አዳፕተር ነው። ጎታች ኣይሆንም።

የብሄር ኢንተርፕሩነርስ

ባላፉት ሃያ ስድስት ዓመታት አገራችን ያለማቋረጥ የምታመርተው ሃይል ይሄ ነው። የብሄር ኢንተርፕሩነርስ እየበዙ ሲሄዱ ይታያል። እነዚህ ሃይላት እድል ፈላጊዎች ናቸው። የብሄር ፖለቲካን ተገን እያደረጉ በዚያ ዙሪያ እየተደራጁ ተቆርቋሪ ነን እያሉ ለግል ህይወታቸው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ይጠቀሙበታል። በአንድነት ጊዜ እንዋጣለን ብለው ያምናሉ። ይህ የብሄር ፖለቲካ እርሻ ግን እነዚህን ኣረሞች ብዙ ኣፍርቷልና እነዚህ ሃይላት የኪዳኑ እንቅፋት ናቸው። በቻሉት ሁሉ ህዝቡ ወደ አዲስ ኪዳን እንዳይገባ የሚቀሰቅሱ ሃይላት ናቸው። መንግስት ደግሞ ምንም እንኳን ፍላጎታቸውን ቢረዳም የመከፋፈሉን ስራ ስለሚይዙለት ይጠብቃቸዋል። እስካሁንም የሚያድጉት የመንግስትን ከፋፍለህ ግዛ ሲስተም ስለሚሰሩለት ነው። ኢንተርፕሩነርስ ፍላጎታቸው ይህን የብሄር ፖለቲካ ተጠቅመው ተሰሚነት ማግኘትና የሚፈልጉትን ሃብት ማጋበስ እንጂ ስለብሄራቸውም ሆነ ስለ ብሄራዊ ኣንድነት የሚገዳቸው ኣይደሉም።

የሲቪክ ማህበራት

ኢትዮጵያ ዓ ም የዓለም ዓቀፍ የሲቪክና የፖለቲካ መብትን ለማክበር ፈርማለች ። ይሁን እንጂ የሲቪክ ማህበራት በኢትዮጵያ ደስተኞች ኣይሆኑም። ከዚህ በፊት ወደ ኣራት ሺህ የሚጠጉ ማህበራት የነበሩ ሲሆን መንግስት የተለያየ ጫና እያሳደረባቸው ብዙዎች ተዘግተዋል። ብዙዎች ደግሞ እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገዋል ወይም እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ የስጋት ኑሮ ይኖራሉ። በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሰሩት ናቸው ዋና የመንግስት ዱላ ሰለባዎች። እነዚህ ሃይላት የአዲስ ኪዳን ጥሪ ሲመጣ ያንሰራራሉ። አብዛኞቹ በአንድም በሌላም መንገድ አንድነትንና ዴሞክራሲን የሚሰብኩ የሚደግፉ በመሆናቸው ለአዲስ ኪዳን ሃይል ናቸው። በርግጥ አንዳንድ የብሄር ፖለቲካ ተቀጥላ የሆኑ ሃይላት የመንግስትን ፖለቲካ ኣስፈጻሚ ስለሆኑ እነሱ የተወሰነ እክል ሊፈጥሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ማጆሪቲ የሆነው የሲቪክ ድርጅት ግን የአዲስ ኪዳን ደጋፊ የሚሆን ሃይል ነው።

ሃያላን ሃገራት

በብዙ መልኩ ኢትዮጵያን ሲረዱ የቆዩ የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት እንደ እስራኤል፣ የተባበረችው አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውስትሬሊያ፣ የአውሮፓ ሃገራት ኢትዮጵያ ወደ አዲስ ኪዳን ብትገባ በከፍተኛ ደረጃ ይደግፋሉ። የብሄር ፖለቲካ ጦስ እያሳሰባቸው ስጋት ላይ ስለሆኑ ይህ ኪዳን ለነዚህ ኣገራት ደስታን ይሰጣል። በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ላላቸው የጸጥታ ጉዳይ የኢትዮጵያ የውስጥ ሰላምና ኣንድነት ወሳኝ በመሆኑ ኣዲስ ኪዳን በጣም ቅቡል አሳብ ነው። ሌላው የሚነሳው ጥያቄ የቻይና ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ወደ ኣዲስ ኪዳን የመግባት ኣሳብ ስታመጣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዓለም ኣቀፍ ተጽእኖዋ እየጎላ የመጣውና በተለይ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ወዳጅ ናት የምትባል ኣገር በመሆኗ በአዲስ ኪዳን ንቅናቄ ሰዓት የቻይና ኣሳብ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጥያቄ መነሳት ኣለበት። ቻይና የውጭ ፖሊሲየ በሰው ሃገር ፖለቲካ ጣልቃ መግባትን ኣይደግፍም ትላለች። በርግጥ ይህ ኣሳብ በመርህ ደረጃ ይደገፋል። ይሁን እንጂ ዓንድ ኣምባ ገነን መንግስት ህዝቡን ሲጨርስ ዝም ብሎ ማየት ከሞራልም፣ ከዓለም ኣቀፍ ስምምነቶችም ኣንጻር ቅቡል ኣይደለምና ቻይና በዚህ ትተቻለች። የሆነ ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ወደ አዲስ ኪዳን ብትገባ ከሆነላት ቻይና ኣትቃወምም። ይልቁን ለኣዲስ ኪዳን ምስረታ ቀናችን እንኳን ለዚህ ኣበቃች ሁ ብላ ደብዳቤ የምትጽፍ ኣገር ነው የምት ሆነው። ሆኖልን ወደ ኣዲስ ምእራፍ ብንሻገር የውጭ ተግዳሮት ኣት ሆንም። ቀጣይ ያለውን የንግድና የቴክኖሎጂ ልውውጥ ስትራተጂዎቿን ነድፋ ወዳጅነቷን የምታጠናክር ነው የምት ሆነው።

ከውጭ ሃይል የአዲስ ኪዳን ተግዳሮት ኣሸባሪ ቡድን ነው። እንደ ኣልቃይዳ፣ ኣልሸባብ፣ ኣይ ሲ ስ የመሳሰሉ ኣሸባሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ የዚህ ኣሳብ ተጋፊዎች ናቸው። የጠነከረች፣ ኣንድነቷ በኪዳን የጸና ኢትዮጵያን ማየት ኣይፈልጉም። በኣሸባሪነት ላይ ኢትዮጵያ የጸና ኣቋም ስለሚኖራት የውስጥ ሰላሟን ኣይሹም። በቀይ ባህር ኣካባቢ የተለየ ዝንባሌ ያላቸው ሃይሎችም እንዲሁ የኢትዮጵያን መጠናከርና ኪዳን ኣይደግፉምና እንደውጭ ተግዳሮት ይታያሉ።

የባህልና የሃይማኖት ተቋማት

እነዚህ ሃይሎች የአዲስ ኪዳኑ ደጋፊዎች ተደርገው የሚታሰቡ ናቸው። ኪዳኑ ፖለቲካዊ ባለመሆኑ በሂደቱም ኣክቲቭ ይሆናሉ። የኪዳናችን ኣሳብ የያዘው እሴት ከነዚህ ተቋማት ጋር የሚዛመድ በመሆኑ ደስታቸው ነው። በተለይ የባህል ተቋማት ከፖለቲካ መጫወቻነት ነጻ ወጥተው የራሳቸውን መንግስት መስርተው እንዲኖሩ የሚያደርግ ስለሆነ ኪዳኑን በሃይል ይደግፋሉ። በርግጥ በባህል የማስመለስ ሂደት ወቅት የባህልና ታሪክ ንጥቂያና ቅርምት እንዳይኖር ከላይ የምንገባው ኪዳን የሁላችን እንደሆነ ስለሚያሳይ ይሄን ያህል ተግዳሮት ኣይጠበቅም።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና አለም ኣቀፍ ተቋማት

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዚህ ኪዳን ዋና ሃይል ደጋፊ ይሆናል። እንዴውም ይህ የኛ ሞዴል ለብዙ ሃገሮች ትምህርት ሊሰጥ ስለሚችል ድጋፉን ከፍ ያደርጋል። ከዚህ ግዙፍ ተቋም ውስጥ ያሉት እንደ UNHCR, UNDP, OHRC, UNICEF, etc. ያሉት ተቋማት ደግሞ ኢትዮጵያ ኪዳን ስትገባላቸው ሻማ እያበሩ ደስታቸውን ይገልጻሉ። እንደ IOM ያሉ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ችግር በቅርብ ስለሚያውቁ አንድነትን ኪዳንን በሙሉ ሃይላቸው ይደግፋሉ።የአፍሪቃ ህብረትም ቢሆን ይህን ሲስተም መደገፉ ኣይቀርም። ኢትዮጵያ ኣሁን የምትከተለውን የብሄር ፖለቲካ የማይደግፉ ብዙ የአፍሪካ ሃገራት ይኖራሉ። ኔልሰን ማንዴላ ወደ ኢትዮጵያ ተጋብዘው ጉዞ የሰረዙት በዚሁ በዘር ፖለቲካ ባለመደሰታቸው ነበር።

ህዝባዊ መሰረት

በአጠቃላይ ወደ ኪዳኑ ስንሄድ ያሉት ተግዳሮቶች እንዳሉ ሆነው ነገር ግን በሰፊው ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ይኖረዋል። በኪዳኑ ንቅናቄ ሰዓት ቀዳሚ ተቀባይ (early adaptors and innovetors) ቀጣይ ተቀባይ (late adaptors) እንዲሁም ጎታች (laggers) ይኖራሉ። ኣዲስ ራእይ ሲመጣና ያንን ራእይ ለማስረጽ ስንነሳ እነዚ ሃይላት ሁሌም ይኖራሉ። ቀዳሚ ተቀባዮች ፈጣን ሲሆኑ የመጣውን ኣሳብ ወዲያው በፍጥነት ተረድተው ወዲያው ወደ ተግባር ይገባሉ። በኢትዮጵያ ሁኔታ በየብሄሩ ማጆሪቲ የሚሆነው ኣንድነትን የሚናፍቀው ህዝብ ይህን ኪዳን ለመቀበል ፈጣን ነው። ሌሎች ቀጣይ ተቀባይ ይኖራሉ። እነዚህ ሃይላት ደግሞ ውጤት ያያሉ ወይም ውጤት ይሻሉ። አይተው ቀምሰው ነው እጅ የሚሰጡት። በመሆኑም የአዲስ ኪዳኑን ውጤት እስኪያዩ ፈጣን ተቀባይ ላይሆኑ ቢችሉም እንቅፋት ግን ኣይሆኑም። ሌሎች በቁጥራቸው ጥቂት የሆኑ ግን (laggers) (ጎታች) የምንላቸው እነሱ የኪዳኑ ተግዳሮት ናቸው። አንዳንዶቹ ከፍ ሲል ያነሳናቸው ጽንፈኞች የብሄር ፖለቲከኞች ናቸው።ከዚህ በተጨማሪ የተዋለደው ህዝብ ደግሞ ይህ ያለፈው የብሄር ፖለቲካ ስላስቆጣው አዲስ ኪዳን ሲመጣ ለመቀበል ፈጣን ኣካል ነው። ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ከሁሉ በላይ ድህነት ያጠቃቸው ናቸው። እነዚህ ወገኖች በፍጥነት ወደ ኣዲስ ኪዳን ገብተን ከረሃብ ቢወጡ ይመርጣሉ። ሌሎች የብሄር ፖለቲካ ሄዶ ሄዶ የዘር ፍጅት እንዳያመጣብን ብለው የሚጸልዩ የሚሰጉ ሃይሎች ኣዲስ ኪዳን ተስፋን ሰጪ ነውና በደስታ ይቀበላሉ። በአጠቃላይ አዲስ ኪዳን ከውስጥና ከውጭ ያሉበት ተግዳሮቶችና ድጋፎች ያሉ ሲሆን ድጋፉ ከፍ ያለ ነው::

VI. መደምደሚያ
በእስካሁኑ ውይይታችን ውስጥ አስር ጊዜ የብሄር ፖለቲካን እያነሳን ጣልን። ዴሞክራሲን፣ ፕሉራሊዝምን መረቅን። ለዚህ ደግሞ የሚሻለው በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት ውስጥ መግባት ነው ለማለት ሞከርን። የ CCU አጀንዳ ከዚህ በፊት በዘውግ ፖለቲካና በግድ በሆነ ውህደት ፖለቲካ ልንፈጥረው ያልቻልነውን ሲነርጂወይም የህብረት ስሜትና ክንድ ለመፍጠር ስለሚረዳን ነው። አገር የሚሻው ዋና ነገር ህብረት ነው። ይህን ህብረት ለመፍጠር ደግሞ የምንገባው ኪዳን የሚፈጥረው የማህበረሰብ ሲነርጂ ወሳኝ ነውና ይህ የሚፈጠረው ኤነርጂ ለኢትዮጵያ ህልውና እንደ መልህቅ ይሆነናል።

በርግጥ ይህ አማራጭ አሳብም ሆነ ሌላ አማራጭ አሳብ ወደ ተግባር የሚለወጠው ቁርጠኛ የሆነ ትውልድ ሲመጣ ነው። ቁርጠኛ ትውልድ ተነስቶ ለውጥ ሲያመጣ ያን ጊዜ አዲስ የተሻለ ሲስተም ለመዘርጋት ይቻላል። አሁን ያለው ትውልድ አንድ ነገር ማድረግ ያለበት ይመስለኛል። አገሩን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየመራ ያለውን አምባገነናዊና ዘረኛ ስርዓት ለመለወጥ ቆርጦ መነሳት አለበት። መንግስትን መጣል ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት፣ ሲነርጂ ለመፍጠር ጥርመሳ ውስጥ ለመግባት መነሳት አለበት። ይህ ሲሆን ነው የተባበረችውን ኢትዮጵያን የምንገነባው። አሳብ ማምጣታችን የወደፊቷን ኢትዮጵያን እንዴት አድርገን ልናስተዳድር እንደምንችል መወያየታችን ተገቢ ሆኖ ነገር ግን ዴሞክራሲን ከሚያዘገይ ኢዴሞክራሲያዊ ሃይል ጋር መታገል ይኖርብናል። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተባበረችውን ኢትዮጵያን ለመገንባት መነሳት ያለበት ሲሆን በተለይ የሚከተሉት የህብረተሰብ ክፍሎች ትልቁን ሃላፊነት የያዙ ይመስለኛል።

ለአንድ ሃገር ፖለቲካ አለመረጋጋት ትልቁን ሚና የሚጫወተውና የዜጎች መከራ የሚረዝመው ዲክቴተር የሆነ መንግስት ስለሚገጥማቸው አይደለም። የትኛውም አምባገነን መንግስት ከህዝብ ክንድ በላይ አይሆንም። የመከራው ጊዜ የሚረዝመውና ዲክቴተርስ ትንፋሽ የሚያገኙት የሌሂቁ ክፍፍል ሲጨምርላቸው ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም የማንነት ፖለቲካ ከመጣ ወዲህ የማይቀንስ እንደውም እያደገ የሚሄድ የሌሁቁ ልዩነት ይታያል። የጎዳው ልዩነት መኖሩ ሳይሆን ልዩነቱ ጽንፈኛ መሆኑና የሚያገናኝ አንድ የጋራ መድረክ አለመኖሩም ነው።

እነዚህ አካላት በቅንነት ለሃገራቸው ዴሞክራቲክ ለውጥ የሚታገሉ ቢሆንም መበታተናቸው ግን በተቃራኒው መንግስትን እየጠቀመ ትግሉን እያዳከመ በመምጣቱ ችግርቻችን እንዳሉ እንዲቆዩ አድርጓል። በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ለሂቃኖቻችን አንድ ሚኒመም የመስማሚያ አጀንዳ በማስቀመጥ በዚያ ላይ ለመስራት መቁረጥ ያስፈልጋል። ይህ መሰረት ደግሞ በጣም ግልጽ በሆነና ቀላል በሆነ መንገድ መቀመጥ ያለበት ሲሆን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር የአስቸጋሪ መንግስት ጉዳይ ሳይሆን በጣም መሰረታዊ የሆነ የዴሞክራሲና የነጻነት ጥያቄን የያዘ በመሆኑ እነዚህ ሌሂቃን በትግል ስልትና በፖለቲካ አስተሳሰብ ከመለያየት ይልቅ ኢትዮጵያ በሽግግር ስርዓት ወደ ዴሞክራሲ መግባት አለባት በሚለው ላይ መግባባት ያስፈልግ ይመስለኛል። ይህ የሽግግር ጊዜ እንዲፈጠርና ይህ የሽግግር ጊዜ ከፖለቲካ ሃይላት በተውጣጡ ሰዎች እንዲመሰረትና በዚህ የሽግግር ጊዜ ብሄራዊ እርቅ እንዲመጣና ኢትዮጵያን ለባህላዊ አንድነት የሚያመቻች ቢሆን መልካም ነው።

ሌሎች የአመለካከት ጉዳዩች መሬቱ ከተደለደለ በሁዋላ በሽግግሩ ጊዜ ቢነሱ መልካም ነው። ኢትዮጵያ ካለፈችበት ጎዳና አንጻር በዚህ በብሄራዊ ስምምነት ጎዳና ውስጥ ማለፍ ስላለባት ወደዚህ ጎዳና ለመግባት የሚያስችላት ላይ ብቻ አጥብቦ መግባባት ቢቻል የተሻለ ነው። ይህ የስምምነት ደረጃ በሽግግር መልክ መጀመሩ ዴሞክራቲክ ሃይላትን ሁሉ የሚያሰባስብ ሰፊ ጥላ ይመስላል። ሌሎች የፖለቲካ አስተሳሰቦች ክርክሮችና ልዩነቶች መነሳት ያለባቸው በመጀመሪያ ፕላት ፎርሙ ሲኖር ስለሆነ ኢትዮጵያዊያን ለሂቃንና የፖለቲካ ፓርቲዎች አሸንፎ ስልጣን ለመያዝ መንግስት ለመመስረት ከሚያደርጉት ትግል ይልቅ ሁሉን አቀፍ የሆነ የስምምነትና የጽሞና ጊዜ ለሃገሪቱ የሚፈጠርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ለዚህም መታገል አለባቸው። ለጊዜው የፖለቲካ አጀንዳቸውን ያስቀምጡትና ወደዚህ ጥላ ገብተው ሃይላቸውን ያሰባስቡ። ይህን በማድረጋቸው የህዝብ ልብ የሚያርፍ ከመሆኑም በላይ ለእዝ ይጠቅማል። በአሁኑ ሰዓት የነጻነት ትግሉ የገጠመው ፈተና የእዙ ሁኔታ እዚያም እዚያም መሆኑ ነው። ሰልፎችን የሚጠራው ቡድን በዛ፣ የትግል ስልቱ በዛ፣ ለትግል ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ትእዛዝ የሚሰጥ ጠፋ፣ በዚህ መሰረት ትግሉ አልራመድ አለ። በመሆኑም ሌሂቃኑ ህዝቡን ለስምምነት ለሽግግር ጊዜ እንዲታገል መጥራት ይቻላል። ይህ ህብርት ሲፈጠር የሚመጣው ጥያቄ የትግል ስልት ጉዳይ ነው። አንዱ የሚያለያይ ጉዳይ ሆኖ የሚታየው ይሄ ጉዳይ ነው። በእኔ እምነት የትግል ስልቱ ምርጫ የሚያለያይ አይመስለኝም። እነዚህ ነፍጥ አንስተው የሚታገሉ ሃይሎች ይህን ምርጫ ስለወደዱት አይደለም። ሁኔታዎች ስለተዘጉ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የለውጡን የመጀመሪያ ምእራፍ ለመክፈት ሁሉም የትግል ስልቶች ውጤታማ ናቸው። ብሄራዊ እርቅ፣ ሰላማዊ ትግል፣ የትጥቅ ትግል፣ የዲፕሎማሲ ትግል እነዚህ ሁሉ በተናጠልም በጋራም መንግስትን የመቀየር ሃይል አላቸው። ችግሩ ያለው እነዚህን የትግል ስልቶች በተናጠል ወይም በጋራ ያላቸውን ሃይል አሟጦ አለመጠቀም ነው። የሃይል መበታተን እነዚህ ትግሎች ውስጥ ያለውን እምቅ ሃይል ተጠቅመን ህዝባዊ ትግሉን ወደፊት እንዳናራምድ አድርጎናል። ለዚህ ነው ወደ አንድ አቅጣጫ ሰብሰብ ማለቱና በአንዱ የትግል ስልት ዙሪያ ጠንከር ያለ ትግል ማካሄድ የሚያሻው። የትግል ስልት መምረጡን እንደ ትልቅ ልዩነት አንየው የምንለውም ለዚህ ነው። ሁሉም የትግል ስልቶች ለውጥ እስከሚያመጡ ድረስ መሰባሰብ ከቻልን በቀላል መስዋእትነት ለውጥ የሚያመጣውን የትግል ስልት መምረጥ እንችላለን።

ወደ ወጣቱ ልመለስና ይህ ትውልድ በተለይ አገሩን ወደ ተሻለ ማህበራዊ ፖለቲካ ለማሻገር ግዙፍ ታሪካዊ ሃላፊነት ትከሻው ላይ ወድቋል። ይህን ሃላፊነት ለመወጣት የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት፣ ወደ አዲስ ኪዳን መሻገር ያስፈልጋል።

ጎልማሶችና አባቶች የካበተ እውቀት ስለሚኖራቸው አቅጣጫ በማሳየት በምክር ይረዳሉ። ነገር ግን ሁል ጊዜም ቢሆን የለውጥ ሃይል በእጁ ያለው ወጣቱ ጋር ነው። ወጣቱ ነው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ አክቲቭ የሚሆነው፣ ወጣቱ ነው አምጾ ለውጥ የሚያመጣው፣ ወጣቱ ነው የማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀምና ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም አምባገነኖችን ወጥሮ የሚይዘው። በማንኛውም የትግል ስልት ውስጥ ሃይል ያለው ከወጣቱ ጋር ነው። ስለዚህ ወጣቱ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት አካባቢ ያለው በሃገራቸን ውስጥ ተፈላጊ ለውጥ ይመጣ ዘንድ በግንባር ቀደምነት ሊመራ ይገባል። ከሁሉ በላይ ከዘር ፖለቲካ ራሱን አጽድቶ ሊቆም ይገባዋል። በሌሎች መስዋእትነት ውጤት ጠባቂ ከሆንን ለውጥ አናመጣም። የተባበረችውን ኢትዮጵያን ለመገንባት መነሳት አለብን። ሌላው ወታደሩ፣ ፖሊሱና የፍትህ አካሉ በቃ ሊል ይገባል። ሳይማር ያስተማረውን ህዝብ እያሰበ ለለውጥ መነሳት አለበት። አስተማሪዎች ሰፊ ሃላፊነት አለባቸው። ያልገቡበት የሃገሪቱ ክፍል የለምና ባሉበት አካባቢ ህዝቡን ማንቃት አገሪቱን ወደ ተሻለ ስርዓት ለማሻገር ማስተማር ያስፈልጋል። ገበሬው፣ ሴቶች ወንዶች ሁሉ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ ግንባታ መነሳት አለብን።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምንም በላይ የፖለቲካ ጨዋታ መጀመሪያ ሜዳውን ለመደልደል መነሳት አለባቸው። ኢትዮጵያውያን ሁሉ ወደ አዲስ ኪዳን ይገቡ ዘንድ የሁሉ ፓርቲዎች ፍላጎት ሊሆን ያስፈልጋል። ይህ የኪዳኑ ኣሳብም የጋራ መሰባሰቢያ ጥላን ይፈጥራልና በዚህ ጥሪ ስር ተሰባስበው ለአዲስ ኪዳን መዘጋጀት ያሰፈልጋል። ከኪዳኑ ማግስት ጀምሮ የፖለቲካ ራእይ ያላቸው ሁሉ ሜዳውም ያው ፈረሱም ያው እንደሚባለው በዚያን ጊዜ ለፍክክሩ ይደርሳሉ። አሁን ለኪዳኑ ኣሳላፊዎች
ኣስተባባሪዎች ቀስቃሾች ሊሆኑ ይገባል።

ውድ ወገኖቼ ቅን የሆናችሁ የገዢው መንግስት ባለስልጣናትና ተራ የፖለቲካ ሰዎች፣ ውድ ወገኖቼ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና አባላት። መቼስ የፖለቲካ ፓርቲ የምንመሰርተው የወገን ቅንዓት ስለሚይዘን ነው። ወገንን ከችግር ለማውጣት። የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ነው። ነገር ግን አሁን እኛ እርስ በርስ በዘውግና በብሄራዊ ማንነት ስንነታረክ ብዙዎች ረሃብ ላይ ወድቀወብናል። ዛሬ ሚሊዩን የሚጠጉ ለጋ ህጻናት ጎዳና ወጥተውብናል። በምግብ እጥረት የሚሰቃዩትን ህጻናት ቤታቸው ይቁጠራቸው። ብታገኝ በልታ ብታጣ ተደፍታ የምታድር እህት እንባ ዝም ብሎ በኢትዮጵያ ምድር ይፈሳል። በእርሻ ስራ ከአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ በ21ኛው ክፍለዘመን የእርሻ ቴክኖሎጂ በመጠቀበት ዘመን አፈርና ውሃ ለውሰን በምግብ ራሳችንን መቻል አቅቶናል:: በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ 76 በመቶ የሚሆነው አምራቹ ክፍል ወጣቱ ድንገት ከሃገር ብን ብሎ መጥፋትን ይመኛል። ዛሬ በሃገር ቤት አትሰደድ የሚል የለም። እንዴውም የመሰደድ እድል ያገጠመው ሰው ሲገኝ ድግስ ይደገስለታል። እንኳን ደስ አለህ ተብሎ ስደት የሚመረቅበት ዘመን ላይ ነን። የአቶ እከሌ ልጅ ወደ ውጭ ሄደ መባል ክብር ሆነ። ወጣት ኢትዮጵያውያን በየቀኑ በአራቱም አቅጣጭ ተዘልሎ ለመኖር ይፈልሳሉ። የሃገራችንን የስደት አስከፊ ደረጃ ለማወቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጥገኞች ድርጅትን(UNHCR) እንደ IOM የመሳሰሉትን ድርጅቶች መጠየቅ ይቻላል። እነሱ የስደት ህይወታችንን ተረድተዋልና የኢትዮጵያን ሁኔታ ይገልጻሉ:: ዛሬ ወጣት አምራች ወገኖቻችን በአንዳንድ አፍሪካ ሃገራት በህገ ወጥ ተጓዥነት እየታሰሩ መከራ ያያሉ። እስራታቸውን ጨርሰው ወደ ሃገር ቤት እንዲመለሱ ፍርድ ቤት ሲወስንባቸው ፈላጊ ተቀባይ እያጡ ሲንከራተቱ እንደማየት ምን የሚያሳዝን ነገር አለ? አንዳንዶቹን የሰሃራ ምድረበዳ በላቸው። አንዳንዶቹ በባህር ሰጠሙብን። የሰሃራን በረሃ አቋርጠው እንጀራ ፍለጋ የሚንከራተቱ ወንድሞቻችንን አሸባሪው አይሲስ አረዳቸው። ወላድ አነባች። ያልገባንበት ምድር፣ ያልተበተንበት ያልተዘለልንበት የዓለም ክፍል ጠፋ። ሴት እህቶቻችን በታሪክ እንዲህ የተሰደዱበት የተዋረዱበት ዘመን የለም። ቢያንስ 15 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የለጋሾችን የምግብ ርዳታ ተስፋ አድርገው ዛሬም ይኖራሉ:: መንግስት ራሱ ከአመታዊ ባጀቱ ውስጥ ከሃምሳ እስከ ስልሳ በመቶ የሚሆነውን ባጀት የሚሸፍነው በእርዳታ ነው። በራሱ የሚቆም መንግስት እንኳን የለንም። ዛሬም የእናቶች የአባቶች እምባ እንደወንዝ ይፈሳል። በውነት ለኢትዮጵያ ህዝብ ይህ አይበቃውምን? በአንድ ወቅት ታላቅ ታሪክ ያለን ሰዎች ለአፍሪካውያን ሁሉ ኩራት የሆንን ሰዎች እነሆ ዛሬ በምግብ እርዳታ ልመና ስማችን ጠፍቷል። ከቶ ይህ ያልቆጨን ምን ሊቆጨን ይችላል? ስናሰለጥናቸው የነበሩ የአፍሪካ ሃገራት ዛሬ በዚህ ስማቸው ፈጽሞ ኣይነሳም። ዓለም ሁሉ አላምጦ የጣለውን የዘውግ ፌደራሊዝም መስርተን ታይቶ በማይታወቅ የብሄር ግጭት ውስጥ ተዘፍቀናል። ዛሬ ኢትዮጵያውያን በሃገር በምድራቸው በማንነታቸው የሚፈናቀሉባት አገር ናት። በአንድ የሃገር ጥላ ስር የሆነ ህዝብ በብሄሩ ማንነት ምክን ያት ሲፈናቀል እንደማየት ምን የሚያሳዝን ምን የሚያሳፍር ነገር አለ? ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህ የብሄር ፖለቲካ እርስ በርስ ያለንን መተማመን እንደ ምስጥ በላብን። ከዚህ ስስታም የኔ የኔ….. ከሚል የፌደራል ስርዓት ወጥተን ወደ እኛ ካላደግን ያቺን ታላቅ አገራችንን ያለማቋረጥ ወደ ኋላ እየነዳት ነው። ከቶ ይህ ያልቆጨን ምን ሊቆጨን ይችላል?:: ይበቃል!። ስለዚህ ፓርቲዎች ሁሉ ተቆጭተው በፍጥነት ወደ አዲስ ኪዳን መግባት አለባቸው። በግድ መግባት አለባቸው:: ስለ ህዝቡ ብሶት ሲሉ ብዙ ዋጋ መክፈል አለባቸው። ለዘውግ ፖለቲከኛ ወገኖቼ አንድ መልእክት አለኝ። በቅርቡ ኦሮምያ ውስጥ በተነሳው ዓመጽ ሳቢያ ብዙ ኦሮሞ ወገኖቻችን ሲያልቁ የጎንደሩ አማራ ተነስቶ በየጎዳናው የሚፈሰው የኦሮሞው ወገኔ ደም የእኔም ደም ነው ሲል፣ ናዝሬት፣ ጊንጪ ያለው ኦሮሞ ጎንደር ላይ የሚፈሰው የአማራው ደም የእኔም ነው ብሎ ተነሳ። አዋሳ ላይ ያሉ የደቡብ ወገኖች ጎንደር ላይ የሚፈሰው የአማራው ደም፣ አምቦ ላይ የሚፈሰው የኦሮሞው ደም የእኔም ደም ነው ሲሉ ተነሱ። ይህ ምን ማለት ነው? It shows that bloodline politics in Ethiopia has been rejected by the Ethiopian people. Ethiopians are saying No bloodline politics! No bloodline federalism! Period. (የደም ሃረግ የዘውግ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ውስጥ ቦታ የለህም ማለት ነው።) በቅርብ ቀን በቅማንትና በዓማራ ህዝብ ሪፈረንደም ላይ የታየው አንለያይም አንድ ነን መልእክት በኢትዮጵያ ውስጥ የብሄር የደም ፌደራሊዝም እንዳከተመለት ነው። አማራም ሆነ ቅማንት ባህሎቻቸው ተጠብቆ ቢኖሩ ደስታውን አይችሉትም። ይሁን እንጂ ይህ ልዩነታቸው ግን የተከፋፈለ የፖለቲካ የመሬት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ እንዲያደርጋቸው አይፈቅዱም። ህዝቡ በልቡ የያዘው ቃል ኪዳን ይህ ነው። በኢትዮጵያውያን ኪዳን ላይ ተመስርቶ የሚራመድ ፓርቲ ነው ፓርቲ ማለት። ስለዚህ ህዝቡን እንዲህ በልቡ ጠብቆ ወደያዘው ኪዳን መሃላ እንውሰደውና መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ኪዳን ከገባ በኋላ በዚያ የማእዘን ራስ ላይ የፖለቲካ ቤታችንን እየሰራን ፍክክር እናደርጋለን። በመሆኑም ፓርቲዎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህን ኪዳን ያደርጉ ዘንድ ታጠቀው የሚቆሙ የለውጥ ሃዋርያት መሆን አለባቸው። ይህን በማድረግ የኢትዮጵያውያንን የእምባ ዘመን እንዲያበቃ ሊያደርጉ ይችላሉ። አስተማሪዎች፣ ተማሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የጥበብ ሰዎች፣ ነጋዴዎች፣ ገበሬው ሴቶችና ወንዶች ሁሉ ኪዳን አድሰው ተማምለው ሃገሪቱን ከገባችበት ሁለንተናዊ ቀውስ የማውጣት ታሪካዊ ሃላፊነት ትከሻቸው ላይ ወድቋል:: ያለፈው አልፎ አሁን ወደ አዲስ ኪዳን የምንሻገርበት ዘመን ይሁንልን። ዘ ጸዓት ለኢትዮጵያ እመኛለሁ። የተባበረችውን ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ!

ያለፈው አልፎ አሁን ወደ አዲስ ኪዳን የምንሻገርበት ዘመን ይሁንልን። የተባበረችውን ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ።

እግዚአብሄር ይርዳን።

LEAVE A REPLY